ባቡር፣ መንገድና የሰው ጠባይ

IMG_5433_zps75glabjg

ተመርቆ የቆየው የባቡር መንገድ ስራ የጀመረ ጊዜ “ከተማችን ዘነጠች” ተባለ። “ዓለሟን አየች” ተባለ። በየልቡ “አሁን ደመቅሽ አዲሳባዬ” ተዘፈነላት። ሰው ደስታውን በተለያየ መንገድ ገለጸ። የትናንት መልካም ታሪኮችን ስለዛሬ መስዋዕት ያቀረቡ አሽቋላጮችም ነበሩ። አንዳንድ የአዲስ አበባ ኗሪዎች እጅጉን ተመጻደቁ። በነዋሪው ግብርና፣ ነገ ላቡን ጠብ አርጎ በሚከፍለው (አልያም ሞልቶ ከተረፈው ተፈጥሯዊ ሀብት በዓይነት በሚከፈል) ብድር መሰራቱን የማያውቁ ይመስል ብሽሽቅ ጀመሩ። የስልጣኔ አልፋ መሆኑን አወሩ። “የ24 ዓመቱ ልፋት አፈራ” አሉ።

ለባቡር መንገድ ስራ ጫካ የተገባ ይመስል “የታጋዮች ደም ፍሬ እያፈራ ነው።” ተባለ። ሬድዮና ቴሌቪዥኑ ሌላ ስራውን ትቶ፥ ከሞላ ጎደል ባቡሩን ማውራት ጀመረ። ከባቡሩ በሚተርፈው ጊዜ ባለጊዜውን “ሞላ” ያቀነቅናል። ሰልፌዎች በየሰዉ ግድግዳ ተለጣጠፉ። ወሬው ባቡርና ባቡር ብቻ ሆነ። ጋዜጠኞቹ ከምን ጊዜውም በላይ መበጥረቅ ጀመሩ። አንዱ “ይሄን ታሪካዊ ትኬት አልበም ውስጥ አስቀምጬዋለሁ” ሲል ገረመኝ። ለወሬ ሲቸኩል፥ “ትልቅ ዋጋ ያለውን አረንጓዴ ትኬት ቆርጬ ረዥሙን መንገድ ነው የሄድኩት።” አለ። (ትልቅ ዋጋ ያለው ትኬት ቀዩ ነው እንጂ አረንጓዴው አይደለም።)

ወዲህ ከፒያሳ ተነስቶ ቃሊቲ፣ ወዲያ ደግሞ ከጦር ኃይሎች ተነስቶ ሀያት የሚዘልቁ ሁለት መንገዶች ተዘረጉና ከተማችን ቄንጠኛ ሆነች ተባለ። ሰዎች ደግሞ መውረጃቸው ጋር ሲደርሱ ወደጉዳያቸው ቶሎ እንደመሄድ ወገባቸውን ይዘው እዚያው ቆመው ወሬያቸውን ሲሰልቁ ይውላሉ። የባቡሩ መንገድ ሊሰራ ሲቆፈርና በልምምድ ወቅት፣ ከብበው ይመለከቱ ከነበረው በላይ ሰዎች የባቡሩን ማለፍ ቆመው ይመለከታሉ። ያወራሉ። ምን እንደሚያወሩ ግን አይገባኝም ነበር። ፖሊሶችና ትራፊኮች የባቡር ጣቢያዎች ላይ ፈሰሱ። በቻይኖች እየተዘወረች ባቡሯ ብቅ ስትል (በየ6 ደቂቃው ነው ተብሏል) ሰዉን ያዋክቡታል። ከድንዛዜው የተነሳ ሀዲዱ ላይ ሲሰጣ፣ ተገርፎ የሚወጣም ነበር። (ሲያንሰው ነው።)

እንዳያያዛቸው፥ የባቡሩ መንገድ ስር፣ እና ጎንና ጎን፣ አንድ ቀን እሳት አንድደው፣ ጀበና ጥደው ቡና ሳይጠጡም አይቀር። ዳስ ጥለው ጠላ ሳያንዶቆድቁም አይቀር። የእድር ስብሰባዎችም እዚያ ሳይካሄዱም አይቀር። መጀመሪያ ሰሞንማ ባቡሩን ለማየት ከቤት ተቀሳቅሰው የሚወጡ ነበሩ። እንደ ቤተ አምልኮ ሊሳለሙት ይመስል ነጠላ ጎትተው ዋናው መንገድ ላይ የሚውሉ ጎልማሶች ተበራከቱ። ጎረምሶችና ኮረዶች ደግሞ መቀጣጠሪያቸውን የባቡሩ መንገድ ያለበትን አቅጣጫ ብቻ አድርገውታል።

