ስለ ረ/አብራሪው ኃይለመድኅን እና ስለተወሩ መላምቶች…

ስጀምር

ባለፈው ሰኞ፥ የካቲት 10 ቀን 2006 ዓ/ም፥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነች et702hijack_coverአውሮፕላን (ET 702) መድረሻዋ ሮም ሳለ፥ ኃይለመድኅን አበራ በተባለ የ31 ዓመት ወጣት የገዛ ረዳት አብራሪዋ ተጠልፋ ጄኔቭ ማረፏን ተከትሎ፥ ብዙ ዓይነት መላምቶችንና ያልተጣሩ ሹክሹክታዎችን ስንሰማ ቆይተናል። ሁሉም በየራሱ፥ ነገሩን ለማወቅ በመጓጓትና በሁኔታው በመደናገጥ፤ እንዲሁም ነገሩን በማለባበስና በጉዳዩ ለማትረፍ በማሰብ መካከል ሆኖ፥ …እውነቱን ከባለቤቱና ከምርመራው ውጤት እስኪሰማ ድረስ፥ ሥራም እንዳይፈታ፥… ‘ይሆናል’ ብሎ የገመተውን ለመግለፅና በመረዳቱ ልክ ጉዳዩን ለመተንተን ቢሞክርም፥ ማሰሪያው ዞሮ ድፍን ያለ ነገር ነው።

የኃይለመድኅን ዓላማና ፍላጎት ጥገኝነት መጠየቅና ማግኘት ብቻ ቢሆን ኖሮ፥ እንዲህ ያለውን ውስብስብና ጉዳት የበዛበት መንገድ ሳይመርጥ፣ እርሱም አደጋ ላይ ሳይወድቅ፣ ወገኖቹን ሳያስጨንቅና ሳያሳቅቅ፣ መስሪያ ቤቱንም ሳያሸማቅቅ በራሱ መንገድ ሊያደርገው እንደሚችልና ያንን ለማድረግ ሁኔታዎችን በራሱ ማመቻቸት እንደሚችል ግን ማንም ካለአስረጅ እንደሚገነዘብ አምናለሁ። ሌሎች ሁኔታዎች ከግምት ሳይገቡ እንኳን፥ በሰላሙ ጊዜና (under normal condition) ካለምንም የተለየ ምክንያት እንዲህ ያለውን ነገር ለማድረግ እንደማይገደድ ለመረዳት፥ ለአውሮፕላን አብራሪነት ያበቃውን የማሰላሰል ብቃቱን (analytical ability) መገመት በራሱ በቂ ይመስለኛል።

«ያውራ የነበረ…!»

አውሮፕላኑ ጄኔቫ ባረፈበት ወቅት ረዳት አብራሪው ለስዊስ ፖሊስ የሰጠው ቃል ሀገሩ ውስጥ ለመኖር ስጋት ስላለበት፥ የስዊዘርላንድ መንግስት ጥገኝነት እንዲሰጠው መፈለጉን የሚገልፅ ብቻ እንደነበር ይታወቃል። ከዚህ በተጨማሪ፥ እዚያ አውሮፕላን ውስጥ ተሳፍሮ የነበረ ምህረቱ ገብሬ የተባለ ወጣት፥ በግል የፌስቡክ ገፁ ላይ ረዳት አብራሪው ኃይለመድኅን፥

Sit down Sit down…I am going to give u more oxygen,….sit down….we are on high altitude…

ሲል እንደነበርና፥ በአማርኛ ጭምር፥ “ዛሬ አምላክ ብቻ ነው የሚያድናችሁ” በማለት አጠቃላይ ሁኔታውን ገልፆ መፃፉን ከወዳጅ ተረድቻለሁ። (ለጊዜው ከፌስቡክ በመራቄ ራሴ አንብቤ አላረጋገጥኩም።) Redditor OK3n የተባለ/ች የ25 ዓመት ወጣት ተሳፋሪ፥

