የሬስቶራንቱ ብርሃን መደብዘዝ… የሙዚቃው ጩኸት… አልረበሹኝም። ከበሩ ሲገባ በስተቀኝ በኩል ካለው ማዕዘን (corner) ላይ ተጎልቼ መፅሐፍ አነባለሁ። በርግጥ መፅሐፉ ያጓጓል። ግን አይሰለቸኝም እንጂ፥ እስኪሰለቸኝ ተመላልሼ አንብቤዋለሁ። …ያን ያህል ወዝጋባም አይደለሁም። …ያን ያህል ሙዚቃ መሀል ሳይቀር የሚጣድ ጎበዝ አንባቢ ሆኜም አይደለም፥ ቢራ ልጠጣ ገብቼ የማነበው።
ከእኔ ጋር ጠረጴዛ የተጋራው ሰው፥ ንግግር ለመጀመር ያለውን አዝማሚያ ተመልክቼ፥ እኔ በርሱ የጨዋታ ሙድ ውስጥ ስላልሆንኩ እርሱን ችላ ለማለት ያመጣሁት ሀሳብ ነበር።
“ቀሽት… ሰው አለው?” ብሎኝ ነበር ሲገባ።
በልቤ ‘ምነው ካልጠፋ ወንበር ብዬ’ እንዲቀመጥ በፊቴ እንቅስቃሴ ጠቆምኩት እንጂ ሌላ ነገር አልተናገርኩም።
“ኡፍ… ተመስገን!” ሲል፥ እኔም በልቤ ‘ኡፍ ተመስገን’ አልኩ እንጂ፥ ብቻውን ያወራው ነው ብዬ መልስ አልሰጠሁትም።
“በቃ የዚህ ቤት ልጆች እኮ…” ብሎ፥ እንደ እህት ጠብ እርግፍ ብለው፣ ተቅለስልሰው የሚያስተናግዱትን ገራም አስተናጋጆች ሊያማልኝ ሞከረ።
አሁንም ዝም አልኩት። ውስጥ ውስጡን ተበሳጭቻለሁ። ‘የዚህ ቤት ልጆች እኮ…’ ብዬ፥ መሀልይ ላዘንብለት ነበር፤ ግን የጨዋታ ጥማቱን እንዳላረካለትና ብዙ እንዳላስጠማው ፈራሁና ተውኩት። የሰው ልጅ በጠጣ ቁጥር ያጣጥማል። ባጣጣመ ቁጥር ደግሞ እንደ አዲስ ይጠማል። መሰለኝ! እንጂማ ‘የማያውቁት ሀገር አይናፍቅም’።
ከርሱ ሽሽት የገለጥኩት መፅሐፍ ዓለም ሆኖኛል። ያዘዝኹትን ዋልያ (ምን እናርግ? “ዘመኑ የዋልያ” ነው አሉና ከአምበር ከረበቱን። ሃሃሃ…) እየተጎነጨሁ ንባቡ ውስጥ ሰጥሜያለሁ። ድንገት ለየት ያለ ጫጫታ ሰምቼ ቀና አልኩ። ከእኔ ጋር ወንበር የተጋራው ሰውዬ፥ ጎረቤት ጠረጴዛ ላይ ካለ ሰው ጋር ጨዋታ ጀምሯል።
በተለይ የመጀመሪያዎቹን ሶስት ቃላት ጎተት አድርጎ… “ች ግ ር… እ ና ቱ… ት**!…. ቀበሌ ለቀበሌ ያንከራትተኛል። የእኔ ጌታ፥ ገና በሩ ጋር ስደርስ ጠንቋይ ቤት የገባሁ ነው የሚመስለኝ። ይኸው ቢያዩኝ ብዬ፥ እንደ ውሻ አፈጣለሁ….” አለ።
ከዚያ በኋላ፥ ዦሮዬን ከእነርሱ ላይ ሀኪም ይንቀለው አልኩኝ።
በልቤም አልኩ፥ ‘አሜን! ች ግ ር… እ ና ቱ… ት—!’
.
.
እናላችሁ፥ የሰውዬውን ንግግር ለእናንተ ሳያጋሩ ማደር ራስ ወዳድነት መስሎኝ ተከሰትኳ። እንዴ… በዛ ላይ አርብ እኮ ነው። 🙂