ቅምሻ፥ ከወንዜ…

ከሰዓት ረፋዱ ላይ፥ ድንገት ካገኘኋቸው በፌስቡክ የሚዛመዱኝ የወንዜ ልጆች ጋር ተገናኝተን ስንጫወት ቆየን። ደስም አለኝ። ከቆይታችንም ይህንን የጨዋታ ጫፍ መዘዝኩ፤… ሌላ ጊዜ ፈታ አድርገን እንጫወተው ይሆናል።
 
ወንዜ መነሻው ሰባተኛ ነው። ከሰባተኛ ሽቅብ በስተሰሜን ወደ አውቶብስ ተራ ይፈሳል፤ ….ቁልቁል በስተደቡብ ወደ አብነት ይሄዳል፤ ….ወደ ምህራብ ወደ አማኑኤል ይጓዛል፤ ….ደግሞ ወደ ምስራቅ ይሄድና በአብዶ በረንዳ፣ በምህራብ ሆቴል አሳልጦ ከሰፊው የገበያ ባህር ከመርካቶ ይቀላቀላል። ….የእኔ ወንዝ! የእኔ ቀዬ! የእኔ ሰፈር! የእኔ መንደር! የእኔ መርካቶ!
 
ከወንዜ ሕይወት ሞልቷል። እያንዳንዱ ቤት የራሱ ታሪክ አለው። እያንዳንዱ ሰው የራሱ፥ ያልተፃፈ ኃላፊነት አለበት። ገድል በየቤቱ ታጭቋል። ያላየው ከውኀው ያልጠጣ፥ ስለ ወንዜ ይህን ሲሰማ ግራ ሊገባው ይችላል። ‘አናውቀውም እንዴ? ምን ይቀባጥራል?’ ሊል ይችላል። አዎ አታውቁትም… እንደዚያው ነው። እላለሁ። …ሰፈሬን ስጠየቅ ከትንታኔው እጀምርና ኋላ ነው ስሙን የምናገረው። (ገፅ ገንብቼ ሞቼ። ሄሄሄ…)
 
የመርካቶ ወዳጅ ነፃ ነው። ፈታ ብሎ ማውጋትና ማስወጋት ይችላል። ታማኝ ነው። ሽርክ ካሉት ከሸቀበና ከቀረቀበውም ቢሆን ያካፍላል። ነገር ዓለሙ በጋራ ነው። (ይዞረው ጋራ ባይኖረውም፥ ይኖርበት ውብ የጋራ ስርዓት አለው።) ሲፈልግ “እናጋጭ” ይልሃል። ሲቸግርህ ተበድሮ ያበድርሃል። ስትከስር፣ ስራህ ሲዳከም እቁብ ሰብስቦ አንደኛ እጣውን ይሰጥህና ያቋቁምሃል። ክፉ ደግ ቢገጥምህ፥ ቤቱ ቤትህ ነው፤ እንግዶቹም እንግዶችህ ናቸው። ካበረብህም ደራሽ ነው። …መስመር ስትስት ሳይናገር፥ በዐይኑ እየተከታተለ ወደ መስመርህ ይመልስሃል።
 
የስጋ ዘመድ ሞቶባት፣ አቅሏን ስታ እዬዬዋን ስታቀልጥ፣ ደግሞ ፀጉሯን እየነጨችና በነሲብ ወዲህና ወዲያ እየተገማሸረች ስታለቅስ፣ እንባዋ ግራና ቀኝ ጉንጮቿ ላይ ሲወርድ…. በፀሐይ ሲያዩት የፊቷን ቀለም ይዞ፥ ጉንጯን የሸረሸረባት የሚመስል እንባ ፊቷን ሲያርሰው፣ ደግሞ በአፅናኞቿ ትግል ትከሻዋ ላይ ጣል የተደረገላት መቅረቢያ ነገር ተንከባሎ ወርዶ፤ አንዴ በእጇ ድለቃ…. አንዴ በልቧ ምት… ከሚተራመሰው ደረቷ ላይ፥ ሳይታሰብ ብቅ ብሎ እንደታየ ጡት…. ውበቱ እንደሚያስደነግጥ፤ …ጆፌ ያለ ሸርዳጅ ለቅሶ ደራሽ እጅ ወደላይ ብሎ ተማርኮ፥ አፅናኝ ይመስል…. ሰልስት፣ ሰባት፣ አስራሁለት እያለ አርባ፣ ሰማንያ ተዝካር እየተመላለሰ ማፅናናት የሚገብርለት፤ በሌለ አቅሙ የእዝን የሚጭንለት… ውበት፤
 
….ሰባተኛ ውበቷ እንዲህ ነው። እንዲህ እሳት በላሰ ኑሮም፣ በተብረከረከ የመግዛት አቅምም፣ በማይቀመሰው የገበያ ሁኔታም፣ በስራ ማጣትና በገቢ መዳከምም፣ ቅልጥ ባለ ግራ መጋባት ውስጥም… አፈትልኮ የሚታይ ውበት አለ። ልብን ትርክክ የሚያደርግ፣ ብዙ ስለመኖር የሚያነሳሳ ልዩ ሕይወት አለ። የመርካቶ ሰው፥ እንኳን አዱኛውን ችግሩንም ያካፍላል። ሳይነጋገር ተግባብቶ ይተባበራል። …ፈለጉም አልፈለጉም፥ የአኗኗር መስተጋብሩ እንደ ወንዙ መፍሰስን ያስገድዳል።
 
አዲስ ከሆንክ ስትቆይ ትለምደውና፥ ከሰፈሩ ‘ሀኪም ይንቀለኝ’ ትላለህ። ድንገት ሰፈር ቀይረህ ብትሄድ፥ ሰበብ ፈልገህ ትመላለሳለህ። ቤተሰብ ወይ ጓደኛ ካለህ ደግሞ፥ ለመምጣት ጥሩ ምክንያት ይዘህ ቅዳሜን አንተ ነህ የምትቀሰቅሳት፤ ዱለቷን አሳምራ “የተንቢ” ትልሃለች። ደግሞ የጨዋታ ዱለት በቡና ታወራርድ ዘንድ ንፁህ ቡና ታቀርብልሃለች። ብቻህን መሆን አትችልም። ብቻ መብላትም አታስብም። ምን ታረገዋለህ? – ነገር ዓለሙ በጋራ ነው። መርካቶ ነዋ!- ፈርጀ ብዙ ሕይወት የሞላበት።
 
መርካቶ ሰፈሬ
¯¯¯¯¯¯¯¯
ቅመም ተራ፣ ሽንኩርት ተራ፣
ሸራ ተራ፣ ሸማ ተራ፣
ጌሾ ተራ፣ ብረት ተራ፣
ብቅል ተራ፣ ገብስ ተራ፣
እንትን ተራ፣. . . እንትን ተራ፣. . .
ተደልድሎ፣ ተሰይሞ፣
ሁሉም መደብ በየተራ፣
እንዴት የለው የሰው ተራ?!
—-
ዮሐንስ ሞላ (2005) “የብርሃን ልክፍት” ገጽ፥ 72

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s