የእኔና የetv፥ የትናንት ማታ አጭር ታሪክ

ደክሜ ነበር የዋልኹት። ….ስብሰባ ተብሎ ጠዋት 3 ሰዓት የተጀመረ፣ ስንዳረቅ – ስደርቅና ሳደርቅ – ምሽት 11 ሰዓት ላይ ነው የተበተነው። ….ስወጣም ታስሮ እንደተፈታ ሰው ነበር የተሰማኝ። — ታስሮ ተፈትቶ በጎዳናው ላይ መመላለስ እንደናፈቀው ወጣት፥ ወጥቼ አስፓልት አስፓልቱን ስንቀዋለል አመሸሁ።
 
ሆዴን ሲሞረሙረኝ — “ኧረ ድፍረት፥…. በቀን 4 ጊዜ መብላት አማረሽ?!” ብዬ ‘ርስበርሴ፥ በሆዴ ስለሆዴ አሹፌ፥ ሰዓት ስመለከት 2 ሰዓት ከ15 ሆኗል። ….መጀመሪያ መክሰስ ያሰኘው መስሎኝ ነበር! ለካስ ራት ነው (በአዋዋሌ ምክንያት እንጂ፥ በመደበኛ ሁኔታ ቢሆን ኖሮ ለራት ገና ጊዜ ነው።) ….አስቸኳይ ጥያቄውን ልመልስለት ብዬ፥ ሆቴል ሳላማርጥ፥ አጠገቤ ከነበረ መለስተኛ ምግብ ቤት እንደበረኛ ተወርውሬ ገባሁ።….
 
ዓይኔ ብቻውን፥ ጎኑ የተጋቢኖ ሸክላ ድስት የተቀመጠበት ሳህን ላይ አረፈ። …..ሶስት ጎረምሶች አንድ ተጋቢኖ አዝዘው ትሪውን ያዋክቡታል። እንጀራውን ያሰቃዩታል። …እኔ ደግሞ በአንጻሩ መሰቃየት አማረኝና፤ አንድ ራሴን ልሰለቅጠው፥ አንድ ተጋቢኖ አዘዝኩኝ። ….. (መቼም ሰው አንድ ምግብ ለሶስት እየበላ፥ አንድ ምግብ ለብቻ መብላት፥ መሰቃየት ነው። መሰልቀጥ ነው።)
 
“አባቱ፥…. ገና ተሰርቶ ስለሆነ ትንሽ ይቆያል” አለችኝ (በልዩ ፈገግታ) ትእዛዜን የተቀበለችው ወፈር ያለች ጎራዳ ወጣት። “ከፍትፍቱ ፊቱ” ማለት ይህኔ ነው።…. አልኹኝ በሆዴ፤ ሆድ ተኮር ተረትና ምሳሌ መዝዤ…. ሃጫ በረዶ ችምችም ጥርሶቿን ብርግድ አድርጋ ነበር የመጣችው። ስታስተናግድና ለሰው ምግብ ለማቅረብ እንዲህ የተፍለቀለቀች፥ “ብዪ” ብትባልና ብትስተናገድ እንዴት ትሆን ይሆን?… ለነገሩ ላወቀ ልቦና ማብላት ደስታ ነው። ማስደሰት እርካታ ነው። — መሰለኝ!
 
ረኀቡ ጠንካራ ቢሆንም፥ ፈገግታዋ ያስገድዳል። እንደዚያ ባይሆን ኖሮ ቢያንስ የምግብ ዝርዝር ስለማማረጥ ማሰብ እችል ነበር። ሆኖም ጭራሽ አላሰብኩትም። ….“ኧረ እጠብቃለሁ! መሽቷል…. የት እሄድ ብለሽ ቆንጂት?” አልኳት። ….ያታስጨርሰኝ፥ እንዳመጣጧ እብስ አለች። — ዳሌዋን ሞንደል ሞንደል እያደረገች፤ ከነፈገግታዋ..
 
