ንፉግ…!

ብር አምባሯን ሽቶ፣ ደፍሮ ለተጠጋ፣1471767_472678226186549_957489850_n
ሲግጣት ለኖረ፥ ለጅበ – ሰብ መንጋ፣
– ፍስሀ ስትታትር፣ ተድላ ስትተጋ፣
አዱኛ ስታጭቅ፣ ሲሳይ ስትሞላ፣
ዓለም ስታሳምር፣ ስታደልብ ገላ፤

ስጋዋን ቸርችራ፣ መታትራ፥ – ገብራ፣
ላቧን አንጠፍጥፋ፣ ደሟን አንቆርቁራ፣
ቆዳዋን ገሽልጣ፣ አጥንቷን ሰንጥራ፣
ተግጣ… ተግጣ… አልቃ፣ ተፈርፍራ፥
አዳርሳ ስትጨርስ…

ለታማኝ ጠባቂው፣ ለምስኪን ወገኔ፣67086_164321147058957_380093110_n
– ለሰነቀው ፍቅር፣ ለሸከፈው ወኔ፥
አንዠቱ ሲላወስ፣ ሆዱን መሸበቢያ፣
ለከርታታ ነፍሱ፣ ለዐይኖቹ ማረፊያ፣
ለስሜቱ ማ’ተም፣ ለልቡ መንቧቻ፣
ለውዱ ስልቻ፣ ለፍቅሩ ማንገቻ፣
ታንበሸብሻለች፥…
አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀለሟን ብቻ፤

/ዮሐንስ ሞላ/

 

 

ተረት ተረት…

በባዶ ቤት፥…ካደመቀው እሳት ብቻ፥
(ለዚያውም ጢስ የበዛበት፥
ሚንጨላጨል በ’ርጥብ እንጨት)
ከእሳቱ ዙሪያ — ጉልቻ…
ጉልቻው ጎን፥ — መወዘቻ፥
(ለወጉ የተሰተረ፥
ክክ የለሽ፥ ግብር አልባ
ሌጣውን የተገተረ…)

እኔና እናት ዓለሜ፥ ተቀምጠን ወለሉ ላይ፥
እሷ – ዓይን ዓይኔን፤… እኔ – እሳት ሳይ፥
ከላይ፥… ጣሪያዋ ደክማ፣
መውደቅ ይሻላት፥ ዘምማ፥
(ስታሾፍብን ነገር…)
ካጠገባችን ወስከምቢያ፥… እላዩ ላይ አሹቁ፥
የባቄላው፥… – ኀይል አድቅቁ፥
ጥርስ የሚይዝ፥… የሚያስጠማው…
ውኀ አንሶት፣ ጨው የበዛው፤
ስጡኝ ስጡኝ የሚያሰኘው…
በበረሀ፥…
በሌለበት ጭላጭ ውኀ፥ ‘ውኀ፣ ውኀ…’
ጠኔ አብርዱ፣ ፈስ አድምቁ…
አጫዋቹ፥ ዜማ አርቅቁ፥
ዝም አደፍርሱ፥ ድብርት አርቁ፥
ብሶት አጅቡ፣ ቁዘማ አሙቁ፤…
አሹቁ…

ቁርጥም ቁርጥምጥም ሳደርገው፥
እንዳያልቅብኝ ሳስቼ፣ ስጫወትበት ስከካው፤
እማንም ሲቆረጥማት፥…
በጉበኑ ሽንቁር ሾልኮ፥ ሲጫወትባት ቁርጥማት፥
እኔ እንድበላ ብላ፥
ቁርጠማውን እንደጠላ፥
እንደ ጠገበች መስላ…
ተኮራምታ፥….
እናት ዓለሜ ዘንካታ…
ቁጭ ብላ ከነኩራቷ፣
ከነታጠፈ አንጀቷ፥…
ተረት ትነግረኛለች…

እዛው በእዛው አሰማምራ፥
ከእኔ ስለ እኔ ፈጣጥራ፥
ጨዋታ ወጉን ጨማምራ፥
ምክር ተግሳፁን ቆጣጥራ፥
ፍቅር መውደዷን ሞጃጅራ፥…
“ተረት ተረት” ትለኛለች፥…
መሰረት በሌለው ቤት ውስጥ፥ “የመሰረት” እላታለሁ፥
ላም፣ በረት በሌለው ቤት ውስጥ “የላም በረት” እላታለሁ፤
ተረቷን ትቀጥላለች፥…
“እናትና ልጅ ነበሩ…”
– “እሺ”
“በአንዲት ደሳሳ ጎጆ ፥ በነጻ ፍቅር ሲኖሩ…”
– “እሺ”
“ሲኖሩ ሲኖሩ…”
– “እሺ”
“ከእለታት ባንድ ቀን…”
– “እሺ”
.
.
.
በመከራ አንድ ቀን፣ በችጋር አንድ ቀን፥
በአፈና አንድ ቀን፣ በበደል አንድ ቀን፥
በስደት አንድ ቀን፣ በድብደባ አንድ ቀን
በእስር አንድ ቀን፣ በውሸት አንድ ቀን…
ከእለታት ባንድ ቀን…
የባሎቿን ክፋት፥ የልጆቿን ልፋት፥
የተገላባጩን፣ አጎብዳጁን ብዛት፥
የውስጥ እግር ላሹን፥ ያሸርጋዱን ብዛት፥…
ያንንም… ያንንም… ታጫውተኛለች፤
የገዛ ታሪኳን በተረት መስላ፥
የገዛ ታሪኬን፥ ‘ተረት ተረት’ ብላ፤

