“ውሻ ወደበላበት ይጮኻል” እንዲሉ፥ ያኔ ሰለሞን ተካልኝ “ይቀጥል” ብሎ በቅሌት መቀጠሉን በይፋ ያሳወቀ ሰሞን፥… ከወሬው ርቀን ጦጣ ላለመሆን ወንድሜ ከኢንተርኔት ላይ አውርዶት እየተቀባበልንና በአግራሞት እየደጋገምን ስንሰማው ከጎረቤትም ብዙ ሰው አብሮን ነበረ።
በዚያ ሰሞን ‘ሰለሞን ተካልኝ ንስሀ ገብቶ ተጠመቀ’ የሚለው ወሬ ትኩስ ስለነበረና ‘እነርሱ ያገኙታል’ ብለው ስላሰቡ፥ ….ልክ በፊት ቴሌቪዥን ብርቅ በነበረበት ጊዜ ሰው ተሰብስቦ አንድ ቤት እንደሚያየው… ብዙ ሰውም እኛ ቤት መጥቶ ዘፈኑን ሲያዳምጠው ነበር። (ልጅነት አልፎ ሆነ እንጂ ስንቱን የጎረቤት ልጅ እናስገብርበት ነበር?!)
….ቤት የነበሩት ትንንሽ ልጆች “ይሄ እኮ፥ ኦሆ… አንድ በሉን’ ብሎ የዘፈነው ነው።” እያሉ ቤት ለትልልቆቹ ለማብራራት ያዋክቧቸዋል። “እንደውም ምን ዓይነት ዘመን ነው ዘመነ ፈጣጣ፥ ያለው” ማንም ሳይጠይቃቸው ይቀጥላሉ፤ ትልልቆቹ ግራ የተጋቡና የጠፋባቸው ሲመስላቸውም ፊታቸውን ያዩና በዜማ እያሉ ሊያስታውሷቸው ይሞክራሉ….
“ቱ ቱ… አስታወስኩት። እርሱ ነው?….አፈር ትብላ ውሻ።”
“ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባ” (መስከረሙ ከጠባ ሰንብቶም)
“እዝጎ…. ምነው በሁለት ቢላ መብላት?”
“ሞት ይሻላል! ድሮ ‘ያልኹት ከሚጠፋ የወለድኹት ይጥፋ’ ይባል ነበር። ያሁን ሰው የቃልን ጥንካሬ የት ያውቃል?”… ቤት የነበሩት ሰዎች ከሰጧቸውና ካስታወስዃቸው አስተያየቶች መካከል ናቸው።
በየመሀሉ እርስ በርስ ግጥሙን ይቀባበሉት ነበር… አንዱ ሲያወራ እንዳይልፋቸውም፥ “እሽሽ… እስኪ ዝም በይ” ምናምን እየተባባሉ በመጎሻሸም ስነስርዓት ይጠባበቁም ነበር። “ያለፈንንም ይደግሙታል። ይኸው እኔ ራሴ 3ኛዬ ነው ስሰማው ስልሽ… አትስገብገቢ” ይቀላለዳሉ….
“እውነታችሁን ነው?” ብለው ጠየቁ፥ ወዲያው…. “አዪ፥ የወለደ አልፀደቀ።…እናቱ ነች የምታሳዝነው።” አሉ እትዬ ሙሉነሽ፥ ለራሳቸው እንደሚያወሩ ሁሉ እጃቸውን አፋቸው ላይ አድርገው እያጉተመተሙ….
“አንቺ ደግሞ ማሰሪያሽ እናት ነች። ፈረደባት እቴ….በማንም እርምጥምጥ እናቱ ምን አደረገች?” አሏቸው የማሙሽ እናት….
“ኧረ ተይ አስኩ (የማሙሽ እናት ስማቸው አስካለ ነው) አሁን እንዲህ ሲያሾፍበት ዝም ይለዋል? ሲሸነግሉት ጎበዝ ካለ መቼም ጉድ ነው። ኧረ ይሄማ ስድብ ነው እንጂ… እኔ መሀይሟ እንኳን ትናንት ሲሰድበኝ የነበረ ሰው ዛሬ እንዲህ ቢለኝ ማሾፉ እንደሆነ አይጠፋኝም። ወይም ለሌላ ተንኮል ነው። እላለሁ ….ሌላ ስንቱን በማሰርና በማሳቀቅ የሰለጠኑ አይደሉ? ወይኒ ነው ሚያወርደው። እናቱማ ስንቅ ታቀብል።” አሉ እትዬ ሙሉነሽ ኮሶ እንደጠጣ ሰው ፊታቸውን አጨማደው….
