IsIsን ለመቃወም በተጠራው ሰልፍ…

የመንግስትን የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ አክብሮ፣ ከማለዳው አንስቶ፣ የሰው ጎርፍ አስፓልቶቹ ላይ ወደ መስቀል አደባባይ ሲፈስ ነበር። ቃሉን ከዚህ ቀደም ለማያውቅ ሰው “በነቂስ” መውጣት ምን እንደሚመስል ሁኔታው ያሳያል። በተለያዩ ርቀቶች፣ ሁለት ሶስት ጊዜያት የሰውነት ፍተሻዎች (body check) ታልፎ፣ እዚያ ሲደረስ፣ ከየመንገዱ እየፈሰሰ የመጣው የሰው ጎርፍ ኩሬ ሰርቶ፣ የመስቀል አደባባዩን መሀል አስፓልት ሌጣውን እንዲተወው ተደርጎ፣ ደረጃዎቹ ላይና በግራና በቀኝ በየጥጋጥጉ ተከትሮ ሲጮህ፣ መፈክር ሲያሰማ ነበር።
 
የመንግስት የመድረክ ዝግጅት፣ ንግግሮችና የመሳሰሉ ነገሮች ሲከናወኑ፣ ቁርጥራጭ የተለመዱ ዓይነት ጡዝጦዛዎች (propaganda) ከመሀል በንፋስ ተገፍተው እየመጡ ይሰማሉ እንጂ፥ በበኩሌ ጥርት ያለ ነገር አልሰማሁም። ሰልፈኛው እርሱን መስማት የፈለገ አይመስልም ነበር። በደንብ መስማት የፈለገና ዙሪያ ገባውን ልቃኝ ያለ ሰው ወደዛ ልለፍ ቢል፥ ፖሊሶቹ ይከለክሉ ነበር። ወደ ጎተራ መታጠፊያ፣ ወደ ጊዮን ሆቴል እና ወደ ስታዲዮም መታጠፊያ መንገዶችን የሚያገናኘው የመስቀል አደባባዩ ጫፍ፣ መሀል አስፓልት ላይ፥ ብዙ ወጣቶች በመፈክር ታጅበው፣ ለቅሶና ብሶታቸውን በጩኸት ያሰማሉ። እንደሚጠበቀው እሮሮና ጩኸት ከመኖሩ በቀር፥ ሁሉም ነገር ሰላማዊ ነበር።
 
የተለመዱ፥ እጆችን ማማታት፣ መቆላለፍና ከፍ ማድረግ፣ በጋራ መጮህ፣ የመሳሰሉት…እንዲሁም የተለያዩ ዓይነት መፈክሮች ይታዩ ነበር። “አቤቱ የሆነብንን አስብ” ከሚል መፈክር አንስቶ እስከ “ISIS እስልምናን አይወክልም”፣ “ከመንግስት ጋር ሆነን ሽብርተኞችን እንዋጋለን” እስከሚሉ የተለያዩ መፈክሮች ድረስ የያዙ ሰልፈኞች ስብስቡ ውስጥ ሆነው በእልህና በቁጭት ያረግዳሉ። ይጮሃሉ። ካሜራዎችም በፌደራል ፖሊስ ሰልፍና በሰልፈኞቹ መካከል ቆመው ይቀርፃሉ። ፌደራል ፖሊሶቹ በሁኔታው በሽቀው ይመስላል እርስበርስ ተነጋግረው በዘዴ ሰልፈኞቹን ከብበው ቆመው ነበር።
 
በየመሀሉ፣ የተወሰኑ ወጣቶች ከውስጥ እየተለዩ በፖሊሶች፣ ከsquare garden በስተቀኝ በኩል ካለ ቦታ ይዘዋቸው በደረጃው ሲወርዱና ወደጀርባ ሲወስዷቸው ነበር። ይሄ ሲሆን ደግሞ የወጣቶቹ ጩኸት የበረታ ነበር። ከዳርም ሆነው ሰልፉ ላይ የነበሩና መፈክሮችንና ድጋፎችን ሲያሰሙ የነበሩ ሌሎች ሰዎችም፥ “ምናለ ዛሬን እንኳን ቢተዋቸው። ደልቶት የመጣ የለ። ራሳቸውን ችለው ጮኹ እንጂ ማንን ጎዱ። ያንን መስማት ካልፈለጉ ምን ቸገራቸው?” ሲሉና ሲያለቅሱ ነበር።
 
