ምን ምን አለህ ያኔ?

ከባህር ዳርቻው በግፍ ወደ ፀና፣ የጭካኔ ማማ፥ video-undefined-27BEC20000000578-440_636x358
እንደ በግ ሲነዱህ ወደ እረፍትህ መንደር፣ በሞቱ ጎዳና፥
ወደ ክብርህ መንበር፥ ወደ ጽድቅ ከተማ፥
ከወንድሞችህ ጋር፥ በመከንዳት ርቀት፣ በረድፍ ስታቀና፣

ምን ምን አለህ ሆድህ… ምን ተሰማህ ከቶ?
ምን ምን አሳሰበህ፣ ልብህን አመሰው ምን ከፊትህ መጥቶ?
ምን ከምን ጋረደህ? ምን ወዴት ሰደደህ ፊትህ ተደቅኖ?
ሰቅዞ አቆየህ የቱ ኬቱ ጎልቶ? የትኛው ነገርህ ተለይቶ ገንኖ?
የትኛው ትውስታህ በምን ተመዝኖ፣ የቱ ልኬት ሆኖ?
እንደምን ከበደህ? እንደምን ቀለለህ?
እንዴት አበረታህ? እንደምን አራደህ?

በልቶ ያልጠረቃ፣ …ልትፈታው በተስፋ፣ ቀን ትጠብቅለት፥
ጠባቃ አንጀትህ እንዴት ተላወሰ?
የስደትን ጽዋ ቆርጠህ ተጎንጭተህ፣ ቤትህን በትነህ የተነሳህለት፥
ቁጥርጥር ጉጉትህ እንደምን ኮሰሰ?

ከቤት ተገፍትረህ፣ እንኳን ከመሬቱ፥ ሰላም አጥተህ ካልጋ፥
ከጎረቤት ጥጋት፣ ሰው ሀገር ሰማይ ስር፣ ጎጆ ልትዘረጋ፣ ኩርማኗን ፍለጋ፥
ሳይቀራረቡ፥ ጉጉትህ ከጠርዙ፣ ሀሳብህ ከሕልምህ ጋ
እንኳንስ አጥንቱ፥ ውስጥ ውስጡን ሲወጋህ በርትቶብህ ስጋ፣
ስትሄድ ስትሄድ መሽቶ፣ እስከዘላለሙ ስትሄድ ሳይነጋ…

ምን ተሰማህ ውዴ? ክርቱት ሰውነትህ ምን አለህ ዓለሜ?
እንደምን ዋለለ ካንድ የተቃዳነው፣ ውስጥህ ያለው ደሜ?
ምን ያል ከል ለበሰ፣ ባንድ የተቃባነው፥ ቀለምህ ቀለሜ?

ምን ከምን ጋረደህ? ምን ወዴት ሰደደህ ፊትህ ተደቅኖ?
ሰቅዞ አቆየህ፣ የቱ ኬቱ ጎልቶ? የትኛው ነገርህ ተለይቶ ገንኖ?

ፊትህ ድቅን አሉ?…

ስትወጣ ስትገባ በስስት ትቃኝህ፣ ዐይን ዐይንህን ታይህ ምስኪኒቱ እናትህ?
መድፈኛው ቸግሯት፣ እንዳታስጨንቅህ በቃል ትከልለው፣ የኑሮ ሽንቁርዋ?

ማኖርህ — ጉጉትህ?
¬ ዘለለት ያዝትህ፥ — “አምላክ አትግደላት ቁም ነገር ሳልሰራ፤
እምዬን አደራ”ን ከተራራው ልብህ ሰርክ የሚንቆረቆር፣ ነገን ሚያስናፍቅህ፣
“ቆይ ብቻ” ያስብልህ፣ ያልተፈታው ህልምህ…
ደግሞም ያልታለመው፣ ሌት ተቀን ያስተኛህ፣ ለቀመር ስምረቱ ምትሻለት አልጋ፣
ፀሐይ ያስጠብቅህ፣ ማለዳ ያሰኝህ፣ ልትፈታው ሲነጋ፣
¬ ከላይ ታች ስትፈጋ፥ በላብህ ጠብታ፣ በመኖርህ ዋጋ፣

መኖርህ — ተስፋዋ?
¬ ዘለለት ያኖራት፣ “አንሙት” ያስብላት፣
“ውለህ ግባ ልጄ!…. ምን አጣሁ? ያኑርህ!”ን ዞ’ትር ያስመርቃት፣

ውል አለህ ዓለሜ?

አንተን ስታቀና መቅናት የተረሳው ጎባጣው ወገቧ፣
አንድ ሁና ያበዛት፣ ገመናህን ከትቶ ከሰው ከፍ ያረገህ ልበ-ሰፊ ልቧ፣
ስታመሽ ይጨንቃት፣ እንቅፋት ሲመታህ ቀድሞ ሹክ የሚላት፣ እረፍት አልባ ቀልቧ፣
በ“ያልፋል” ታቀናው፣ በህልሟ ትደግፈው ደሳሳ ጎጆዋ?