[በዚህ ላይ ብዙ አስተያየቶች “ምንም አያረገውም” እና “አይለቀውም” በሚሉ ጎራዎች ተከፍለው ተሰጥተው ነበር፤ ጨዋታዬን ላለማንዛዛት ግን አልፅፈውም…]
ሙዚቃው (ከዜማው መውረድና ከግልብነቱ አንፃር ‘ማላዘን’ ብንለው ሳይሻል አይቀርም።) እየተደጋገመ ማላዘኑ ቀጥሏል….
“ይቀጥል ይቀጥል ሊቁ ሰው
ይቀጥል ጥበብ የተካነው
ይቀጥል ከፊት ሆኖ ይምራን
ይቀጥል እኛ እንከተለው”
“ሆሆ…. ምናባቱ ይንኳተታል? ኮተታም!…. ራሱን ችሎ አያወራም? እኛ ሲል ማንን ነው?” ጎልማሳዋ የእትዬ ሙሉነሽ አበልጅ ሰብለ በመገረም ጠየቀች። ማንም መልስ አልሰጣትም። ማላዘኑ ግን ቀጠለ።
“ከብልህ ጋር ጉዞ አልጠገብንምና
አሁንም ይቀጥል ይምራን እንደገና፤
በብልህ አመራሩ በዓለም ተወድሷል
ትናንት ብቻ አይደለም ዛሬም ይመረጣል።”
“እርፍ ነው! ….ተነበየው እኮ። ጎሽ! ይሄ ነበር የቀረህ… የእንግዴ ልጅ” የማሙሽ እናት ነበሩ… “ኧረ ባኮት ዝም ይበሉ የማሙሽ እናት። ተመራርጠው የጨረሱትን እኮ ነው እኛ የምናዳምቀው። እነሱ ደጋሽ፥ እያ ጠበል ቀማሽ…. ጆሮ ጠቢው ብዙ ነው…. ተናግሬያለሁ። እርሶ ወደ እግዜሩ ኖት፤ ልጆችዎት ላይ ነገር አይምዘዙ….” አሉ እትዬ ሙሉነሽ…. እነርሱ እያወሩም ማላዘኑ ቀጥሎ ነበር…
“እርምጃው ጅምር ነው ገና መቼ በቃን
ምርጫችን ነውና ዛሬም እርሱ ይምራን።
ውበት ካይኑ ሽፋን የፈለቀለት
እውቀት ካምሮው ውስጥ የዘለቀለት”
ብዙ ሰው ሳቀ። ሙዚቃው ሲደጋገምና ልክ እዚህ ጋርና ቅንድቡ የሚለው ጋር ሲደርስም ድጋሚ ይስቁ ነበር። “ቂቂቂ…. ወይ ካይኑ ሽፋን የፈለቀለት፤ ምንጭ ነው?” ስትል ሰብለ ሁሉም ይስቃል። “ትልቁን ሰውዬ ውበት ምናምን ይለዋል? ማፈሪያ…” ሰብለ ቀጠለች። ሰዉ ሁሉ ሳቀ።
“አይለቀውም ስልሽ” እትዬ ሙሉነሽ ነበሩ። ማላዘኑም ቀጠለ…
“ንግግሩ ጣፋጭ ርቱዕ አንደበት
ስብህናው የፀዳ የእውነት ተምሳሌት
በለምለም ጎዳና ጉዞ ያስጀመረን
ዛሬም ይሁንልን የቀረን ስራ አለን።“
“ምናለ?” ጆሯቸውን ቀጥ አድርገው ይጠይቃሉ እትዬ ሙሉ። “ዝም በይ” እያሉ ይጎሽሟቸዋል የማሙሽ እናት ቀጣዩ እንዳያልፋቸው እንዳደፈጡ…
“ራዕይና ጉዞው ዓላማና ግቡ
ሞላ ብሎ ያማረ ልክ እንደ ቅንድቡ”
ሌላ ሳቅ ተስተጋባ። “ማሪያምዬ! ለዚህ ነው ያቆየሽኝ ከነበሽታዬ? ቂቂ…. ወይ ቅንድቡ።” ከት ብለው ይስቃሉ የማሙሽ እናት። “የፍቅር ዘፈን ነው እንዴ? ቅንድቡ ጋር ምን ወሰደው?” ሰብለ እየተመናቀረች ጠየቀች። ዘፈኑም ማመናቀሩን ቀጥሏል…
