የት ሄዱ?!

ባንድ እነርሱ፥
— ብዙ —
እየተሸከሙ፣
ያደምቁኝ የነበር፣
ተስፋ ያለመልሙ፤
ዞር ባልኩኝ አፍታ፥
ባንጋጠጥኹኝ ቅፅበት፥
ካ’ይኔ ሲጋጠሙ፥
ያፍታቱኝ የነበር፥
ሀሴት ይቀምሙ፤
የብርሃን ቁሶች፣
የወጋገን ኳሶች…

ከሰማይ ተሰቅለው፥
ምሽቱን ያቀልሙ፣
ብትንትን ፈርጥ ሆነው፥
ውበት ይሸልሙ፤
ጨለማውን ሰማይ፥
ያሞግሱ፣ ያገርሙ፤
ምኞት ይቀምሩ፣
ተስፋን ይቀምሙ፣
የነበሩት ያኔ፥
የተስለመለሙ…
የብርሃን ነጠብጣብ፥
የተስፋ እንክብሎች
የት ሄዱ ከዋክብት?

ታነቃቃ የነበር፥
ታጃጅል የነበር፥
እያቁለጨለጨች…
የብርሃን ግንዲላ፥
በውብ ምሽት በቅላ፤
ያዙኝ ያዙኝ ‘ምትል፣
አውርዱኝ፣ አውርዱኝ፥
ብሉብኝ፣ ብሉብኝ፣
(ዋጡኝ ዋጡኝ፥ ወላ፥
ሰልቅጡኝ፣ ሰልቅጡኝ)
የምትል የነበር…
የወጋገን ግግር፣
የብርሃን ትሪ፥
ከሰማይ ተሰቅላ፥
ተስፋን ታለመልም፣
ባዶውን ትሞላ፤
የነበረች ያኔ፥
ስጋ ትቀባባ፥
ኩስምንምኑን ገላ፤
ሞጌ ጉንጩን ሁላ፥
ድንቡሽቡሽ ታስመስል፣
ፈገግታ ደልድላ፤
ታስውብ የነበረች፥
ዳፍንታሙን አየር፥
ብቅ ባለች ቅፅበት፥
ታፍመው የነበር፣
ታቀላ እንዳለላ፤
የት ሄደች ጨረቃ?

እ’ሷ ስታረፍድ፥
ከዋክብት ሲቀሩ፥
ብቅ ይሉ የነበር፣
ደስታ ይቆሰቁሱ፣
ሳቅ ይወተውቱ፣
ተስፋን ያነቃቁ፥
እምነትን ያደምቁ፥
ያጫውቱ የነበር፥
ካ’ሳብ ያናጥቡ፣
ኦናን ያዋክቡ፥
ድብርት ያጣጥቡ፣
ያጓጉ የነበር፥
የት ሄዱ አብሪ ትሎች?

ቅርንጫፎቻቸው፣
እርስ በ’ርስ ሲጋጩ፥
ሲያረግዱ፣ ሲንሿሹ፤
ንፋስ እያፏጨ፥
ሲገፋቸው ጊዜ፣
ደርሰው ሲወራጩ፣
እዚህ እዚያ ሲነኩ፥
ከብበው ሲፈነጩ፥
ያበሩ ይመስለኝ፥
የነበረው ያኔ፣
የት ሄዱ ዛፎቹ?

ቀን ሲመሽ ጠብቆ፥
ምሽቱ የጠመመ፣
ተደቅድቆ ጠቁሮ፥
ሰማይ የፀለመ፥
ሳቅ፣ ተስፋ የራቁ፥
እምነት የዘመመ፣
አልጋ እግሩ የዛለ፥
እንቅልፍ የታመመ፣
እረፍት የደከመ፣
ከቶ ለምን ይሆን?
ድፍንፍን ማለቱ፥
ከሌላ ተስማምተው፥
ከሌላ ተዋድድደው፣
ጨልሞ ሊቀር ነው?
የሚነግረኝ ማነው?
ከጊዜ በስተቀር፥
የሚያሳየኝ ማነው?

ብቻ ግን…
ይኽ ምሽት ካለፈ፥
ሌ’ቱ ከተገፋ፣
ፅልመት ከረገፈ፣
እንደምንም ብሎ፥
አንድ’ዜ ከነጋ፥
ዳግም አይጨልምም፣
ብርሃን ትቆማለች፥
(ብትፈልግ ከሰማይ—
እልም ስልም ትበል)
አትጠፋም ደጄ ጋ፥
አትጠልቅም ከእኔ አልጋ!

