“የዚህ ሰፈር ልጆች እቴ፥ ንቅሳት ይሰርቃሉ” ሲባል የሌብነታቸውን ዓይነት ስላችሁ ተገርማቹ ታውቃላችሁ?
“ኧረ እነሱስ፥ ሀሳብ ሳይቀር ይቀማሉ“ ሲባል ተደንቃችሁ “ሆ” ብላችኋል?
“ምራቅሽን ሰብስቢ፥ ኋላ ተመንትፈሽ እሪሪ ስትይ እንዳንሰማሽ” ተብሎ ሌብነት በግነት ሲወራ ሰምታችሁ ፈገግ ብላችሁ ታውቃላችሁ?
እርሱት!
ይኸው፥ ከወደ ኮልፌ ቀራንዮ፣ የምስኪን እናት ቀጤማ ይመነተፋል። እስር የወይራ እንጨቷ ሳይቀር ይነጠቃል። ጎመን፣ ሽንኩርት፣ ድንች፣ ቆስጣ፣ ሰላጣና ሎሚም አይቀሩ። ኧረ ምን እነሱ ብቻ፥ የዳቦ መጋገሪያ ኮባ ቅጠልና ኩበት ሳይቀሩ ይወረሳሉ። – “ህገ ወጥ ነጋዴ” የሚል ታርጋ እየተለጠፈ፥ በጠራራ ጸሐይ፣ ህገ ወጥ ህግ ማስፈፀም ይካሄድባታል።
እድሜዋ ከጠና ወደ ልመና፣ ጉልምስናው ላይ ከሆነች ደግሞ ወደ አረብ አገር ትገፋለች። ሄዳ ከፎቅ ተወርውራ ስትመጣ፥ ተሰብስበው የገፏትን ትትተው፣ ፍላጎቷን ተገንዝቦ የጎተታትን ደላላ ይረግሙላታል። ድንቁርናዋ ያመጣው ጣጣ መሆኑ ይወራላታል። (‘ማንበብና መጻፍ እንኳን ሳይችሉ ከአገር እየወጡ’ እየተባለ) ለልመና እንደው አዲስ አበባ ሆዷ ሰፊ ነው። እንደምንም ብለው አንዴ እሳቱን የሰው ፊት ደፍረው ማየት ይጀምሩ እንጂ፥ ማንንም ታስተናግዳለች።
ዝርዝሩ ላይ ያሉት ሁሉ የእናት እቃዎች ናቸው። የድሀ እናት እቃዎች ናቸው። የልጇን ሆድ ለመሙላት ላይ ታች የምትል፣ አሮጌ ነጠላ ለብሳ የምትዳክር፥ ኮስማና እናት እቃዎች ናቸው። ከዝርዝሩ ጋር አብሮ ምስሏ ይታያል። ሁኔታዋ ይታያል። ልጇ ፊቷ ላይ የተሳለባት እናት፥ ከነልጇ ምስል ትታያለች። (ሲቀሟት እንዴት አለች ይሆን? ባዶ ሆዱን የሚውለው ልጇን አስባ “ልጄን ልጄን” ብላ አለቀሰች? በ“ሽልንጌን ሽልንጌን…” ዓይነት አጯጯኽ… መረገደች? ቤቷን ጠላችው? እጇ ሙሉ የለመደ፥ እንዴት ባዶዋን ትግባ?) የቡና ቁርስ እንኳን ከሆዷ ቆጥባ ለልጇ የምትሸክፍ ምስኪን፥ የእለት ጉርሷ ሲቀማ እንዴት አደረጋት? “እኔ እናትህ እያለሁ” ያለችው ልጇን የተቀማች ለታ ምን ነገር ተካችለት?