“ሲናገር ተደማጭ በእውቀት የታጀበ
ልበ ሩህሩህ ሆኖ ሰላም ያነገበ
ህዝቡን ያስቀደመ የራስ ጉዳይ ትቶ
እንደ ሻማ ቀልጦ ለእኛ ብርሃን ሰጥቶ።”
“ቱልቱላ…. ለዚያ ነው ታዲያ መብራት ብልጭ ድርግም የሚለው? ቤቱንማ ትቶታል እኮ። እዚያ የውጭውን ጉዳይ ይበርታበት እንጂ። እንደሞኝ ተሰብስቦ ካርቦን ጉሎ ሲል ይውላል… ወይ ደግሞ ሲዘልፈንና ሲያስቅብን ይውላል…. ” ተበሳጭተው ተናገሩ እትዬ ሙሉነሽ፥… ማንም ሳይሳተፍላቸው ማላዘኑ ቀጠለ፡
“አርቆ በማሰብ በሰከነ ኧእምሮ
ማስተዋል መቻሉ ግራ ቀኙን ዞሮ
በልባዊ ዓላማው ቃል ኪዳን ፅናቱ
ብልህና አዋቂ ሆኖ መገኘቱ
ከፊት ለፊት ሆኖ ጉዞን በመምራቱ
ታይቷል ባደባባይ የአውራነት ብቃቱ።”
“እናንተዬ ይሄ ነገር ለሌላ ሰው እንዳይሆን። እርግጠኛ ናችሁ? ….ሰውዬውን ግን ያውቀዋል?” የማሙሽ እናት ጠየቁ….“የሚያውቀው ከሆነማ የት አደባባይ እንደታየ ይንገረና።” ብለው ቀጠሉ። የማሙሽ እናት አታስመልጪኝ በሚል ስሜት “ቆይ ከስር ይነግረን ይሆናል። ምን አስቸኮለሽ?” ብለው አቋረጧቸው።
“ብሩህ ተስፋ ታየ ወጋገኑ ፈካ
ሀገር ሰላም ሆነ ወገን ሁሉ ረካ
ለእድገቱ ጎዳና ሰልፉን እየመራ
መጥቷል ቅዱሱ ሰው ፍሬውን ሊያፈራ
መለስ ብለን ስናይ ያን መንገዳችንን
እንኳንም ደግ አረግን ብልህ መምረጣችን።”
“አበስኩ ገበርኩ የእኔ ጌታ!….እግዚአብሔር ግን እንዴት ታጋሽ ነው። ፈጣሪውን ትተው ፍጡሩን ‘ቅዱስ’? ታምር አያልቅ” እትዬ ሙሉነሽ ተናገሩ። ሁሉም አስተያየቱን ጎን ለጎን አደራው።
“ኧረ አይለቀውም! ሙሉነሽ ትሙት…. ዝም ካለው ጉድ ነው። እንዲህ ሲያሾፍበት ዝም ይለዋል? ግንባር አይቶ ያስር የለ? ይሄንማ አይለቀውም….” እርሳቸው እንዲህ እየተናገሩ ማላዘኑ ከመጀመሪያው ይቀጥላል። ጨዋታውም እንዲሁ በየመሀሉ…. መልሶ መጨረሻው ላይ ሲደርስም “ኧረ አይለቀውም” ይላሉ እትዬ ሙሉነሽ።
ሰዎች የሙት ወዳጃቸውን የቀድሞ ፍቅር ሲያስታውሱ “ዛሬ አይውደደኝና ይወደኝ ነበር ይላሉ።” ….ሰለሞንን ግን ቅንድቡ ያማረው ዛሬ ቢወደው!! 🙂
Moral of the story:
ሰው በማይመስል ነገር ሲያወድሰንና ዝም ብሎ ወዳጃችን መስሎ ሲያደፍጥ ማስተዋል መልካም ነው። ማንም ባልሆነበት ነገር ቢሞገስ ሽንገላ መሆኑን አይስተውምና እኛም መስመራችንን በእውነትና ከይሉኝታ የፀዳ እናድርገው።