ከመድረኩ የሰልፉ ፍፃሜ መሆኑ በተነገረበት ቅፅበት። ፊትለፊት የነበሩ የእስልምና እና የሀይማኖት አባቶች ቀድመው ወደ ጊዮን ሆቴል አቅጣጫ ሰያፍ መሄድ ሲጀምሩ፣ የቆመውን ሰልፈኛ ፌደራል ፖሊሶች “በቃ ተበተኑ፣ ምን ትፈልጋላችሁ? ሰልፉ አልቋል።” ብለው ሰዉም መንቀሳቀስ ጀመረ። ከበው የሚጨፍሩትን ግን ፖሊሶች እንደከበቧቸው ጠበቋቸው እንጂ፥ ተበተኑ ያላቸውም አልነበረም። “ተበተኑ” የተባሉትም፥ “እነርሱ ቆመው የለ? ምንም አላረግንም። ሰዉ ቀለል ሲል እንሄዳለን።” ብለው ሲመልሱ ነበር።
 
ወዶም ተገዶም ሰዉ መንቀሳቀስ ሲጀምር፥ …ጭስ መልቀቁ፥ የሰልፉ አንዱ አካል ይመስል፣ ከመቅፅበት፥ ከበስተግራ፣ ቶታል አካባቢ የነበሩ ፌደራሎች የአስለቃሽ ጭሳቸውን በየአቅጣጫው ላያችን ላይ ለቀቁብን። የጭሶቹ ፍንዳታዎች ድምፅ እና የሰዉ እሪታ ተስተጋባ። ፌደራሎቹም እጃቸው የገባውን መደብደብ ጀመሩ። ድንጋዮችም ተወረወሩ። ለቅሶ በየቦታው ሆነ። “እንኳንስ ዘንቦብሽ እንዲሁም ጤዛ ነሽ።” እንዲሉ፥ ቀድሞም ችጋርና ለቅሶ ላጎሳቆለው ምስኪን ጭስ አላቃሽ ሆነለት።
 
ሁኔታው ጋብ ሲል፥ ሰልፈኛው ወደ የመንገዱ ብቻውን እየተናገረና እየተራገመ ሄደ። መሀል አስፓልቱ ላይ ሞባይል ስልኮች፣ ጫማዎችና ልብሶች ወዳድቀው ነበር። ወደ ሜክሲኮ የሄዱት ሰልፈኞች፥ እየጨፈሩና፣ እየጮኹ ሰልፉ በነበረበት ድባብ በኅብረት ሆነው በተቃውሞ ሰልፉ ቀጥለው ሄዱ….
 
“አቤቱ የሆነብን አስብ።”
— ሰቆቃወ ኤርሚያስ 5:1
10923448_760431044077931_7448087792960252853_n
ልክ፥ ሰላማዊ ሰልፉ ወደ ጥቃት ከመለወጡ በፊት ለመጨረሻ ጊዜ በስልኬ ያነሳሁት ፎቶ። በአንድ ጊዜ ምድር ቀውጢ ስትሆንና ጥቃት ሲዘንብ፣ ሰው በእንባ ሲራጭ በጭስ በጨነበሰ፣ በሚያነባ ዐይኔ ተመልክቼ ልቤ ተሰባበረ።

ቅምሻ፥ ከወንዜ…

ከሰዓት ረፋዱ ላይ፥ ድንገት ካገኘኋቸው በፌስቡክ የሚዛመዱኝ የወንዜ ልጆች ጋር ተገናኝተን ስንጫወት ቆየን። ደስም አለኝ። ከቆይታችንም ይህንን የጨዋታ ጫፍ መዘዝኩ፤… ሌላ ጊዜ ፈታ አድርገን እንጫወተው ይሆናል።
 
