ከሰበታ አካባቢ እየመጣሁ፥… ታክሲ ውስጥ ነበርኩ። የተለያዩ ዓይነት ሰዎች ይጫናሉ… ትንሽ ሄዶ የሚወርዱት ይወርዳሉ… ደግሞ ሌሎች ይጫናሉ። ሰዓቱ እየመሸ በመሄዱ ምክንያት ብበሰጫጭም በመጫን ማውረዱ መሀል የማየው ነገር ሁሉ…የበዓል ትርምሱ ተጨምሮበት…አልደበረኝም ነበር።
እኔ ከተቀመጥኩበት ወንበር ፊትለፊት… እግር ስር እቃ ያለበት ቀይ ፌስታል አለ። ወንበሩ ላይ የተቀመጡት ሰዎች ሲወርዱ፥ ረስተውት እንደሆነ ብዬ ልጠይቃቸው ሞክሬ ነበር… ዞር ብለው አይተውኝ …ባላየ… ተገላምጠው ወረዱ። (ወጣት ሴቶች ስለነበሩ ለከፋም መስሏቸው ይሆናል።) እኔም ታዝቤ ችላ አልኳቸው።
ወዲያው ከኋላ የነበረች ልጅ መጥታ አጠገቤ ቁጭ አለች። …ቆንጅዬ ነች። የጠይም ቆንጆ። ትንሽ ኑሮ ያጎሳቆላት ዓይነት ነች። ጎልመስ ያለች። ማድያት አፍንጫዋን ይዞ ሊሰመርባት የሚጣጣር ዓይነት ይመስላል።…. [ግን ጭል ጭል የሚለው የታክሲው መብራት ከቆዳዋ ጠይምነት ጋር ተዳምሮ አጨናብሮኝ ስለነበር የራሴ ግምት ነው።]…. ቀሚስ ለብሳ ጥቁር ሻርፕ ነገር አንገቷ ላይ ጣል አርጋለች። የሆነ የቤት እመቤት ለዛ ያላት ዓይነት ናት።
እንደመጣች…
“እረስተውት ወርደው ነው?” አለችኝ፥ ፌስታሉን በዓይኗና በአገጯ እያሳየችኝ።
“እኔ እንጃ! እንደዚያ መስሎኝ ብጠራቸው እኮ ገልምጠውኝ ወረዱ።” — መለስኩላት።
ጥርሷን ነክሳ…. “ዝም በላቸው! ጥጋበኞች… የተረፈው ሲጥል የቸገረው ይወስዳላ።” …
“ጥለውት ነው ብለሽ? ወይ አላወቁት እንደው እንጂ….” — ዝም ከማለት ብዬ ነበር….
ወዲያው ነቃ ብላ አማከረችኝ። እያዋራችኝ ኧፈፍ አድርጋ ፌስታሉን ከአፉ ይዛ አሳየችኝ። (በግምት ከ10 ኪሎ በላይ ይሆናል።) ….”ይዘነው እንውረድ።“ አለችኝ። … ሳቅ አለች።
ሳቅ ብዬ ”ትወስጂው?…ግን እኔ ምን ያደርግልኛል?“ አልኳት።
ዝም ብላ ቆየችና… “ግን ብወስደውስ ምን ይመጣል? የልጆች እናት ነኝ።” ብላ ጠየቀችኝ። (በጎን ዓይን ዓይኔን እያየች)
“አይደብርም? …ድንገት የረዳቱ ቢሆንስ?” – ጠየቅኋት።
“የርሱማ ሊሆን አይችልም። ዶሮ አይሰራም። ደግሞ ያሁን ጊዜ ልጅ ለእናቴ ይዤ ልግባ ሲል አይደል?የእኔም ልጆች አምጪ እንጂ፥ እንቺ አይሉም….ለነገሩ ልጆች ናቸው ገና”…
“ግን ማን ያውቃል? ባይሆኑስ…. ልጅ ሁሉ እኮ አንድ አይደለም።“
“እርሱስ ልክ ነህ! ግን ይዤው ልሂድ…” (ልቧ ዞሮ እሱው ላይ ነበር። ደንግጣበታለች።)
”ኧረ እኔ ግን የለሁበትም! ደግሞ ምን ይሰራልሻል ያንቺ ያልሆነ ነገር? ቆንጅዬ ወጣት ነሽ እኮ….” (ከዝምታ ብዬ ፈገግ ብዬ ስቀባጥር….)
“ሌባስ አልነበርኩም።….ግን ምን ላርግ?“ (ክፍት አላት!)
“ኧረ ባክሽ ይቅር! ደግሞ የረዳቱ ከሆነ፥ ሌባ ሌባ ብሎ እንዳያዋርድሽ።” ….
