ትናንትና… የገጠር ቀበሌ ውስጥ የሚኖሩ ነፍሰ ጡር እናቶች የቅድመ ወሊድ እንክብካቤ ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ ስለ መውለጃ ሁኔታቸው እንዲያቅዱና፣ ጤና ጣቢያ ሄደው እንዲወልዱ ለመጀንጀን፤ ….እንዲሁም፥ ከወሊድ ጋር ለተያያዙ ችግሮች ብቻ፥ በደግ ድርጅት የተመቻቸላቸውን ነፃ የአምቡላንስ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለመወስወስ የሚደረግ የነፍሰ ጡር እናቶች ኮንፈረንስ ላይ፥ የአካባቢው ነዋሪዎች እንዲሳተፉ ቤት ለቤትና ገበያ መሀል ቅስቀሳ እየተደረገ ነበር።
አንዲት፥ እድሜዋ 30ዎቹ መጀመሪያ የሚገመት ገራገርና ታታሪ ሴት፥ “ፕሮግራሙ ለምንድን ነው?” ብላ ጠየቀች።
“ስለእርግዝና እና ወሊድ ግንዛቤ እንድታገኙ ለማድረግ ነው። እናት ስትወልድ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳይደርስባት ለማገዝ ነው።” መለሰች አስተባባሪዋ፥
“እህ… ጥሩ ነው። እናት አትሙት! ኧረ ሲወልድ ማንም አይሙት…” ወደ ጉራጊኛ በሚወስደው ድምፀት እየሳቀች መለሰችላት…
“ነይ እነዛን አብረን እንጥራና እንማማራለን…”
“ተዉ ስራ አታስፈቱኝ። እኔ አልመጣም።” አስረግጣ ተናግራ ወደ ቤቷ መለስ አለች…
“ቆዪ፥ ለምን ትሄጃለሽ? አትሳተፊም እንዴ? በኋላ ችግር እንዳይፈጠር ለማገዝ ነው። እናትም ልጅም ጤና እንዲሆኑ ይረዳል…” ምናምን ምናምን ብላ፥ በትህትና አግባባቻት፤
“ግድ የለም መርካሞ (ቆንጂት ማለት ነው በጉራጊኛ) እርግዝናውን ባሉ ሲመጣ እማራለሁ።”
“ባለቤትሽ የት ሄዶ ነው? ነይ አንቺ ከተማርሽ ትነግሪዋለሽ…” አለች የግርምት ሳቋ ቀድሟት… (ኮንፈረንሱ አባወራዎችንም ያካትታል)
“አላገባሁም።” እንደመቆዘም ብላ፥… “የቤተሰብ ኃላፊ ነኝ። ደካማ እናቴንና ታናናሾቼን እረዳለሁ ብዬ፥ እድሜው ሳላስበው ሄደ። መልክም ጠፋ። …መስራት ለምደሽም ስራ ፈትቶ መቀመጥ እሺ አይልም። ይኸው የቤቱን ስራ ስንጨርስ ሰፈሩን እናስተካክላለን… ደግሞ ኑሮም እሳት ነው። እኔም ስራ አበዛሁና ረሳሁት መሰለኝ…”
“አይዞሽ። ገና ነሽ ኧረ… ጎበዙን ታገቢና ነገ ጥሩ ይሆናል።” አለቻት እንደማፅናናት። (ምን ታርግ ያልጠበቀችውን ስትሰማ?)
“ተስፋ በፈጣሪ ነው ባክሽ! አዬ… ልቡስ ነበረኝ። ግን ልብ ማን ያያል? እንጂማ ለቤቴ ልባም ነበርኩኝ። ግን ሰዉ የሰለጠነ መስሎት ብልጭልጭ ካየ ተከትሎ ገደል ይገባል። …ኧረ ሥራ ፈት አልወድም እንጂ ባልስ ሞልቷል።” አለች እርስ በርሷ፤ ፊቷ ሳይዳምን…
አስተባባሪዋ እንደመደንገጥ ብላ፥… “ታዲያ እኮ ያንቺ ዓይነት ሰው ግንዛቤው ሲሰፋ ሌላውንም ይረዳል። ስለዚህ ነይና ተምረሽ ሌላውንም ታስተምሪያለሽ። እንዳንቺ ዓይነት ጎበዝ ሰው ሲያውቅ ሌላውንም ይለውጣል።”
ጣፍጦ በሚያስፈግገው የጉራጊኛ አክሰንቷ… “እሱስ ልክ ነሽ። የራሴን ሳይ ጎረቤቴን ተውኩት አይደል? ኦኦ… ይቅርታ አርጊልኝ። ልጅ ቢኖረኝ ደስ ይለኝ ነበር እንጂ ልብ የሌለው ባልስ እንኳን ቀረብኝ። ሙች! እንዲህ የምልሽ አሁን የለም ብዬ አይደለም፤… ቢኖር ልጅ ደስ ይለኛል። ግን ጥሩ አባት የሌለው ልጅ ከምወልድ ብዬ ተውኩት እንጂ ለስሙ ጓደኛም ነበረኝ…
…ተይው ባክሽ። ትንንሾቹ ከተማሩልኝ ምን እፈልጋለሁ? ልጄ ነው ካሉት ሁሉም ነፍስ ነው። አምና ቡና ስንጠጣ፥ ከተማ ቴሌቤዥን ላይ ያየ ሰው ገርሞት ሲናገር ሰማሁ… ፈረንጂ መውለድ ሳያቅተው የሰው ልጅ ያሳድጋል አሉ። እውነት ነው? …ታዲያ ነፍስ ሆኖበት እንጂ በሰው ልጅ ሚቃጠል፥ ወልዶ አያሳድግም ነበር? አንዳንዶች ፈረንጅ ሞኝ ስለሆነ ነው አሉ። እህ በይ፥ ታዲያ ስራ ከመፍታት ጊዜ ካለ ሁሉም ቢረዳዳ አይሻልም?” ብላ ሌላውን ለመቀስቀስ ፊት ፊት እየመራቻት ሄደች፤…
በብስለቷ መስኮት አጮልቄ ሀገሬን ከነነዋሪዎቿ አየኋት! …ዕድል ቢሰጠው ግን በየጓዳው፣ በየመንደሩ ስንት አዋቂ ሞልቷል?!