ወንዜ መነሻው ሰባተኛ ነው። ከሰባተኛ ሽቅብ በስተሰሜን ወደ አውቶብስ ተራ ይፈሳል፤ ….ቁልቁል በስተደቡብ ወደ አብነት ይሄዳል፤ ….ወደ ምህራብ ወደ አማኑኤል ይጓዛል፤ ….ደግሞ ወደ ምስራቅ ይሄድና በአብዶ በረንዳ፣ በምህራብ ሆቴል አሳልጦ ከሰፊው የገበያ ባህር ከመርካቶ ይቀላቀላል። ….የእኔ ወንዝ! የእኔ ቀዬ! የእኔ ሰፈር! የእኔ መንደር! የእኔ መርካቶ!
 
ከወንዜ ሕይወት ሞልቷል። እያንዳንዱ ቤት የራሱ ታሪክ አለው። እያንዳንዱ ሰው የራሱ፥ ያልተፃፈ ኃላፊነት አለበት። ገድል በየቤቱ ታጭቋል። ያላየው ከውኀው ያልጠጣ፥ ስለ ወንዜ ይህን ሲሰማ ግራ ሊገባው ይችላል። ‘አናውቀውም እንዴ? ምን ይቀባጥራል?’ ሊል ይችላል። አዎ አታውቁትም… እንደዚያው ነው። እላለሁ። …ሰፈሬን ስጠየቅ ከትንታኔው እጀምርና ኋላ ነው ስሙን የምናገረው። (ገፅ ገንብቼ ሞቼ። ሄሄሄ…)
 
የመርካቶ ወዳጅ ነፃ ነው። ፈታ ብሎ ማውጋትና ማስወጋት ይችላል። ታማኝ ነው። ሽርክ ካሉት ከሸቀበና ከቀረቀበውም ቢሆን ያካፍላል። ነገር ዓለሙ በጋራ ነው። (ይዞረው ጋራ ባይኖረውም፥ ይኖርበት ውብ የጋራ ስርዓት አለው።) ሲፈልግ “እናጋጭ” ይልሃል። ሲቸግርህ ተበድሮ ያበድርሃል። ስትከስር፣ ስራህ ሲዳከም እቁብ ሰብስቦ አንደኛ እጣውን ይሰጥህና ያቋቁምሃል። ክፉ ደግ ቢገጥምህ፥ ቤቱ ቤትህ ነው፤ እንግዶቹም እንግዶችህ ናቸው። ካበረብህም ደራሽ ነው። …መስመር ስትስት ሳይናገር፥ በዐይኑ እየተከታተለ ወደ መስመርህ ይመልስሃል።
 
የስጋ ዘመድ ሞቶባት፣ አቅሏን ስታ እዬዬዋን ስታቀልጥ፣ ደግሞ ፀጉሯን እየነጨችና በነሲብ ወዲህና ወዲያ እየተገማሸረች ስታለቅስ፣ እንባዋ ግራና ቀኝ ጉንጮቿ ላይ ሲወርድ…. በፀሐይ ሲያዩት የፊቷን ቀለም ይዞ፥ ጉንጯን የሸረሸረባት የሚመስል እንባ ፊቷን ሲያርሰው፣ ደግሞ በአፅናኞቿ ትግል ትከሻዋ ላይ ጣል የተደረገላት መቅረቢያ ነገር ተንከባሎ ወርዶ፤ አንዴ በእጇ ድለቃ…. አንዴ በልቧ ምት… ከሚተራመሰው ደረቷ ላይ፥ ሳይታሰብ ብቅ ብሎ እንደታየ ጡት…. ውበቱ እንደሚያስደነግጥ፤ …ጆፌ ያለ ሸርዳጅ ለቅሶ ደራሽ እጅ ወደላይ ብሎ ተማርኮ፥ አፅናኝ ይመስል…. ሰልስት፣ ሰባት፣ አስራሁለት እያለ አርባ፣ ሰማንያ ተዝካር እየተመላለሰ ማፅናናት የሚገብርለት፤ በሌለ አቅሙ የእዝን የሚጭንለት… ውበት፤
 
