ዛሬ በጠዋቱ ቀንቶኝ (እንደፈራሁት ሳይሆን ቀርቶ) ቅያሪ ካልሲ ስላገኘሁኝ፥… በውሀ መጥፋት ምክንያት ሁለት ቀን ካልቀየርኩት ካልሲ ‘ጥብስ ጥብስ’ ሽታ ተርፌ… ቁርሴን ጥብስ በላሁና፥ ፓስፖርት የማሳደስ ቀጠሮ ስለነበረኝ ኢሚግሬሽን ሄጄ ተሰለፍኩኝ። መቼስ እዚያ ያለውን ቀፋፊ ሁኔታ ዘርዝረው አይዘልቁትም። ‘ቀፋፊ ነው’ም አይገልፀውም።
ፓስፖርት ለመውሰድ ከተሰለፉት ውስጥ አብዛኞቹ አረብ አገር ለመሄድ ልቦቻቸው የቆሙ እንደሆኑ ከሁኔታው መገመት ይቻላል። ጆሮው ቢቆረጥ አማርኛ ከማይሰማው፥ ስሙን መፃፍ እስከማይችለው ድረስ ሰልፉ ላይ ይተራመሳሉ።….ፓስፖርታቸውን የወሰዱ ሰዎች ‘እንኳን ደስ አለሽ/ህ’ ሲባባሉ የተለየ ሲሳይ ያገኙ ይመስላል። ከሰልፉ ወጥተው ወይ ደግሞ ረዥም ቀጠሮ ተሰጥቷቸው፥ እርስ በርስ ‘አይዞሽ/ህ’ ሲባባሉም በልዩው ነው። ለነገሩ ከጥበቃ ሰራተኞች አንስቶ እስከ ቢሮ ሰራተኞች ድረስ የሚያደርሱት እንግልት ነገሩን አባብሶታል።
አንዴ ‘መብራት ጠፋ’ አንዴ ‘ሲስተሙ ደከመ’ ምናምን እየተባለ ምክንያት ሲደረደር ቆይቶ እስከ 6ሰዓት ድረስ የተስተናገደው ሰው ቁጥር በጣም ጥቂት ነበር። ፓስፖርት የሚጠይቁት ኗሪዎች የልባቸው መነሳሳት ላይ ‘አናድጄያቸው ቢከለክሉኝስ’ የሚል ስጋት ተጨምሮበትም ነው መሰል ሰጥ ለጥ ብለው ለዘበኞቹ ይገዛሉ። ቢገፈትሯቸው ቢሰድቧቸው ምንም መልስ የለም።…ስንቱን እየታዘብኩና በስንቱ እየተማረርኩ፥ ፀሀዩ ላይ ተሰጥቼ አረፈድኩኝ።
ስሜ ሳይጠራ ቆይቶ 6 ሰዓት ሲጠጋ ቁርጤን አውቄና ተስፋዬን ቆርጬ፣ ከሰዓት ልመለስ ወጣሁ። ከዚያም ምሳዬን ቁርጥ በልቼ ተመልሼም እዚያችው ፀሀይ ላይ (ከሰፊው ህዝብ ጋር) እየተንቆራጠጥኩኝ፥ በጅምላ ስሰደብ ስገፈተር ቆየሁኝ። የውሀው መጥፋት ላይ ሙቀቱ ተደምሮበት አየሩ ‘ኮርቤሶ ኮርቤሶ’ ይል ነበር። በሙቀት ስቀቀል ቆይቼ መጨረሻ ላይ (10:50 ሰዓት ላይ) ስሜ ተጠራ። ታዲያ ግን ልክ እንደገባሁኝ መብራቱ ጠፋ። በብስጭት ተቀቀልኩኝ። እነሆ መቀቀሌንም ምክንያት በማድረግ ደግሞ ራቴን ቅቅል ልበላ እያሰብኩ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። ሃሃሃ….
ጥብስ… ቁርጥ… ቅቅል…
Btw, ይህ ሳምንት ለኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ጫፍ ጫፉን ካርኒቫል ነው። የካርኒቫል አመጣጥ (etymology) ካርን (carne)ና ቫሌ (vale) ከሚሉ የላቲን ቃላት ነው። ካርን ማለት ስጋ (flesh) ማለት ሲሆን፤ (“ስጋ በሊታ” ለማለት “carnivorous” እንደምንል…) ቫሌ ማለት ደግሞ ‘ቻዎ ቻዎ’ (farewell) ማለት ነው። [ይለናል የኖርማን ሌዊስ Word Power Made Easy መፅሀፍ፤ Btw, it is one of my favorites]
ስለሆነም ‘ካርኒቫል’ ስንል “ስጋ ሆይ ቻዎ ቻዎ” እንላለን። እንደ ደምበኛ ካርኒቫል በየጎዳናው ባንቀውጠውም በየቤቱና በየሆቴሉ በስጋ እንቀውጠዋለን። …ስጋ ሆይ ቻዎ ቻዎ!! ከሰኞ ጀምሮ የአብይ ፆም ወቅት በመሆኑ ይህ ሳምንት ባይሰየምም ለብዙዎች ካርኒቫል ነው። – ለሚፆሙትም ለማይፆሙትም! …መቼም ልብ ካልነው የምንታዘበው ነገር ለጉድ ነው።
እናም ጥብስ… ቁርጥ… ቅቅል… ሌላም ሌላም የስጋ ዘሮች… እንደጉድ ይበላሉ። ጥብስ መብላት ባይችሉ ካልሲን ጥብስ ጥብስ ማሰኘት ይችላሉ/ይገደዳሉ። ቁርጥ መቁረጥ ካልቻሉ ተስፋ መቁረጥ ቀላል ነው። ቅቅል መብላት ካልቻሉ በነገሮችና በአየር ንብረት ለውጡ ይቀቀላሉ። ሌላም ሌላም… ያው ምርጫ ነው።
እላዩ ላይ ደግሞ ቢራ፣ ውስኪ፣ ቮድካ፣ ጠጅ፣ አረቄ…. ሌላም ሌላም… 🙂
ቺርስ!!