ዴቭ ኢዝ ዴድ!… (የልጅነት መሳጭ ጆሮ)

ልጅ እያለን የውጭ ሙዚቃዎችን ስንሰማ እንደተባለው ሳይሆን እንደቀለለን ነበር የምንደግመው። ዝም ብለን ድምፁን ተከትለን ዘፋኙ ያለ የመሰለንን ተቀብለን እናስተጋባለን። ራሳችን አስማምተን በምናወጣው ድምፅ ተደስተን ማጀቢያ ቆርቆሮና ዙሪያችን ያለ ለመደብደብ ብቁ የሆነን እቃ ሁሉ እየደበደብን፥ ያረጁ ጎማዎች ላይ እግራችንን ትይዩ በልቅጠን እንዘላለን፤ ክብ ሰርተን እንናጣለን፤ ተደርድረን እንወዘወዛለን…

ሙዚቃው አማርኛ ወይም የሌላ የሀገር ውስጥ ብሔር ከሆነና ግጥሙን ባናውቀው ግድ የለንም ነበር። እንደፈለገው አፋችንን እያላቀቅን በአንድ ዓይነት ስሜት ውስጥ ገብተን፥ የተባለ የሚመስለንን ቃል ለማውጣት እንሞክራለን… በምርጫ እስክንጣላ፣ ቋንቋችን እስኪደበላለቅ፣ ፀሐይ ፀሐይ እስክንል፣ ፀሐይ እስክትጠልቅ፣ ላባችን ጠብ እስኪል ድረስ ነዋ! ሙዚቃ የሰማ፥ “ተው” ቢሉት የት ይሰማል?! — ውብ የልጅነት ‘ኪነት፥ ኪነት’፥ ‘ሕብረ ትርዒት፥ ሕብረ ትርዒት’ ጨዋታ…

…ደግሞ ለኪነት ጨዋታ ጊዜያችን፥ ሙዚቃ ሸክፈን እንድንመጣ በማሰብ ከቤተሰብ ተደብቀን ‘ባቡር መንገድ’ ሄደን ሙዚቃ ቤት በራፍ ላይ ተኮልኩለን አፋችንን ከፍተን ካለምርጫ እናዳምጥ ነበር። የቸብ ቸቦ ሙዚቃ ሲመጣም ከመካከላችን ብድግ ብሎ ቢቱን ተከትሎ የሚናጥና ደናሽም አይጠፋም ነበር። ከዚያ ስንመለስ አፋችን ላይ የቀረውን ሙዚቃ እየተጯጯኽን ወይም ውስጥ ውስጡን እያንጎራጎርን ወደቤት እናቀጥነዋለን… (እንዲህ ባቡር መንገዱን ከከርሰ ምድር ለማውጣት ቁፋሮው ሳይጀመር በፊት፥ እናቶቻችን የመኪናውን መንገድ “ባቡር መንገድ” ነበር የሚሉት።)

በጣም ካልራቁት ብናይ፥ ማርክ ሞሪሰን “but you did… but you did…” ሲል “በች ዩጂጅ… በች ዩጂጅ” እንላለን፤ “በት ዮዲት በት ዮዲት” ብሎ የሚሰማም ነበር… (ዛሬም ሳስበው የሚገርመኝ ግን፥ በተለያየ ጊዜ የሰማነውንም በተመሳሳይ መልኩ ነበር የምንሰማውና ደግመን የምንለው።) “you lied to me, but I do…but I do…” ሲል፥ “ዩ ላይ ቶሚ በሻዱ በሻዱ….” ብለን እንደግማለን… “yes I tried… yes I tried…” የሚለውን፥ “የሳት ራት…. የሳት ራት…” ብለን እንቀጥላለን…

“all those times I said that I loved you” ሲል ደግሞ “የሹቄ ሹቄ ባሳሎሜ” ብለን እየቀወጥነው ነገር ዓለሙን እናሾቀዋለን… ቀለሙ ከዜማው ጋር ስምም ይሁንልን እንጂ ያን ረጅሙን ለማጣራት ማን ይታገላል? ምናልባት ደግሞ ሙዚቃውን አንዴ በቴሌቪዥን፣ ሬዲዮ፣ ወይ ደግሞ ሙዚቃ ቤት በራፍ ላይ ሲያልፍም ሊሆን ይችላል የምንሰማው… እናም፥ የሰማናቸውን እንደተረዳናቸው ሆነን ሙዚቃውን እናነካካዋለን። ጭንቀታችን ሁሉ የሙዚቃውን ስልትና ምት ለመጠበቅ ነበር…

ያም ሆኖ ግን በሙዚቃው ልጅነታችንና የቋንቋ ችሎታችን ሳያግደን እንዝናናለን። ከፍ ከፍ ያሉትንም እናዝናናለን። (የሙዚቃ የዓለም ቋንቋነትም በዚያው ነበር የተገለጠልን… ብለን እንቀጥል? ሄሄሄ….) ዛሬ ዘፋኞቹንና ትክክለኛ ግጥማቸውን የማላውቃቸው፥ ግን ዛሬም በዜማ ከራሴ ጋር ተስማምቼ የምላቸው ብዙ ሙዚቃዎች አሉ…