ከሰንዳፋ ይሁን ከጫንጮ፥ ሳጠራ ቅርጫት ሸክፋ ሌሊት ተጉዛ አይብ የገዛች እናት፥ ልጆቿ ዳቦ ይዛ ትመጣለች ብለው ሲጠብቋት ባዶ እጇን ይቀበሏታል። መምጣቷን ደጅ ላይ ሲጠብቅ ውሎ፥ ከሩቅ ሲያያት “እማዬ መጣች” ብሎ፥ ከጉንጯ በፊት፥ እንደማገዝም፥ ቅርጫቷን የሚሳለመው ልጇ ቅርጫቷም ይናፍቀዋል። ። (ምናልባት ጸሐይ ጸሐይ ማለቷን እያማገቻቸው፣ ላቧን እያጠጣቻቸው።) ከፊት ለፊቷ ያለውም መስከረም ነው። የምዝገባው፣ የደብተሩ፣ የዩኒፎርሙ ጣጣ ያሳስባታል። አሁን እንደው እነሱ፥ “ቀጤማ በእንጀራ ለዋጮች”፣ “አይብ በዳቦ ለዋጮች” እንጂ “ነጋዴ” ሆነው ነው? ደግሞ እኮ ካዩት ከበሉት ጋር ቫት ከፋይም ናቸው።
ምድር ላይ፥ የሰው ልጅ ሊደርስበት ከሚችሉ ጉዳቶች ከፍተኛው ለወለዱት መሆን አለመቻልና የአብራክን ክፋይ ቁስቁልና ማየት ነው። በተለይ ለእናት። በተለይ ለደሀ እናት። – ሀብቷም፣ ተስፋዋም፣ እስትንፋሷም፣ ዓለሟም ያው ልጆቿ ናቸውና። ወላጅ ሆኜ ስሜቱን ባላረጋግጥም እንደዚህ ይሰማኛል። በዚህም ምክንያት የእናት ጉስቁልና ተለይቶ ያመኛል።
ደሀ ላይ ቆመው ከፍ ይሉና በሀብት ይታዩልኛል።
ይፈጥፈጡና!
ዛፍ ነቅለው የተከሉትን የመስታወት ህንጻ ቆጥረው አድገናል ይሉኛል።
ላያቸው ላይ አረም ይደግና!
ጥቃቅንነትና አነስተኛነት ላይ መደራጀቱ እንኳን ቅንጦት የሆነባትን “የደሀ ደሀ” እናት እየገበሩ “በጥቃቅንና አነስተኛ ያስመዘገብነው…” ብለው ይደሰኩሩልኛል።
ጥቃቅንና አነስተኛ ተባይ ይብላቸውና!
በነፍስ ወከፍ ገቢያችን ይህን ያህል ደርሷል ይላሉ።
አንዳች በሽታ ይወክፋቸውና!
(አውቃለሁ፥ እርግማን የአቅመ ቢስ ነው። ምነው ባለፈው ደላላ በቀጥታ ስርጭት ሲረገም አልነበር?)
“ህገ ወጥ” አንባል
እንባችንን ነጥቀው፥
ሳቃችንን ዘርፈው፣
መታረዛችንን ራባችንን ወስደው፥
አያውጡት ጨረታ፥
ጓሮ ጓሮ እናስስ፣
ቀን ቀን አንጎዳ፥
ውጭ ውጭ ይቅርብን
እናልቅሰው ጓዳ፣
እንሳቀው ማታ።
(እንጉርጉሮስ የማን ሆነና? ያው የአቅመ ቢስ ነው።)
11781814_1181906321825847_7677626806791924924_n

