ንፋስ እወዳለሁ፤…
ንፋስ ማን ይጠላል?
ከገለባ ጋራ መውደድ እንዳይደረጅ
የበራሮች ፍቅር እንዳያንቦጃቡጅ፥
እንዳያንጎላጅጅ፣
እንዳያሳር እግር፣ እጅ፤
በጊዜ ጠራርጎ ይወለውልና፥
ብርቱውን ያስቀራል፤
አቁሽሹን አብርሮ፥
ቋሚውን ያስበራል፤
አፍዝዙን ወልውሎ፥
ጥንኩሩን ያደምቃል።
ንፋስ ማን ይጠላል?!
ንፋስ እጠላለሁ፤…
ንፋስ ማን ይወዳል?
ገለባ፣ ልጣጩን፣ ጥራጊውን ሁሉ፥
ኬ’ትም ደጃፍ ዘግኖ፥
ኬ’ትም ሰፈር ለቅሞ፥
ሰውነት ላይ ጭኖ፥
ገላን አሸክሞ፥
ብርቱን ያቆሽሻል፥
ደማቁን አዳክሞ፤
መልኩን ይጋርዳል፥
ብርሃኑን ጨላልሞ።
ንፋስ ማን ይወዳል?!
ሲበሩ፣ ሲያበሩ፥
ተገትሬ ቁሜ እቀዣበራለሁ፥
ንፋስ አልወዳለሁ።
/ዮሐንስ ሞላ/
Note: Photos are found from internet.