የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ እያለሁ…. አንዳንዴ ደብተሬን ይቀበልና ይፈትሻል። (እርሱ ስላልተማረ ፍተሻው ሳይፃፍ የተዘለለ ቦታ አለመኖሩና እርማት መኖሩ ላይ ያተኮረ ነው።) የሆነ ቀን በነበረው ፍተሻ ወቅት፥ (የህብረተሰብ ደብተር ይመስለኛል) ምንም የታረመ ነገር አልነበረውም።
“ምንድን ነው ይሄ?” አለ፥
“ምን ሆነ?” አልኩት።
“ምንም የታረመ ነገር የለውም።”
“አዎ”
“እሱንማ እያየሁ ነው። ለምንድን ነው የማታሳርመው?”
“አስተማሪው አያርምማ”
“ታዲያ ምንድን ነው የሚሰራው?” ብሎ በመነጋው ትምህርት ቤት ሄደ።
———-
9ኛ ክፍል እያለሁ ትምህርት አልቆ ተዘግቶ የእረፍት ጊዜያችን ላይ…
“ትምህርት ቤት አንጠራም እንዴ? መቼ ነው… ጉዳይ እንዳልይዝ….”
“ለምን?”
“ሽልማት የለም እንዴ?”
“አይ አባዬ፥ 7ኛ ነው የወጣሁት።”
“ትቀልዳለህ?”
ፈርቼ ስሳቀቅም፣ ለነገ ሳመቻችም….
“እውነቴን ነው። ትምህርቱ እኮ ከእንግዲህ ይከብዳል።”
“ሸቀቡህ!? መቼስ ደሀ ነኝ። ጎን ቢኖረኝ ሄጄ አስመረምርልህ ነበር። ተዋቸው ለመጪው ይሳካል።”
አብራራሁለት።
———-
12ኛ ክፍል ልንፈተን ስንል የድንጋጤ ጥናት ማጥናት ጀመርኩኝ። በፊት ሲሉኝ ሲሰሩኝ አልሰማ ብዬ፥ 11ኛ ላይና ከዚያ በፊት ያለፈኝ ብዙ ውዝፍ ጥናት ነበረብኝ። (ከዚያ ቀደም ለፈተና ያህል ለብለብ ነበር የማጠናው) የሩጫ ነው ሁሉ ነገር። ወዲህ ከወንድሞቼ የወረስኳቸው ብዙ መፅሐፍትና በራሴ የገዛኋቸው በጣት የሚቆጠሩ ማጣቀሻ መፅሐፍት አሉ። ወዲያ፥ የማትሪክ ፈተና ወረቀቶች ‘እየኝ እየኝ’ ይሉኛል። ሰርገኛ እንደመጣባት ሴት እዋከባለሁ። ተኝቼ እየነቃሁ ለማጥናት እሞክራለሁ። ፈተናው ወር ገደማ ሲቀረው፥ አባቴ ጠራኝና…
“ሰማህ?” አለኝ
“ምን?”
“ድካምህን አያለሁ። ካልተሳሳቱ በቀር ታልፋለህ። ከተሳሳቱም ከፍለን እናስመረምራለን። እንግዲህ ይህን ሁሉ ሞክረህ ባታልፍም ምንም አይደለም። ቴሌቪዥን ኮሌጅ ብሎ ያስተዋውቅ የለ? መሬቴን ሸጬም ቢሆን ትማራለህ። በል እንግዲህ ይብቃ እረፍት አድርግ።” አለኝ።
[በቂ እንዳልተዘጋጀሁ ግን ወንድሞቼ ሲናገሩም ስለሚሰማ ነፍሱ ያውቃል።]
————-
“የብርሃን ልክፍት” የታተመች ሰሞን (ከመመረቋ በፊት) አንድ ፍሬ መፅሐፍ ጠረጴዛ ላይ ተቀምጣለች። (ብርቅ የሆነበት የእህቴ ልጅ ሲያነበው፣ ሲያገላብጠው ቆይቶ ሲደክመው አስቀምጦት ነበር።) ገብቶ እንዳረፈ፥ አንስቶ ገላለጠው….
