እንድናሳያችሁ…

“በሀገራችን ሰርቶ የመለወጥ ዕድል እየሰፋ በመሆኑና በቀጣይነት በህዝባችን ርብርብ ይበልጥ እየሰፋ የሚሄድ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ምንም አይነት ጥበቃ ሊያገኙ በማይችሉበት አቅጣጫ በመሄድ አደጋ ላይ ከሚጥላቸው ህገወጥ ስደት እንዲታቀቡ የሃይማኖት ተቋማትና ቤተሰቦች በዚሁ ላይ ጠንክረው እንዲሰሩ ያሳስባል።” — የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት
 
“መንግስት ባመቻቸው የልማት ስራዎች ላይ በመሳተፍ።” — ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ
 
“በሀገር ውስጥ እየኖሩ ኑሮን ማሻሻልና መለወጥ ይቻላል።” — ኢዴፓ
 
“መንግስት ሙሉ ወጪ ሸፍኖ ዜጐቹን ለመመለስ ዝግጁ ነው።” — የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኃኖም
———————————
ሌላም ሌላም ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው መልእክቶች ከተለያዩ ተቋማት ተሰምተዋል። እኔም ቢሆን፣ ቢርብም ቢጠማም በሀገር ያምራል ሁሉ ነገር ብያለሁ። ሀቅም ነው።
 
ከስሜት መለስ ብለን እውነታውን ስናጤነው ግን….
 
ሀበሻ ከፍትፍት ፊት ነው የሚያየው። ማንም እንደ ጤዛ መድረቅን አይናፍቅም። እንደቅጠል መርገፍን አልሞ ከቤቱ አይወጣም። ተቀራርቦ የመኖሩን ያህል፥ ኢትዮጵያዊ አይደለም ከሀገር ውጭ፣ የኖረበትን ቀዬ ትቶ ሰፈር ሲቀይር እንኳን የሕይወቱን ትልቁን ውሳኔ ወስኖ፥ በኀዘንና በለቅሶ ነው።
 
አንድ ነገር ተፈጠረ ሲባል “መንግስት ሙሉ ወጪ ሸፍኖ ዜጐቹን ለመመለስ ዝግጁ ነው።” ከማለት ይልቅ፥ ቀድሞ ሰው ከሀገሩ እንዳይወጣ፣ ቤቱ እንዲመቸው መንግስት ሙሉ ቅንነት ያድርግ። ችግሮቻችንን ይስማ። ችግሮቹ ሲነገሩትም ይስማ። በፍቅርና በስስት እሰሩን። መለወጥ በገንዘብ ብቻ አይደለም። ምቾት ስለቁስ ብቻ አይደለም። …ስለአእምሮ ሰላም፣ ስለኅሊና እርጋታና ስለነፃነትም ጭምር እንጂ።
 
ሌላ ሌላውን ተዉትና በትንሽ በትልቁ አታሳቁን። ሁሉም ፈርቶ ነው ያለው። መጡብኝ አልመጡብኝ እያለ በሰቀቀን ነው ያለው። ቤቱ ውስጥ ጥበቃ እንደሚያገኝ አይሰማውም። ኑሮው እንደ እንግዳ ስደተኛ ነው። መችና በምን እንደሚሻገራት የማያውቃትን ቀዩዋን መስመር ፍራቻ ዘለለት እየራደ ነው ያለው። ስራና እድል በችሎታ ምዘና እንደማይሰጠው ጠንቅቆ ያውቃልና ከራሱ ጋር እየተሟገተ ነው ያለው። የጎደለበትን “አሜን” ብሎ እሮሮውን ማሰማት ቢፈልግ አፀፋው ምን እንደሚሆን ያውቃልና እንደታፈነ ነው ያለው። ዜጎቹ በሰው ሀገር በግፍ ሲረገጡበት አዝኖ ተቃውሞውን ሊያሰማ ቢወጣ፥ ከዚህ ቀደም የገጠመውንም አይዘነጋምና፥ ምን እንደሚከተለው ገምቶ በየመኝታ ቤቱ ነው እያለቀሰ ያለው።
 
“ተነፈሳችሁ” ተብለው፣ የረባ ክስ እንኳን ሳይጠናቀርባቸው እስር ቤት የተጣሉት ወዳጆቼ – ልክ የትናንት 3 ዓመት፥ አረብ ሀገር ውስጥ በግፍ ሕይወቷ ለተቀማው ዓለም ደቻሳ፥ የገቢ ማሰባሰቢያና ቤተሰቧን የማፅናናት ስራ በጋራ ከሰራን በኋላ፥ የጋራ ስሜታቸውን ለመወጣትና ተቆርቋሪነታቸውን ለማሳየት በጋራ የተሰባሰቡት – እንኳን የፊታችን ቅዳሜ፥ እንደቀልድ 1 ዓመታቸው ይሆናል።
 
በእውቀትም፣ በድፍረትም፣ በንቃትም፣ በያገባኛል ባይነትም የተሻለ የአስተሳሰብ ደረጃ ላይ ያሉ፣ ህብረተሰብን ለማገዝ ደፋ ቀና የሚሉ ወገኖች ነበሩ። እኩዮቻቸው በዐይኖቻቸው ጭን እያገላበጡ ሲያማርጡ፣ እነርሱ ግን የሀሳብ ጥልቀት ላይ ነበር ያተኮሩት። ብዙ ከሀገር መውጣት የሚችሉበት መንገድ እያለ፥ ሀገር ውስጥ መቆየትን ነበር የመረጡት። ነገር ግን ወጣትነታቸው፣ ጥረታቸው፣ ጉጉታቸው በ“ፀረ ሽብር ህግ” ሽፋን ተቀማ።
 
ራሳችሁን ፈትሻችሁ ያለውን ውጥረት አርግቡልንና ከሀገር ስላለመሄድ፥ ባለመሄድ ስንመሰክር እዩን።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s