አንድ አብሮ አደጋችን፣ እሱ ቢያጠፋው ኖሮ እናቱ ሳትቀጣው የማትቀርበት ነገር፥ እናቱ ስታጠፋ ተመልክቶ (ለምሳሌ፥ ብርጭቆ ሰብሮ ነበር በሉት። እናቱ ለቅጣት እጇን ባታነሳበት እንኳን “እያየህ አትሄድም? ደንባራ። እቃዎቹን እኮ ፈጀኻቸው።” ልትለው ትችላለች)፥ “እሺ አንቺንስ ማን ይምታሽ? እግዚአብሔር ይምታሽ።” አላት አሉ። …ልጅ ነበርና፥ እናቱን በእግዚአብሔር ለማስቀጣት መፈለጉ ከማሰላሰል ብቃቱ የመጣ ነበርና ተደናቂ ነገር ሆኖ እስካሁን ድረስ ይታወሳል። እኔም በምክንያት አስታውሼ አመጣሁት።

ከዚህ ጋር ያለውን ጽሁፍ፥ በመስቀል አደባባይ ስትተላለፉ አይታችሁት ታውቁ ይሆናል። (ከኤግዚቢሽን ማዕከል ፊትለፊት አስፓልቱን ተሻግሮ ካለ ህንጻ ላይ ከተሰቀሉ መፈክሮች መካከል አንዱ ነው።) ሳየው ኖሬ፣ ዛሬ ድንገት አስፓልት ስሻገር ተገጣጥመን፣ በእጅ ስልኬ ፎቶ አነስቼው ነው ያመጣሁት። እንደሚነበበው፥ ጽሁፉ “የሃይማኖታችን ዋስትና ህገ መንግስታችን ነው። ህገ – መንግስታችን ይከበር!!” ነው የሚለው። ይህን ጽሁፍ ባየሁ ቁጥር የዞን 9 ወዳጆቼ ትዝ ይሉኛል።

እንደሚታወሰው፥ ከበይነ መረብ ዘመቻዎቻቸው መካከል “ህገ መንግስቱ” ይከበር የሚለው ይገኝበታል። (ከዚህ ዘመቻ በቀር፥ በሌሎቹ ሁሉ ተሳትፌ ነበር። መሳተፍ ያልመረጥኩት ለራሴ በቂ በሆነ ምክንያት ነው።) በምርመራ ወቅትም፥ ሲዘልፏቸው “ህገ መንግስቱ ተከብሮ ሳለ ምን ስለሆናችሁ ነው ይከበር የምትሉት?” የሚል ጥያቄ ተሰንዝሮባቸው ነበር። (እንደሰማሁት ቃል በቃል አልጻፍኩትም።)

ታዲያ ከዚያ ጊዜ አንስቶ፥ ይህን የለጠፈው/ያስለጠፈው ሰው ምን ቆርጦት ነው “ህገ መንግስታችን ይከበር” የሚለው?

ማንስ ነው ህገ መንግስቱን የሚያከብር የሚያስከብረው?

ህገ መንግስቱ በደንብ ይታወቅና ይከበር! በደንብ መታወቁ፥ አከባበሩ ላይ ባለድርሻዎች የሚኖራቸውን ሚና ግልጽ ያረጋልና፥ መጀመሪያ በደንብ ይታወቅ። ከዚያ ይከበር! (አሃ! ይከበር ስንል ግን፥ ቀን ተቆርጦለት የህገ መንግስት ቀን የሚባለውን አይደለም።) ህዳር 29 ብቻ ሳይሆን፥ ከህዳር 30 – ህዳር 28 ድረስም ህገ መንግስቱ ይከበር!

11692578_797852720335763_2642146807227495581_n

“የደከመበትን አናውቅም።”

ከወዳጄ ጋር፥ 1815 ብር ዋጋ የተተመነለት የአርከበ መፅሐፍ ዋጋው ገርሞኝ ስናወራ የሰጠኝ መልስ ነው። መልሱ አብሽቆኝ እርር ያለ ንትርክ ውስጥ ገብተን ነበር። ስለ ዋጋ ትመና ሊያስረዳኝ ሞከረ። እኔም መልሼ የማውቀውን ጠቅሼ ተከራከርኩት። ካሰብነውም፣ ሊሆን ከሚችለውም በላይ ንትርካችን ቀጠለ። ወዳጄ ገራገር ሆኖ አይደለም። ሆኖም ይህን ሲል፥ በቅንነትና በነፃነት ነገሩን ማየት ፈልጎ እንደሆነ (100 %) እርግጠኛ ነኝ። ከራስ በላይ ማመን ቢኖር፥ እንዲህ ባለ ነገር ከራሴ በላይ አምነዋለሁና እሱ ማለቱን ትቼ፥ ነገሩ ላይ ላተኩር። በነፃነትና በተናጥል ለማየት መሞከሩንም አከብራለሁ። ቢሆን መልካም ነው ብዬ የምመኘውም ነገር ነው። ግን እንዴት ይሆናል?
 