Everybody looked at each other, thinking what’s going on. Suddenly, a deep and angry voice talked through the cabin radio: “SIT DOWN, PUT YOUR MASKS ON, I’M CUTTING THE OXYGEN”, three times

በማለት ሁኔታውን ገልጿል/ለች። (ሙሉውን ከዚህ ያንብቡ)

ትንሳኤ vs ዓለሙ/ እህት vs አጎት

ከዚህ ውጭ የኃይለመድኅን ቤተሰቦችን በማነጋገር ረገድ፥ ከጉዳዩ ዓይነት (sensitivity of the issue) የተነሳ ምንም ዓይነት አስተያየት መስጠት እንደማይፈልጉ ተገልጿል ቢባልም፥ እህቱ እና አጎቱ (በበኩሌ፥ እውነተኛ ዝምድናቸው ላይ ጠበቅ ያለ ጥያቄ አለኝ…) ገደምዳሜው አንድ ሆኖ እርስ በርሱ የሚጣረስ አስተያየት ሰጥተዋል። – እህቱ ትንሳኤ አበራ በፌስቡክ ገጿ ላይ። (ከፌስቡክ ገጿ ላይ እንዳገኙት ገልፀው ካጋሩት ጦማሮች እንዳነበብኩት) አጎቱ ዓለሙ አስማማው ደግሞ ለAssociated Press (እዚህ ይመልከቱ). እህቱ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ እንደመንስኤ የጠቀሰችው ሁኔታ ባይኖርም፥ አጎቱ መንስኤው የሌላ አጎቱ ድንገተኛ ሞት መሆኑን ለወሬ አውታሩ ገልፀዋል።

የትንሳኤ ገለፃ የሚያጠነጥነው የወንድሟ የአእምሮ ጤና ችግር ተጠቂነትን በመግለፅና እርሱን ለማሳመን በመሞከር ነው። እንዲህ ትላለች…. (ሙሉውን ለማንበብ)

ሃይለመድህን ሁሉንም አስታዋሽ ቤተሰቡን የሚወድና ተጫዋች ሰው ነበር እስከ ቅርብ ጊዜ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ለኛ ያለውን ፍቅር ደህነታችንን በማረጋገጥና የሚያስፈልገንን ሁሉ በመታዘዝ ቢገልጽም ከዘመድ ወዳጆቹ ጋር መገናኘትና አቆመ። የወትሮው ጨዋታና ደስተኝነቱ ቀርቶ ብቸኝነትን የሚወድ ዝምተኛ ሆነ። ህይወቱ ደስታ የራቀው መሰለ። በሁኔታው ተደናግጠን ደጋግመን በመጠየቅ ያወቅነው ሊያጠቁት የሚከታተሉት ጠላቶች እንዳሉ እንደሚያምን ነው። ስልኩን እንደጠለፉት ያስባል፤ በላፕቶፑ ካሜራ ሳይቀር ያዩኛል ብሎ ስለሚሰጋ ካሜራውን ሳይሸፍን አይከፍተውም፤ ወጥቶ እስኪገባ ቤቱን ሲበረብሩ የቆዩ ስለሚመስለው ካሜራ ጠምዶ መሄድ ሁሉ ጀምሮ ነበር። ባጠቃላይ በታላቅ የመንፈስ ጭንቀት እየተሰቃየ ነው። የሚያሳዝነው ደግሞ ይህንን ጉዳቱን ለኛ ለቤተሰቡንኳ አብራርቶ አለመናገሩ ነው። ወንድሜ ለሰዎች እርዳታ ለመድረስና የሌሎች አዳኝ ለመሆን የማይታክት ሰውንጂ እንዲህ በሚያንገበግብ ስቃይ ውስጥንኳ ለራሱ አስቦ እርዳታን የሚጠይቅ ሰው አይደለም። ሁኔታውን በደበስባሳው በታወቀበት ጊዜንኳ የሚያስፈልገውን የህክምና በማቅረብ ስላልረዳነው ቤተሰቡ ሁሉ እንደግር ሳት ይከነክነዋል።እሱ ግን እንዲህ ባለ ጥልቅ የመንፈስ ጭንቀት ውስጥንኳ ለኛ አንድም ቀን ሳያስብ ቀርቶ አያውቅም።

Really?

