ብልጭ ድርግም አይነት…
በጉም መሀል ፀሐይ፥ ወጥቶ እንደሚገባ፤
ካ’ንቺ ጋር ስገናኝ ጊዜ እንደሚሮጠው፥
ታይቶ ሳይጠገብ፥ አንጀት እንዳባባ…
ጥድፊያ ነው ፍጥረቱ፥ የጽጌ አበባ፥
እንደማይጨበጥ… ሕልም እንደመሰለ፣
ልብ እንዳሰለለ፥ እንዳነሆለለ…
እንደ ስምረታችን፣ እንደጥምረታችን፥
ስክት፣ እምር፣ እጅብ፤ ፍክት፣ ክምር… – እ-ር-ክ-ት
ቅዝዝ፣ ፍዝዝ፣ እርግፍ፤ ብትን፥ ድንግዝ… – ክ-ፍ-ት፣
ዓይኔም ትክት፣ ቅትት፣ ክርትት… -ክ-ት-ት፤
ደጅ ደጁን አያለሁ፥
እንግዳዬን ባጣ ቆሜ እጠብቃለሁ፤
አትክልተኛዬ፥ ከመስኬ ላይ ጠፍተሽ፥
ናፍቆት ስትቃርሚ፣ ፍቅር ስታርሚ፥
ተስፋ ተሸክመሽ፥ ትዝታ ስትለቅሚ…
የጥቅምት አበባ እደጄ አቆጥቁጦ፥
አክርማ ለበሰ፣ ቸግረው ቀማሚ፤
ባ’ንድ ውሎ ቀላሚ፥ ቀላልሞ ሸላሚ፤
ቀጣፊዬ ቀርተሽ፣ አራሚዬ ጠፍተሽ…
ስማትር ደጅ ደጁን፥ ቆሜ ስጠብቅሽ፥
ዝም ብዬ ስወድሽ፤…
የልቤ አበባ ሳይታጀብ ቀረ፥ ባትኖሪ ከፊቴ፤
ብትን አለ ቀልቤ፥ ከዳኝ ሰውነቴ፥
ነተበ ጉልበቴ፣ ደከመ ብርታቴ፥
ከሰመ ተስፋዬ፣ ጫጨብኝ ጉጉቴ፤
በእውቅ እንደቀለመ፥ ሳር ቅጠሉ ጥሩ፥
ሁሉ አንቺን አስታዋሽ፥ ገና ከጅምሩ፣ ወር ከመቃየሩ፤
የሳሮኑ ግርማ፥ በአደይ የተተካ፥
ጽጌ ረዳ አበባ መሀል ልቤ የፈካ፥…
ኩምሽሽ አለ ባንዴ፥ ገላው ጠወለገ፥
ሾህ፣ ግንዱ ሞገገ… ጭራሮው ሰገገ፤
ቆሜ ስጠብቅሽ፣ ዝም ብዬ ስወድሽ፥
ቀጣፊዬ ቀርተሽ፣ አራሚዬ ጠፍተሽ…
እንዴት እንደምሆን ሳስበው ከበደኝ…
ጣፋጩን ፍቅርሽን፥ የማር ወለላዬን ወይን ጠጄን ባጣ
የልቤ ጉሮሮ ደርቆ ያንገላታኛል፥ በእሾህ እንደተበጣ፤
እንደ ሱፍ አበባ ከፀሐይ ጋ እዞራለሁ፣
ወይኔን ስፈልግሽ ላይ ታች አዘግማለሁ፥
እንደ ሱፍ ነጋዴ በፀሐይ እነጉዳለሁ፥
ወይኔ መጣች እያልኩ እንከራተታለሁ፤
ወዳጄ ሆይ ድረሽ፣ ምጪ መድኃኒቴ፥ ገስግሽ ወደ ቤቴ፥
ከነማረፍረፊያሽ፥ ብቅ በይ ከመስኬ፣ ዋዪ ከአትክልቴ፤
ፍቅርሽን ልቅመሰው፥ ይንኳለል ካ’ፌ ላይ፣
¬ ይንቆርቆር ካ’ንገቴ፥ ጠብ ይበል ከአንጀቴ፥
ውስጥ ውጩን ይንፏለል፥ ይከልበስ ከላዬ፥
¬ ይፍሰስ ከአከላቴ፣ ይውረድ ከደረቴ፤
አቤቱ፥ የአሰራሩ ጥበብ… ማር ይፈልቃል ካ’ፍሽ፣
ወይን ይወርዳል ካ’ይንሽ፥ ሾላ ከምላስሽ፥ ሮማን ከጉንጭሽ፥
የውበቴ እመቤት፣ ልዩ የደም ገንቦ… ወፍ ያብዳል ሲያስብሽ፥
ይደነቃቀፋል፣ እልም ስልም ይላል፥
¬ ወንዝ ይቆማል ሲያይሽ፤ ይከተራል ፊትሽ፤
በይ ውረጅ እንውረድ፥ ገፅሽ ገፄን ይንካ፤ ታጠቂ ልታጠቅ፥ ‘እኔክሽ እኔካ’፤
የልብሽን ጡቱን አጉርሽኝ በሞቴ፥ ለዓለም ዓለም ልርካ፥ ለይኩን፣ ለይኩን፤