….ሰባተኛ ውበቷ እንዲህ ነው። እንዲህ እሳት በላሰ ኑሮም፣ በተብረከረከ የመግዛት አቅምም፣ በማይቀመሰው የገበያ ሁኔታም፣ በስራ ማጣትና በገቢ መዳከምም፣ ቅልጥ ባለ ግራ መጋባት ውስጥም… አፈትልኮ የሚታይ ውበት አለ። ልብን ትርክክ የሚያደርግ፣ ብዙ ስለመኖር የሚያነሳሳ ልዩ ሕይወት አለ። የመርካቶ ሰው፥ እንኳን አዱኛውን ችግሩንም ያካፍላል። ሳይነጋገር ተግባብቶ ይተባበራል። …ፈለጉም አልፈለጉም፥ የአኗኗር መስተጋብሩ እንደ ወንዙ መፍሰስን ያስገድዳል።
 
አዲስ ከሆንክ ስትቆይ ትለምደውና፥ ከሰፈሩ ‘ሀኪም ይንቀለኝ’ ትላለህ። ድንገት ሰፈር ቀይረህ ብትሄድ፥ ሰበብ ፈልገህ ትመላለሳለህ። ቤተሰብ ወይ ጓደኛ ካለህ ደግሞ፥ ለመምጣት ጥሩ ምክንያት ይዘህ ቅዳሜን አንተ ነህ የምትቀሰቅሳት፤ ዱለቷን አሳምራ “የተንቢ” ትልሃለች። ደግሞ የጨዋታ ዱለት በቡና ታወራርድ ዘንድ ንፁህ ቡና ታቀርብልሃለች። ብቻህን መሆን አትችልም። ብቻ መብላትም አታስብም። ምን ታረገዋለህ? – ነገር ዓለሙ በጋራ ነው። መርካቶ ነዋ!- ፈርጀ ብዙ ሕይወት የሞላበት።
 
መርካቶ ሰፈሬ
¯¯¯¯¯¯¯¯
ቅመም ተራ፣ ሽንኩርት ተራ፣
ሸራ ተራ፣ ሸማ ተራ፣
ጌሾ ተራ፣ ብረት ተራ፣
ብቅል ተራ፣ ገብስ ተራ፣
እንትን ተራ፣. . . እንትን ተራ፣. . .
ተደልድሎ፣ ተሰይሞ፣
ሁሉም መደብ በየተራ፣
እንዴት የለው የሰው ተራ?!
—-
ዮሐንስ ሞላ (2005) “የብርሃን ልክፍት” ገጽ፥ 72
ፋክት መፅሔት በርዕሰ አንቀፁ “የማኅበረ ቅዱሳን ዝምታ ይብቃ!” የሚል ፅሁፍ አትሟል። የርዕሰ አንቀፁ የመጨረሻዎቹ ሁለት አንቀፆች (ለድህረ ገፅ ንባብ እንዲቀል በ3 ከፍያቸው) እንዲህ ይነበባሉ…
“እስከዚህ ቀን ድረስ የማኅበሩ ይፋዊ አቋም ሆኖ የተሰማው የመንግስት ክፉ ድርጊቶችን በለዘብተኛ መግለጫዎች የመከላከል እንዲሁም የተፈጠሩትን ቀውሶች በፆምና በሱባኤ ለመቋቋም የመሞከር አካሄድ ነው። እንደ ፋክት እምነት፣ ይኽኛው የማኅበሩ አማራጭ ከአምባገነኑ መንግስት የተጠና አፍራሽ ዕቅድ አያድንምና፣ ህጋዊ የመብት ጥያቄዎቻችን ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ በአደባባይ ማሰማት ይኖርባቸዋል።
 