ለምሳሌ፥ ዳርና ዳሩን በማናውቀው ሙዚቃ “ሞጃዬ ሞጃ…ኤሄ ሞጃ” እያልን ሰፈሩን ቀጥ አድርገነዋል… ቴሌቪዥን የነበራቸውን የሞጃ ልጆች አብሽቀንበታል። ብዙም ባልገባን ዜማ እየጮኽን… “አምቤባ” እያልን የሰፈሩን ሰው በሳቅ አፍርሰነዋል… የቦብ ማርሌይን “could you beloved”፥ “ኩጁ ቢላ…. አን ቢላ…” እያልን አብደንበታል፤…

የAvin and the Chipmunksን “ፈንኪ ታውን” ሙዚቃ ተከትለን፥ “ጋራሙቫ” ብለን በቀልባችን የሰራነውን የልጅነት ጋራ ዞረናል… ሙዚቃው ቀጥሎ “Won’t you take me to, Funkytown” እያለ የሚደጋግምበትን ቦታ፥

ኮቱ ጃኬቱ ቆሽሿል፥
ነገ በኦሞ ይታጠባል

ብለን ለጆሮ ብቻ ሳይሆን ለቀልብም የሚመስል ስሜት ሰጥተን አብደንበታል።….

talk about,
talk about,
talk about….

ሲል፥…

ቆሽሿል፣
ቆሽሿል፣
ቆሽሿል….

ብለን በስሜት ጮኸናል።
ዘፋኙ በፈረንሳይኛ “comment tu t’appele…” እያለ ሲያቀነቅን፥

ጎማው ሲቃጠል፥
ዝም አትበል…
ቡሄ ቡሄ… ኤሄ ቤምባ!

ብለን ተወዝውዘናል።
እውቋ ካናዳዊቷ ሴሊን ዲዮን….

Where does my heart beat now
Where is the sound…

….ብላ ተመስጣና ተጨንቃ የጠፋባትን የልቧን የወትሮ ሁኔታ በውብ የዜማ ቀመር ስትጠይቅ፣ ስትፈልግ…. እኛም:

ዌሪዝላ ሃፒ ናው….
ዌሪዚሳ አአአ….

ብለን፥ ስሜቷን ሰርቀን፣ ቋንቋ ፈጥረን፥ ተንጠራርተን በስሜት ጠፍተናል።

የAce of Base ግሩፕ

All that she wants is another baby
She’s gone tomorrow boy
All that she wants is another baby

የሚለውን፥ ሙዚቃ ባስታወስን ጊዜ፥….

ኦ ዋ ሺባ… ሺዝኖት ቤቤ
ሺ ዶንት ቱሞ… ኦ ዋን ሺባ፥
ኦ ዋ ሺባ….ሺዝኖት ቤቤ ኤኤ…

እያልን፥ እንግሊዘኛውን እንዳይሆን ማድረጋችን ሳያንስ

So if you are in sight and the day is right
She’s the hunter you’re the fox

ብሎ ሙዚቃው የቀጠለበትን ቦታ፥

በዚ ቤት ግባ፥…. በዚህ ቤት ውጣ፥
….በዚ ቤት ግባ… አአ…

ብለን፥ በአማርኛ ሚክስ አድርገን በኩራት አቀንቅነነዋል። ሙዚቃውን ሚክስ ማድረጋችንን ሲያልፍ እንጂ ያኔ የት አውቀነው?- እንደዛ ነዋ የሰማነው!…መሳጭ የልጅነት ጆሮ፥ ጣፋጭ የልጅነት አንደበት!

ታዲያ የቶኒ ዊልሰን “ኒውዮርክ ሲቲ ላይፍ” ሙዚቃ ስንዘፍንም Eddyን በDave እንተካው ነበር። እንደውም ትርጉሙን ሳናውቅ ዴቭ ለሚባል ጓደኛችን የተዘፈነ እየመሰለን እርሱ ሲመጣ እናቀልጠው ነበር። …ታዲያ ዛሬ የዊልሰንን ሙዚቃ፥ እንደ ልጅነቴ “ዴቭ ኢዝ ዴድ” እያልኹ እያንጎራጎርኹኝ ከእንቅልፌ ነቃሁ። …”ዴቭ” ማለቴን ሳስተውልም ብቻዬን ሳቅሁኝ። ግን ምን አሳቀኝ?

“መለየትና ሞት ምን አንድ አደረገው?
ሞት አይሻልም ወይ ቁርጡ የታወቀው።” እያለ እያንጎራጎረ በሚያሳድግ ማህበረሰብ ውስጥ ለኖረ፥… “ያልኩት ከሚጠፋ የወለድኹት ይጥፋ” በሚል ፅኑና የቃልን ጥንካሬ በሚያሳይ ንግግር እየተቃኘ ላደገ ሰው፥ በራሱ ጊዜ አፀናሁ ካለው ዋና መንገድ ተገንጥሎ መለየት ሞት ነው። ቃልን ማጣጠፍ ሞት ነው። New york city life ቀጥሏል…

Eddy’s dead,
shot in the head for a dollar.
Who’s gonna tell his mama?
Who’s gonna tell his wife?

