፩
ከአሲድ፣ ከዱላ፣
ከጥፊ፣ ከቢላ፥
የተረፈ ገላ…
በሎሚ ታክሞ፣ ጃንሜዳ ተበላ፤
ዳግም እስኪታመም፤ —
— እስኪያገኘው ሌላ።
፪
በ ‘ስሟ ለማርያም’ ከደጅሽ ታድሜ፣
ቁራሽ ልማጠንሽ፥ ከበራፍሽ ቆሜ፣
ካ’የሁሽ ጀምሮ፣…
ፍቅርሽ ሰቅዞኛል፣ ልብሽ ልቤ ገብቶ፤
ሐሳቤ ካ’ንቺው ነው፣ ከደብሩ ሸፍቶ፤
ፍቀጅ እመቤቴ!…
ሎሚ መግዣ የለኝ፣ ውርወራ አላውቅ ከቶ፣
ጥምቀት ብቅ ብዬ፣ ልንካሽ በ’ስክሪፕቶ፤
፫
መበተኑንማ ማንም ይበትናል፤ —
— (ቅርጫቱ ከሞላ) ያገኘ እንደው ሎሚ፤
መታመሙንማ ሁሉም ታማሚ ነው፤ —
— (ደረቱን ከመቱት) ካገኘ አስታማሚ።
ልብ የሚጠይቀው፣ የማይገኘውስ…
(ወዳቂን ለቃሚ) ለቅሞ ተጠቃሚ፤
ፍሬውን ፍለጋ ካ’ፈር ተንከባልሎ፥…
(መድኃኒት ቀማሚ) ቀምሞ ታካሚ።
፬
አቅላቢ፣ ቀላቢ፥… ነበረ ግብራችን፣
ወርዋሪ ወዳቂ፥… ነበር ልማዳችን፣
መቺና ተመቺ፥… ነበር ጨዋታችን፤…
“አንበላለጥም፣ እኩል ነን!” ካላችሁ፣
አቅማችሁ ከቻለ፣ ሎሚ ካገኛችሁ፤
ሞክሩት እንግዲህ፥ ቦታ እንቀይራችሁ፤
— እናንተ ወርውሩ፥ ከቀለብንላችሁ።
፭
ለመድኃኒት ጠፍቶ፣ ዋጋው ጣሪያ ደርሶ፣
ደረት ሁሉ ጠብቦ፣ ከአንገት ተቀልብሶ፣
እንጀራ ለቀማ፥ ሰው ሁሉ አጎንብሶ፣
“አለሁ” ማለት ከፍቶ፣ ሰውነት ኮስሶ፣
ሎሚ መወራወር ጡር ሆነ ጨርሶ።
፮
ሴቱ ባ’ይን ጥቅሻ፥ ወድቆ እያስቸገረ፣
ወንዱ የግርንቢጥ፣ በ ‘አዩኝ አላዩኝ’፣
— በ’ጣሉኝ አልጣሉኝ’፥ እየተሸበረ፣
በጨዋታው ደንቦች፣ በሕግጋቱ ብዛት፥ እየተማረረ፣
ፀሐይ ወጥታ በገባች፥ ‘ሚገዛ እየጠፋ፣ ዋጋው እየናረ፣
ሎሚ መወራወር፥ ታሪክ ሆኖ ቀረ።
ዮሐንስ ሞላ (2005) “የብርሃን ልክፍት” ገጽ 77