በእርግጥ፥ ሰው በመፅሐፉ ዋጋ ተናዶ፣ በጅምላ “እነሱ እኮ አምባገነንነታቸው ልክ የለውም።” ቢል፣ ከመፅሐፍ ውድነት ጋር አምባገነንነት ምንም ባይገናኝም፣ ሰው እንዲያ ይል ዘንድ ግን ምክንያት አለው። መፅሐፉ ውድ ነው ሲባል፥ የአሰብን ወደብ ጠቅሶ ውድነቱ ላይ ቢከራከር፣ አልያም የታሰሩ ሰዎችን አጣቅሶ ግፍ ነው ቢል፥ ወደቡም እስር ቤቱም ከመፅሐፉ ውድነት ጋር ባይገናኝም፣ እንዲያ ይል ዘንድ ግን ምክንያት አለው። ቁስል ምክንያት አለው። አነሳሽ ምክንያት አለው። ካለበለዚያ ግን፥ “የደከሙበትን አናውቅም” ካልን፣ ለብዙ ነገር ጥሩ ማስተባበያ ይሆናልና አደጋ አያጣውም። (ስልጣኑን ከአረመኔው ደርግ እጅ ሲፈለቅቁ የደከሙትንስ እንዴት እናውቃለን?)
 
በትክክለኛና ቀጥተኛ ቅዋሜዎች መኖር ብስማማም፥ የሚቃወመው ነገር እውነት ባለበት ሁኔታ፥ አቀዋወሙ ጉዳይ ሆኖ ሊያነታርክ ይገባል አልልም። (ቀላል ምሳሌ፥ አንድ ሰው “የጨረባ ተዝካር” ላይ ጥሪ ተደርጎለት ቢሄድ፥ የአለባበሱ አጨራረብ ይብጠለጠል ዘንድ አግባብ አይሆንም። ከዚያ ቀደም ተዝካሩ መተቸት አለበት። ተዝካሩ መብጠልጠል አለበት።) ስለዚህ መፅሐፍ የማወራው መፅሐፍ ስለሆነ፣ “እንደ መፅሐፍ ነው”። ነገሩ እውቀት ነውና መታተሙ ላይም ቅሬታ የለኝም። መሸጫ ዋጋው ላይ ግን ቅሬታ አለኝ። የፈለገው ዓይነት pricing system ቢጠቀም ኢትዮጵያ ገበያ ላይ መፅሐፍ በዚህ ዋጋ ውድ ነው።
 
(በርግጥ ከዋጋ ውድነት ውስጣዊ ምክንያቶች አንዱ፥ ነገሩን ከሆነው በላይ ተምኖ ማሻሻጥን ማለም፣ ራስን ከፍ አድርጎ ማየት ሊጠቀሱ ይችላሉ። ተነበበ አልተነበበ፥ የዋጋው ውድነት በራሱ የተፃፈውን ነገር ከተፃፈው በላይ በማግነን ሚና ሊጫወት ይችላል። መፅሐፉን ወዶ የሚገዛ ሰውም፥ ለመፅሐፉ ያወጣው ዋጋ እንደባከነበት እንዲሰማው ስለማይፈልግ፥ እጅግ በጣም የተለየ መፅሐፍ እንደገዛ ሊያስብ ይችላል። መፅሐፍ ገዡ ከሻጩ ጋር ዝምድና ሲኖረው ደግሞ፥ የመፅሐፉ እጅግ ልዩነት ሌላ ፈርጅ ይኖረዋል።)
 