እህ፥ ዴቭ ኢዝ ዴድ!
But, who’s gonna tell his mama? Who’s gonna tell his wife?

አይለቀውም!

“ውሻ ወደበላበት ይጮኻል” እንዲሉ፥ ያኔ ሰለሞን ተካልኝ “ይቀጥል” ብሎ በቅሌት መቀጠሉን በይፋ ያሳወቀ ሰሞን፥… ከወሬው ርቀን ጦጣ ላለመሆን ወንድሜ ከኢንተርኔት ላይ አውርዶት እየተቀባበልንና በአግራሞት እየደጋገምን ስንሰማው ከጎረቤትም ብዙ ሰው አብሮን ነበረ።

በዚያ ሰሞን ‘ሰለሞን ተካልኝ ንስሀ ገብቶ ተጠመቀ’ የሚለው ወሬ ትኩስ ስለነበረና ‘እነርሱ ያገኙታል’ ብለው ስላሰቡ፥ ….ልክ በፊት ቴሌቪዥን ብርቅ በነበረበት ጊዜ ሰው ተሰብስቦ አንድ ቤት እንደሚያየው… ብዙ ሰውም እኛ ቤት መጥቶ ዘፈኑን ሲያዳምጠው ነበር። (ልጅነት አልፎ ሆነ እንጂ ስንቱን የጎረቤት ልጅ እናስገብርበት ነበር?!)

….ቤት የነበሩት ትንንሽ ልጆች “ይሄ እኮ፥ ኦሆ… አንድ በሉን’ ብሎ የዘፈነው ነው።” እያሉ ቤት ለትልልቆቹ ለማብራራት ያዋክቧቸዋል። “እንደውም ምን ዓይነት ዘመን ነው ዘመነ ፈጣጣ፥ ያለው” ማንም ሳይጠይቃቸው ይቀጥላሉ፤ ትልልቆቹ ግራ የተጋቡና የጠፋባቸው ሲመስላቸውም ፊታቸውን ያዩና በዜማ እያሉ ሊያስታውሷቸው ይሞክራሉ….

“ቱ ቱ… አስታወስኩት። እርሱ ነው?….አፈር ትብላ ውሻ።”

“ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባ” (መስከረሙ ከጠባ ሰንብቶም)

“እዝጎ…. ምነው በሁለት ቢላ መብላት?”

“ሞት ይሻላል! ድሮ ‘ያልኹት ከሚጠፋ የወለድኹት ይጥፋ’ ይባል ነበር። ያሁን ሰው የቃልን ጥንካሬ የት ያውቃል?”… ቤት የነበሩት ሰዎች ከሰጧቸውና ካስታወስዃቸው አስተያየቶች መካከል ናቸው።

በየመሀሉ እርስ በርስ ግጥሙን ይቀባበሉት ነበር… አንዱ ሲያወራ እንዳይልፋቸውም፥ “እሽሽ… እስኪ ዝም በይ” ምናምን እየተባባሉ በመጎሻሸም ስነስርዓት ይጠባበቁም ነበር። “ያለፈንንም ይደግሙታል። ይኸው እኔ ራሴ 3ኛዬ ነው ስሰማው ስልሽ… አትስገብገቢ” ይቀላለዳሉ….

“እውነታችሁን ነው?” ብለው ጠየቁ፥ ወዲያው…. “አዪ፥ የወለደ አልፀደቀ።…እናቱ ነች የምታሳዝነው።” አሉ እትዬ ሙሉነሽ፥ ለራሳቸው እንደሚያወሩ ሁሉ እጃቸውን አፋቸው ላይ አድርገው እያጉተመተሙ….

“አንቺ ደግሞ ማሰሪያሽ እናት ነች። ፈረደባት እቴ….በማንም እርምጥምጥ እናቱ ምን አደረገች?” አሏቸው የማሙሽ እናት….

“ኧረ ተይ አስኩ (የማሙሽ እናት ስማቸው አስካለ ነው) አሁን እንዲህ ሲያሾፍበት ዝም ይለዋል? ሲሸነግሉት ጎበዝ ካለ መቼም ጉድ ነው። ኧረ ይሄማ ስድብ ነው እንጂ… እኔ መሀይሟ እንኳን ትናንት ሲሰድበኝ የነበረ ሰው ዛሬ እንዲህ ቢለኝ ማሾፉ እንደሆነ አይጠፋኝም። ወይም ለሌላ ተንኮል ነው። እላለሁ ….ሌላ ስንቱን በማሰርና በማሳቀቅ የሰለጠኑ አይደሉ? ወይኒ ነው ሚያወርደው። እናቱማ ስንቅ ታቀብል።” አሉ እትዬ ሙሉነሽ ኮሶ እንደጠጣ ሰው ፊታቸውን አጨማደው….
[በዚህ ላይ ብዙ አስተያየቶች “ምንም አያረገውም” እና “አይለቀውም” በሚሉ ጎራዎች ተከፍለው ተሰጥተው ነበር፤ ጨዋታዬን ላለማንዛዛት ግን አልፅፈውም…]

ሙዚቃው (ከዜማው መውረድና ከግልብነቱ አንፃር ‘ማላዘን’ ብንለው ሳይሻል አይቀርም።) እየተደጋገመ ማላዘኑ ቀጥሏል….

