ልጅ ሳለን ቢሆን ኖሮ፥ ይህኔ ወንዶቹ “አበባ” ስለን እንኳን አደረሳችሁ ብለን ከዘመድ ጎረቤት ቤት የሰበሰብነውን ፍራንክ እያሰብን፤ ሴቶቹም “አበባዮሽ” ጨፍረው ያገኙትን ሽልማት ሳንቲም እያብሰለሰሉ፣ እንቅልፍ አይወስደንም ነበር።
የበዓል ዋዜማው የፎርም (አበባ) ቆጠራ እና የገቢ ቅድመ ስሌት ቀን ነው። ከሰሞኑ በቀለም የተጨማለቀው እጅም በዚህ ቀን ተፈቅፍቆም ቢሆን ይጠራል። ከዚያ ሲነጋ፥ በየጎረቤትና ዘመድ ቤት “እንኳን አደረሳችሁ” እየተባለ አበባ ይሰጣል። ቀኑ ረፍዶ ረስተን አበባ ያልወሰድንባቸው ቤት እማወራ/አባወራዎች ‘ለምን አበባ አላመጣህም?’ ብለው እንዳይቆጡን ስለምንፈራ የምንሄድበትን ቤት ዝርዝር ቀድመን አዘጋጅተን፥ አበባውንም ቆጥረን ነው የምናዘጋጀው።
…ቤትም፥ “ኧከሌ ቤት ውሰዱ” እያሉ የረሳነውን ያስታውሱን ነበር። ሴቶቹም አዲስ የተገዛላቸውን ልብስ በዋዜማው ለብሰው “አበባዮሽ” እያሉ በየቤተዘመዱና ጎረቤቱ ቤት እየዞሩ ይጨፍሩ ነበር።
ነበር….!?
በርግጥ አበባዮሽ የሚጨፍሩ ጥቂት ልጆች ዛሬም ይታያሉ። ለዛና አጨፋፈሩ ግን እየተበላሸ እየተበላሸ፣ ስሜቱም እየቀዘቀዘ፣ እየቀዘቀዘ ነው የመጣው። ሰዉም ለልጆቹ የሚሰጠው ምላሽ፥ ነገሩን ከልመና ጋር እያቀራረበው የሚያሳፍራቸውም ይመስለኛል። ….አበባ የሚስሉ ጥቂት ልጆችም እንዳሉ ዛሬ ቤት ሲመጡ ተመልክቻለሁ። – ምናልባት ከቤቶቻቸው ተደብቀው?!
ሆኖም ግን ዘመናዊ (ነን ባይ) ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲህ ባሉ የበዓል እንቅስቃሴዎች ላይ እንዲሰማሩ የሚፈቅዱ አይመስለኝም። ከማጣትና ከመሳጣት ጋር ሲያገናኙት ይስተዋላል። ነገር ግን፥ በዓልና ባህል ከማግኘትና ከማጣት ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር ስለሌለ፥ ከማሸማቀቅና ከመከልከል ይልቅ ሊያበረታቷቸው ይገባል። አበባ ሲስሉ ቀለም እናቀብላቸው…. አበባዮሽ ሲሉ ትክክለኛውን ዜማ እናስተላልፍላቸው….
“ሰዶ ማሳደድ ካማረህ፥ ዶሮህን በቆቅ ለውጥ” ይባላል፥… እናም፥ ኋላ ማሳደዱ እንዳያደክመን፥ ባህሎቻችን እንዳይጠፉ እንንከባከብ። ከትውልድ ትውልድ፥ ከነሙሉ መልካቸው ስለመዝለቃቸው እንምከር።
ሸጋ እንቁጣጣሽ አሳለፍን!
ወዳጄ ወዳጄ የምንባባልበት፣ እርስበርስ በመመካከርና በመከባበር የምናፈራበት ዓመት ይሁንልን።
አሜን!