ስሜ ጎላ ብሎ ስለሆነ የተፃፈው እርሱን አንብቦ ለእህቴ ልጅ “በኋላ ታነብልኛለህ“ አለው።
ትንሹ የእህቴ ልጅ፥ ”አባዬ የጆኒ እኮ ነው“ አለው በኩራት።
“አውቄያለሁ። ግሩም ነው”
“እንዴ፥ ታዲያ እንዲህ ነው የምትለው? ምንም አይመስልህም ወይስ ቀድሞ ነግሮሃል፡፡?”
”አልነገረኝም። ምን መፅሐፍ መፃፍ አዲስ ነገር ነው እንዴ? ካልለገማችሁ ከዚህ በላይም ማድረግ ትችላላችሁ።“ አለው….
————-
የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ፥ ሰፈር ውስጥ ቧንቧ ለሌላቸው ሰዎች ቧንቧ እንዲገባ ተብሎ ሰፈሩ ተቆፋፍሮ ነበር።
“አደጋ አይምጣ እንጂ እሳት ቢነሳ መኪና እንዴት ይገባል?….ለወሬ ስለሚፈልጉት ነው የማይደፍኑት እንጂ ወዲያው ቀብረው አይነሱም ነበር? ሰው ገብቶ ይወድቅና የት ወደቀ ሲባል ቀበሌ ውሀ ለሌላቸው ውሀ ሊያስገባ የቆፈረው ጉድጓድ ውስጥ ይባላል።” አለ ሲገባ እየተበሳጨ
————-
ከዓመት በፊት ለምሳ ወደ ቤት መጥቶ፥
“ለአንድ ሰውዬ 200 ብርሰጠሁት” አላት ለእናቴ፥
“የለኝም ስትል አልነበር?”
“ምን ላርግ ባለቤቴ ታማለች ሆስፒታል መውሰጃ አጣሁ። ብሎ ያለቅሳል…. አውቆታለሁ። አበድሩኝና ቤት አመጣለሁ አለኝ”
“ማነው? ታውቀዋለህ?”
“እኔ አላውቀውም። እንደዚያ ሲሆን፥ ባውቀው አልጨምርለት። ባላውቀው አልከለክለው። ያለኝን ሰጠሁት። እንግዲህ የሽማግሌ ገንዘብ ነው ካለ ያምጣው….”
————-
የቀድሞው ጠሚ ያረፉ ጊዜ ለቅሶ በየቀበሌው ሲደረስ፥ መጣና እናቴን
“በስተርጅና ጉድ እንዳያመጡብን እንድረስ” አላት
“እኔ አልደርስም። በፊት የሚያደርጉልኝ የነበረ ነገር ካለ አሁን ይተዉት” አለችው።
እርሱ ተነስቶ ሄደ….
ሲመለስ፥
“ሄድክ?” አለችው፥
“ማንስ ሲሞት እንሄድ የለ? ሄድኩ” አላት
“ምን አሉ?” አለችው
“መዝገብ አለ…. ምን ብዬ ልፃፍ ስትለኝ፥ ‘እመቤት ለምን እንደመጣሁ ታውቂዋለሽ። አታድክሚኝ እንደፈለግሽ አድርጊው።’ አልኳት“ አለ።
————-
“ሞት ምንድን ነው? ቁም ነገር ነው እንዴ? አያጉላላኝ…. እስካለሁ ድረስ ጥሩ ያናግረኝ፣ ልመርቅ እንጂ ለምን ዛሬ ይዞኝ አይሄድም?”