“ይቀጥል ይቀጥል ሊቁ ሰው
ይቀጥል ጥበብ የተካነው
ይቀጥል ከፊት ሆኖ ይምራን
ይቀጥል እኛ እንከተለው”

“ሆሆ…. ምናባቱ ይንኳተታል? ኮተታም!…. ራሱን ችሎ አያወራም? እኛ ሲል ማንን ነው?” ጎልማሳዋ የእትዬ ሙሉነሽ አበልጅ ሰብለ በመገረም ጠየቀች። ማንም መልስ አልሰጣትም። ማላዘኑ ግን ቀጠለ።

“ከብልህ ጋር ጉዞ አልጠገብንምና
አሁንም ይቀጥል ይምራን እንደገና፤
በብልህ አመራሩ በዓለም ተወድሷል
ትናንት ብቻ አይደለም ዛሬም ይመረጣል።”

“እርፍ ነው! ….ተነበየው እኮ። ጎሽ! ይሄ ነበር የቀረህ… የእንግዴ ልጅ” የማሙሽ እናት ነበሩ… “ኧረ ባኮት ዝም ይበሉ የማሙሽ እናት። ተመራርጠው የጨረሱትን እኮ ነው እኛ የምናዳምቀው። እነሱ ደጋሽ፥ እያ ጠበል ቀማሽ…. ጆሮ ጠቢው ብዙ ነው…. ተናግሬያለሁ። እርሶ  ወደ እግዜሩ ኖት፤ ልጆችዎት ላይ ነገር አይምዘዙ….” አሉ እትዬ ሙሉነሽ….  እነርሱ እያወሩም ማላዘኑ ቀጥሎ  ነበር…

“እርምጃው ጅምር ነው ገና መቼ በቃን
ምርጫችን ነውና ዛሬም እርሱ ይምራን።
ውበት ካይኑ ሽፋን የፈለቀለት
እውቀት ካምሮው ውስጥ የዘለቀለት”

ብዙ ሰው ሳቀ። ሙዚቃው ሲደጋገምና ልክ እዚህ ጋርና ቅንድቡ የሚለው ጋር ሲደርስም ድጋሚ ይስቁ ነበር። “ቂቂቂ…. ወይ ካይኑ ሽፋን የፈለቀለት፤ ምንጭ ነው?” ስትል ሰብለ ሁሉም ይስቃል። “ትልቁን ሰውዬ ውበት ምናምን ይለዋል? ማፈሪያ…” ሰብለ ቀጠለች። ሰዉ ሁሉ ሳቀ።

“አይለቀውም ስልሽ” እትዬ ሙሉነሽ ነበሩ።  ማላዘኑም ቀጠለ…

“ንግግሩ ጣፋጭ ርቱዕ አንደበት
ስብህናው የፀዳ የእውነት ተምሳሌት
በለምለም ጎዳና ጉዞ ያስጀመረን
ዛሬም ይሁንልን የቀረን ስራ አለን።“

“ምናለ?” ጆሯቸውን ቀጥ አድርገው ይጠይቃሉ እትዬ ሙሉ። “ዝም በይ” እያሉ ይጎሽሟቸዋል የማሙሽ እናት ቀጣዩ  እንዳያልፋቸው እንዳደፈጡ…

“ራዕይና ጉዞው ዓላማና ግቡ
ሞላ ብሎ ያማረ ልክ እንደ ቅንድቡ”

ሌላ ሳቅ ተስተጋባ። “ማሪያምዬ! ለዚህ ነው ያቆየሽኝ ከነበሽታዬ? ቂቂ…. ወይ ቅንድቡ።” ከት ብለው ይስቃሉ የማሙሽ እናት። “የፍቅር ዘፈን ነው እንዴ? ቅንድቡ ጋር ምን ወሰደው?” ሰብለ እየተመናቀረች ጠየቀች። ዘፈኑም ማመናቀሩን ቀጥሏል…

“ሲናገር ተደማጭ በእውቀት የታጀበ
ልበ ሩህሩህ ሆኖ ሰላም ያነገበ
ህዝቡን ያስቀደመ የራስ ጉዳይ ትቶ
እንደ ሻማ ቀልጦ ለእኛ ብርሃን ሰጥቶ።”