ዘመኗን በሙሉ ያንተን ስስ ሰውነት ስትዘረጋጋ፣ የረሳችው ፊቷ፣ ሽብሽብ አካላቷ፣
ያንተን የወጣት ገጽ በፍቅር ስትወለውል አይታው የማታውቀው፥ ማድያታም ገጿ፣
ቁመናዋን ተክላ፣ ችላ የኖረችው፣ ዘማማ ማገርዋ… ሰንጣቃ ጉበኗ፣
በፀፀት አለንጋ ራሷን ትገርፍበት ራቁት ሌማቷ፣
ያልጠገበ ሆዷን ‘ምታጋድምበት ቆርፋዳ ቁርበቷ…
እንኳን ሞትክን ሰምታ፣ ሲያምህ ‘ምትደልቀው ደቃቃ ደረቷ፣

ባንተ ከፍ ማለት፣ በለውጥህ ትለካው፣ በርካታህ ትቃኘው ከርታታው ዘመኗ፣
ከጎረቤት ቡና፥ ቁርሱን በሹራቧ ከልላ ይዛልህ፣ ላንተ ታመጣልህ…
“አፈር ስሆን ይህችን” እያለች በስስት ታጎርስህ የነበር፣ ከራሷ አፍ ነጥቃ፣
ወጥተህ እስክትመለስ ‘ሚጨንቃት ‘ሚጠብባት፣ ምትቆይህ ተሳቅቃ፣

ባይንህ ላይ ዋለሉ?

ምን ምን አለህ ሆድህ… ምን ተሰማህ ከቶ?
ምን ምን አሳሰበህ፣ ልብህን አመሰው ምን ከፊትህ መጥቶ?

ወይስ… የቀን ውሎህ? የሰፈር ጓዶችህ፣ አብሯ አደግ ውዶችህ ሳቅና ጨዋታ፣
ባንድ ፉት ያላችሁት የመዋደድ ጽዋ፣ ባንድ የተሻማችሁት የአብሮነት ገበታ፣
የክፉን ቀን ቁር፣ ብርድ፣ ፊት የምትነሱበት የትብብር ኩታ፣
“ስንት አለህ? …ይህ አለኝ!” ብላችሁ አጋጭታችሁ፥
የበላችሁት ምሳ፣ የሞላችሁት ሽንቁር፣ ክፍቱን የተዋችሁት የሕይወት ጎዶሎ፣
“አብሽር ይህ ይሳካ” ትባባሉ የነበር፣ ብድር ለመመለስ ልባችሁ ቸኩሎ፣
በተስፋ መንገድ ላይ በሀሳብ ስትነጉዱ ትንፋሻችሁ ሰልሎ፣
ይታያችሁ የነበር ዓለም ፍንትው ብሎ…

ፊትህ ድቅን አለ?

ደግሞ እላይ ታቹ፥ ማኅበራዊ ኑሮ፣
ቀዬ ማስተባበር፣ መሯሯጡ አብሮ
በስራ ፍለጋ ካንዱ ደጅ አንዱ ደጅ፣ የዘለላችሁበት፣
ካንዱ ቦርድ አንዱ ቦርድ፣ ደጅ የጠናችሁበት፣ ቀበሌ ደጃፍ ላይ የዋላችሁት ውሎ፣
ሰሌዳ ሰሌዳ ዐይናችሁ ተተክሎ፣ ለማግኘት ምትጓጉት እንጀራችሁ በስሎ፣

ከድድ ማስጫው ላይ ስትውሉ፥ ገላችሁ፥ በቀን ፀሐይ ከስሎ፣
ከጋዜጣ ገጾች በስራ ፍለጋ፣ ይውል የነበረው ፊታችሁ ተተክሎ፣
ልባችሁ ፈልጎ የልቡን ማውጣቱን፣ መውቀስ ማማረሩ
ካፍ የመለሳችሁት፣ ቅጣት እንግልቱን ስትፈሩ ስትቸሩ፣

ትውስ አለህ ይሆን?

በልቶ ያልጠረቃ፣ …ልትፈታው በተስፋ፣ ቀን ትጠብቅለት፥
ጠባቃ አንጀትህ እንዴት ተላወሰ?
የስደትን ጽዋ ቆርጠህ ተጎንጭተህ፣ ቤትህን በትነህ የተነሳህለት፥
ቁጥርጥር ጉጉትህ እንደምን ኮሰሰ?

ወንድም እህቶችህ በስስት ታያቸው፣ ስትወጣ ስትገባ፣
ኪስህ ሲነጣብህ፣ ሲሹህ እጅህ ሲያጥር ሆድህ የሚባባ፣
ዓለም ዓለሞችህ…
“ምነው ቤት ዋልክ አያ” ይሉህ የነበሩ፣
የጎረቤት ሰዎች፣ ሰፈሩ መንደሩ…
ያኔ ባይንህ ዞሩ?