ደግሞም ከስር ከስሩ፥ ‘ይሻል ቀን ይመጣል’፥
ብላ እያፅናናችኝ፥…
እምነት አስሰንቃ፣ ተስፋ እያስያዘችኝ፥
ታጫውተኛለች፥
እኔም “እሺ” እላለሁ…
“እሺ” ልበል እንጂ፥ ሌላ ምን አውቃለሁ?
ባውቅስ ምን እላለሁ?…ብልስ ማን ሊሰማኝ?
ከአምባው የገነኑት፥ አቆርቋዥ ገዦቿ፥
አቃቤ ሰቀቀን፣ ስግብግብ ሻጮቿ፥
ሆደ ዝርጣጦቹ፥ ሽግናም ባሎቿ፥
ተስፋዬን ሊቀሙ፥…. ሳቄን ሊያጨልሙ፥
ጉልበቴን ሊያደክሙ፥ ይንጠራወዛሉ…
ልጅነቴን ዳምጠው፥ ጉጉቴን ሊቀሙ፥ ይተራመሳሉ…
እናስ ምን እላለሁ?
– “እሺ” ልበል እንጂ እስከጊዜው ድረስ፥
.
.
ተረቷን ቀጥላ፥
ስደካክም ጊዜ የጨረሰች መስላ፥
“ተረቴን መልሱ
አፌን በዳቦ አብሱ።” ብላ ታፌዛለች…
ታሳቅቀኛለች…
ዳቦ እየቸገራት ለቅምሻ ለዝክር
አሹቅ እያገባች፥ ለራት ምሳ ግብር፥
“ዳቦ” ትለኛለች፥
– እንቆቅልሽ እማ፥
– ቅኔ እናት ዓለም
.
.
ይኸው ነው ወጋችን…
.
.
ስንኖር፥ ስንኖር፣
ስንኖር፥ ስንኖር…

ከእለታት ባንድ ቀን፥
ወጉ ደርሶኝ ዛሬ፥
አወራላት ጀመር፥ ተረት ቀማምሬ፥
ከራሷ መዝዤ፣ ለርሷው ቆጣጥሬ፥
ለራሷ ሰፍሬ፥ ከራሷ ቆንጥሬ፥
ወንድም እህቶቼን ልጆቿን ናፍቄ፥
በባሎቿ አፍሬ፥…
እንዲህ ጀመርኩላት….

“ተረት ተረት…”
– “የላም በረት”
“እንዴ… የላም በረት? …የቱን ላም ነው?
በረት ቢኖር ላም የለበት…
ላሙ ቢኖር እረኛ አልባ፥
ከተኩላ ጋር የሚያደባ፤
…የለም በረት”
– “ኡፍ… አታድርቀኝ፥ ይሁንልህ የመሰረት”
“የትኛው መሰረት እማ?
ያንኛው መሰረት፣ ሲፈርስ ያላየሽው?
ባሎችሽ ሲንዱት፥ ቆመሽ ያፋረስሽው?
ፈርተሽ ያላስጣልሽው?
በተበላ ቁማር፥…
ስጋ፣ ደም፣ ቆዳ፣ አጥንት የተገበረለት?
ያንኛው መሰረት?”
– “ኡፍ… ቀጥል”
“እሺ”
– “እሺ”…
“አንዲት ጋለሞታ…”
– “እሺ”
“ብዙ የወለደች፥ ብዙ መንታ መንታ፥
ልጆቿን የጣለች፣ ብዙ ባል አግብታ፥
ይህን ያህሉ ሞተው፣ ይህን ያህሉን ፈትታ፥
ይህን ያህሉ ታስረው፣ ይህን ያህሉን ረስታ”
– “እሺ”
“ከርታታ ልጆቿ…
በባሎቿ ክፋት ተማረው ሲነጉዱ፥
ማደሪያ ፍለጋ፥ ከቤት ሲሰደዱ፥ ጎረቤት ሲሄዱ…”
– “እሺ”
“ሲሄዱ ሲሄዱ ሲሄዱ…
ሲሄዱ ሲሄዱ ሲሄዱ…”
– “እሺ…”
“ሲሄዱ ሲሄዱ ሲሄዱ…”
– “እሺ”
.
.
“ተረቴን መልሱ” እንዳልላት፥ ፈራሁ…
ዳቦ የላት ከእጇ፥
አፌ እንዳይታበስ፥ በእግረ ሙቅ በዱላው፥
በጉልቤ ባሎቿ…
እናም ዝም ብዬ፥
“ልጆቿ በየመንገዱ፥
ሲሄዱ…
ሲሄዱ…
ሲሄዱ…
ሲሄዱ….
.
.
/ዮሐንስ ሞላ/