ነፍስ ኄር ሚካያ በኃይሉ (ከ1969 – 2006 ዓ/ም)

ሚካያ በኃይሉን ከሀሳቤ ልለያት አልቻልኹም። በየመሀሉ ገጭ ትልብኛለች። …አንዠቴን በላችው። 15001_103357143037030_6673039_nከተፈጥሮ ጋር አጋጨችኝ። ከእምነት ጋር አፋጨችኝ። ቆሞ ከመሄድ ጋር አቃቃረችኝ። ተጠራጣሪነቴን አበዛችው። ከንቱነትን ለሌላ ብዙኛ ጊዜ አስተማረችኝ። ‘በቃ ለዚሁ ነው ይኽ ሁሉ መባከን? ይህ ሁሉ መበላለጥ? ይህ ሁሉ መገጫጨት? ይህ ሁሉ መባላት? ይህ ሁ… ሉ መሆን? ’ አሰኘችኝ። በጣም እወዳት ነበር። በጣም ማለት፥ በጣም። …በጣም ማለት፥ እንደ ሙዚቃ ወዳጅና እንደ ሙዚቀኛ አክባሪ። አልበሟ ለእኔ ብቻ የወጣ ነበር የሚመስለኝ። …ይህ ሲሰማኝ ረከሰብኝ። በጣም ረከሰብኝ። …ማለት፥ ዋጋው ረከሰብኝ።

ይሄን ሁሉ ዓለም የያዘ አልበም በዚህች ትንሽ ብር ብቻ? ይሄን ሁሉ የሙዚቃ ድግስ በዚህች ሚጢጢዬ ዲስክ አጮልቆ መታደም? ወይ ጉድ፥ ፈጣሪ የእጁ ሥራ ልዩ! …ብዬ፥ ሙዚቃ ሲቀረፅ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ ሁሉ እንዳዲስ ስገረም…. እንደልጅ ስቦርቅና ስደሳሰት…. ከዚያ ለቡዳውም ለመጋኛውም፣ ለብሶቱም ለደስታውም፣ ለእሮሮውም ለእንጉርጉሮውም፣ ለመተኛውም ለመንቂያውም፣ ለዘመዱም ለወዳጁም፣ ለክፉውም ለደጉም… ብዬ፥ ፌጦ ይመስል በርከት አድርጎ መሸከፍ እያሰኘኝ ብቻዬን ስስቅ። …ከራሴ ጋር ሲያጣላኝ።

(ይህ ስሜቴ ‘cliche’ ነው መሰለኝ። ብዙ የድሮ ሙዚቃዎችን ስሰማ፥ የትዕግስት (ኒኒ)ን አልበም ስገዛ፣ የጂጂን ሙዚቃዎች በሰማሁ ቁጥር፣ የዘሪቱን፣ የሚካኤልን፣ የቴዲ ጃ ያስተሰርያልን፣ የኢዮብን…. ሌላም ሌላም፥ ልዩነታቸው በስሜት መረቤ ልኬት ብቻ ተወስኖ፤ የሙዚቃ ባህር ላይ ከሚታዩ መደበኛ ዓሶች መካከል በሆነ ዓይነት የጣዕም ልዩነት ብቅ የሚሉ ልዩ ዓሶችን ስመለከት… ለመጀመሪያ ጊዜ ከንፈሯን እንደተሳመች ኮረዳ ጭውውው ይልብኛል።)

…ለነገሩ ስወድ እንዲህ ነኝ። ስደመም እብድ ነኝ። የሆነው ሁሉ ለእኔ ብቻ የሆነ ይመስለኝና እፍነከነካለሁ። ገራገሯን ሚካያ መጀመሪያ ያወቅዃት ሁለት ነጠላ ዜማዎቿን በለቀቀች ሰሞን አለቤሾው ላይ ከአለባቸው ተካ ጋር በነበራት የጨዋታ ጊዜ ነበር። “ሸማመተው”ም አንድ ማስተር ቅጂ ብቻ ኖሮት እርሱም እኔ ጋር ብቻ እንደሆነ እያሰብኹኝ ልቤን አሳብጥ ነበር። ሰው ቢያውቅልኝም ባያውቅልኝም፥ ለራሴ የሆነ ከፍታ ላይ እሆናለሁ። ሰው እንዳይታዘበኝ፥ “ሞኙ” ብሎ እንዳይስቅብኝ ብዬ፥ አስብና ‘የርሱንስ ማን አየ?’ ብዬ የስሜቴን የጋራነት በመገመት መለስ እላለሁ።

