“የፍትህ ያለ” ብለን እንጩህ? ወይስ፥ የጆሮው ልኬት ይሄው ነው??

/A.S. ከዚህ በታች የምታነቡት፥ ከ200 ሜትር በላይ በማይራራቁ 2 መንደሮች ውስጥ የተከናወነ ነው።/

የመጀመሪያው፥ ከዓመት በፊት የተፈፀመ ነው።

አንዱ ጎረምሳ፥ 8 ወንድ ህፃናትን መድፈሩ ተጠርጥሮ ተይዞ፣ የሀኪም ማስረጃና የተጠቂዎች ምስክርነት ተደርጎ፥ ጥፋተኛ ነህ ተባለና 17 ዓመት ተፈርዶበት መዝገቡ ተዘግቶ ተመለሰ። ነገር ግን ፍርዱ ከወሬነት ሳይዘል ቀርቶ፥ ከ6 ወራት እስራት በኋላ ተፈትቶ፣ ወንጀለኛው በሰፈሩ ይንጎማለል ያዘ። የተጠቂ ህጻናት ወላጆች ‘ኡኡ’ ብለው እንባቸውን እያዘሩ ነገሩን ለማጣራት ሲሞከሩ፥ “የደረሰን በ1 ዓመት መቀጣቱን ነው።” ብለው መዝገብ ያሳኋቸዋል። (እንዳሉት) “ይግባኝ” ለማለት ሞከሩ። ግን ተጠቂዎች ፣ አቅመ ቢስ ናቸውና፥ “እኛ አጣርተን እንነግራችኋለን” ተብሎ ቤት ቤታቸው ገቡ። ተረሳሳ መሰለኝ እስካሁን ወፍ የለም። ጎረምሳውም ይንጎማለል ይዟል። ተጠቂዎችም ከነጥቃታቸው ተኮራምተው ተቀምጠዋል 😦

ሌላኛው፥ የዛሬ ወር ገደማ የተፈፀመ ነው።

ሌላው ጎረምሳ 4 ወንድና 2 ሴት ህፃናትን በመድፈር ተጠርጥሮ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለና፥ ምርመራው ተጀመረ። ነገሩን ለፖሊስ አመነ። ፍርድ ቤትም ሄዶ የጥፋተኝነት እምነት ቃሉን ሰጥቶ ጥፋተኛ መሆኑ በእምነት ቃሉ ተረጋገጠ። የተጠቂ ህፃናት ወላጆች የልጆቻቸውን ጉዳት ባይጠግንላቸውም፣ እንባቸውን ይደባብስላቸው ዘንድ ፍርዱን ሲጠባበቁ፥ ዳኞች “ለአባይ ስለምንሄድ ለ1 ወር ያህል አንኖርም። እስከዚያ ታስሮ ከሚቆይ የ15 ሺህ ብር ዋስ አቅርቦ ይፈታ።” ብለው ቀጥረው ተለያዩ አሉ። (እንዳሉት) :-/

ከተጠቂ ህፃናት ወላጆች መሀል አንዷ ጤና የላትም። (የሰማናትን እንጂ የሌሎቹንም ሁኔታ አናውቅም።) ምክንያቷና አገባቧ ባይታወቅም ራሷን በመጠጥ ሱስ ጠምዳ ይዛለች። ለጉድ ትጠጣለች። ሆኖም ልጇ ነውና የእናት አንጀቷ እሺ አይላትም። ዘለለት ባሰበችው ቁጥር ታለቅሳለች። ጎንጨት ስትል፥ የጠጣችው እንባ ይመስል ማልቀስ ትጀምራለች። ስካሩም ተደርቦባት ነው መሰል፥ ሲመሽ ጠብቃ ትወጣና ለቅሶዋን ለመንደሩም ታጋራለች።

ወዳጆቿ ገመናዋን፣ ሰክራ መጮኋን ለመሸፈን ሊያስገቧት ያግባቧታል። ይቆጧታል።

በሌላው ዘንድ ደግሞ፥ “ጀመራት” ይባልላታል።

ልጇ የፊንጢጣ መቁሰል ስለገጠመው እየተሰቃየ ነው። ሀኪም ቤት ቶሎ እንድትወስደው ተነግሯታል። ገንዘብ የላትም። ተስፋ ያደረገችው፥ የህጉን የበላይነት ነበር። (ይህም ሆኖ፥ ሌሎች ጨዋ ጎረምሶች ፍራንክ እያሰባሰቡላት ነው።) …ኋላ ግን ልጇ ብቻ ሳይሆን ህግም እንደሚደፈር ታዘበች። የልጇ አጥቂ መፈታቱን ስትሰማ ቀበሌ ደጃፍ ላይ ሄዳ፥

“ኡኡ… ” ብላ ጮኸች። አሉ።

“ዝም በይ! በጎን በሽማግሌ ተስማምተሽ አስፈትተሽ” አሏት፥ እዚያው ደጃፍ ላይ ስትጮህ የሰሟት።

ይበልጥ አዘነች። አምርራ አለቀሰች። እንባዋን እያርከፈከፈች ቤቷ ስትደርስ የአጥቂ ዘመድ ነን፣ ባዮች፤ “አዛኝ ቅቤ አንጓች”ኦች…

“በሽማግሌ ጨርሱ። ልጅሽ ቢድን ይሻልሻል። እንጂ ምን ህግ አለ?” ይሏት ጀመር።

ስትሰማው፥ ልጇን እርም የበላች ያህል ዘገነናት። ግን ልጇ መዳን አለበት።

የእርሷ ወዳጆች ደግሞ፥ ሱሱም ስላለባት ‘ገንዘብ ያታልላት ይሆን ወይ?’ ብለው ተጨንቀዋል።

ምን ትወስን ይሆን?

😦 😦

የህግ ባለሞያዎች… በረባውም ባልረባውም ነገር የተጠረጠሩ ሰዎች፣ ታርጋ እየተለጠፈላቸው በእስር በሚማቅቁበት ሀገር፥ ጥፋተኝነቱን ያመነን ሰው በ15 ሺህ ብር ዋስ መፍታት ይሆናል? አላመነም ቢባል ኖሮ እንኳን ምርመራው ፈር ሳይዝ ዋስ ይባላል ወይ?

የሆነው ሆኖ ግን፥ ምናለ እዚህ ላይ የታየው ቅልጥፍና ሌሎች የፍ/ቤት ሂደቶች ላይም ቢታይ? :-/

P.S.
ነገሩን ማጣራት የምትፈልጉ የምርመራ ጋዜጠኞች (investigative journalists) ወይም ሌሎች የሚመለከታችሁ ሰዎች ካላችሁ፥ በውስጥ መስመር ልታወሩኝ ትችላላችሁ።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s