በየስልኩ “ሃሎ! እሺ… አልቆይም ኧረ። ባቡሯን ይዤ ነው የምመጣው።”፣ “ውይ ባቡሯ አመለጠችኝ። በቃ ቀጣይዋን እይዛለሁ።”፣ “ባቡር አትይዥም? አቦሉ ላይ ድረሺበት…”፣ “ለትንሽ አረንጓዴዋ ትኬት አለቀችብኝ። በቀይዋ መጥቼ አቆራርጣለሁ። አልቆይም…” የሚሉ የስልክ ወሬዎች መሰማት ጀመሩ። “ችግር ያቅልል ተብሎ ችግር ሆነ እኮ። ታያለህ መንገዱን እንደዘጋጋው?” የሚሉ አሽከርካሪዎች በዙ። ።

የባቡሩ መጫኛና ማውረጃ ቦታዎች ሁልጊዜ ትርምስ ሆነ። መንገድ መዘጋጋት ጀመረ። በተለይ ባቡሩ ዝቅ ብሎ፣ ከመኪና ጋር እየተጠባበቀ በሚያልፍበት ቦታዎች ላይ የትራፊኩ ጭንቅንቅ በዛ። ታቦት እንደሚሸኙ ሁሉ ተሻጋሪዎች ተከትረው ቆመው ይጠብቃሉ። የመርካቶ በራፎች ትርምስ በዛባቸው። ወትሮም ግር ብለው ሲወጡና ሲገቡ ቀብር የሚሄዱ የሚመስሉት የመርካቶ ሰፈር ነዋሪዎች መውጫና መግቢያ ላይ፥ አስከሬን ቆመው የሚያሳልፉ ይመስል… አልቃሽ ያዙኝ ልቀቁኝ ብላ ስትፈጠፈጥ ቆመው እስክትነሳ ይጠብቋት ይመስል…መውጫና መግቢያው ላይ መገደብ ጀመሩ። ትራፊክና ፖሊሶች ላይም ጭንቅ ሆነ። መጀመሪያ ሰሞን፥ ሰዉ ጉዳይ ሳይኖረውም ለሙከራ ይሳፈር ነበር። “እስኪ ሽርሽር እንውጣ” ይላሉ። ለሙከራ የሚሳፈሩት ሰዎች ፊት የመገረም ፈገግታ ፊታቸውን ሞልቶት ይታያል።

ትንሽ ከርሞ ከተማዋ በዚህ ባቡር ከዘነጠች በኋላ እናቴ አንድ ሀሳብ ተከሰተላት። ካልጠፋ ነገር ባቡሩ ጣቢያ ጋር ቆሎ የማዞር ሀሳብ ተከሰተላት። መንገድ ሲሄዱ መኪና ተበላሽቶ ወርደው የሚተራመሱ ሰዎችን ሲያይ፥ “እዚህ ጋር ሻይ ቤት መክፈት ነበር” እንዳለው ስራ ፈጣሪ ጉራጌ እናቴም የስራ ሀሳብ ተከሰተላት። በቆሎ ጀምረነው፣ የሰዉን ፍላጎት እያየንና እንደ ወቅቱ ድንችና በቆሎም እንጨምራለን አለች። በፕላስቲክ የተለበጠ “ሞባይል ካርድ አለ” የሚል ወረቀት አንገቴ ላይ አንጠልጥዬ፣ ማልጄ ቆሎዬን ይዤ እንድወጣ ተፈረደብኝ።

ባቡሩ እንቅልፌን ቀማኝ። ባቡሩ ልጅነቴ ላይ ተደራደረ። እንደፈረደብኝ ባቡር ለሚጠብቁ ሰዎች ቆሎዬን መስፈር ጀመርኩ። እንደ ስራ ሳይሆን እንደቅጣት ስለምቆጥረው በደስታ አድርጌው አላውቅም። ባቡሯ እንዳታመልጣቸው ሲዋከቡ መልስ ጥለው የሚሄዱ ሰዎች ሲያጋጥሙኝ ደስ ይለኝ ጀመር። እንደዛ ሲሆን “ስትመጣ ትከፍላለህ… ቅመሳት” እያልኩ መቀናጣትና ገበያተኛ ማማለል ይቃጣኛል።

