የወዳጅ ኀዘን…?!

ሜሪ አርምዴ፥ “ኧረ የጁ የጁ” በሚለው ሙዚቃዋ ላይ፥…. “አይገድልም መስሎሀል የወዳጅ ኀዘን?!” ትላለች…. እውነቷን ነው፤… – ይመስለኛል…. የወዳጅ ኀዘን ይገድላል። በመበደሉ ምክንያት ሰዎች/ተበዳዮች አምርረው ያለቀሱበት ሰው አይሳካለትም። የቆመ፣ የገደለ፣ ያሰቃየ፣ ያሰረ… ቢመስለውም አይዘልቅም። …ለዚያም፥ ብዙ ጊዜ ኅሊናውን ቢንቅ እንኳን፥ ከቀልቡ ያለ ሰው በልቡም ቢሆን ግፍ ይፈራል።

አምላክ ግፍ ይቆጥራል። …በህሊና ቢስነቱና በጭካኔው ሰው ያቃሰተበት ሰው ዋጋውን ያገኛል፤ በተራው ያቃስታል። እዚያው በዚያው አይወራረድ እንጂ፥ እግዚአብሔር ይፈርዳል። እርግማን ያሽመደምዳል። …እግዚአብሔር በግፈኞች ፍርድ መጠን ፈርዶ፥ እግዚአብሔር መሆኑን እንዲያውቁ እንደሚያደርግም በትንቢት ተነግሮናል። …ያው ለሚያምኑት ነው! (የማታምኑ እምነት ማለት አመክንዮና ሀልዮት የማይደረድሩለት፣ ማረጋገጫ የማይሹለት እውቀትና ከራስ ጋር መስማማት ነውና፥ አትድከሙ። አለማመናችሁን እመኑትና፥ ይህን ባላየ ላሽ በሉት።) …በበኩሌ፥ እንዲህ ተነግሮኛልና እንዲህ አምናለሁ! እንዲህ ሲሆን ተመልክቻለሁና እንዲህ አውቃለሁ!

…ሆኖም ግን እግዚአብሔር ለሚፈርድ፥ ሰው ጣልቃ መግባት የለበትም። “ኧከሌ ዋጋውን አገኘ” በማለት ውስጥ፥ ‘እኔ ግን ያልጠፋሁት ስለምሻል ነው’ የሚል ያልተፃፈ መልዕክት ይነበባልና፥ ግብዝነት ምንም አይረባም። ግፈኛ ሰው/አካል ላይ የሆነው ሲሆን “እሰይ” ብለው በተመለሱበት ቅፅበት፥ ራስ ላይ የሚሆነውን አያውቁም። …“ስለዚህ እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ።” ~ (1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 10:12) ተብሎ ተነግሮናልና፥ ደግሞ ስለሌላው አቋቋም እንከንና አወዳደቅ ከማውራታችን በፊት፥ የራሳችንን አቋቋም መሻልና ፅናት ብንመለከት መልካም ነው።
.
.
.
እግዚአብሔር ሁሉን የሚችል (omnipotent) እና ሁሉም ቦታ የሚገኝ፥ ምሉእ በኩልሄ (omnipresent) መሆኑን ባምንም፥ …በሳውዲ አረቢያ ግዛት ላይ የደረሰውን በደል ‘የእግዚአብሔር ቅጣት ነው/አይደለም’ አልልም። ይህን የማልለው አሁን በማልዘረዝራቸው ብዙ ምክንያቶችና ጥያቄዎችም የተነሳ ነው። …ያ ለምን እንደሆነ የሚያውቀው እግዚአብሔር ብቻ ነውና በአሰራሩ ላይ ጣልቃ አልገባም። ይልቅስ ጥያቄዬን ለባለቤቱ አሳስብ ዘንድ እመኛለሁ።

በእነርሱ ላይ በሆነውና ካለሀጢአታቸው በ“አባት እዳ ለልጅ” ብሂል ለሚጠፉና ለሚጎሳቆሉ ነፍሳት ግን አዝናለሁ። ተንፈራግጠው ራሳቸውን ማዳን ስለማይችሉ ህፃናትና አዛውንት (አስራ ምናምን ሚሊዮን የሚሆኑ) አዝናለሁ። በመካከሉ መጠጊያና መሸሸጊያ ለሌላቸው፥ ምናልባትም እርዳታ ቢያሻቸውና ቢደረግ ለኗሪና ለቤተዘመዱ ሁሉ ከተደረገ በኋላ ለሚደረስላቸው ስደተኞች (የተረፉ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ) አዝናለሁ። …ካለጥፋቱ ስለሚቀጣ ሁሉ ከልቤ አዝናለሁ። ይህ የስሜት ጉዳይ ነውና፥ ለትችትና ወቀሳ አይበቃም። ማዘን ባይቻል እንኳን ያዘነን ሰው ‘ለምን?’ ማለትም ጥቅም የለውም።

በጌቶችና በአሽቃባጮቻቸው ክፋት የተነሳ መላው አዲስ አበባ ላይ እንዲህ ያለ የተፈጥሮ አደጋ ቢደርስ እንደማልደሰት፥ እንዲሁ በዚያም አልደሰትም። ደግሞስ በዚያ ለመደሰትና፣ “እሰይ” ለማለት እኔ ማን ነኝ? “ጌታም እንዲህ አለው፦ አሁን እናንተ ፈሪሳውያን የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ታጠራላችሁ፥ ውስጣችሁ ግን ቅሚያና ክፋት ሞልቶበታል” ~ 11:39 የሉቃስ ወንጌል ….ታዲያ ለጥፋት ጎርፍ ከታዘዘ፥ እኛስ በየትኛው ንፅህናችን ነው የምንተርፈው?

በሌላው ጉስቁልና በመደሰትና፣ በመስፈር ግን፥ ማዘንና በዚያው መስፈሪያ መሰፈር ሊመጣም ይችላልና፥… “አቤቱ፥ እንደ በደላችን ሳይሆን እንደቸርነትህ”!
አሜን!!
.
.
.
P.S.
ለአንዳንድ ጥቃቅንና አነስተኛ ተሳዳቢዎች: ….እንግዲህ እኔ እንደመሰለኝ ነውና፥ “ለምን እንዲህ ይመስልሀል?” ማለቱ ጉንጭ ማልፋት ነው። ይልቅስ፥ እናንተ የሚመስላችሁ ከዚህ የተለየ ከሆነ፥ ሳትሳደቡና ሳትበሳጩ፥ በማክበር ከጎኑ ቁጭ አድርጉት። የሚማር የትም/ከማንም ይማራልና፥ ይመዝን ዘንድ እንዲረዳው አንፃር ይሆነዋል።

ኢአማኒ (atheist) ብትሆኑ ደግሞ፥ አለማመናችሁን በንግግርና የእኔን ማመን በመንቀፍና በንፅፅር (comparing and contrasting) ሳይሆን፥… ባለማመን ፀንታችሁና፥ በሕይወታችሁ ኖራችሁት አሳዩኝ።

ሰላም ለሁሉም!!

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s