ዛሬ፥ በልጅነታችን ለመልካም ምኞት መግለጫ የምንስላቸው አበባዎች፥ ስዕሎች፥ ፎርሞች፥ ትዝ አሉኝ።
ከቡሄ በኋላ የምንጠመደው ፎርሞችን በመንደፍ፣ በማባዛትና ቀለም በመቀባት ነበር። በተለያዩ ዲዛይኖች በA4 ወረቀቶች ላይ ስለን እናዘጋጃለን… ስዕል ላይ ጎበዝ ያልሆነ ደግሞ ጎበዝ ለሆኑት እየተላላከ ያስላቸዋል። ወይ ደግሞ የተሳሉትን በሳንቲም ገዝቶ ያዘጋጃል።

ጳጉሜን 5 ቀን የፎርም ቆጠራ እና የገቢ ቅድመ ስሌት ቀን ነበር። ከሰሞኑ በቀለም የተጨማለቀው እጅም በዚህ ቀን ተፈቅፍቆም ቢሆን ይጠራ ነበር። ከዚያ ሲነጋ፥ በየጎረቤትና ዘመድ ቤት “እንኳን አደረሳችሁ” እየተባለ አበባ ይሰጣል። ቀኑ ረፍዶ አበባ ያልወሰድኩባቸው (ረስ…ቼ) ቤት ሰዎች ይቆጡኝ እንደነበር ትዝ ይለኛል። …ቤትም፥ “ኧከሌ ቤት ውሰድ” እያሉ ች የረሳሁትን ያስታውሱኝ ነበር። ሴቶቹም አዲስ የተገዛላቸውን ልብስ በዋዜማው ለብሰው “አበባዮሽ” እያሉ በየቤተዘመዱና ጎረቤቱ ቤት እየዞሩ ይጨፍሩ ነበር።
ነበር…. ነበር…. ነበር….!?
በርግጥ አበባዮሽ የሚጨፍሩ ጥቂት ልጆች ዛሬም ይታያሉ። ለዛና አጨፋፈሩ ግን እየተበላሸ እየተበላሸ፣ ስሜቱም እየቀዘቀዘ፣ እየቀዘቀዘ ነው የመጣው። ሰዉም ለልጆቹ የሚሰጠው ምላሽ፥ ነገሩን ከልመና ጋር እያቀራረበው የሚያሳፍራቸውም ይመስለኛል። ….አበባ የሚስል ልጅ ግን፥ እንጃ! እስኪ ሲነጋ ይመጣልን አበባ ይኖር እንደው እንጠብቃለን።
….ወላጆችም ልጆቻቸውን እንዲህ ባሉ የበዓል እንቅስቃሴዎች ላይ እንዲሰማሩ የሚፈቅዱ አይመስለኝም። ከማጣትና ከመሳጣት ጋር ሲያገናኙት ይስተዋላል። ሆኖም ግን፥ በዓልና ባህል ከማግኘትና ከማጣት ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። እናም፥ ከማሸማቀቅና ከመከልከል ይልቅ ሊያበረታቷቸው ይገባል። አበባ ሲስሉ ቀለም እናቀብላቸው…. አበባዮሽ ሲሉ ትክክለኛውን ዜማ እናስተላልፍላቸው….
“ሰዶ ማሳደድ ካማረህ፥ ዶሮህን በቆቅ ለውጥ” ይባላል፥… እናም፥ ኋላ ማሳደዱ እንዳያደክመን፥ እየጠፉ ያሉ ባህሎቻችንን እንንከባከብ። ስለመዝለቃቸው እንምከር።
እንቁጣጣሽ!