‘በከበረች ሰንበት’

ሙዚቃ አሁንም እየፆምን ነው። የስራውን ይስጠው፥ መብራት ኃይል ከሙዚቃ የተፋታ በዓል እንድናሳልፍ አድርጎናል። ሞባይሎቻችን ያቆሩትን ኃይል እስኪያሟጥጡ ድረስ ሬድዮ ያመጣውን ሙዚቃ ሁሉ ተቀብለው ወደ ጆሮዎቻችን እንዲያሳልጡ ፈቅደንላቸው ነበር። …ነበር። (ለመነጋገሪያ የሚጠቅሙን እንደው እንደ እድል ነው። በዓመት በዓል ደግሞ ይብስባቸዋል። ዛሬ ወንድሜ “Merry Christmas” የሚል የፅሁፍ መልእክት ደርሶት ስንስቅ ነበር። ግን የቴሌ ነገር ስለማይታወቅ ያን ያህል አያስቅም።) …ይብላኝ ለእነሱ እንጂ፥ ለበዓል የቤተሰብ ጫጫታ ሙዚቃ ነው። የዓመት በዓል ድባቡ ራሱ ድምፃም ሙዚቃ ነው። ቀጤማውና ጭሳጭሱም ይዘምራሉ። …ዋዜማውን እንደው ዶሮና በጉ ያደምቁታል።
 
ያው ትናንት እንዳጫወትዃችሁ፥ ነፍሴን ካወቅኹኝ ጊዜ ጀምሮ፥ ከአንድ ጊዜ በቀር፥ ለፋሲካ በዓል መብራት በርቶልን አያውቅም። ….በዋዜማው ከጠዋት ጀምሮ ሌሊቱንም ጠፍቶ ያድርና እሁድ ይከሰት ነበር። መብራቱ! ”እንኳን አደረሳችሁ“ የሚል ዘመድ ይመስል ድንገት ብቅ ይልና የሁላችንም ገፅ ላይ ፈገግታ ይዘራል። በሰው አምሳል ሆኖ ያፌዝብን ይመስለኝ ነበር።
 
እኛም ወስደው ሲያመጡት እናመሰግናቸዋለን። “እሰይ!ኧረ እግዜር ይስጣቸው” ትላለች እናቴ። እንደ ትናንት የነሱንን አስታውሶ ሊራገም የሚያስብ ካለ፥ አይዘልቀውም… እናቴ “ሁሉ በእጃቸው አይደል? አሁንስ ቢከለክሉን ምን እናመጣ ነበር? ዝም ወሄ!” ስትል ያቋርጠዋል፥ (ዝም ወሄ፥ በጉራጊኛ “ይህም መልካም ነው” እንደማለት ነው።)
 
መብራት ማግኘት እንደውመብታችን ሳይሆን የመብራት ኃይል ፈቃድ መሆኑን በደንብ ተገንዝበን ለምደነዋልና ብንንጨረጨርም ለአመላችን ነው። ለያውም በአፍታ የሚረሳ መንጨርጨር። ኤሌክትሪክ ይዞ እንደሚያንጨረጭር ዓይነት መንጨርጨር። ….ባለፈው፥ አንድ ጉብል የመኝታ ቤቱን ሶኬት አስተካክላለው ሲል መብራት ይዞት ሞቶ ተገኘ ተባለ። እንዲህ ነን!መድኃኒት የተቀመጠበትን ቦታ ለማየት ጭላጩ የጠፋ መብራት፥ የሰው ነፍስ ለመቅጠፍ ደራሽ ሆኖ ይመጣል።
 
የዛሬው ግን የተለየ ነው። በከፊል ነው የጠፋው… ትይዩ ካለው ሰፈር አለ። ትናንት ጠዋት የጠፋ እስካሁን አልመጣም። “እንኳን አደረሳችሁ” አላለንም። …ጭራሽ ቅርብ ሰፈር መብራት እየታየ በከፊል መጥፋቱ “ከእኛ ጋር ምን አላቸው?” ያሰኛል። አንድ ጓደኛዬ ደውሎ፥ ስንጫወት “ከምርጫ ጋር በተያያዘ ቂም አስቋጥራችሁ እንዳይሆን” ብሎ አሾፈብኝ። አብረን ሳቅን። ቻዎ ሳንባባል ስልኩ ተቋረጠ። ይህንንም ለምደነዋል። ኔትዎርኩ ነው! …ደግነቱ በጨዋታ መሀል ካልሆነ በቀር ማን ያስታውሳቸዋል? እንዲህ ሲጨላልም፣ ፀሐይቱ ቻዎ ስትል ግን መብራት ግድ ይታወሳል።
 
“ወይኔ… እንዲህ ይቀልዱብን?” ትላለች የጎረቤት ሰራተኛ።
 
“ምን ታረጊዋለሽ?” ሌላዋ ትቀጥላለች። (በራፍ ላይ ተገትረው ነው የሚያወሩት)
 
“ተስፋ መቁረጥ ነው ባክሽ! እንዲህ ለይተው ከወሰዱት አይመልሱትም። ከ3 ቀን በኋላ ስንረሳው ይመጣል።”
 
“ጊዜው በእጅ መሄጃ፥ እኛ የምንሄደው በእግር። ምን ያድርጉ?”
 
