ብር አምባሯን ሽቶ፣ ደፍሮ ለተጠጋ፣
ሲግጣት ለኖረ፥ ለጅበ – ሰብ መንጋ፣
– ፍስሀ ስትታትር፣ ተድላ ስትተጋ፣
አዱኛ ስታጭቅ፣ ሲሳይ ስትሞላ፣
ዓለም ስታሳምር፣ ስታደልብ ገላ፤
ስጋዋን ቸርችራ፣ መታትራ፥ – ገብራ፣
ላቧን አንጠፍጥፋ፣ ደሟን አንቆርቁራ፣
ቆዳዋን ገሽልጣ፣ አጥንቷን ሰንጥራ፣
ተግጣ… ተግጣ… አልቃ፣ ተፈርፍራ፥
አዳርሳ ስትጨርስ…
ለታማኝ ጠባቂው፣ ለምስኪን ወገኔ፣
– ለሰነቀው ፍቅር፣ ለሸከፈው ወኔ፥
አንዠቱ ሲላወስ፣ ሆዱን መሸበቢያ፣
ለከርታታ ነፍሱ፣ ለዐይኖቹ ማረፊያ፣
ለስሜቱ ማ’ተም፣ ለልቡ መንቧቻ፣
ለውዱ ስልቻ፣ ለፍቅሩ ማንገቻ፣
ታንበሸብሻለች፥…
አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀለሟን ብቻ፤
/ዮሐንስ ሞላ/