ሻካራ ድምጿ ከእርጋታዋ ጋር ተደምሮ፥ አስተያየትና ፈገግታዋ የቤተሰብ ይመስሉና፥ በጆሮዬ መጥታ የምታንሾካሹክልኝ እንጂ ማጫወቻ ውስጥ ከትቼ የምሰማው አይመስለኝም ነበር። በዚያም ላይ አፏ ሲኮለታተፍ ወደ ውስጥ የሚቀሩ ግጥሞችን ለመስማት አደርግ የነበረው ትግልም ሌላ መሳጭ ትዕይንት ነበረ። (ሙዚቃው ላይ ቢያናድደኝም፥ በኋላ ግን በሰጠቻቸው ቃለ መጠይቆች ላይ የእውነትም የሚኮላተፍ ነገር እንዳላት ተረድቼ ትቼዋለሁ)

…እንዲህ ያለ አቅም ኖሯት ደፋር ብትሆን ኖሮ ግን አንድ አልበም ብቻ አበርክታ ታቆም ነበር? ወይስ ስንፍና ነው? – በተለይ እንደሌለች ሳስብ ራሴን እጠይቃለሁ። ከትምህርት ዓለም በ995 ብር (ሳይቆራረጥ) የወር ደመወዝ በዩኒቨርስቲ ረዳት ምሩቅነት፥ ራስን ወደ መቻያ የሥራ ዓለም በተሸጋገርኹበት ዓመት ውስጥ የወጣው አልበሟ ብዙ እቃ ላልነበራት 1ክፍል የኪራይ ቤቴ ሲሳይ ነበረች።

ይድረስ ለማስብህ ለማልምህ ላንተ
ፍቅርህን ለማግኘት ልቤ ከዘመተ፥…

የሚለውን ሙዚቃ ስሰማ፥ ሲሻኝ በቁሙ፣ ሲሻኝ ደግሞ የተዘፈነበትን ፆታ ለራሴ ቀይሬ “ይድረስ ለማስብሽ” ብዬ አብሬያት ጮኽ ብዬ እዘፍን ነበር። …ወጣቷ አከራዬ መጥታ “ጆኒ ዛሬ ደግሞ ተነስቶብሀል” ብላ እስክታናጥበኝ ድረስ ደጋግሜ። …ለነገሩ መጥታም እንደዚያ ብላኝም ሙዚቃው ይቀጥላል። ጩኸቱ ይቀንሳል እንጂ በሀሳብ ነጉዶ ማጉተምተሙ አይቀርም። አከራዬም አልጋዬ ጫፍ ላይ ቁጭ ብላ በራሷ ዓለም ትነጉዳለች።

ጉድለቴ ባፈጠጠበትና ማማረሬ በዝቶ መሸሸጊያ ለውጥ እፈልግ በነበረበት ወቅት ሳይቀር…

ሞላልኝ፣ ሆነልኝ፣ ተሳካልኝ
ልቤ ረካ፥ መጨረሻውን አይቶ
እቅዱን አሳክቶ…

የሚለው ዜማ ልክክ ያለ ታዛ ሆኖ ደብቆኝ ያውቃል። “አይ ይሄ ሀሳቡ ከእኔ ጋር አይሄድም” ብዬ አልተውኩትም። የምሩን ቢሞላ እንደምሆንበት …ሽሽግ፣ ሽጉጥ፣ ድብቅ ብዬበት “ሞላልኝ” ብዬ በጎዶሎ አብጃለሁ። ወላ ዛሬም ድረስ የሚካያን አልበም ማዳመጥ ስፈልግ የምጀምረው ከ4ኛው ትራክ ነው። 4ኛው ትራክ ሞላልኝ ነው። …ሙዚቃ ውበቱ ይሄ ነው። ዓለም አቀፋዊ ቋንቋነቱም ሙላቱም እንዲህ ባለ ጊዜያት ይገለጣል መሰለኝ። ኦ ሚካያ!