ትዕዛዝ ስታቀብል ሁላ ይሰማል። የሚሰማው ድምጽ፥ ፈገግታው እንዳልለቀቃት ዓይነት ምስል ይከስታል። — “አንድ ተጋቢኖ! ለቤተሰብ ነው። ቃሪያም አርጊበት።” …….“ወይ ጉድ” — ኧልኩኝ በልቤ… ፈገግታውም ማባበያና ለገበያ መሸንገያ እንደሆነ ተሰማኝ። ግን ደግሞ ልማድ ሆኖበትም ይሆን እንደው እንጂ የምር ነበር የሚመስለው። ወይ ደግሞ…… ኤጭ! የራሷ ጉዳያ!
 
አንዱን ምግብ የሚሻሙት ሰዎች ላይ ላለማፍጠጥና፥ “እንብላ” ብለውኝ በመሳቀቅና በመሳቅ መካከል እንዳልጨነቅ ሽሽት….. ዓይኔን ግራና ቀኝ፤ ላይና ታች…. ሳንከራትት ቆይቼ፥ ኮርነሩ ላይ የተሰቀለ ፍሬም ነገር ላይ አሳረፍኩት። — ትኩር ብዬ ሳየው 14 ኢንች ቴሌቪዥን ነው።…. የተከፈተው ደግሞ ኢቲቪ። — “በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ” ….ለነገሩ ለኢቲቪስ 14 ኢንች ሲበዛ ነው፤ ኧረ እንዲያውም ቢቻል መክፈል ነበር። ….
 
ብርሀኑ በደበዘዘ ቤት ውስጥ ከርሱና ጎኔ ካሉት ተመጋቢዎች በቀር ሌላ ለማየት አማራጭ ስላልነበረኝ ተስተካክዬ ክላም ማድረግ ጀመርኩኝ።…. ለዜና ሽግግር ማስታወቂያው ይግተለተል ያዘ። መጀመሪያ ያየሁት ማስታወቂያ፥ በዜና መሀል ብቅ ያለው የፍሊንትስቶን ሆምስ ማስታወቂያ ነበር…. “ይህን የአየር ሰዓት ስፖንሰር ያደረገላችሁ ፍሊንት ስቶን ሆምስ ነው።” ይልና ቄንጡን የበጠሰ ምስል ይለቀቃል። የሆነች ቀሽት ሴትዮ ትታያለች። ….ባቡር ውስጥ ነው። ፓ! ይኽን የባቡር ወሬ ከምኔው ለጥብስ አደረሱት?
 
ማስታወቂያው ራሱ “መገናኛ ስቴሽን፣ ኡራኤል ስቴሽን፣ 22 ስቴሽን…..” ሲል፥ ለማያውቅ መንገድ ለመሸጥ የሚያስተዋውቁ ነው የሚመስለው። “ከፈረሱ ጋሪው ቀደመ” የሚባለው እንዲህ ያለው ይሆን? ….ደግሞ ቤቱን የሚሸጡት አሁን ነው ወይስ ባቡሩ ሲያልቅ? ….ታዲያ ምናለ “ባቡሩ እስከሚገባ አይሸጥም” ብለው ቢጨምሩበት? ወይስ ያልገባኝ ነገር አለ?…..በጣም የሚያምር ምስል የሚታይበት ብሽቅ ማስታወቂያ! በመብሰክሰክ በሸቅኩኝ።
 
ማስታወቂያው ቀጥሎ፥ ሴትዮዋ ከባቡር እየወረደች፥ “የእምነትሽ ውጤት…. ላንቺ” ይልና ያበቃል።….. “የእምነትሽ ውጤት” የሚለው ሀረግ ዝም ብሎ ሆኖ ቢያናድደኝም፤ ልክ “ላንቺ” እንዳለው፥ በነካ እጁ “ላንተም” ብሎ ቀጥሎ ያስጎመዠኛል ብዬ ስጠብቅ፥ ወፍ የለም። …. የማስታወቂያው ሰንካላነት ጎልቶ ባያበሳጨኝ ኖሮ፥…. ‘ቆይ ግን ከእኔ ጋር ምናለው? ምናለ እኔን ደስ ቢለኝ?’ ምናምን ምናምን ብዬ እቀውጠው ነበር። በመካከሉ ያለፈኝን እንጃ፤ ማስታወቂያው ቀጠለ….
 