የማኅበሩ ይፋ ድርሳናት እንደሚጠቁሙት፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቀናኢነት ያላቸው ወጣት የከተማ የሀይማኖቱ ተከታዮች እንዲሁም በቂ ተቋማዊ ስርዓት ያለው ከመሆኑ አኳያ፤ ይህን ማኅበር ከመፍረስ ለማዳን ብቸኛው መንገድ፣ ሕጋዊ የአደባባይ ተቃውሞ ማሰማት እንደሆነ ፋክት ታምናለች። ይህን ሕጋዊና ሰላማዊ የአደባባይ ሕገ-መንግስታዊ የመብት ትግል ከማድረግ በተቆጠበ ለዘብተኛ አካሄድ፣ የማኅበሩ ህልውና ስለመቀጠሉ እርግጠኛ መሆን እንደማይቻል ማስታወስ እንሻለን።
 
ከዚህ አኳያም ዛሬም ያልተቋጨውንና በብዙ መስዋዕትነት እየተጠየቀ ያለውን የህዝበ-ሙስሊሙ ሕገ መንግስታዊ የመብት ጥያቄ የተጓዘበትን አባጣ ጎርባጣዎች ተመልክቶ፥ ድክመቶችና ስኬቶች፣ እንዲሁም አገዛዙ ለንቅናቄው ያሳየውን አፀፋዊ ምላሽ አካቶ በመገንዘብ፤ ማኅበረ ቅዱሳን ከተመክሯቸው ሊማርበት ይገባል ስትል መፅሔታችን ታምናለች።”
 
የርዕሱ መፈክር መሰልነት ሳያንስ፥ በርዕሰ አንቀፅ ላይ በመቀመጡ ምክንያት በግራ መጋባት ስሜት በአእምሮዬ የተመላለሱትን ጥያቄዎች፥ አብረን፥ ከስሜትና ከተራ መዘላለፍና መፈራረጅ በፀዳ መልኩ፥ ብንጫወትባቸው ብዬ በፅሁፍ አሰፈርኳቸው።
 
1. በመፅሔቱ ርዕሰ አንቀፅ አንድን የሀይማኖት ማኅበር መምከር አይከብድም? (I mean, it seems too much መቆርቆር, and irrelevant)
 
2. መፅሔቱ ሲመክርና ሲያሳስብስ እንዲያው ‘ብዬ ነበር’ ለማለት ነው ወይስ ተደማጭነቱን አስልቶ ነው?
 
3. አንድ የራሱ አስተዳደራዊ መዋቅርና ብዙ አባላት ያሉትን ሕጋዊ ማኅበር ለመምከርና ለማስታወስ መሻቱ ማኅበሩ ‘አለኝ’ ከሚለው (ወይም በብዙአን አእምሮ ‘አለው’ ተብሎ ከምታሰበው) የፀና መሰረት ጋር አይጣረስም? በመሆኑም፥ (ከጉዳዩ ሀይማኖታዊነት አንፃርም) ማኅበሩ ‘ያዋጡኛል፤’ እንዲሁም ‘ቤተክርስቲያንና ሕዝቧን በፅናት ለማቆየት ይበጃሉ’ የሚላቸውን መንገዶች ከአባላቱ ጋር እንዲመክር፣ እንዲያሰላስልና በራሱ ሀላፊነት እንዲንቀሳቀስ መተው አይቀልም?
4. “የማኅበረ ቅዱሳን ዝምታ ይብቃ!“….ስንል፥ ምናልባት ዝምታው ቢጎዳው ማኅበሩንና አባላቱን ነው። የዝምታው ማብቃት ግን ማኅበሩን ብቻ ላይጠቅም ይችላል። ወይስ በግርግርና በእግረ መንገድ ሊኖሩ ስለሚችሉ ነገሮች ምን ያህል ማወቅ ይቻላል?
5. አንድ የሀይማኖት ማኅበር ላይ የደረሱ ክፉ ድርጊቶችን ለመከላከልና ለማውገዝ፥ እንደ እምነቱ… ከፆምና ከሱባኤ የተሻለ መሳሪያ አለና ነው ፆምና ሱባኤ ከ‘ለዘብተኛ አካሄድ’ የሚፈረጁት?
6. ፋክት መፅሔት፥ ቀድሞ በነበሯት መልክና ስሞችም ጭምር (በፍትህ፣ በልእልና፣ በአዲስ ታይምስ…) ስለ ‘ሰላማዊ የአደባባይ ሕገ-መንግስታዊ የመብት ትግል’ ስታቀነቅንና ስታበረታታ ትታወቃለች። ነገሩ “የጎበዝ ወዳጅ…” ነገር ነው? ወይስ የምሩን መፅሔቷ የምታምንበት ጉዳይ ነው?
 