ይቀኝልኝ ነፍስህ ለነፍሴ ዝማሬ
እድሜዬን ለካሁት በፍቅርህ ጅማሬ።

የሚለውን ሙዚቃ፥ ቀልቤን ሰብስቤ …ሰበቤ ብዬበታለሁ። ባለቤት በሌለበት እሪሪሪ ብዬ ከነስሜቱ ከንፌበታለሁ። ወላ የሰማሁት ዕለት፥ በኋላ የሆነውን ዓይነት ክሊፕ በቀልቤ ስዬ ጠፍቼ ነበር። እውነቴን ነው።

ውዴ የኔ ነህ፥ ለነጠላ ነፍሴ ተድላን እየሞላህ
ፍቅሬ ላንተ ነው እንደፀሐይ ጨረቃ ዘመኔን ላሰላህ

ብላ ከፍታ ስትወጣ፥ እኔም ፊቴን ቁጥር አድርጌ እጆቼን ዘርግቼ፣ በስሜት፥ ውዴን በመናፈቅ ተከትያታለሁ። ፍቅር አልበረክት ባለኝ ጭጋጋማ ወቅት እንኳን “ውዴ ሆነልን ብራ ቀን፥ ወረት እንደሰማይ የራቀን” ብዬ እሪሪ ብያለሁ። ሙዚቃ ነዋ!

አበባ የመሳሰሉ፥ ቀንበጥ ልጆችን ተመልክቼ ስሜቴን መቆጣጠር አቅቶኝ፤… ከወዲህ ክብር ጥበቃና ይሉኝታ፣ 24206_103543823018362_1756953_nከወዲያ ውበትና አስገዳጅ ቁመና እየፈተኑኝ እንደሁኔታው መስመር በመተላለፍ ለዚያችው ቅፅበት ባላለፈ ጨዋታ የሰው ቆንጆ ሳሽኮረምም፥… ወይ ደግሞ እንኳን ቁንጅናቸውን ፆታቸውን እንኳን ከቁብ በማልዶልበት አጣዳፊ ማኅበራዊ ወቅቶች (ለምሳሌ፥ ቦታ ጠፍቶ አቅጣጫ እንደመጠየቅ፣ ወይ ለስራ ጉዳይ በሚደረግ ውይይት ውስጥ) ሴቶቹ ታየሁ ተለከፍኹ ብለው ሲንቀባረሩ (በነገራችን ላይ ሲያናድዱኝ!) ሁኔታቸውን ከተገነዘብኹ፥…

የማነህ ቀብራራ የጌታ ልጅ መሳይ
ለሌላ እንዳይመስልህ አንተን ቆሜ ሳይህ

የሚለው ሙዚቃ ፆታው ተገልብጦ እንጂ ሌላ ምን ውልብ ሊልብኝ?

ድንገት ሲቀናኝ… ጀግና ማረኹኝ
ያ ባተሌ ያ ቆፍጣና
የስራ ሰው ያ ሳተና
ለኑሮው ሲል ደፋ ቀና
ላይ ታች ሲል ቤት ሊያቀና
ሲክብ ባየው ወደድኹት…

ስትል አብሬያት ተደምሜ፥ በፍቅር የመዘንዃቸውና የቀለሉብኝ፣ ሞላልኝ ስል የጎደሉብኝን፥… የእኔንም ልኬት – መመዘን መቅለሌን – በነሱ ዓይን ለመገመት እያሰብኹ፥ ‘ተሸውዳለች’ እያልኹ፤ ‘አመለጠችኝ’ እያልኹ፤ ‘እሷስ ምን ትል ይሆን?’ እያልኹ፥ ከራሴ ጋር ተጫውቼባቸዋለሁ።

በሰጠኸው ፍቅር፣ ልቤ ተቀማጥሎ
ሹመት ንግስናህን አላውቅበት ብሎ
ጠግቦ ጌትነቱን አልችል ብሎ
ሄደ ክብሩን ጥሎ፥ ከቤትህ ኮብልሎ…

ብላ በቁጭት እሮሮዋን ስታሰማና ዞሬ መጣሁ ስትል፥ ጨምላቅነቷን እየታዘብኹ፣ ትህትናና እምነቷን እያደነቅኹኝ፣ የጌታዋን ጌትነት እየሳልኹ …አብሬያት በሀሳብ አቀርቅሬ አንጎርጉሬያለሁ። ከዚያ በኋላ ያለውንም አስቤው ከራሴ ጋር ተጫውቻለሁ። በርሱ በኩል ሾልኬ የራሴን ጉዳዮች ጎልጉያለሁ።