ወረድ ብላም….

በኛ አገር መስሪያ ቤቶች የሰዎችን እውቀት ብቃትና ቁመና ሳይቀር ሲመዝኑ የዐይምሮ ጤንነት ሁኔታን አለመከታተላቸው እጅግ የሚያሳዝን ነገር ነው።

በማለት ዛሬ በልበ ሙሉነት ለመተንተንና ለማስረዳት እስኪያስችላት ድረስ፥ በወንድሟ ጤና ዙሪያ ላይ በቂ ግንዛቤ እንደነበራት የምትገልፀው እህቱ፥ ወንድሟ አስፈላጊውን ህክምና አግኝቶ ወደ መደበኛ ሕይወቱ እንዲመለስ እንደመርዳት፥ ‘ሥራ’ ብሎ ሲሄድ ዝም ብላ ስትመለከት ኖራና፥… ሊፈጠርበት ስለሚችለው ጉዳይ ሳትጨነቅ [ችግሩ የአእምሮ ሁከት ከሆነ፥ ከቤት ወጥቶ ስራ ወይንም ርቆ ባህር አቋርጦ ሲሄድ ሊደርስ የሚችልበትን ቀውስ (crises) በመገመት ስለህክምናው መምከር፤… ‘ያምናል’ እንዳለችውም፥ የእውነት ሰዎች ሊያጠቁት ይከታተሉት ከነበረም ሊደርስ የሚችልበትን አካላዊ ጥቃት በማሰብ ቀድማ ለማስቀረት መመካከር ስትችል] ችላ ብላው ኖራ፥… ዛሬ ጣቷን ቀጣሪ ድርጅቱ ላይ ትቀስራለች። አሳዛኝነቱንም አበክራ ትናገራለች።

ይሄ ለእኔ ግራ የሚያጋባ ነገር ነው። ትናንትና ችግሩን ይህን ያህል አስረድቷትና ተገንዝባ ከነበረችና ወደ ሆስፒታል ወስዳ ልትረዳው ካልቻለች እህት፥ ዛሬ ላይ ቢበዛ ከፍተኛ የሆነ ፀፀት ይጠበቅ ይሆናል እንጂ፥ እርሱን ሞያ እንደሰራ ሰው ስትተነትን መመልከት የምር ግራ የሚያጋባ ነገር ነው። ደግሞም ነገሩን ይበልጥ አሳማኝ ልታደርገው ስትል…

በተስተካከለ የዐይምሮ ጤንነት ላይ የሚገኝ ሰው ላይገባው ይችላል። እኔ ግን የሱን ግማሽ ባያክልም የተወሰነ ይህንን መሰል ችግር ስላለብኝ ህመሙን አውቀዋለሁ።

ትላለች። ይህኔ ነው ግራ መጋባቴ ስር ሰድዶ፥ “የምር እህቱ ነች?” የሚል ጥያቄዬን አነሳ ዘንድ ያስገደደኝ። ጥርጣሬ ውስጥ የከተተኝ። ሲጀመር፥ “የርሱን ግማሽ ባያክልም” ብሎ ለመናገር መለኪያዋ ምን ሆኖ ነው? “ይህንን መሰል ችግር ስላለብኝ ህመሙን አውቀዋለሁ” አባባሏስ፥ ችግር አለ ብላ የጠቀሰችውን ቤተሰባዊ (hereditary) ለማድረግ ነውን? እንደዚያ ከሆነስ እንደምን ተረጋግታ ስለጉዳዩ ማስረዳት ቻለች? እንደምንስ 5 ዓመታት ውስጥ ያልተገለጠ ባህርይ ሆኖ ሊኖር ቻለ? ይህንንም እንተወው…. ምናልባት የወሬ ምንጮች ካልዘባረቁ በቀር፥ ስለ ኃይለመድኅን ቤተሰብ እንደተረዳሁት፥ ቤተሰቡ ውስጥ ሁለት የህክምና ዶክተሮች መኖራቸውን ነው። ታዲያ እንዲህ ያለ ጭንቀት ሊከሰትና በቀላል ህክምና ሊወገድ እንደሚችል ሲያውቁ፥ እንደምን የጤንነቱን ጉዳይ ችላ ሊሉት ቻሉ? ብዙ ግራ መጋባት…