አንዳንዴ ደግሞ የፋጤ እድል ይገጥመኛል። ማንጎ ሸጣለት “ሽልንጌን” እያለች የጮኸችው የሀረሯ ፋጡማ ትዝ ትለኛለች። አንዳንዱ ቆሎዬን ሰፍሬለት ሳይከፍለኝ ባቡሯ ውስጥ ይገባል። እንዲህ ሆነ ስራዬ። ባቡሯ በመጣች ቅጽበት እንደ ሀይለኛ ዝናብ ሿ ይልና፣ ወዲያው ቀጥ ብሎ ያባራል። ሰፌዴን ይዤ እንደነገሩ ትከሻዬ ላይ ጣል አድርጌው እወጣና ባቡር መንገዱ አካባቢ በፀጥታ ገዢ እቃርማለሁ። ባይኖቼ እለማመጣለሁ።

ባቡር ጠባቂው “መጣች መጣች” ይባላልና አንገት ሁሉ ሰግጎ ባይኑ አቀባበል ያደርግላታል። እሪ ይባላል፣ ይጮሃል፣ ይገፋፋል። ጨዋ የሚመስሉ ሴቶች እንኳን ቀሚሳቸውን ሰብስበው ይሯሯጣሉ። ቆሎዬን ሽጬ እቤት ከተመለስኩ በኋላ ሌላ ቆሎ ከሌለ፣ የሞባይል ካርዶቼን ይዤ ሰፌዱን አስቀምጬ እወጣለሁ። ከዚያ ለተባራሪ ፈላጊ ሞባይል ካርድ እየሸጡ ወሬ መስማት ነው።

ባቡሩ መጀመሩ አንድ ትልቅ የወሬ ለውጥ አመጣ። ሕዝቡ ለታክሲ መጋፋቱን በባቡር መጋፋት ተካው። የሚሄድበት መንገድ አጭር የታክሲ ወይም የእግር መንገድ ቢሆን እንኳን፥ እንደምንም ብሎ ባቡሩ በሚሄድበት አቅጣጫ ሄዶ፣ በታክሲ ማቆራረጥ ጀመረ። ባቡሯን ለመጠቀም ቀደም ብሎ እየወጣ ራሱ ላይ መከራ ከመረ። ወሬው በየቦታው በየቤቱ በየቅያሱ ስለባቡርና በባቡር ስለመሄድ ሆነ። ቃሊቲና ቂሊንጦ ያሉ እስረኞችን የሚጠይቅና መንጃ ፍቃድ የሚያወጣው ሰው በዛ። ባቡሯን ቃሊቲ ድረስ ለመጠቀም ብሎ ወጥቶ ደብረ ዘይት ሄዶ የሚዝናናውም ሰው ጨመረ።

“ፍጥነቱ ደስ ሲል። ደግሞ የሚሄድም አይመስልም… ”

“መንገጫገጭ የለ… ታክሲው እኮ ሲንጠን እንዴት ገድሎን ነበር?”

“አንቺ ባቡሩን ሞከርሽው? ወደ ሀያት ስትሄጂበት ደግሞ ከቃሊቲው ይለያል።” ትንታኔዎች ተደሰኮሩ።

“ትላንት ለቅሶ ሄጄ… እንዴት ፈጥኜ መጣሁ መሰለሽ።” (ሰው ሲሞቱና ትልልቅ ጉዳዮቹ እንዳያልፉት ባቡሩ መንገድ ተከትሎ ያሉ ዘመዶቹ ጋር ዝምድናውን አጠበቀ።)

“ደግሞ ከታክሲው ሲናጸር ዋጋው መርከሱ… ታክሲዎቹማ ሲበዘብዙን ኖሩ እኮ።”

“ኧረ የረዳቶቹን ስድብ መጠጣቱና የጣሉትን ቂጥ ማየት መቅረቱስ”

“’ድመት መንኩሳ ዐመሏን አትረሳ’ …አሁን ምንድን ነው መስገብገብ። ሆዱ እኮ ሰፊ ነው። ሁላችንንም ይችለናል። ኧረ ተዉ ቻይኖቹም ይታዘቡናል…”

“ኧረ ደቂቃው እንዳይሞላብሽ ፍጠኚና ውጪ”