ልኑር ልንጠላጠል፣ ልሰብሰብ ልጠለል፣… ከፍቅር ማማዬ፥ ከመውደዴ ዋርካ፣
በእንብርክክ ላመስግን፥ ውዴን እጅ ልንሳ “ሰላም ለኪ” ልበል፥ “አሰላማለይካ”፤
ከረጣባው ቦታ፥… ከወይኑ ጎን ውዬ፥ ከምንጭ አቆልቁዬ
አንቺን ስጠብቅሽ፣ ዝም ብዬ ስወድሽ፥ ጥም ቆራጬን ሳስስ፥
ጠኔውን ሸኘብኝ፣ አዲስ ፀሐይ በላኝ፣ ከሰለ ገላዬ፥
የወይን ተክሌ ሆይ፥ ድረሽልኝ ፈጥነሽ፤…
ቅጠልሽ ይንዠርገግ፥ ዳሱን ተከትሎ ፥
አፌ ውስጥ ይሰንቀር ፍሬሽ ተንከባልሎ፥
ባንቺ ጥላ ልድመቅ፥ ገራርጂልኝ ቶሎ፤
የጫካ እንኮዬ፥… የጫካ ቡና፣ ማር… የጫካ ዘቢቤ፥
ተሰማምረሽ ውጪ፥ ከቤት ተረጫጪ፣ ዋዪ ከመደቤ፥
ንገሺ ከልቤ… ውበቴ ሆይ ምጪ፥ ተከሰች ዓለሜ፥
ክረምት ሄዶ በጋ፥ ሲገባ እኔም ልረፍ፤ ልዳን ከሕመሜ፤
እንባዬ ይታበስ፥ ጉንጬ ባንቺ ይፍካ፥
ዓለሙ ይሽኮርመም፥ አፌም ባፍሽ ይርካ፥
ቃላችን ይንቆርቆር፥ ፍሬያችን ይጎምራ፥
ሳር ቅጠል ያሸብሽብ፥ እናዚም በጋራ፣
ተገለጭ የእኔ ውድ፥ በወርሀ ጽጌ ካ’በቦቹ መክረሽ፤
ዝም ብዬ ስወድሽ፤ ቆሜ ስጠብቅሽ፤
በወርቅ ተለብጦ፣ በፍቅር ተላቁጦ ልቤ ሲንከወከው፥
ማረፊያው ነይለት፥ መልክሽን አሳይው፣ ድምፅሽን አሰሚው፥
ወይናችን ይለምልም፥ ወይኔ ማለት ይቅር ድረሽና አካብቢው፤
በክብረት ተውበሽ፣ በእንቁ ድሪ ደምቀሽ፣ አምረሽ ተንቆጥቁጠሽ፥
ናርዶሴ ድረሺ፣… ሜሮኔ ፍሰሺ፤…
ልዩ ከርቤ፣ እጣኔ… ከልቤ ላይ ጢሺ፤
ፍሙ ተንተርክኮ ሲፍለቀለቅ ጊዜ፥ ማጤሻው ላይ ደምቆ፥
አንቺን አንቺኑ ሲል፥ “እኔን እኔን” በይው አትቅሪበት ናፍቆ፥
እኔም ደስ ይበለኝ…. በሽታዬ ይጥፋ፣ በሽታው ልፈወስ፣
ገላዬ ይታጠን፣ በላቦቱ ልርጠብ፣ በፍቅርሽ ልታደስ፤
ይበለን ደስ ደስ… አንድ እንሁን በቃ፥ ፍቅር እንጋባ፥
¬ ላባችን ይቃባ፣ ሀሴት እንቋደስ፣ መዓዛ እንቃመስ፤
በምድረ በዳው ላይ ቀጥ ብለሽ ውጪ፥
ላይ ታች፥ ተንቀሳቀሽ፥ በቀመር አርግጂ፥
በቁጥር ተንሳፈሽ፣ በቁጥር ውረጂ፥
ዝቅ ብለሽ ሂጂ፥ ከፍ ብለሽ ምጪ፣
እኔን አስከትለሽ በፍቅር አሳብጂ፤
ላይ ታች፣ ቀኝ ግራ፥… ስምም ባለ ስራ፥
በስልት በተቃኘ በፍቅር ዳንኪራ፤
እንወዝወዝ አብረን እንዝመት በጋራ፤
ዓለሙ ጉድ ይበል በእኔና አንቺ ጥምረት፣
በእኔና አንቺ ስምረት፣ በቋንቋችን ውበት፥
በመደቡ ጽጌ፥ ጓዳችን በሚለው የሊባኖስ ሽቶ፤
እንደ ጉድ ይግረመው፥ ይየን ተጠራርቶ፥
ይየን አጮልቆ፣ ይየን ተንጠራርቶ
ይደመም ዘለዓለም፥ ዓለም አፉን ከፍቶ!
የእኔን ዓለም ማያ፥
የእኔን መደምደሚያ!
ዝምምም…. ብዬ ስወድሽ፥
ቆሜ ስጠብቅሽ!
/ዮሐንስ ሞላ/