ትንሳኤ ጭንቀት አለበት ማለቷን ድፍን ያለ ነው ያደረገችው። የጭንቀቱ መንስሄ የቅርብ ቤተሰብ ሞት መሆኑን ለመግለፅና መረጃ ለመስጠትም ከአጎት በቀረበ ባይሆን እንኳን፥ ቢያንስ ከአጎት እኩል መገንዘብ እንደምትችል አስባለሁ። ታዲያ ግን አጎቷ አቶ ዓለሙ፥ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር በነበሩ እምሩ ስዩም በተባሉ ሌላ አጎቱ ድንገተኛ ሞት ምክንያት ኃይለመድኅን ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ መግባቱን ነው የገለፁት።

Schizophrenia? Depression? Or what?

በእኔ ጥቂት መረዳት፣ ልምድና፥ በጉዳዩ ላይ ቀደም ያለ ምክንያታዊ ንባብ (previous purposive reading on the topic)፥ እህቱ ከተነተነቻቸው ምልክቶች ተነስቼ፥ ችግሩ schizophrenia ሲመስለኝ፥ ደግሞ የአጎቱን ትንታኔ ስመለከት depression ይመስለኛል። (የህክምና ባለሞያዎች በዚህ ላይ ያለንን ግንዛቤ ትክክለኛ ለማድረግ ይረዱን ይሆናል) የሆነው ሆኖ፥ ሁለቱም የአእምሮ መታወኮች በስነ አእምሮ ባለሞያዎች በሚደረግ ክሊኒካዊ ምልክቶችን የመመርመር ዘዴ እንጂ፥ በአካላዊም ሆነ የናሙና ምርመራ መንገድ የላቸውምና፥ ሰው በዘፈቀደ እርስበርሱ ሲፈራረጅ ማየት አዲስ አይደለም።

በትንሳኤ መንገድ ሄጄ እንደተረዳሁት፥ የረዳት አብራሪ ኃይለመድኅን ችግር ሺዞፎርኒያ ቢሆን ኖሮ በሁኔታዎች መጠርጠር ይቻላልና፥ ከርሷ በተጨማሪ ምልክቶቹን የስራ ባልደረቦቹና የቅርብ ወዳጆቹም ሊያዩት ይችሉ ነበር። ደግሞም እዚህ ጋር የምናምነው ሀቅ፥ ማናችንም ብንሆን፥ ስራ ፈት ካልሆንን በቀር፥ ቤት ውስጥ ከምናሳልፈው ጊዜ የበለጠውን ስራ ቦታ ነው የምናሳልፈውና የየዕለት ለውጦቻችንን ለመገንዘብ የስራ ባልደረቦቻችንም ሩቅ አይሆኑም። (ቤት ውስጥ የምናሳልፈው የእንቅልፍ ጊዜንም ይጨምራልና፤ እንዲሁም፥ ኃይለመድኅን ብቻውን ነውና የሚኖረው፥ ሲመስለኝ የስራ ባልደረቦቹ ከእህቱ ሰፋ ላለ ጊዜ ሊያገኙት ይችላሉ።)