7. የ6 መልስ “አዎ“ ከሆነ፥… መች ይሆን ከ‘ዘማች ወስዋሽነት’ ወደ ‘አዝማችነት’ እና ‘ዘማችነት’ የምታድገው? ይህንን መጠየቄ፥… ሳላነብ ካላለፈኝ በቀር መፅሔቷ ላይ ከዚህ ቀደም ቢያንስ ከተማው ላይ ስለተካሄዱ ሰላማዊ ሰልፎችና የአደባባይ ተቃውሞዎች ዘጋቢ ፅሁፍ አንብቤ ስለማላውቅ ነው። (ከባህር ዳሩ በቀር)
 
8. ጥያቄ ቁጥር 6ን ሳንለቅ፥… ለመካሪነትና አሳሳቢነት የበቃ መፅሔት፥ ቢያንስ በተደጋጋሚ በሚያማርርባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ‘የአደባባይ ሕገ-መንግስታዊ የመብት ትግል’ ስለማድረግ እንዴት አያስብም? ሀላፊነቱን ወስዶና ሕጋዊ ፈቃድ ጠይቆ ሰላማዊ ሰልፍም ሆነ ተቃውሞ ለማድረግ ከኗሪው የተሻለ አቅምና ሁኔታ የለውም?
 
9. እንዲሁም ሌሎች…. 🙂 (ይኽች እንኳን እንደ ጨዋታም ነች። 🙂 )
 
ሰላም!

‘በከበረች ሰንበት’

ሙዚቃ አሁንም እየፆምን ነው። የስራውን ይስጠው፥ መብራት ኃይል ከሙዚቃ የተፋታ በዓል እንድናሳልፍ አድርጎናል። ሞባይሎቻችን ያቆሩትን ኃይል እስኪያሟጥጡ ድረስ ሬድዮ ያመጣውን ሙዚቃ ሁሉ ተቀብለው ወደ ጆሮዎቻችን እንዲያሳልጡ ፈቅደንላቸው ነበር። …ነበር። (ለመነጋገሪያ የሚጠቅሙን እንደው እንደ እድል ነው። በዓመት በዓል ደግሞ ይብስባቸዋል። ዛሬ ወንድሜ “Merry Christmas” የሚል የፅሁፍ መልእክት ደርሶት ስንስቅ ነበር። ግን የቴሌ ነገር ስለማይታወቅ ያን ያህል አያስቅም።) …ይብላኝ ለእነሱ እንጂ፥ ለበዓል የቤተሰብ ጫጫታ ሙዚቃ ነው። የዓመት በዓል ድባቡ ራሱ ድምፃም ሙዚቃ ነው። ቀጤማውና ጭሳጭሱም ይዘምራሉ። …ዋዜማውን እንደው ዶሮና በጉ ያደምቁታል።
 
ያው ትናንት እንዳጫወትዃችሁ፥ ነፍሴን ካወቅኹኝ ጊዜ ጀምሮ፥ ከአንድ ጊዜ በቀር፥ ለፋሲካ በዓል መብራት በርቶልን አያውቅም። ….በዋዜማው ከጠዋት ጀምሮ ሌሊቱንም ጠፍቶ ያድርና እሁድ ይከሰት ነበር። መብራቱ! ”እንኳን አደረሳችሁ“ የሚል ዘመድ ይመስል ድንገት ብቅ ይልና የሁላችንም ገፅ ላይ ፈገግታ ይዘራል። በሰው አምሳል ሆኖ ያፌዝብን ይመስለኝ ነበር።
 