“ማለት?”
 
“ስልክ እንጨቱ ላይ የሚያስተካክሉት ነገር አለ። እንዲህ ተከፋፍሎ የሚሄድባቸውን ሳንቲም ተቀብለው ያስተካክላሉ እኮ”
 
“እውነትሽን ነው?”
 
“አዎ! ታች ሰፈር እንደዛ ነው ያስተካከሉት። አሉ”
 
“ስንት ከፈሉ?”
 
“150፣ 200 ቢሰጣቸው ያስተካክሉታል።”
 
ስለ አሰጣጡ ማውራት ቀጠሉ
 
አሰጣጥ….
 
በምክንያት (ከዚህ ቀደም “ፋሲካ” በሚል ርዕስ የለጠፍኩትን ለመተየብ) ይዤው ሳላስብ ማንበብ (ከመሀል መገረብ) የቀጠልኩትን “ግራጫ ቃጭሎች” መፅሐፍ እያነበብኩ ነው የምሰማቸው። ወንድሞቼ ደግሞ እንድንወጣ ያዋክቡኛል። (እግረ መንገዳችንን የሙዚቃውን ፆም ለአፍታ እንገድፋለን።)
 
“ቆይ አንዴ… ይህችን ላንብብ….”
 
“ኧረ ፋሲካ ነው!”
 
“አንቀፁም የፍስክ ነው ኧረ ።”
 
ተሳሳቅንና አነበብኩላቸው….
 
—–
“ዋናው አሰጣጥሽ ነው።” አልኳት።
በዚህ አባባሌ ቤቱ ውስጥ የነበሩ ጥቂት ሰዎች በሙሉ በሳቅ አይፈነዱም! ጫልቱ ራስዋ አፍዋን ወደ ሰማይ ሰቅላ ተንካካች። እየሳቁ፣ እያረፉ ደ’ሞ የተናገርኩትን ቃል እየደጋገሙ:….
“አሰጣጥሽ አላ !”
“ሆሆይ… አሰጣጥ! እ?”
“አሃ…. የት ትተዋወቃላችሁ?!”
በቃ የመሳሰለ የሚያበሽቅ ነገር መናገር ጀመሩ። ምን ለማለት እንደፈለግሁ እንዳልገባቸው ሁሉ ዕንባ ባቀረሩ ዐይኖቻቸው።
(ለመሆኑ ዕንባ የሚያስቀርር ምን ነገር ተናግሬ ነበር?)
 
[አዳም ረታ (1997) “ግራጫ ቃጭሎች” ገፅ 148]
—–
ሴቶቹ ስለ 150 እና 200 ብር አሰጣጥ አውርተው ጨርሰዋል። (አልሰማዃቸውም)
 
“ውኃውን መልቀቃቸው ግን ደስ አይልም?“ አለች ሴትዮዋ። ወሬው ጥሟት እንዳትገባባት መያዟ ይመስላል።
 
“ኧረ ባይለቁት ይሻል ነበር። ክንዳችን እስኪገነጠል፣ የትናየት ሄደን ቀድተን ካጠራቀምን በኋላ…” አለች ተበሳጭታ። (‘አንቺ አትቀጂ ምናለብሽ? እንደኛ ሞክረሽው ስቃዩን ብታውቂ ኖሮ ለመንግስት አቤት ትዪ ነበር’ የምትልም ይመስላል።
 
“ሆ… እውነትሽን ነው እኮ። እኛን ማቃጠል ነው ግን ስራቸው?”
 
“ስታዪው! በይ አፌን አታስለቅሚኝ።”
 
ማፅናኛ ይመስል ውኀው ተለቆልናል። እኛም ብርቅ ሆኖብን ውኃውን እየደጋገምን ነው። – ለናፍቆቱም። ለማቆሩም። ለምኑም። ለመርሳቱም። …መጠጣት ጥሩ ነው። ደግሞ ውኀ ስንፆም ነበር። ማለቴ ከቧንቧ እንደወረደ ውኀ መጠጣት ስንፆም ነበር። ይኸው ዛሬ ከቧንቧ ውኀ ቀድቶ በመጠጣት ፆማችንን ገደፍን።
 
መብራት ግን እየፆምን ነው። በፊትም አመጣጡ በፆም መሀል እንደማፍረስ ዓይነት ‘ብቅ’ ነበር። መብራቱ ብቅ ይልና ከብርሃን ፆማችን አፋርሶን እልም ይላል።
 
ልቤ ግን ይህን ትዘምራለች…
 
“በከበረች ሰንበትበአምላክ ትንሳኤ፥
ሰላም ተሰበከ በመላው ጉባኤ!
በመላው ጉባኤ በመላው ዓለም
የሰው ልጅ ተፈትቶ ታሰረ ሰይጣን!”
 
እንደመፈታታችን፥ ስርዓት ባለው ነፃነት የምንኖር ያድርገንማ!በድጋሚ መልካም የትንሳኤ በዓል ለምታከብሩት ክርስቲያን ወዳጆቼ ሁሉ!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s