እናም ወንድም ኃይለመድኅንን ሺዞፎርኒክ ነው ከተባለ፥ ማንም በሁኔታው ለውጡን ሊገነዘበው ይችላልና፥ መስሪያ ቤትም ቢሆን፥ ለእርሱ ቢቀር ለንብረትና ለደንበኞች በማሰብ እረፍት እንዲወስድ ያመቻቹለት ነበር እንጂ፥ መደበኛ ስራው ላይ እንዲሰማራ ይፈቅዱለታል ብዬ አላስብም። (“ካላበደ በቀር ዱባ ቅል አይጥልም።” ይባላል። እናም ማንም እንዲህ ዓይነት ችግር አይቶ ችላ ቢል፥ የዱባ ተክል ቅል ቢጥል እንዳለ እብደት ነው።) በዚህ በኩል፥ ወዳጆቹ ምንም ዓይነት ችግር እንዳልነበረበት ገለፁ መባሉን አንብበናል። የአጎቱ ልጅ ነኝ ያለች ሴት ደግሞ፥ በኢሳት ቴሌቪዥን የስልክ ቃለ ምልልስ ላይ፥ “የሀገሪቱን ችግር ለህዝቡ ለማሳወቅ ፈልጎ ነው ይህን ያደረገው።” የሚል መልእክት አስተላልፋለች። (ለማድመጥ)

በአጋጣሚ ሆኖ፥ ብዙ ሺዞፎርኒክ ሰዎች አጋጥመውኝ ያውቃሉ። ሳይንሳዊ ትንታኔ ይኑረው አይኑረው ባላውቅም፥ ተደጋግሞ ከገጠመኝ በመነሳት፥ የሺዞፎርኒክነት ባህርይ አንዱ አለማስመሰልና ሀቀኝነት መስሎ ይሰማኛል። ሺዞፎርኒክ ሰው ራሱን ከማዳመጥና በገባበት ዓለም ከመመላለስ በቀር አይሞቀውም አይበርደውም ብዬ አስባለሁ። ስለሆነም፥ አውሮፕላኑን ወደ ጄኔቫ ጠልፎት ሲሄድ ለሺዞፎርኒክ ተጠቂ ትክክለኛ እርምጃና ስራ ነውና፥ ለማስፈራራትና ጥፋት እንደሚደርስ ተገንዝቦ “ዛሬ አምላክ ብቻ ነው የሚያድናችሁ” የሚል አይመስለኝም። እንደዚያ ካለ ከቀልቡ ሆኖ የሚሰራውንም ያውቃልና የአእምሮ መታወክ ችግር አለበት ማለት ይከብዳል።

Sign and symptoms of schizophrenia

Schizophrenia.com

People diagnosed with schizophrenia usually experience a combination of positive (i.e. hallucinations, delusions, racing thoughts), negative (i.e. apathy, lack of emotion, poor or nonexistant social functioning), and cognitive (disorganized thoughts, difficulty concentrating and/or following instructions, difficulty completing tasks, memory problems).

በማለት የሺዞፎርኒያ ህመም ምልክቶችን በደምሳሳው ያስቀምጣቸውና፥

Please refer to the information available on this page (see below) for common signs and symptoms, as well as consumer/family stories of how they identified schizophrenia in their own experiences.

በማለት ለበለጠ ንባብና ትንታኔ ይጋብዛል። እኔም ለጠቅላላ ግንዛቤም ሊረዳን ስለሚችል፥ የሚችል ያነባቸው ዘንድ እጋብዛለሁ።

Sign and symptoms of Depression

እንዲሁም በአጎቱ የገለፃ መስመር ሄደን፥ የኃይለመድኅን ችግር ዲፕረሽን ነው ብንል፥ ከሺዞፎርኒያ በላቀ መልኩ በቀላሉ ተለይቶ ሊታወቅ የሚችል ነገር ነው።

Beyondblue ገፅ

A person may be depressed if, for more than two weeks, he or she has felt sad, down or miserable most of the time or has lost interest or pleasure in usual activities, and has also experienced several of the signs and symptoms across at least three of the categories below.

