ባይገርምሽ 15 (ጥምቀት እንዳትቀሪ)

‘አንቺ ያ’ለላ ሙዳይ’ የልቤ ማህደር፣
የነፍሴ ይባቤ፣ የህይወቴ መስመር፣
– ዜና መዋዕሉ፣ መዝገቡ፣ ጦማሩ፣
ቅኔ፣ መሀልዩ፣ መወድስ፣ መዝሙሩ፣
ሲጠብቅሽ ሂጂ፣ ቀድመሽው ስፈሪ፣
ከውድሽ ጋር አብሪ፣
ጥምቀት እንዳትቀሪ!

በምንጭ ውሀ ታጥቦ፣ ገላሽ ተሞናሙኖ፣
በቀስል ጠራርቶ፣ በወይባ ጢስ ታጥኖ፣
__ገፅሽ ተሽሞንሙኖ፣
ባ’ደስ ቅቤ ልውስ፣ አምሮ ተሰማምሮ፣
ተለቃልቆ፣ ልቆ፣… ፀጉርሽ ተጎንጉኖ፣
ቀንበጤ ድረሺ፣ ደርሰሽ ተዟዟሪ፣
ጥምቀት እንዳትቀሪ!

ወርቀዘቦ ለብሰሽ፣ ሜሮን ተቀብተሽ፣
ፍቅር ተለብጠሽ፣ በ’ንቁ ተንቆጥቁጠሽ፣
ባ’ይነ ርግብ ተውበሽ፣ ሽፎን ተሸፍነሽ፣
በአልቦ፣ በአሸንክታብ፣ በድሪ አምባር አምረሽ፣
ከፀሀይ – ሁለት እጅ፣
ከጨረቃ – መቶ፣…
ከሴቶች – አንድ ሺ… ብርሀን ተደጉሰሽ!
ዐይንሽን አንከባይ፣ ጥርስሽን ፈልቅቂ፣
መንደሩን አድምቂ፣ ገላዬን አሙቂ!
በአደባባይ አብሪ!
ጥምቀት እንዳትቀሪ!

ምን ይላት ፃ’ይቱ?!… ትበደርሽ ካንቺ!
ካ’ንቺ ተውሰድና፣ ከብርሀንሽ ሰርቃ፣
ታብራለት ላ’ለሙ፣ ትዋልለት ደምቃ።
ጨረቃማ ልምዷ፣ መስረቅ መበደሩ፣
ከደማቅ ጋር ውሎ፣ ሲያበሩ መኖሩ፤
ትስረቅ ፍቀጂላት፣ ውጪላት ከጓዳ፣
‘አዬ ጉድ!’ ይበሉ! ድረሽ የ’ኔ እንግዳ
ባ’ል ነው ዛሬ ነዪ!…
ደርሰሽ ለባ’ል ታዪ፣
ደርሰሽ በባ’ል አብሪ፣
ጥምቀት እንዳትቀሪ!

በቀናው ተፃፊ፣ በደምቡ ስመሪ፣
በደማቅ ቅለሚ፣ በእውቁ ተሰሪ፣
በንፁህ ታተሚ፣ በወግ ተሰተሪ፣
ነይልኝ መፅሀፌ፥…
ተሰማምረሽ ውጪ፣
አምረሽ ደምቀሽ ምጪ፣
በ’ባል ተነበቢ፣ ከጀማው ስፈሪ፣
ጥምቀት እንዳትቀሪ!

በጥበብ ቀሚስሽ፣ ተውበሽ ድረሺ፣
በጎዳናው ታዪ፣ ወጥተሽ ተምነሽነሺ፣
ወገብሽን ሸብ አርጊው፥ በመቀነትሽ፣
ወገቤን ልጠፍንግ፣ ታጥቄ ልይሽ፣
በይ ውረጅ፣ እንውረድ፣
‘ያሸነፈ’ ይባል፣ ነይ እንወራረድ፣
ከእኔ ጋር ጨፍሪ፣
ጥምቀት እንዳትቀሪ!

ነጠላው ይገረም፣ ይውረድ ተንሸራትቶ፣
ሻሽሽም ይደመም፣ ይሽቀንጠር ተፈትቶ፣
ዝናር፣ መታጠቂያ፣ ቀበቶዬ ይላላ፣
ልግጠም ካ’ንቺ ገላ፣
ይውደቁ ሜዳ ላይ፣
‘ያዥልኝ ያዝልኝ’ ከእኔ ጋ እንተያይ፤
በባ’ሉ ጨፍሪ፣ አብረሽኝ እመሪ፣
ጥምቀት እንዳትቀሪ!

በነፃነት ደምቀን… እንበል ‘ዋካ ዋካ’
ከከተሜው ቀድተን፣ ዳንሱን ባርሞኒካ፣
ብር ዋንጫ ልቅለቃ፣ እኔክሽ እኔካ፣
በይ እንወራረድ፣ ወርደን እናስነካ፣
በባህል ጨዋታ፣ በስሙር ሽክሸካ፣
ተጎኔ ግጠሚ፣ ከጎንሽ ልሰካ፣

የአምስት የአስር ሳልል፣ ሳልለካ ሳልሰፍር፣
ላ’ንቺ ለ’ኔ ፍቅር፣ ላስመትር አገዳ፣
ከአገዳም – የፍቅር፣ የመውደድን ቃና፣
– የመውደድን ጥንቅሽ፣ የፍቅርን ሸንኮራ፣
አስቆርጬ ልስጥሽ፣ በይ ነይ ከእኔ ጋራ፣
ከውድሽ ስመሪ፣
ጥምቀት እንዳትቀሪ!