እንዳልኩት፥ ስለመፅሐፉ ማወራው እንደመፅሐፍ ነው። (በርግጥ፥ ከፀሐፊው – ከዶ/ር አርከበ – ጋር የግብር ከፋይና የግብር ተከፋይ ዝምድና አለን። ያ ዝምድና ደግሞ የፈጠረብን ቅያሜዎች ብዙ ናቸው። ሆኖም፥ ያንን ከግምት ከትቼ አይደለም ይህን የምለው። ቢሆንም ግን፥ ስለ “ድካም/ጥረት” ነውና የምናወራው፥ ለንፅፅርና ለነገር ማማር፥ ፀሐፊው ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ ማጣቀስ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም።)
 
1) ፀሐፊው ከባለስልጣናቱ ጎራ ስለሆኑ ሲማሩና ሲፅፉ የሚደረግላቸው (ሊደረግላቸው የሚገባ) የተለየ እንክብካቤ ይኖራል። (ለምሳሌ፥ የት/ት ወጪ አያስጨንቃቸውም። የአየር ቲኬት አያሳስባቸውም። ሲፅፉ የቡናና መሰል ማነቃቂያዎች ወጪ አያሳቅቃቸውም። ማጣቀሻ መፅሐፍትና መጣጥፎችም ምንጮች አይደርቁባቸውም። መቼስ ጉዳዩ ለ“እድገትና ልማቱ” የሚያበረክተው ነገር ስለማይጠፋ፥ ወጪው ተሸፍኖላቸው ሊታተምም ይችላል።) ስለዚህ፥ እርሳቸውን በዚህ ለክተን “የደከሙበትን አናውቅም” ብለን 1815 ብር ዋጋ አግባብ ሊሆን የሚችልበት ክፍተት አይኖርም።
 
(አንድ የሙሉ ሰዓት ፀሐፊ ወይም የአደባባይ ምሁርን ወስዳችሁ አስቡት። ሲፅፍ የቡና እንኳን ከየት እንደሚያመጣና ምን ዓይነት ድካሞች ውስጥ እንደሚያልፍ ገምቱ።)
 
2) ዋጋ ትመና ሲካሄድ የሚሸጥበት ቦታም ከግምት ይገባል። በኢትዮጵያ ገበያ የፈለገው ዓይነት ነገር ቢታተም 1815 ብር “ውድ” ለመባልም ሩቅ ነው። (ገበያ ወጥተን ዋጋ የምንደራደረው፣ ቀንስ የምንለው፣ መጨረሻው ብለን የምንሟገተው፥ የሻጩ ዋጋ ከገዡ አቅም ጋራ ሲቀራረብ ነው።) ስለሆነም፥ እንዴትም ቢደከምበት 1815 ብር ለውድነትም ሩቅ ነው።
 
(አንድ በዓለም አንደኛ የሆነ ሙዚቀኛ፣ ሲዲ ሲያሳትም፣ የፈለገውን ያህል ቢደክምበት፣ ለስራው ማማር የከፈለውን ያህል ቢከፍልበት፣ ጨረቃ ላይ ወጥቶ ቢያስቀርፀው፥ የሚሸጠው ከገበያው የሲዲ ሽያጭ ዋጋ ብዙ ሳይርቅ ነው። የሆነ ሰው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ሙዚቃ ቤት ሄዶ የሆነ ዓይነት ሲዲ ሊገዛ ፈልጎ ዋጋ ሲጠይቅ “1000 ብር” ቢባል ሳይሳደብና በአፀፋው ሳይሰደብ/ወይ ሳይደበደብ ይመለሳል? እዚያ አምባጓሮ ለመፍጠር አቅምና ድፍረት ቢያንሱትስ፥ ተገርሞ ከወዳጆቹ ጋር ሲያወራና ሲብሰለሰል መዋሉ ይቀራል? ስንት ጊዜስ፥ “ህግ የሌለበት አገር አረጉት እኮ” ይላል በሆዱ? ዛሬ እንኳን ፌስቡክ ውሎ ይግባ፣ እዚህ መጥቶም ቢሆን ይተነፍሰዋል።)
 