እኛም ወስደው ሲያመጡት እናመሰግናቸዋለን። “እሰይ!ኧረ እግዜር ይስጣቸው” ትላለች እናቴ። እንደ ትናንት የነሱንን አስታውሶ ሊራገም የሚያስብ ካለ፥ አይዘልቀውም… እናቴ “ሁሉ በእጃቸው አይደል? አሁንስ ቢከለክሉን ምን እናመጣ ነበር? ዝም ወሄ!” ስትል ያቋርጠዋል፥ (ዝም ወሄ፥ በጉራጊኛ “ይህም መልካም ነው” እንደማለት ነው።)
 
መብራት ማግኘት እንደውመብታችን ሳይሆን የመብራት ኃይል ፈቃድ መሆኑን በደንብ ተገንዝበን ለምደነዋልና ብንንጨረጨርም ለአመላችን ነው። ለያውም በአፍታ የሚረሳ መንጨርጨር። ኤሌክትሪክ ይዞ እንደሚያንጨረጭር ዓይነት መንጨርጨር። ….ባለፈው፥ አንድ ጉብል የመኝታ ቤቱን ሶኬት አስተካክላለው ሲል መብራት ይዞት ሞቶ ተገኘ ተባለ። እንዲህ ነን!መድኃኒት የተቀመጠበትን ቦታ ለማየት ጭላጩ የጠፋ መብራት፥ የሰው ነፍስ ለመቅጠፍ ደራሽ ሆኖ ይመጣል።
 
የዛሬው ግን የተለየ ነው። በከፊል ነው የጠፋው… ትይዩ ካለው ሰፈር አለ። ትናንት ጠዋት የጠፋ እስካሁን አልመጣም። “እንኳን አደረሳችሁ” አላለንም። …ጭራሽ ቅርብ ሰፈር መብራት እየታየ በከፊል መጥፋቱ “ከእኛ ጋር ምን አላቸው?” ያሰኛል። አንድ ጓደኛዬ ደውሎ፥ ስንጫወት “ከምርጫ ጋር በተያያዘ ቂም አስቋጥራችሁ እንዳይሆን” ብሎ አሾፈብኝ። አብረን ሳቅን። ቻዎ ሳንባባል ስልኩ ተቋረጠ። ይህንንም ለምደነዋል። ኔትዎርኩ ነው! …ደግነቱ በጨዋታ መሀል ካልሆነ በቀር ማን ያስታውሳቸዋል? እንዲህ ሲጨላልም፣ ፀሐይቱ ቻዎ ስትል ግን መብራት ግድ ይታወሳል።
 
“ወይኔ… እንዲህ ይቀልዱብን?” ትላለች የጎረቤት ሰራተኛ።
 
“ምን ታረጊዋለሽ?” ሌላዋ ትቀጥላለች። (በራፍ ላይ ተገትረው ነው የሚያወሩት)
 
“ተስፋ መቁረጥ ነው ባክሽ! እንዲህ ለይተው ከወሰዱት አይመልሱትም። ከ3 ቀን በኋላ ስንረሳው ይመጣል።”
 
“ጊዜው በእጅ መሄጃ፥ እኛ የምንሄደው በእግር። ምን ያድርጉ?”
 
“ማለት?”
 
“ስልክ እንጨቱ ላይ የሚያስተካክሉት ነገር አለ። እንዲህ ተከፋፍሎ የሚሄድባቸውን ሳንቲም ተቀብለው ያስተካክላሉ እኮ”
 
“እውነትሽን ነው?”
 
“አዎ! ታች ሰፈር እንደዛ ነው ያስተካከሉት። አሉ”
 
“ስንት ከፈሉ?”
 
“150፣ 200 ቢሰጣቸው ያስተካክሉታል።”
 
ስለ አሰጣጡ ማውራት ቀጠሉ
 
አሰጣጥ….
 
በምክንያት (ከዚህ ቀደም “ፋሲካ” በሚል ርዕስ የለጠፍኩትን ለመተየብ) ይዤው ሳላስብ ማንበብ (ከመሀል መገረብ) የቀጠልኩትን “ግራጫ ቃጭሎች” መፅሐፍ እያነበብኩ ነው የምሰማቸው። ወንድሞቼ ደግሞ እንድንወጣ ያዋክቡኛል። (እግረ መንገዳችንን የሙዚቃውን ፆም ለአፍታ እንገድፋለን።)
 
“ቆይ አንዴ… ይህችን ላንብብ….”
 