ቀና ስል የራኒ ጁስ ፕላስቲክ ጠርሙሶች ተደርድረው ይታያሉ። ተናጋሪው ከጀርባ አንበሳ እንደገደለ ሰው ይቀውጠዋል። እኔማ ወላ ዶክመንተሪ መስሎኝ ነበር። — “በራኒ ጁስ አሸበሩ፣ የህብረተሰቡን ሰላም አደፈረሱ” ምናምን ዓይነት።… ‘የኢትዮጵያ የምግብና መድሀኒት ጤና ክብካቤና ቁጥጥር ክትትል ጽ/ቤት’ ማስታወቂያ ነበር።…. እንዲህ ቀጠለ
 
“ራኒ ጭማቂ የአገልግሎት ማብቂያ ጊዜው (expiry date) ባለፈው ግንቦት ሳለ፥ ቀኑን ቀይረው እስከ መስከረም ብለው ቀይረው ሲሸጡ፥ በህብረተሰብ ጥቆማ ደርሰን ነገሩን እያጣራን ነው።…. ክፍለ ሀገር ያላችሁም ስትገዙ ቀኑን አጣርታችሁ ግዙ። ሌላ እቃም ላይ ጠቁሙን።” ምናምን…. እያለ ይቀጥልና “ለጥቆማችሁ የነጻ የስልክ መስመራችንን 8482ን ይመቀሙ።” የሚል ጽሁፍ ብቅ ብሎ ያቆማል። …..መቀመቅ ያውርደው አቦ! ምናለ በትክክል “ይጠቀሙ“ ብለው ቢጽፉት?
 
ደግሞ ሸክላ ፈጭተው በርበሬ ብለው የሚሸጡ፣ ሙዝ ቀይጠው ቅቤ ብለው የሚሸጡ፣ በአይጥ ስጋ ዱለት ሰርተው የሚሸጡ ሰዎች አሉ በሚባልበት ሀገር ውስጥ ይሄ ምን ይገርማል? ….በጎጆ ኢንዱስትሪ የተመረተ ምግብ በነሲብ የማብቂያ ጊዜ ተፅፎለት በየሱፐር ማርኬቱ ሲሸጥ ዝም የሚባልበት ሀገር ውስጥ ይሄ ምን ይደንቃል? ደግሞ ጠቀም ያለ ተመጣጣኝ ቅጣት ለማይቀጧቸው ነገር ምን አቀያየመን ብለን እንጂ ከተማው ውስጥ ያሉ ትልልቅ ሱፐር ማርኬቶች ለinventory ብለው ሱቃቸውን ሲዘጉ የexpiry date ለመቀየር እንደሆነ እንሰማለን።….ማስታወቂያው “የነጻ የስልክ መስመራችንን 8482ን ይመቀሙ” የሚለው ስም ታይቶ የአስተዋዋቂው ድርጅት ስም ተጠቀሰና በሌላ ተተካ።
 