ደለለኝ ደለለኝ ደለለኝ
ማሬ ነሽ ብሎ አታለለኝ
ወተቴ እያለ ሸነገለኝ
ቅቤ ምላስህ ገደለኝ።…

የሚለውን ሙዚቃ ስሰማ እቆምና፥ እግሬ መሬቱን በስልት እየረገጥኹ፣ ክሊፑን እንደሚሰራ ሰው በለስላሳ ውዝዋዜ ታጅቤ ጨሼበታለሁ። በንፅፅሩ ውበት ተደምሜያለሁ። ሰማይና ምድር የእኔ ግዛቶች የሚመስሉኝ ጊዜም ትዝ አለኝ። ወላ ክለብ ውስጥ ዲጄውን ባይኔ ተለማምጬ ደለለኝን ያስከፈትኹበት ጊዜ ብዙ ነው።

የሰው ስጋ እርም ነው ብሎ ያለው
እኔስ ልበላህ ነው በቃ ማበዴ ነው
ሰው በልተሻል የሚከሰኝ ማነው?
ምበላህ ምውጥህ ስሜ ባልጠግብህ ነው።

የሚለውን ስሰማ ደስ ይለኝና፥ ድንገት ሳቅ ያፍነኛል። ፈገግ ብዬ ነው የምጨርሰው። ትዕይንቱ ማርኮኝ ‘ና ትብላህ’ እያልኹ አብሬ እየጠራሁት። …ደግሞ ከወዲህ ውዴን ሳስብ ነይ እያልኹኝ። “የዛሬን እንጫወት የነገን አናውቅም፤ አትሰስቺው ፍቅርሽን ግድ የለሽም አያልቅም።” እያልኹ እየጎተትዃት። ስበላት ስሰለቅጣት እየታየኝ፥ ዘግንኖኝ ሳማትብ። ደግሞ በብልሀት ስቀረጥፋት። በዓይኔ በቀልቤ ስውጣት። ዓለሜን ቀይሬ በራሴ ዓለም ሳብድ። ያበድኹባቸውን ዓለሞች በዓይነ ህሊናዬ ስቃኝ ።

ያንተ መሆኑ እፈልጋለሁ
ግን እፈራሀለሁ።
የልብ እምነትና የሴት ልጅ ክብር
መተኪያ የለውም አንዴ ቢሰበር
እቀርብህና ደግሞ ይርቅሀል
ልቤ ይጨነቃል።
ድብቅ ነሽ ትላለህ ልቤን ባታገኘው
ልቤን ያገኘህ እለት ቅስሜንስ ብትሰብረው?

እያለች ስጋቷንና ጉጉቷን በጋራ፥ በአያዎ ዘይቤ፥ ልሂድ ወይስ ልቅር ዓይነት እያለች ግራ ስትጋባ። …ደግሞ ተረዳኝ ብላ ስትማፀነው። ደግሞ ሌላ ዓይነት የመወደድ ፍርጃ ስታሳየኝ። …እንዲሁ አብሬያት እንከራተታለሁ።

በሌሎቹ ሙዚቃዎቿም ብዙ! ድጋሚ ስሰማቸው ድጋሚ እየወደድዃቸው፤ ድጋሚ ስሰማቸው ድጋሚ እየናፈቅዃቸው ፈታ የምልባቸው አጃቢዎቼ። …ስሰማቸው ባለሁበት ሆኜ በስልት ልቤ ይናጣል። ሰውነቴ በስሜት ይንቀሳቀሳል። …ነጠላ ዜማዎቿም አሟቂ ጋቢዎቼ ነበሩ። ሕይወት ይቀጥላል! ልዩነቱ ሌላ አዲስ ሙዚቃ አታመጣም እንጂ፥ ሚካያ ወደፊትም በሥራዎቿ ከእኔ ጋር ነች።

ነፍስ ኄር MICAIAH BEHAILU ! ኦ ድምፅ! ኦ ብስለት! ኦ ልዩነት! ኦ ግጥም! ኦ አተያይ! ኦ ዜማ! ኦ እርጋታ!…ኦ ሚካያ!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s