ከባህር ዳርቻው በግፍ ወደ ፀና፣ የጭካኔ ማማ፥
እንደ በግ ሲነዱህ ወደ እረፍትህ መንደር፣ በሞቱ ጎዳና፥
ወደ ክብርህ መንበር፥ ወደ ጽድቅ ከተማ፥
ከወንድሞችህ ጋር፥ በመከንዳት ርቀት፣ በረድፍ ስታቀና፣

ምን አልከው? ምን አለህ አራጅ አሳዳጁ?
ካንገትህ ጋር አብሮ ተስፋህን ቀንጥሶ ሊጥል ሲያሰፈስፍ፣
ጠምቶት ሲያቆበቁብ፣ ደምህን ሊያፈሰው ሊያርድህ በደም በእጁ፣

ተማጠንከው ከቶ? ያንን አራሙቻ…

“በማርያም ልጅ” ብለህ አትለምነው ነገር፣ እናትና ልጁን የት አውቋቸው ከቶ፣
“በእናትህ” አትለው፥ የእንግዴ ልጅ ልቡ፥ የሽርት ውኀ ቀልቡ፣ ድሮ ሳይድህ ጠፍቶ፣
ጥንት ፈስሰው ያለቁ፥ ሀሞቱ እንኳን ሳይቀር… ጭንብል ያስጠለቁት፣
“በአላህ” አትለው፥ “በምታምነው ባክህ” አርፎ ይነግድ እንጂ፣ መች አምኖ በስሙ?
ቁርዓን መቼ ቀራ? እስላምን የት አውቆ? ቀድሞ ቃሉን ንቆ፣ ከፍቶባት በዓለሙ፣

ታዲያ እንዴት አረገህ?
ምን ምን አለህ ሆድህ… ምን ተሰማህ ከቶ?
ምን ምን አሳሰበህ፣ ልብህን አመሰው ምን ከፊትህ መጥቶ?

ካራውን ሲያፎጫጭ ስጋህን ሊቀላ፣ የፍርሀት ቡካቱን በድብቅ ሲያሽላላ፣
ፍፃሜህ ሲገባህ፣ ሲባል እንደሰማህ…ጉሮሮህ ደረቀ? ነፍስህ ጠማት ጠላ?
ምን አማረህ ከቶ?
የአሪቲ የጠጅ ሳር ሀገርኛ ጠረን ካፍንጫህ ስር መጥቶ?
ሀገር አሳሰበህ፣ ባህል አኗኗሩን፣ ውብ ውቡን ጎትቶ፣ ከፊትህ ተከስቶ?

“ቀንን ከነጓዙ፥ አስሬ፣ ጠፍሬ፣ ጭኜ እገፋበትን፤
ጭንቀት፣ ብስጭቴን፣ ሁሉን ሰባስቤ፥ ዘላለማዊ ሕይወት እናፍቅበትን፣
ከእምነቴ ስልቻ፣ ከልቤ ከትቼ እቋጥርበትን፤
የእኔነቴን አርማ፥ ክሬን አልበጥስም፣ ማኅተሜን አልፈታ፣
መነሻው መድረሻው፣ የፍጥረት ባለቤት፣ አልፋና ኦሜጋ፣
ልምጣ ወዳንተ ጋ ነፍሴን ተቀበላት፣ የሰራዊት ጌታ፣
በክሬ ተጉዤ፥ ልውጣ ከመንበርህ፣ ከጽድቅህ ተራራ፣
አስበኝ በቤትህ፣ እናቴን ወገኔን፣ ህልሜንም አደራ”
አልከው ይሆን ከቶ?

እኔንማ ባየህ….

አራጅህ ደንፍቶ፣
ባህሩን ሲያቀልም አንገትህን ቀልቶ…
የሰማዕትነት የክብር አክሊልን በግፉ አቀዳጅቶ፣
ሲያነግስህ ንጉስ ፊት፥
ግፉ አገዳደሉ ሰቅጥጦኝ ዘግንኖኝ፣ ባነባም ደም እንባ፣
ሁኔታው ቢነደኝ ነፍሴን ቢያቆስላትም፣ አንጀቴን ቢያባባ፣
ለክብር ሲገፋህ፣ ጽዋህን ሲሞላት…
ቁሱን ግሳንግሱን፣ ዓለም ደስታን ንቆ፣
ዘላለማዊ ቤት፣ የገነትን ደጃፍ ቁልፉን ማግኘት ናፍቆ፣
በረከተ እረፍቱን ለማግኘት ተቻኩሎ፣ ፅናት ፍቅር ታጥቆ፣
እስከሞት ጫፍ ድረስ መቆየትን ታምኖ፣
ተምሬያለሁ ባንተ!

እንግዲህስ ባነባ በለቅስም ለእኔ ነው፣
ለከርታታው ነፍሴ ውሉ ላልተለየው፤
በኑሮ ፍም መሀል ለምንከላወሰው፣
እበስል፣ እከስል ቁርጤ ላልታወቀው።

ለምስኪኑ ለእኔ… ወዮ!

/ዮሐንስ ሞላ/

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s