3) ዋጋ መተመን ሌላ፣ አሻሻጥ ደግሞ ሌላ ናቸው። በመደበኛው የስነ ምጣኔ ሳይንስ፥ ዋጋ ትመና ውስጥ ከግምት ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል፥ የፍላጎትና የአቅርቦት ሁኔታ ይጠቀሳሉ። ይህም በሆነበት፥ ሻጭ ዋጋውን ሲተምን የገበያውን ባህርይ ማወቅና ያንን ከግምት መክተት ይኖርበታል። እንዲያ ሲያደርግ ነው ሀቀኛ ነጋዴ (rational seller) የሚባለው። እና ይህ ባለበት ሁኔታ፥ መፅሐፉ የሚሸጥበት ገበያ ከግምት አልገባም። በዚህም አልነው በዚያ፥ ንቀት ታክሎበታል። – ‘የማን ምን ያመጣል’፣ ወይም የ’ማን ሊያነብ’ (አንባቢን የመገመት) ንቀቶች። እንዲህም ከሆነ፥ መድከም የሚፅፉለትን ማኅበረሰብ ሁኔታ መረዳትና ከግምት መክተትም ይጠይቃልና አሁንም ደከሙ ማለት አንችልም።
 
(በእርግጥ ስለአሻሻጡ መላ ላይጠፋ ይችላል። ለመንግስት ቢሮዎች፣ በመንግስት ወጪ በትኖ ለሰራተኞችና አባላት በስጦታ ማደልም ይቻላል። – as simple as this. ይህን የምለው ከመሬት ተነስቼ አይደለም። ከዚህ ቀደም ቀበሌ ውስጥ የሰለጠኑ ሰዎች፣ ካለፈቃዳቸው፥ በጅምላ፥ ከአበላቸው መቶ መቶ ብር ተቆርጦ የአዲስ ልሳን መፅሔት ተረካቢ (subscribers) ተደርገው እንደነበር አጣቅሼ ነው። ስለዚህ፥ 100% “መራጭ”ና ይህ ሁሉ አባል ባለበት ሁኔታ፥ ሽያጩ እዳው ገብስ ነው።)
 
4) የሆነ ጊዜ ተወርዶ የእነ ስጋና ቢራ ዋጋ ሳይቀር ተተምኖልን ያውቃል። (ያው ፖሊሲ ፖሊሲ ነው ብዬ ነው።) “ስግብግብ ነጋዴ” የምትለው ታርጋም የእኛው እድሜ ያላት ናት። እና እንዴት ነው ይሄ የሚታየው? 1815 ብር ለመፅሐፍ፣ በኢትዮጵያ ገበያ? (ነገ አንዱ ብድግ ብሎ ጤፍ 10000 ብር ቢል፥ ነፃ ገበያ ተብሎ ጣልቃ አይገባበትም?)
 
5) ይሁን። ደክመው ሊሆን ይችላል። የደከሙትንም ልክ አላውቅም። …ግን እርግጠኛ ነኝ፣ አንድ የመንግስት ተቃዋሚ አንድ መጣጥፍ ላይ የፈለገውን ሀሳብ ለመፃፍ ከሚደክመው በላይ አይደክሙም። እኔ ካቅሜ፥ ይህችን ቁራጭ ሀሳብ ‘ልፃፋት/ልተዋት’ ብዬ ከደከምኩት በላይ ሊደክሙ አይችሉም። በጭራሽ!
 
ሌላም ሌላም።
 
በነገራችን ላይ፥ መፅሐፉን የምትገዙ ሰዎች ታስነኩኛላችሁ። ወይ ደግሞ እንደራጃ። 😉
 
P.S. ይሄ የተፃፈው አሳታሚው ኦክስፎርድ መሆኑን ሳላውቅ በፊት ነው። አሁንም ቢሆን ግን፥ ኦክስፎርድ ሲያሳትም ካለርሳቸው እውቀት ነው? Just curious.