“ቱልቱላ…. ለዚያ ነው ታዲያ መብራት ብልጭ ድርግም የሚለው? ቤቱንማ ትቶታል እኮ። እዚያ የውጭውን ጉዳይ ይበርታበት እንጂ። እንደሞኝ ተሰብስቦ ካርቦን ጉሎ ሲል ይውላል… ወይ ደግሞ ሲዘልፈንና ሲያስቅብን ይውላል…. ” ተበሳጭተው ተናገሩ እትዬ ሙሉነሽ፥… ማንም ሳይሳተፍላቸው ማላዘኑ ቀጠለ፡

“አርቆ በማሰብ በሰከነ ኧእምሮ
ማስተዋል መቻሉ ግራ ቀኙን ዞሮ
በልባዊ ዓላማው ቃል ኪዳን ፅናቱ
ብልህና አዋቂ ሆኖ መገኘቱ
ከፊት ለፊት ሆኖ ጉዞን በመምራቱ
ታይቷል ባደባባይ የአውራነት ብቃቱ።”

“እናንተዬ ይሄ ነገር ለሌላ ሰው እንዳይሆን። እርግጠኛ ናችሁ? ….ሰውዬውን ግን ያውቀዋል?” የማሙሽ እናት ጠየቁ….“የሚያውቀው ከሆነማ የት አደባባይ እንደታየ ይንገረና።”  ብለው ቀጠሉ። የማሙሽ እናት አታስመልጪኝ በሚል ስሜት “ቆይ ከስር ይነግረን ይሆናል። ምን አስቸኮለሽ?” ብለው አቋረጧቸው።

“ብሩህ ተስፋ ታየ ወጋገኑ ፈካ
ሀገር ሰላም ሆነ ወገን ሁሉ ረካ
ለእድገቱ ጎዳና ሰልፉን እየመራ
መጥቷል ቅዱሱ ሰው ፍሬውን ሊያፈራ
መለስ ብለን ስናይ ያን መንገዳችንን
እንኳንም ደግ አረግን ብልህ መምረጣችን።”

“አበስኩ ገበርኩ የእኔ ጌታ!….እግዚአብሔር ግን እንዴት ታጋሽ ነው። ፈጣሪውን ትተው ፍጡሩን ‘ቅዱስ’? ታምር አያልቅ” እትዬ ሙሉነሽ ተናገሩ። ሁሉም አስተያየቱን ጎን ለጎን አደራው።

“ኧረ አይለቀውም! ሙሉነሽ ትሙት…. ዝም ካለው ጉድ ነው። እንዲህ ሲያሾፍበት ዝም ይለዋል? ግንባር አይቶ ያስር የለ? ይሄንማ አይለቀውም….” እርሳቸው እንዲህ እየተናገሩ ማላዘኑ ከመጀመሪያው ይቀጥላል። ጨዋታውም እንዲሁ በየመሀሉ…. መልሶ መጨረሻው ላይ ሲደርስም “ኧረ አይለቀውም” ይላሉ እትዬ ሙሉነሽ።

ሰዎች የሙት ወዳጃቸውን የቀድሞ ፍቅር ሲያስታውሱ “ዛሬ አይውደደኝና ይወደኝ ነበር ይላሉ።” ….ሰለሞንን ግን ቅንድቡ ያማረው ዛሬ ቢወደው!! 🙂

Moral of the story:
ሰው በማይመስል ነገር ሲያወድሰንና ዝም ብሎ ወዳጃችን መስሎ ሲያደፍጥ ማስተዋል መልካም ነው። ማንም ባልሆነበት ነገር ቢሞገስ ሽንገላ መሆኑን አይስተውምና እኛም መስመራችንን በእውነትና ከይሉኝታ የፀዳ እናድርገው።

ሲመስለኝ፥ ወአደራ…

ሲመስለኝ
¯¯¯¯¯¯
ስንወድና ስናከብር የወዳጃችንን ቀዳዳ ደፍነን ነው የምናልፈው። ውዳችን የማይገባ ነገር ሲልና ስለተፈጠረ ግራ መጋባት ለማስረዳት ሲሰንፍ፥…“እንዲህ ማለቱ ነው፤ እንዲያ ማለቱ ነው” ብለን፥ እኛ ነን ስለርሱ የምናስረዳለትና እምነታችንን የምናድነው። ካላሰብነው/ካልጠበቅነው ሲውል ስናይ፥ ዐይናችንን ነው የምንጠራጠረው፤… ክፉ ሲናገር ስንሰማ፥ ስለ ጆሯችን የጤና ችግር መጨነቅ ነው የምንመርጠው፤…

…ቀድሞም አጣመን በማሰባችን ራሳችን እየወቀስንና በራሳችን እያዘንን፥ እኛው ነን፥ ሸፋፍነንና አስተካክለን የምንሰማው፤… ወዳጃችን ምንም ቢል – ከነድክመቱም – ትክክል ነው። ወደነዋላ! — ያ ጤናማ እና ሰዋዊ አስተሳሰብ ነው፤… የመውደድ ጣጣ ነው። የማክበር እዳ ነው። ….የፍፃሜ ማሰሪያ ፍቅር እንደሆነና፥… እርስ በርስ ከመዋደድ በቀርም ለማንም ዕዳ እንዳይኖርብን ተነግሮናልምና፥ ይበል!! (ወደ ቆላስይስ ሰዎች 3፥14; ወደ ሮሜ ሰዎች 3፥8)

