ሲመስለኝ፥ ወአደራ…

ሲመስለኝ
¯¯¯¯¯¯
ስንወድና ስናከብር የወዳጃችንን ቀዳዳ ደፍነን ነው የምናልፈው። ውዳችን የማይገባ ነገር ሲልና ስለተፈጠረ ግራ መጋባት ለማስረዳት ሲሰንፍ፥…“እንዲህ ማለቱ ነው፤ እንዲያ ማለቱ ነው” ብለን፥ እኛ ነን ስለርሱ የምናስረዳለትና እምነታችንን የምናድነው። ካላሰብነው/ካልጠበቅነው ሲውል ስናይ፥ ዐይናችንን ነው የምንጠራጠረው፤… ክፉ ሲናገር ስንሰማ፥ ስለ ጆሯችን የጤና ችግር መጨነቅ ነው የምንመርጠው፤…

…ቀድሞም አጣመን በማሰባችን ራሳችን እየወቀስንና በራሳችን እያዘንን፥ እኛው ነን፥ ሸፋፍነንና አስተካክለን የምንሰማው፤… ወዳጃችን ምንም ቢል – ከነድክመቱም – ትክክል ነው። ወደነዋላ! — ያ ጤናማ እና ሰዋዊ አስተሳሰብ ነው፤… የመውደድ ጣጣ ነው። የማክበር እዳ ነው። ….የፍፃሜ ማሰሪያ ፍቅር እንደሆነና፥… እርስ በርስ ከመዋደድ በቀርም ለማንም ዕዳ እንዳይኖርብን ተነግሮናልምና፥ ይበል!! (ወደ ቆላስይስ ሰዎች 3፥14; ወደ ሮሜ ሰዎች 3፥8)

አያድርስ!
¯¯¯¯¯¯
ሆኖም ግን ‘አያያዙን አይተህ ጭብጦውን ቀማው’ እንዲባል፥ የፍቅር ስሜቱ መጋረዱ ሲበዛ ያስፈራል፤ ….ዋ ፍቅር ሚዛኗ የተንሸራተተ ለታ!…ዋ ያ ሙሉ ልብ የጎደለ ለታ!…ዋ አፍቃሪ የደከመው ለታ! ዋ ስሜት የነጠፈ ለታ! …ዋ ከጀርባ የዶለተ ለታ! …ዋ ወረኛን ማዳመጥ የመጣ ለታ! ….ዋ ችሎ፣ ችሎ፥ ያፈረጠው ለታ!…. ዋ ወዳጅ ፍቅሩ እንደተቃለለበትና እንደ ተራ (for granted) እንደተወሰደበት የተሰማው ለታ!….ዋ መዋደድ ከንቱ! …ዋ ከህልም እንደመንቃት፥ የሆነ እውነት እንደተገለጠለት የተሰማው ለታ!…
ዋ…
ዋ መዋደድ ከንቱ!
ዋ ሰውነት ብላሽ!
ዋ መቻል ልፍስፍስ!…

አ – ያ – ድ – ር – ስ – !

ወዳጅነት?!
¯¯¯¯¯¯¯¯

…ደግሞ መውደዳችን እንዲታመን የወደድነው ሰው ልክ ባልሆነበት ሁኔታ ባንናገር፥ የወደድን መምሰላችን ሁሉ ሽንገላ መስሎ ነው የሚታየው። ፍቅርም በቅጡ ሲሆን ነው መልካም፤ ከነጥንካሬውም ሩቅ ይጓዛል። የወደድነው ሰው ከመስመር ሲወጣ፥ በማክበር ‘ተመለስ’ የማለትና የመገሰፅ ሞራሉ ከሌለን ግን ፍቅር ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል…. አብሮነት ንፋስ ይመታዋል…. ከወዳጅ ጋር አስተሳሳሪው ማሰሪያ ገመድ ፍቅር መሆኑ እየቀረ በፍርሀት ይተካል፤ …’ቢሄድስ? ባጣውስ?…’ ሌላም ብዙ ጥያቄ ይኮለኮልና በፍርሀት ይሸብባል፤ በራስ ወዳድነት ይለጉማል፤…

…የወደድን ያከበርነው ሰው መንገዱን ሲስት እኛ ካልመለስነው ማን ይመልሰዋል?!…- ሌላውማ ይስቅበታል። ሌላውማ ከጀርባው ይመክርበታል፤…. ሌላውማ ከባላጋራዎቹ ጋር ይሳለቅበታል። …ወደነዋልና ሌላው ሰው እኛ የወደድነው ሰው ከጀርባ ሲቦጨቅ መስማትስ እንዴት ያማል?! ዛሬ ነገር ዓለሙ ያስጠላ እንደው እንዴትስ ያሳፍራል?!… ዋ ትናንት ከንቱ! ዋ ሽንገላ ብላሽ!
.
.
.

እናም፥ አ-ደ-ራ-!
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯

እውነተኛ ወዳጄ ቢኖር፥ በወዳጅነታችን መሀል ያልበገባውን ነገር ይጠይቀኝ!…ያጠፋሁ ሲመስለው በግልፅ ይጠቁመኝ! ይገስፀኝ! ከጆሮ ጠቢም ይጠብቀኝ! …ማስረዳት በምችልበት አስረዳለሁ…. ባጠፋሁበት ይቅርታ እጠይቃለሁ…. በአቋሜ በምፀናበት ቦታ የእኔን ሀሳብ በአመክንዮና በማስረጃ ለመደገፍ እሞክራለሁ…. በመሀሉም መስማማትን እናገኛለን፤

… አደራ! ከልጓሞቼ የሆነኛው ገመድ ወዳጆቼ እጅ ውስጥ ናትና ባክና እንዳትቀርብኝ አደራ! የእውነት እንዋደድ። የእውነት መዋደድ መደናነቅ ብቻ ሳይሆን፥ መወቃቀስና መተቻቸትም ነውና እንዳስፈላጊነቱ እርሱን እንተግብር፤ …ታዲያ ግን ወቀሳና ትችቱም፥ ክብረ ነክና ለማሳጣት ባልሆነ መልኩ ሲቀርብ ለፍሬ ነው፤ ፍቅርንም ያጠነክራል!

እንዲመስለኝና አደራዬን እንዳሳስብ ላደረጋችሁኝ ወዳጆቼ፥ ምስጋና!