የዘገሊላም ‘ለት…
ከብቦ፣ ተሰብስቦ…
“ሚካኤሊፊ ገብርኤሊ ወጂን፣
ሃደ ዋቀ ኬኛ ማሪያሚ፥ ኮቱ…”
እያለ በዜማ ሲያዜም ምእመኑ፣
‘ከሚካኤልና ከገብርኤል ጋራ፥
ያ’ምላክ እናት ማርያም፥ ምጪልን አደራ…’
እያለ ሲጣራ፣
ናልን የእኛ ጌታ! ጠጃችን ተንጣፏል…
እያለ ሲማፀንራ፣ ሲለው ማራናታ፣
ምህረቱን ሲጠና፣ በሆታ በእልልታ…

ሌላ ምን አውቃለሁ?
ዜማውን ሰርቄ ዝም ብዬ እጣራለሁ
– ‘ኮቱ ውዴ ኮቱ…ኪያ ኮቱ’ እላለሁ፣
ህይወቴን አጣፍጪ፣
ናፍ ኮቱ በሬዱ!… በነፍሴ ድረሺ፣
ወይን ጠጄ ምጪ፣
ጥምቀት እንዳትቀሪ!

ልቤ ባንቺ ፍቅር፣ በመውደድሽ ታማ፣
በትዝታሽ ዝላ፣ በናፍቆት ቆዝማ፣
ጃርሳ ቢያ ፈርደው… እንዲጥሉሽ ጉማ፣
ከተራው ላይ ጉማ፣
ጥምቀቱ ላይ ጉማ፣
ጃንሜዳ ላይ ጉማ፣
…የመውደዴን ካሳ፣ እጠባበቃለሁ፣
‘ያደ ኪያ’ ብዬ ደጅ ደጁን አያለሁ።
ናፍ ኮቱ ጃለሌ! አስኮቱ በሬዱ!
ወደ እኔ ብረሪ፣
ጥምቀት እንዳትቀሪ፣

እንትን ሙሉ መውደድ፤ ተስፋ፣ ፍቅር እምነት፣
እንትን ሙሉ ክብር፤ ናፍቆት፣ ኩራት፣ ጉልበት፣
– ጎንሽ እንዲጠገን፣ እንድትታከሚ፣
ዋጋው ሳያግደኝ፣ ቅርጫት ሙሉም ሎሚ፣
ይዤ እቆይሻለሁ!
አንበሳ ገድዬ፣ አንፋሮ ሰርቼ፣ አጠብቅሻለሁ፣
ውዴ የእኔ ጋሻ፣ በቶሎ ገስግሺ፣
ፍጠኝ ባንቺው መጀን፣ ‘ሀሀይጉማ’ እንበል፣
ዘልቀሽ እንጨፍር፣ ደርሰሽ እንንፏለል፤
ከእኔ ጋር ስመሪ፣
ጥምቀት እንዳትቀሪ!

ፍቅርሽ ያሰከረኝ፣ መውደድሽ ያዛለኝ፣
ትዝታ ያከሳኝ፣ ናፍቆት ያቀጨጨኝ፣
የፍቅርሽ ምርኮኛ፣ ጥበቃ ያደከመኝ፣
ሲንቢሮን ሂንታኔ፥ በርሬ ‘ማልደርስ፣
ወፌ ብር ብለሽ፥ አቀዝቅዥኝ ደርሰሽ፥
እጠብቅሻለሁ…. እንዳትቀሪ በቃ!
ተኝተን ስንነቃ… ጥምቀት ነው፤…
ባ’ልሽ ነኝ፤…. በዓሌ ነው፤
አደራኬ ውዴ፥….
ጩጳ ሂን ሀፊኒ!
ጥምቀት እንዳትቀሪ!

ዮሐንስ ሞላ

መፍቻ
——
ዋካ – በስዋሂሊኛ ‘መቃጠል’ እንደማለት ነው።
ሚካኤሊፊ ገብርኤሊ ወጂኒ ሃደ ዋቀ ኬኛ ማርያሚ ኮቱ – “የአምላክ እናት ማርያም ሆይ ከሚካኤልና ከገብርኤል ጋር ነይ” ማለት ነው።
ኮቱ (ጠብቆ) – በኦሮሚኛ ‘ነይ’ ማለት ነው።
ናፍ ኮቱ በሬዱ – ‘ነይልኝ የኔ ቆንጆ’
ጃርሳ ቢያ – ‘የአገር ሽማግሌዎች’
ጉማ (ማ ላልቶ) – ካሳ
ያደ ኪያ – የእኔ ናፍቆት
ጃለሌ – ፍቅሬ
አስኮቱ በሬዱ – እዚህ ነይ የኔ ቆንጆ
ሲንቢሮን ሂንታኔ – ወፍ አይደለሁ
አደራኬ – እባክሽን
ጩጳ ሂን ሃፊኒ – ጥምቀት እንዳትቀሪ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s