“ተራ ይጠብቃል እንጂ ከሞት የሚቀር አለ? ያቆየውን ለመመረቅ ለመታዘብ ያቆየዋል። ደግሞ የፈለገውን አቀላጥፎ ይዞት ይሄዳል።”
የቅርብ ሰው ሞቶ ድንኳን ከሁለት ቀን በላይ መቆየቱን ካየ “ኧረ ባካችሁ። ድንኳን ካለ ሰው ይቀየሙኛል ብሎ ይመጣል። ተስተናጋጁም ብዙ ነው። ያለችውን ትንሽ የእድር ብርም ሆነ ሰው የእዝን የሰጠውን አትበትኑት። ድንኳኑን አፍርሱ በቃ” ብሎ ይቆጣል።
“ጥሩ ንግግር እንጂ ሁሉም ተትቶ ነው የሚኬደው።” (ሞት የማይፈራው ነገር ይገርመኛል።)
————-
እናቴ ለቅሶ ሄዳ ቤት ካጣት፣ ወይም እሱ ቤት እያለ ለቅሶ እሄዳለሁ ብላ ከተነሳች “ምንድን ነው እንደዚህ መሆን? በቁም እያሉ ነው መጠያየቅ፥ ሲሞቱ ነጠላ መጎተት ምን ይሰራል?”
————-
የዛሬ ዓመት ገደማ….
ኦሮሚኛ ቋንቋ የምትናገር አዲስ ልጅ ከገጠር መጥታለች። እኔ በጣም ሚጢጢውን የኦሮሚኛ ቋንቋ የመማር ጅምሬን ለማብዛትም እንዲረዳኝ በመጓጓት፣ የማውቀውን ያህል እንተባተብና ሲቸግረኝ ራሷን መግለፅ የምፈልገውን ነገር በምልክት ገልጬ “ማልጀቹዳ?” እላታለሁ። ትነግረኝና ራሱን መልሼ እጠይቃታለሁ።
አባቴ ካለ ደግሞ “እንዲህ ማለት ምን ማለት ነው?” እለዋለሁ፥ ካልሰለቸው ይነግረኝና እጠይቃታለሁ። እሱ አቀላጥፎ ነው የሚናገረው። ትናንት ሲያንበለብለው ሰምቼ ገረመኝና…
“ፓ! ጎበዝ ነህ ግን፤ እንዴት አትረሳውም?” አልኩት።
“እንዴት እረሳዋለሁ? ጅማ እያለሁ እኮ አማርኛ አይቀናኝም ነበር። ኦሮሞ ነበርኩ።” አለ።
“አንተ ደግሞ ዘር ይቀያየራል እንዴ? ምን ማለት ነው ኦሮሞ ነበርኩ ማለት?”
“ቋንቋ ይለያይ እንጂ ሁሉም አንድ ነው። ማንም ስለኖረና ንግግር ስለቻለ እንደዚህ ነኝ ይላል፥ ሌላ ምን አውቆ ነው?”
————————–
የእኔ አባት ❤ የእኔ መምህር፥ በክፉም በደጉም ካንተ የተማርኩት ብዙ ነው። በዚህ እድሜህ እንኳን ያለህን ንቃትና የአስተሳሰብ ልክ ሳይ፥ አወቅን ተራቀቅን የሚሉት ያሳዝኑኛል። አንድም ቀን “አያገባኝም” ስትል አልሰማሁህም…. አንድም ቀን ቂም ስትቋጥርና ስትቀየም አላየሁህም…. የተቸገረ አይተህ ስትነፍግ አላየሁም…. አንድም ቀን ምን ይሉኛል ብለህ ያሰብከውን ከመናገር ወደኋላ ስትል አላየሁህም… ከሰው ጀርባ ስታወራ አልሰማሁህም….. አንድም ቀን ሞት ስትፈራ አላየሁህም…. – አባዬ ይህን አስቀዳኝ!!
እድሜና ጤና ይስጥህ ❤ ❤
Happy fathers day to all fathers!