“ለትንሽ ጥሎኝ ሊፈረጥጥ። ሀዲዱ ላይ መዳመጤ ነበር…ብቻ ብረቱን ይዤ ተረፍኩ።”

“ባቡር ላይ እያስቸገረኝ ነበር። ስልኬን ወስዶ…”

“እንዴ ባለቤቴ እኮ ባቡሯ እንዳታልፈው ስለሚጣደፍ ማምሸቱም ቆሟል። ይኸው በጊዜ፣ መጥቶ ስንላፋ ነው የምናመሸው ስልሽ…”

ጨዋታው ባቡርና ባቡር መንገድ ሆነ።

ባቡር ባቡር የሚሉ ዘፈኖች፣ የድሮ የዘፈን ክሮች እየተራገፉ ወጡ። አዳዲስ ግጥምና ዜማዎችም ተቀመሩ። ችኮላው አላደርስ ያላቸው የቀድሞ ዘፈኖችን ግጥሞች አድሰው ሬድዮዎቹን አጨናነቁ።

ባለጋሪው ባለጋሪው፣
ቶሎ ቶሎ ንዳው…

የሚለው ዘፈን ግጥም ተቀይሮ…

ባለባቡሩ ባለባቡሩ፣
ሸገር ሆኗል ሀገሩ!

ተሳፋሪ ሁሉ ባለ ጉዳይ ነው
ታክሲና አቶቢሱን አሻግሮ ሚያየው
የሞላ የሞላ ባለና በፊቴ
ባሳፈረኝና እፎይ ባለ ስሜቴ፤
እፎይ ባለ ስሜቴ፤

ተብሎ በየኤፍ ኤሙ ተሰማ።

በባቡር በፍቅር መንገድ ላይ በባቡር
በባቡር በመውደድ መንገድ ላይ በባቡር
መጓዝስ ካልቀረ ካንቺ ጋር ነበር

የሚለው ሙዚቃ እንዳንዲስ መጠባበሻ ሆነ።

በባቡሩ መንገድ የቆምኩት አሁን
ስንቱን አሳልፌ ልዘልቀው ይሆን?

የሚለው የሜሪ አርምዴ ዘፈን ከነክራሩ ከተሰቀለበት ወረደ።

በየታክሲው ጭቅጭቁ፣ ማስፈራራቱና ዛቻው በዛ።

“ኤጭ አትጨማለቅ እንግዲህ! ባቡር እኮ…” እያሉ የሚያስፈራሩ፣ “’እጸድቅ ብዬ ባዝላት…’ አንተ በባቡር መሄድ አቅቶኝ አይደለም።” እያሉ የሚመጻደቁ፣ “እንደውም ተወው ባቡሯ ብቅ አለች” ብለው የሚያኮርፉ ተሳፋሪዎች በረከቱ።

“ታክሲ ጥንቡን ጣለ” ተባለ።

ስጋቶችም አልጠፉም።

“መብራት ቢጠፋስ?”፣ “ደግሞ ሲዘንብ ቢነዝረኝስ?”፣ “ይሄ ደንባዛ ቻይና ቢያስነጥሰውና ዐይኑ ጭራሽ ድርግም ቢልስ?” የሚሉና ሌሎች የፍርሃት ወሬዎች በሹክሹክታና በየሰዉ ልብ ውስጥ ይብላሉ ጀመረ።

“ባቡር ጣቢያው ጋር ጠብቂኝ” “ምስጢራዊ የባቡር ጉዞዎች” “መሀልየ መሀልይ ዘባቡር” “የባቡሩ ጉዶች” “ባቡር ላይ ያየሁት ወንድ የወሰደው ልቤ” “ባቡር ተሳፍሬ” “የዘገየው ባቡር” “ከባቡር አደጋ ለመትረፍ የሚያስችሉ 8 ነጥቦች” “ባቡርን ወደ ቢዝነስ የመቀየር ጥበብ” “የባቡር ኬሚስትሪ” “ባቡሩ” “ከባቡር የወጣች ነፍስ” “ባቡር መንገዱ ዙሪያ ያሉ የወሲብ ሕይወቶች”…የሚሉ የተለያዩ ከተፋ መፅሐፍትና ፊልሞች በዙ። ሙዚቃዎችም ባይነት ባይነቱ ሆኑ። ገጣሚያንም ወገባቸውን ቋጥረው ስለባቡር ተቀኙ። ናፍቆትና ጥበቃ በባቡር ተሰማመሩ።