/ዮሐንስ ሞላ/

“ሰዶ ማሳደድ ካማረህ…”

“መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ፣1233402_436151109839261_1389450980_n
እንኳን ሰው ዘመዱን፣ ይጠይቃል ባዳ።”

ልጅ ሳለን ቢሆን ኖሮ፥ ይህኔ ወንዶቹ “አበባ” ስለን እንኳን አደረሳችሁ ብለን ከዘመድ ጎረቤት ቤት የሰበሰብነውን ፍራንክ እያሰብን፤ ሴቶቹም “አበባዮሽ” ጨፍረው ያገኙትን ሽልማት ሳንቲም እያብሰለሰሉ፣ እንቅልፍ አይወስደንም ነበር።

የበዓል ዋዜማው የፎርም (አበባ) ቆጠራ እና የገቢ ቅድመ ስሌት ቀን ነው። ከሰሞኑ በቀለም የተጨማለቀው እጅም በዚህ ቀን ተፈቅፍቆም ቢሆን ይጠራል። ከዚያ ሲነጋ፥ በየጎረቤትና ዘመድ ቤት “እንኳን አደረሳችሁ” እየተባለ አበባ ይሰጣል። ቀኑ ረፍዶ ረስተን አበባ ያልወሰድንባቸው ቤት እማወራ/አባወራዎች ‘ለምን አበባ አላመጣህም?’ ብለው እንዳይቆጡን ስለምንፈራ የምንሄድበትን ቤት ዝርዝር ቀድመን አዘጋጅተን፥ አበባውንም ቆጥረን ነው የምናዘጋጀው።
…ቤትም፥ “ኧከሌ ቤት ውሰዱ” እያሉ የረሳነውን ያስታውሱን ነበር። ሴቶቹም አዲስ የተገዛላቸውን ልብስ በዋዜማው ለብሰው “አበባዮሽ” እያሉ በየቤተዘመዱና ጎረቤቱ ቤት እየዞሩ ይጨፍሩ ነበር።

ነበር….!?

በርግጥ አበባዮሽ የሚጨፍሩ ጥቂት ልጆች ዛሬም ይታያሉ። ለዛና አጨፋፈሩ ግን እየተበላሸ እየተበላሸ፣ ስሜቱም እየቀዘቀዘ፣ እየቀዘቀዘ ነው የመጣው። ሰዉም ለልጆቹ የሚሰጠው ምላሽ፥ ነገሩን ከልመና ጋር እያቀራረበው የሚያሳፍራቸውም ይመስለኛል። ….አበባ የሚስሉ ጥቂት ልጆችም እንዳሉ ዛሬ ቤት ሲመጡ ተመልክቻለሁ። – ምናልባት ከቤቶቻቸው ተደብቀው?!

ሆኖም ግን ዘመናዊ (ነን ባይ) ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲህ ባሉ የበዓል እንቅስቃሴዎች ላይ እንዲሰማሩ የሚፈቅዱ አይመስለኝም። ከማጣትና ከመሳጣት ጋር ሲያገናኙት ይስተዋላል። ነገር ግን፥ በዓልና ባህል ከማግኘትና ከማጣት ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር ስለሌለ፥ ከማሸማቀቅና ከመከልከል ይልቅ ሊያበረታቷቸው ይገባል። አበባ ሲስሉ ቀለም እናቀብላቸው…. አበባዮሽ ሲሉ ትክክለኛውን ዜማ እናስተላልፍላቸው….

“ሰዶ ማሳደድ ካማረህ፥ ዶሮህን በቆቅ ለውጥ” ይባላል፥… እናም፥ ኋላ ማሳደዱ እንዳያደክመን፥ ባህሎቻችን እንዳይጠፉ እንንከባከብ። ከትውልድ ትውልድ፥ ከነሙሉ መልካቸው ስለመዝለቃቸው እንምከር።

ሸጋ እንቁጣጣሽ አሳለፍን!

ወዳጄ ወዳጄ የምንባባልበት፣ እርስበርስ በመመካከርና በመከባበር የምናፈራበት ዓመት ይሁንልን።

አሜን!