“ባክህ! ሆድ አዋርዶኝ የለ?! ይበለኛ። እመልስለታለሁ።“…. “ወይኔ ግን ያስፈራል እኮ። ሰው ግን እንዴት ነው የሚሰርቀው? የሰው ዓይን እንዴት ያስፈራል?“
እንደምትለው ከሆነ፥ ጀማሪነቷ አንጀቴን በላው። ግራ ግብት አለኝ። ከዚያም ሳላማክራት….
“ረዳት…. እዚህ ጋር እቃ አስቀምጠሃል እንዴ?” አልኩት….
“በቀይ ፔስታል ሽንኩርት አለ…” አለኝ።
ኩም አለች። የሆነ ባሏ ጥሏት የሄደች ይመስል ድርቅ ብላ ቀረች። ማልቀስ ቀጠለች። ሲቃ የሌለው ለቅሶ። ዝም ብሎ የእንባ ጉንጭ ላይ መንከባለል። የ’እዩልኝ ስሙልኝ’ ያልሆነ… ይበልጥ አንጀቴን በላችው!
“አታልቅሺ! ምነው? ድሮም እኮ ያንቺ አይደለም። ይቅርታ… እኔ እኮ ይዘሽ ስትወርጂ እንዳያዋርድሽ ብዬ ነው።” ቀበጣጠርኩ….
አልሰማችኝም! አልተቀየመችኝም!
ዘከዘከችልኝ….
“ኧረ እንኳን ጠየቅከው። እኔም ካላመሌ ግራ ቢገባኝ ነው። ቅድም የወጣሁት ሽንኩርት ልገዛ ነበር። ከሰፈር ይረክሳል ብዬ ላይ ሄድኩ። ግን የታክሲ ከስሬ ተመለስኩ። ሴቶቹ የሉም ጉሊት። ያሉት ደግሞ ብላሽ ሽንኩርት ነው የያዙት። ደቃቅ ነው። … ደግሞ እኮ ባለቤቴ ዶሮ ይዞ ከመጣ ብዬ ነው።
….ሾፌር ነው። ሳምንት ሆነው…ለስራ ወጥቷል። ምናልባት ርካሽ ካገኘ ዶሮ ካመጣ ብዬ ነው እንጂ እርግጠኛም አይደለሁም። ግን ሽንኩርቱ ቢገኝ ቁሌቱን እንበላ ነበር።….. እነ ፅጌ 4ዶሮ ገዝተዋል። እነ ጋሽ ተሰማ ወላ በግ አላቸው። ልጆቼ ይቀናሉ።…. (ስለማላውቃቸው ጎረቤቶቿ በስም ነገረችኝ።)
(ከፍ ባለ ብሶት አዘል ድምጽ)… አዪዪ…. ግን ምነው በዓል ባልኖረ? መንግስት ግን ለምን በዓል አታክብሩ ብሎ አያውጅም? ለሌላ ለስንት ነገር ሲሆን መች ይተኛል? ፍራንክ ስላላቸው እየገዙ ያሸብሩናል። ይሄ አያስቀጣም? እነ ፅጌ አሸባሪ አይደሉም?….
አንጀቴን በላችው፥ አንዳንድ ነገሯ ግን የግድም ፈገግ ያስብል ነበርና ፈገግ ስል… “አያስቅም!” እያለች ብሶቷን ሁሉ ዝርግፍ አደረገችልኝ። ሰዉ እየዞረ ያየናል።…. ብር ካልሰጠሁሽ ብዬ ተግደረደርኩኝ። “አሻፈረኝ!” አለች።
”ምነው… በቃ እኔ ፍራንክ ልስጥሽና ጨምረሽ ከሰፈር ትገዢያለሽ ሽንኩርቱን።“ አልኳት። እምቢ አለችኝ። — ብላት ብሰራት፤ ወይ ፍንክች?!……. “ታዲያ ለምን ቅድም ያንቺ ያልሆነን እቃ ተመኘሽ?” ….ስላት፤
“ቅድምማ ደንግጬ ነው። ሻጮቹን ሳጣቸው፥ እግዜርን አማርሬው ታክሲ ውስጥ ስለገባሁ ፀሎቴን ሰማኝ ብዬ ነበር። ከሰማይም መስሎኝ ነበር። ደግሞ በኔ ቤት ሚዛን ማስተካከሌም ነበር። እነሱ ገዝተው ሲያሸብሩኝ… እኔ ደግሞ የወደቀ አንስቼ እኩል አሸባሪ ለመሆን ነበር።…”
አስደነገጠችኝ። … ይበልጥ አንጀቴን በላችው። “ብር ልስጥሽ” ጭቅጭቁም ጉንጭ አልፋ ሆነብኝ። እምቢ አለች። ለነገሩ የማትለምነውን የማበላሽ እኔስ ማነኝ?…ብዬ ትቼው ሌላ ሌላውን ስናወራ ካራ ቆሬ ደርሳ “ወራጅ አለ!“ ብላ ወረደች።
…እየተመናቀረች…. ቻዎም ሳትለኝ!