አያድርስ!
¯¯¯¯¯¯
ሆኖም ግን ‘አያያዙን አይተህ ጭብጦውን ቀማው’ እንዲባል፥ የፍቅር ስሜቱ መጋረዱ ሲበዛ ያስፈራል፤ ….ዋ ፍቅር ሚዛኗ የተንሸራተተ ለታ!…ዋ ያ ሙሉ ልብ የጎደለ ለታ!…ዋ አፍቃሪ የደከመው ለታ! ዋ ስሜት የነጠፈ ለታ! …ዋ ከጀርባ የዶለተ ለታ! …ዋ ወረኛን ማዳመጥ የመጣ ለታ! ….ዋ ችሎ፣ ችሎ፥ ያፈረጠው ለታ!…. ዋ ወዳጅ ፍቅሩ እንደተቃለለበትና እንደ ተራ (for granted) እንደተወሰደበት የተሰማው ለታ!….ዋ መዋደድ ከንቱ! …ዋ ከህልም እንደመንቃት፥ የሆነ እውነት እንደተገለጠለት የተሰማው ለታ!…
ዋ…
ዋ መዋደድ ከንቱ!
ዋ ሰውነት ብላሽ!
ዋ መቻል ልፍስፍስ!…

አ – ያ – ድ – ር – ስ – !

ወዳጅነት?!
¯¯¯¯¯¯¯¯

…ደግሞ መውደዳችን እንዲታመን የወደድነው ሰው ልክ ባልሆነበት ሁኔታ ባንናገር፥ የወደድን መምሰላችን ሁሉ ሽንገላ መስሎ ነው የሚታየው። ፍቅርም በቅጡ ሲሆን ነው መልካም፤ ከነጥንካሬውም ሩቅ ይጓዛል። የወደድነው ሰው ከመስመር ሲወጣ፥ በማክበር ‘ተመለስ’ የማለትና የመገሰፅ ሞራሉ ከሌለን ግን ፍቅር ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል…. አብሮነት ንፋስ ይመታዋል…. ከወዳጅ ጋር አስተሳሳሪው ማሰሪያ ገመድ ፍቅር መሆኑ እየቀረ በፍርሀት ይተካል፤ …’ቢሄድስ? ባጣውስ?…’ ሌላም ብዙ ጥያቄ ይኮለኮልና በፍርሀት ይሸብባል፤ በራስ ወዳድነት ይለጉማል፤…

…የወደድን ያከበርነው ሰው መንገዱን ሲስት እኛ ካልመለስነው ማን ይመልሰዋል?!…- ሌላውማ ይስቅበታል። ሌላውማ ከጀርባው ይመክርበታል፤…. ሌላውማ ከባላጋራዎቹ ጋር ይሳለቅበታል። …ወደነዋልና ሌላው ሰው እኛ የወደድነው ሰው ከጀርባ ሲቦጨቅ መስማትስ እንዴት ያማል?! ዛሬ ነገር ዓለሙ ያስጠላ እንደው እንዴትስ ያሳፍራል?!… ዋ ትናንት ከንቱ! ዋ ሽንገላ ብላሽ!
.
.
.

እናም፥ አ-ደ-ራ-!
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯

እውነተኛ ወዳጄ ቢኖር፥ በወዳጅነታችን መሀል ያልበገባውን ነገር ይጠይቀኝ!…ያጠፋሁ ሲመስለው በግልፅ ይጠቁመኝ! ይገስፀኝ! ከጆሮ ጠቢም ይጠብቀኝ! …ማስረዳት በምችልበት አስረዳለሁ…. ባጠፋሁበት ይቅርታ እጠይቃለሁ…. በአቋሜ በምፀናበት ቦታ የእኔን ሀሳብ በአመክንዮና በማስረጃ ለመደገፍ እሞክራለሁ…. በመሀሉም መስማማትን እናገኛለን፤

… አደራ! ከልጓሞቼ የሆነኛው ገመድ ወዳጆቼ እጅ ውስጥ ናትና ባክና እንዳትቀርብኝ አደራ! የእውነት እንዋደድ። የእውነት መዋደድ መደናነቅ ብቻ ሳይሆን፥ መወቃቀስና መተቻቸትም ነውና እንዳስፈላጊነቱ እርሱን እንተግብር፤ …ታዲያ ግን ወቀሳና ትችቱም፥ ክብረ ነክና ለማሳጣት ባልሆነ መልኩ ሲቀርብ ለፍሬ ነው፤ ፍቅርንም ያጠነክራል!

እንዲመስለኝና አደራዬን እንዳሳስብ ላደረጋችሁኝ ወዳጆቼ፥ ምስጋና!