ሜሮን ጌትነት አንዱን (ለማስታወቂያው ባሏን) “የኔ ፍቅር እንዲህ ተዋድደንና ተከባብረን የምንኖርበትን ሚስጥር ታውቃለህ” ምናምን ትለዋለች። …..“እንዴታ” ይላትና የሆነ የሆነ ነገር ይባባላሉ። የመፋቀር ሚስጥር ምንድን ነው? በሚስጥርና በመመሪያ መፋቀርስ አይደብርም? ….እርሱን ሳስብ ቀጥሎ የሚያወሩትን አልሰማሁም ነበር። …..ከዚያም የወሊድ መቆጣጠሪያ “ሉፕ”ን ጠቅሰው ስለቤተሰብ ምጣኔ ያስተምራሉ። ….ሁለት ህጻናት መጥተው ያቅፏቸዋል። የዚህ ማስታወቂያ ባለቤት ደግሞ የፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ነበር።
 
ማስተማራቸውስ ደግ! ግን ምናለ ‘የመዋደድ ሚስጥር’ ምናምን ብለው ትዳርን አውርደውት ተመልካቹን ባያበሳጩ? ‘ሉፕ ካልተጠቀማችሁ መከባበርና መፋቀር አትችሉም’ ዓይነት ያልተገለጸ መልክት ባያንፀባርቁ? ….ዶ/ር አቡሽ ስንት ገጽ የሚቀባጥርበትን ጉዳይ በአንድ በሉፕ ሲጠቀልሉበት ምን ይሰማው ይሆን?ሄሄሄ….. (ከዚህ በፊት ደግሞ ለዘይት (ዘይቱ “ሸዲ ለጋ” መሰለኝ) “ለአስተማማኝ ትዳር” ነገር ሲሉ ተመልክቼያለሁ።)
 
መቼስ ቁሰል ብሎኝ የለ? ማስታወቂያው ቀጠለ….. ይሄ ደግሞ፥ ‘የአእምሯዊ ንብረቶች ጽ/ቤት ከኢትዮጵያ ኦዲዮ ቪዡአል አሳታሚዎች ጋር’ በመተባበር የቀረበ ነው። ….ሲዲዎች ሲቃጠሉ ይታያል። አቃጣዮቹም የሚቃጠለውን ሲያገላብጡ ይታያል። …የሆነ በሽታን ከአገር የማጥፋት ፅዳት ዘመቻ ነው የሚመስለው። ለነገሩ ለጽዳትስ ቢሆን ቆሻሻን መቅበር እንጂ ማቃጠል ለአየር መዛባት ያጋልጣል ብለው ይከለክሉ የለ? “ህዳር ሲታጠን”ስ ለአመል ይደረጋል እንጂ የት ቆሻሻ ይቃጠልበታል? እንጂማ ስንት ግንቦት ያፈራው ደረቅ ቆሻሻ ችቦ በሆነ ነበር።
 
በብስጭት፥ “ምናለ የአካባቢና የተፈጥሮ እንክብካቤ ጽ/ቤት ‘ከእኔ ህልውና ጋር የሚፃረር አሉታዊ ት/ት አስተምራችኋል’ ብሎ በከሰሳቸው” ብዬ ተመኘሁ። ….ቅሉ የት ፍ/ቤት ሄዶ ነው የሚከሳቸው። “የገደለው ባልሽ፣ የሞተው ወንድምሽ” ይሆንባቸዋል። ….ከዚህ በፊትም ከጉምሩክ በኮንትሮባንድ የተገኙ ቁሶችን ፖሊስና ህብረተሰብ ፕሮግራም ላይ ሲቃጠሉ ሳይ አብሬ እቃጠል ነበር። ….ስንት የሚለብሰው አጥቶ በሚራቆትባት ሀገር ውስጥ ልብስን እንደ ቆሻሻ ብሎ ማቃጠል። ስንቱ ተርቦ ምግብን እንደ ቆሻሻ ማቃጠል።….“እዬዬም ሲደላ ነው።…..
 