“የከሸፈው የአሸባሪዎች ሴራ በባቡሩ መንገድ ላይ”፣ “እንደ ባቡራችን ፈጣኑ ኢኮኖሚያችን”፣ “ባቡር ላይ በሻዕቢያ ተላላኪ ፀረ ሰላም ኃይሎች የተቀነባበረው ፍንዳታ ምስጢር ተጋለጠ”፣ “አቶ አንዳርጋቸው እንደ ኤክስፕረስ መንገዱ የባቡሩንም ጎበኙት። ይህኛው የባቡር ጉዞዬ ከእስከዛሬው ሁሉ ለየት ያለ ነው አሉ።” እና የመሳሰሉ ዶክመንተሪዎችና የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ርዕሶች በብዛት መታየት ጀመሩ።

እኔ ግን ኑሮ ባቡር ላይ ተጭኜ ቆሎ እሰፍራለሁ እንጂ እስከዛሬ ባቡር ተሳፍሬ አላውቅም። ባቡሩ ሆዴን እያሰብኩ ባቡር ተሳፋሪን አሳድዳለሁ። በቆሎና ስለቆሎ ያየሁት ጉድ ይበዛል። ሳድግ ግን “ባቡር መንገድ ላይ ያሳለፍኩት ልጅነቴና ትዝብቶቼ” ወይም “ባቡር መንገድና የሰው ልጅ ጠባይ” ወይም “ባቡርና ሕይወት” ወይም “ባቡር ጣቢያ ላይ የተረሳው የትንሹ ልጅ ሕይወት” የሚል መጽሐፍ ብጽፍ ደስ ይለኝ ነበር። ትምህርት ቤት አልሄድኩም እንጂ መጻፍ ብለምድና መጽሐፍ ብጽፍ ደስ ይለኝ ነበር።

‘ግን ሰው ከባቡር መሳፈርና ስለባቡር ማውራት ምን ጊዜ ተርፎት ያነብልኛል?’ ስል አስባለሁ።

ማስታወሻ
ይህንን የጻፍኩት የአዳም ረታ “ግራጫ ቃጭሎች” ላይ ገጽ፥ 127-128 ባለው “ቧንቧ፣ ልብስና የሰው ጠባይ” በሚል ንዑስ ርዕስ በተጻፈው ታሪክ መቆስቆስና ቅርጽ ነው። አንዳንድ አረፍተ ነገሮችንም በቀጥታ ከግራጫ ቃጭሎች ላይ ገልብጫለሁ።

ምስጋና ለጂጂ!

(ቢንያም በኃይሉ)547326_3699537895706_2029155825_n

በበዙ እንቅልፍ አልባና ለብዙ ነገር ስሜት ኣልባ የሆኑ ለሊቶቼ ላይ ሳይቀር ኩርፊያዬ በሷ ላይ አይጠናም ለመፃፍም ለማንበብም በማይመቸኝ ስሜት ውስጥ ስሆን ከጥቂት የመፅናኛ ምርጫዎቼ መካከል ቀዳሚዋ ናት…ድንቅ በሆነ ብቃት የሚንቆረቆር ውብ ድምፅ …ጥልቅ በሆኑ ቃላት የተቀኘ ቅኔ… ረቂቅ የሙዚቃ ቅንብር… በጆሮዎቼ ወደ ውስጤ ሲንቆረቆሩ… የተሳሰሩ ህዋሳቴ ሲፍታቱ… ያኮረፈች ነብሴ ስትፈግግ ይታወቀኛል… የኔ ጂጂ ለሰው ስትሰጥ ስስት አታውቅም።

በተለይ የሃገራችን የሙዚቃ ግጥሞች በመቅለል ላይ (simplicity) በብዙ የተንጠለጠሉ ከመሆናቸው የተነሳ የሃሳብ ወይም የፍሰት አራምባና ቆቦነት ለብዙዎቹ ብሄራዊ መለያቸው ነው።