ባይገርምሽ 24

ብልጭ ድርግም አይነት…
በጉም መሀል ፀሐይ፥ ወጥቶ እንደሚገባ፤
ካ’ንቺ ጋር ስገናኝ ጊዜ እንደሚሮጠው፥
ታይቶ ሳይጠገብ፥ አንጀት እንዳባባ…
ጥድፊያ ነው ፍጥረቱ፥ የጽጌ አበባ፥
እንደማይጨበጥ… ሕልም እንደመሰለ፣
ልብ እንዳሰለለ፥ እንዳነሆለለ…
እንደ ስምረታችን፣ እንደጥምረታችን፥
ስክት፣ እምር፣ እጅብ፤ ፍክት፣ ክምር… – እ-ር-ክ-ት
ቅዝዝ፣ ፍዝዝ፣ እርግፍ፤ ብትን፥ ድንግዝ… – ክ-ፍ-ት፣
ዓይኔም ትክት፣ ቅትት፣ ክርትት… -ክ-ት-ት፤
ደጅ ደጁን አያለሁ፥
እንግዳዬን ባጣ ቆሜ እጠብቃለሁ፤

አትክልተኛዬ፥ ከመስኬ ላይ ጠፍተሽ፥
ናፍቆት ስትቃርሚ፣ ፍቅር ስታርሚ፥
ተስፋ ተሸክመሽ፥ ትዝታ ስትለቅሚ…
የጥቅምት አበባ እደጄ አቆጥቁጦ፥
አክርማ ለበሰ፣ ቸግረው ቀማሚ፤
ባ’ንድ ውሎ ቀላሚ፥ ቀላልሞ ሸላሚ፤
ቀጣፊዬ ቀርተሽ፣ አራሚዬ ጠፍተሽ…
ስማትር ደጅ ደጁን፥ ቆሜ ስጠብቅሽ፥
ዝም ብዬ ስወድሽ፤…

የልቤ አበባ ሳይታጀብ ቀረ፥ ባትኖሪ ከፊቴ፤
ብትን አለ ቀልቤ፥ ከዳኝ ሰውነቴ፥
ነተበ ጉልበቴ፣ ደከመ ብርታቴ፥
ከሰመ ተስፋዬ፣ ጫጨብኝ ጉጉቴ፤
በእውቅ እንደቀለመ፥ ሳር ቅጠሉ ጥሩ፥
ሁሉ አንቺን አስታዋሽ፥ ገና ከጅምሩ፣ ወር ከመቃየሩ፤

የሳሮኑ ግርማ፥ በአደይ የተተካ፥
ጽጌ ረዳ አበባ መሀል ልቤ የፈካ፥…
ኩምሽሽ አለ ባንዴ፥ ገላው ጠወለገ፥
ሾህ፣ ግንዱ ሞገገ… ጭራሮው ሰገገ፤
ቆሜ ስጠብቅሽ፣ ዝም ብዬ ስወድሽ፥
ቀጣፊዬ ቀርተሽ፣ አራሚዬ ጠፍተሽ…
እንዴት እንደምሆን ሳስበው ከበደኝ…

ጣፋጩን ፍቅርሽን፥ የማር ወለላዬን ወይን ጠጄን ባጣ
የልቤ ጉሮሮ ደርቆ ያንገላታኛል፥ በእሾህ እንደተበጣ፤
እንደ ሱፍ አበባ ከፀሐይ ጋ እዞራለሁ፣
ወይኔን ስፈልግሽ ላይ ታች አዘግማለሁ፥
እንደ ሱፍ ነጋዴ በፀሐይ እነጉዳለሁ፥
ወይኔ መጣች እያልኩ እንከራተታለሁ፤

ወዳጄ ሆይ ድረሽ፣ ምጪ መድኃኒቴ፥ ገስግሽ ወደ ቤቴ፥
ከነማረፍረፊያሽ፥ ብቅ በይ ከመስኬ፣ ዋዪ ከአትክልቴ፤
ፍቅርሽን ልቅመሰው፥ ይንኳለል ካ’ፌ ላይ፣
¬ ይንቆርቆር ካ’ንገቴ፥ ጠብ ይበል ከአንጀቴ፥
ውስጥ ውጩን ይንፏለል፥ ይከልበስ ከላዬ፥
¬ ይፍሰስ ከአከላቴ፣ ይውረድ ከደረቴ፤

አቤቱ፥ የአሰራሩ ጥበብ… ማር ይፈልቃል ካ’ፍሽ፣
ወይን ይወርዳል ካ’ይንሽ፥ ሾላ ከምላስሽ፥ ሮማን ከጉንጭሽ፥
የውበቴ እመቤት፣ ልዩ የደም ገንቦ… ወፍ ያብዳል ሲያስብሽ፥
ይደነቃቀፋል፣ እልም ስልም ይላል፥
¬ ወንዝ ይቆማል ሲያይሽ፤ ይከተራል ፊትሽ፤

በይ ውረጅ እንውረድ፥ ገፅሽ ገፄን ይንካ፤ ታጠቂ ልታጠቅ፥ ‘እኔክሽ እኔካ’፤
የልብሽን ጡቱን አጉርሽኝ በሞቴ፥ ለዓለም ዓለም ልርካ፥ ለይኩን፣ ለይኩን፤
ልኑር ልንጠላጠል፣ ልሰብሰብ ልጠለል፣… ከፍቅር ማማዬ፥ ከመውደዴ ዋርካ፣
በእንብርክክ ላመስግን፥ ውዴን እጅ ልንሳ “ሰላም ለኪ” ልበል፥ “አሰላማለይካ”፤