ከዚያ ማስፈራሪያው ቀጠለ “በሚሞሪ፣ በiPhone፣ በምናምን በምናምን….. ቢሆን ሙዚቃ የምታረጉ ወዮላችሁ። ይህን ያህል ዓመትና ይህን ያህል ብር ትቀጣላችሁ።” ምናምን ምናምን…. “ጉድ….. ቆይ ሀገሩን እስር ቤት ሊያደርጉት ነው እንዴ? የስንቱ ሞባይል ጥሪ ሙዚቃ ነው?…. ከዚህ ሁሉ ለምን ቴሌ አገልግሎቱን አያቋርጥምና ስልኮችን አይለቅምም? …..እንዲያውም ቴሌ የውስጥ ጥሪ ሙዚቃዎቹን ሲያደርግ ከፍሎ ይሆን? ብዙ ጥያቄዎች…
 
እንደምንም ከአቃጣይ ማስታወቂያዎቹ ጋብ ብሎ ወደ “ሚዲያ ዳሰሳ” ሲሻገር ትንሽ ፋታ አገኘሁ ብዬ ተረጋጋሁ። ….ሁለቱ የፕሮግራሙ አስተናጋጆች በግብጽ የአብዮት ወሬ ነበር የጀመሩት። አንደኛው፥ “አንዳንዶች የግብጽ አብዮት የዛሬ ሁለት ዓመት ከጀመረ አልቆመም እያሉ ነው። ሌሎች ደግሞ…” ብሎ ይቀጥላል። ከዚያ ግብጽ ውስጥ ስላሉ የውስጥ ችግሮች ያወራል። ስለ ደመወዝና ስራ መጥፋት፣ ስለበጀት አለመብቃት፣ ስለነዳጅ ሰልፍ፣ ….ሀገሬን ሰማኋት። “አንድ አይን ያለው በአፈር አይጫወትም።” ይባላል። ስንት የታፈኑ ድምፆች አሉ አይደል? ሆሆ….. ከዚህ በላይ መቆየት ለነገር ነው። …ክፉ ሊያናግሩኝ!
 
ተጋቢኖዬ ከች አለች። እኔም ሳልቀምሳት ሂሳብ ከፍዬ ልወጣ ብድግ ስል ቆንጂት ደነገጠች። ፈገግታዋ ባንዴ ከል ለበሰ።…. “ምነው? ምን አገኘህበት?” አለችኝ ደንግጣ። “ኧረ ይስተካከላል። ኧረ አባቱ….” ተንተባተበች።…. “ኧረ ምንም።…. እንዲሁ ነው። ከፍትፍቱ ፊቱ ይባል የለ? ፈገግታሽ በቅቶኝ ነው” ስላት በሸራፋ እንደመሳቅ ብላ እንድቀመጥ በመሳቀቅ ጋበዘችኝ። ” ….. “አይ ስቀልድ ነው። ስልክ ስለተደወለልኝ ቸኩዬ ነው። በፌስታል አድርጊው።” ብያት አደረገችልኝና በራፉ ላይ ለነበረ የጎዳና ተዳዳሪ ሰጠሁት። አንድ ሰው ጠግቦ አደረ። — እድሜ ለetv!
 
Etv የሌለው መጠጥ ያለው ቤት ፍለጋ መንገዴን ቀጠልኩ። ከቀናኝ ብስጭቴን ልረሳ። ካልሆነ ደግሞ “ከነገሩ ፆም እደሩ!” ልል። አልቀናኝም ነበር። የአገልግሎት ማብቂያ ጊዜውን ሳላነብ የጾም “ሂፕ ሆፕ” ብስኩት ገዝቼ ገባሁ። የetv ግን expiry date ግን መች ይሆን? :-/
 
P.S.
እዚህ ፅሁፍ ላይ ያለው ነገር በሙሉ ትናንት ምሽት በአንድ የተጋቢኖ ዝግጅት ጊዜ ውስጥ (ምናልባት 15 ደቂቃዎች?) የሆነ እንጂ ፈጠራ አይደለም። ….ማስታወቂያዎቹን ግን ቃል በቃል አይደለም የገለበጥኳቸው።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s