ብሎ የዲፕረሽን ምልክት ሊሆኑ ይችላሉ ያላቸውን behaviour, feelings, thoughts, እና physical በማለት በየመደቡ አስቀምጧቸው ምልክቶቹን ይዘረዝራል። (read more)

እናም ከምልክቶቹ እንደምንረዳው ዲፕረሽን ውስጥ ያለ ሰው ከሺዞፎርኒያም ጋር ሲነፃፀር በቀላሉ ታይቶም ሊታወቅ የሚችልበት ሁኔታም ጭምር መኖሩን ነውና፥ ኃይለ መድኅን እንደዚያ ዓይነት ችግር ቢኖርበት ኖሮ ከቤተሰቡ ባልተናነሰ በስራ ባልደረቦቹም መታወቁ አይቀርም ነበር ይመስለኛል። ያንን እያወቁ ስራ ላይ ካሰማሩት አሁንም “ካላበደ በቀር ዱባ ቅል አይጥልም።” እንጂ ሌላ ምን ማለት ይቻላል?

አየር መንገዳችን – እንደመደምደሚያ!

አየር መንገዳችን ብዙዎች እንደ ብርቅ የምንንከባከበውና የምንኮራበት ሀገራዊ ንብረታችን ነው። ከነድክመቱም፥ በነገሮች አንገታችንን በደፋንና በተሸማቀቅንባቸው ጊዜያት፥ ልክ እንደ አትሌቶቻችንና የድል ታሪኮቻችን አንገታችንን ቀና ያደረገልንና ዛሬም ደረታችንን የሚያስገለብጠን ባለውለታችን ነው። …ከተሳፈረበት አንስቶ፥ እንደ አሞራ ሰማይ ላይ ብቻ እስከሚመለከተው ኗሪ ድረስ፣ የአውሮፕላናችንን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም ሰንደቅ አላማ ሲያይ ልቡ ወከክ የማይል የሚኖር አይመስለኝም። በልጅነት እንኳን የአውሮፕላን ድምፅ ስንሰማና በእኛ መኖሪያ አካባቢ ሰማይ ላይ ሲያልፍ፥ እጅ ነስተን “አባባባባባ….” በማለት መዳፋችንን አፋችን ላይ እያገጫጨን ነበር የምናሳልፈው። ሌላም ሰፈር እንዲሁ ነበር ይመስለኛል።

እናም አካሄዳችን ይለያይ እንደሆን እንጂ ማንኛውም የኢትዮጵያዊነት ስሜት ያለው ሰው ለአየር መንገዳችን ደህንነትና ዓለማቀፋዊ ተቀባይነት መጨነቁ አይቀርም። ስለሆነም፥ ኃይለመድኅን ድርጊቱን የፈፀመው የአእምሮ ሁከት ስላለበት ነው ማለቱ ለአየር መንገዳችን ስምና ዝናም መልካም የሚሆን አይመስለኝምና፥ ቢያንስ ጉዳዩን ከባለቤቱ እስክንሰማ ድረስ መላምቶቻችንን በኃላፊነት ብንሰነዝር መልካም ይመስለኛል። በዚያም ላይ ኃይለመድኅን አሁን ያለበትን ሁኔታ ማንም አያውቅምና ዛሬ የምንናገረው ነገር ጉዳዩን በማጦዝና በማሾር ረገድ የሚጫወተውን ሚና ላናውቅም እንችላለንና ነገሩ እስኪጠራ ድረስ ዝም ብንል የተሻለ ይመስለኛል።

እስከዚያው ድረስም ግን፥ አየር መንገዳችን የሁላችንም ኩራት ሆኖ እንዲዘልቅ፥ በፓርቲ መቀያየርና በመንግስት መለዋወጥ ማዕበሎችም ጭምር እንዳሸበረቀና እንዳኮራን እንዲኖር የአስተዳደር ቦርዱ ውስጡን በመፈተሽ እንደ ላዩ ያማረ አሰራር ስለማበጀት ቢመክር ጥሩ መሆኑ አይጠረጠርም። አዎ! የአየር መንገዳችንን ስኬት እንደምንጋራና እንደምናደንቅ ሁሉ፥ መጥፎ ነገሩንም አንፈልግምና ኃላፊዎች ያስቡበት ዘንድ ይገባል።

ቸር ቸሩን ያሰማንማ!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s