ከረጣባው ቦታ፥… ከወይኑ ጎን ውዬ፥ ከምንጭ አቆልቁዬ
አንቺን ስጠብቅሽ፣ ዝም ብዬ ስወድሽ፥ ጥም ቆራጬን ሳስስ፥
ጠኔውን ሸኘብኝ፣ አዲስ ፀሐይ በላኝ፣ ከሰለ ገላዬ፥
የወይን ተክሌ ሆይ፥ ድረሽልኝ ፈጥነሽ፤…
ቅጠልሽ ይንዠርገግ፥ ዳሱን ተከትሎ ፥
አፌ ውስጥ ይሰንቀር ፍሬሽ ተንከባልሎ፥
ባንቺ ጥላ ልድመቅ፥ ገራርጂልኝ ቶሎ፤

የጫካ እንኮዬ፥… የጫካ ቡና፣ ማር… የጫካ ዘቢቤ፥
ተሰማምረሽ ውጪ፥ ከቤት ተረጫጪ፣ ዋዪ ከመደቤ፥
ንገሺ ከልቤ… ውበቴ ሆይ ምጪ፥ ተከሰች ዓለሜ፥
ክረምት ሄዶ በጋ፥ ሲገባ እኔም ልረፍ፤ ልዳን ከሕመሜ፤
እንባዬ ይታበስ፥ ጉንጬ ባንቺ ይፍካ፥
ዓለሙ ይሽኮርመም፥ አፌም ባፍሽ ይርካ፥
ቃላችን ይንቆርቆር፥ ፍሬያችን ይጎምራ፥
ሳር ቅጠል ያሸብሽብ፥ እናዚም በጋራ፣
ተገለጭ የእኔ ውድ፥ በወርሀ ጽጌ ካ’በቦቹ መክረሽ፤
ዝም ብዬ ስወድሽ፤ ቆሜ ስጠብቅሽ፤

በወርቅ ተለብጦ፣ በፍቅር ተላቁጦ ልቤ ሲንከወከው፥
ማረፊያው ነይለት፥ መልክሽን አሳይው፣ ድምፅሽን አሰሚው፥
ወይናችን ይለምልም፥ ወይኔ ማለት ይቅር ድረሽና አካብቢው፤
በክብረት ተውበሽ፣ በእንቁ ድሪ ደምቀሽ፣ አምረሽ ተንቆጥቁጠሽ፥
ናርዶሴ ድረሺ፣… ሜሮኔ ፍሰሺ፤…
ልዩ ከርቤ፣ እጣኔ… ከልቤ ላይ ጢሺ፤
ፍሙ ተንተርክኮ ሲፍለቀለቅ ጊዜ፥ ማጤሻው ላይ ደምቆ፥
አንቺን አንቺኑ ሲል፥ “እኔን እኔን” በይው አትቅሪበት ናፍቆ፥
እኔም ደስ ይበለኝ…. በሽታዬ ይጥፋ፣ በሽታው ልፈወስ፣
ገላዬ ይታጠን፣ በላቦቱ ልርጠብ፣ በፍቅርሽ ልታደስ፤
ይበለን ደስ ደስ… አንድ እንሁን በቃ፥ ፍቅር እንጋባ፥
¬ ላባችን ይቃባ፣ ሀሴት እንቋደስ፣ መዓዛ እንቃመስ፤

በምድረ በዳው ላይ ቀጥ ብለሽ ውጪ፥
ላይ ታች፥ ተንቀሳቀሽ፥ በቀመር አርግጂ፥
በቁጥር ተንሳፈሽ፣ በቁጥር ውረጂ፥
ዝቅ ብለሽ ሂጂ፥ ከፍ ብለሽ ምጪ፣
እኔን አስከትለሽ በፍቅር አሳብጂ፤
ላይ ታች፣ ቀኝ ግራ፥… ስምም ባለ ስራ፥
በስልት በተቃኘ በፍቅር ዳንኪራ፤
እንወዝወዝ አብረን እንዝመት በጋራ፤

ዓለሙ ጉድ ይበል በእኔና አንቺ ጥምረት፣
በእኔና አንቺ ስምረት፣ በቋንቋችን ውበት፥
በመደቡ ጽጌ፥ ጓዳችን በሚለው የሊባኖስ ሽቶ፤
እንደ ጉድ ይግረመው፥ ይየን ተጠራርቶ፥
ይየን አጮልቆ፣ ይየን ተንጠራርቶ
ይደመም ዘለዓለም፥ ዓለም አፉን ከፍቶ!

የእኔን ዓለም ማያ፥
የእኔን መደምደሚያ!
ዝምምም…. ብዬ ስወድሽ፥
ቆሜ ስጠብቅሽ!

/ዮሐንስ ሞላ/