“ኧረ ፋሲካ ነው!”
 
“አንቀፁም የፍስክ ነው ኧረ ።”
 
ተሳሳቅንና አነበብኩላቸው….
 
—–
“ዋናው አሰጣጥሽ ነው።” አልኳት።
በዚህ አባባሌ ቤቱ ውስጥ የነበሩ ጥቂት ሰዎች በሙሉ በሳቅ አይፈነዱም! ጫልቱ ራስዋ አፍዋን ወደ ሰማይ ሰቅላ ተንካካች። እየሳቁ፣ እያረፉ ደ’ሞ የተናገርኩትን ቃል እየደጋገሙ:….
“አሰጣጥሽ አላ !”
“ሆሆይ… አሰጣጥ! እ?”
“አሃ…. የት ትተዋወቃላችሁ?!”
በቃ የመሳሰለ የሚያበሽቅ ነገር መናገር ጀመሩ። ምን ለማለት እንደፈለግሁ እንዳልገባቸው ሁሉ ዕንባ ባቀረሩ ዐይኖቻቸው።
(ለመሆኑ ዕንባ የሚያስቀርር ምን ነገር ተናግሬ ነበር?)
 
[አዳም ረታ (1997) “ግራጫ ቃጭሎች” ገፅ 148]
—–
ሴቶቹ ስለ 150 እና 200 ብር አሰጣጥ አውርተው ጨርሰዋል። (አልሰማዃቸውም)
 
“ውኃውን መልቀቃቸው ግን ደስ አይልም?“ አለች ሴትዮዋ። ወሬው ጥሟት እንዳትገባባት መያዟ ይመስላል።
 
“ኧረ ባይለቁት ይሻል ነበር። ክንዳችን እስኪገነጠል፣ የትናየት ሄደን ቀድተን ካጠራቀምን በኋላ…” አለች ተበሳጭታ። (‘አንቺ አትቀጂ ምናለብሽ? እንደኛ ሞክረሽው ስቃዩን ብታውቂ ኖሮ ለመንግስት አቤት ትዪ ነበር’ የምትልም ይመስላል።
 
“ሆ… እውነትሽን ነው እኮ። እኛን ማቃጠል ነው ግን ስራቸው?”
 
“ስታዪው! በይ አፌን አታስለቅሚኝ።”
 
ማፅናኛ ይመስል ውኀው ተለቆልናል። እኛም ብርቅ ሆኖብን ውኃውን እየደጋገምን ነው። – ለናፍቆቱም። ለማቆሩም። ለምኑም። ለመርሳቱም። …መጠጣት ጥሩ ነው። ደግሞ ውኀ ስንፆም ነበር። ማለቴ ከቧንቧ እንደወረደ ውኀ መጠጣት ስንፆም ነበር። ይኸው ዛሬ ከቧንቧ ውኀ ቀድቶ በመጠጣት ፆማችንን ገደፍን።
 
መብራት ግን እየፆምን ነው። በፊትም አመጣጡ በፆም መሀል እንደማፍረስ ዓይነት ‘ብቅ’ ነበር። መብራቱ ብቅ ይልና ከብርሃን ፆማችን አፋርሶን እልም ይላል።
 
ልቤ ግን ይህን ትዘምራለች…
 
“በከበረች ሰንበትበአምላክ ትንሳኤ፥
ሰላም ተሰበከ በመላው ጉባኤ!
በመላው ጉባኤ በመላው ዓለም
የሰው ልጅ ተፈትቶ ታሰረ ሰይጣን!”
 
እንደመፈታታችን፥ ስርዓት ባለው ነፃነት የምንኖር ያድርገንማ!በድጋሚ መልካም የትንሳኤ በዓል ለምታከብሩት ክርስቲያን ወዳጆቼ ሁሉ!