እንደ

የዝንጀሮ ቆዳ አይሆንም ከበሮ
ማረፍያ አላገኘም ልቤ በሮ በሮ

አይነት የዘፈን ግጥሞችን ለማግኘት ብዙ ማሰብም አይጠይቅም። ታዲያ በዚህ በምንም ግጥም የተሞላ የሙዚቃ መንደር ውስጥ በእያንዳንዱ ስራዎቿ ላይ የግጥሟ ርቀት እና ጥልቀት ያለ ስስት ከሰማያት እንደሚለቀቅ ዝናብ የሚጎርፍ ሲሆን … እንደ ቡና ደጋግመን ብንኮመኩማት… በሙሉ ልብ ስሟን ስናንቆለጳጵስ ብንውል… “ከጂጂ ወዲያ” ላሳር ብንል… እንዴት ማንስ ይፈርድብናል። ይሄ አገላለፅ ጂጂን ለማወደስ የተጋነነ አይደለም
ላለመሆኑም እነሆ ማሳያ፦

በተለይ ይህ ዘፈኗ እጄን ባፌ ላይ ያስጭነኛል አንድ አጠናን ገዝተው ለብዙ ሰነጣጥረው የበዛ ስቴኪኒ አድርገው እንደሚሸጡ ፋብሪካዎች ይሄ አንድ ዘፈኗ ለሌሎች ዘፋኞች ተሰነጣጥሮ ሙሉ አልበም ይሰራል።

ዘፈኑ አንድ ወንድን የሚያወድስ መሃልይ ነው።

ሳላየው አላድርም አይነጋም ለሊቱ
ጀንበሯን ቀድሜ እደርሳለሁ ቤቱ

ዶፍ ዝናብ ሳይፈራ ወንዙ ሙላት ሳያግደው
የሃምሌ ነሃሴ ቆፉ ብርዱ ሳይመልሰው
ፍልቅልቅ ብራቁን ወንዙን ሽብሩን ሳይፈራ
ልቤ ገሰገሰ ዛሬ ሊኖር ካንተ ጋራ
በካህን ሽብሻቦ በሊቅ በዲያቆኖች ዜማ
ቢወደስ ቢመለክ በታላቅ ጉባኤ ቢሰማ
ሺ ቃላት የሚያንሰው የወንድ የቆንጆዎች አውራ
የታተምከው ፈሳሽ በልቤ ገነት አዝመራ

ጎምላልዬ…ግርማው እንዳንበሳ…
ጎምላልዬ
ጎምላልዬ …ውበቱ እደፀሃይ …ጎምላልዬ
ጎምላልዬ …ያይኖቼ ማረፊያ …ጎምላልዬ
ጎምላልዬ …የልቤ ሲሳይ …

አ_ዝ

በራሴ ጠል ሰፍሯል ውዴ በሹሩባዬም ስም
ደረስኩ ንጋት ሳይለይ ክፈትልኝ የኔ ህመም
ፀሃይ ብልጭ አለ ጠራ ፈካ ገመገሙ
ክፈት አይንህን ልይ ውዴ ያገር ልጅ ድማሙ
ጠል እና አንዛቦ ብርዱ እሳትና ዋዕይ
ዝናብና ዶፉ ጎርፉ ውርጩና አመዳይ
ከንቱ ላያግደኝ አትፍራ አትሸበር ልቤ
ሳላየው አላድርም ያንን ናርዶስ ያንን ከርቤ

ያንተ ያለህ!! በሃገሬ ሙዚቃ ላይ በዚህ መጠን መራቀቅ የቻለች ፈርጥ ጂጂ ብቻ ናት። ኢትዮጵያን ለማወደስ የምናደምጠው ሙዚቃ በፈለግን ጊዜ…የአደዋን ድል በውብ ልሳን በረቂቅ ቅንብር ልንሰማ በናፈቅን ጊዜ…የአባይን ውበት በረቂቅ ገለፃ በተስረቅራቂ ድምፅ ማድመጥ በወደድን ጊዜ…በአጠቃላይ የእውነት ሙዚቃን የሻትን ጊዜ ከጂጂ በተሻለ ጥምን ለመቁረጥ ለአምሮትየሚሰማ ድምፃዊ አለ ብዬ አላምንም።

ዘመንሽን ያርዝመው ጌጣችን ጂጂ!!!

ያለስስት ለሰጠሽን የጥበብ ስጦታ መልሳችን ምስጋና ነው እንወድሻለን።

GIGI (Ejigayehu Shibabaw)​ Gigi, Ethiopian Singer, Ejigayehu Shibabaw​ I love Gigi ( Ejigayehu Shibabaw )​

እኔን!

ከ6 ዓመቱ የእህቴ ልጅ ጋር በስልክ እያወራን ነበር።

“ድምጽህ አይሰማም ነው የምልህ። ጮክ ማለት ትችላለህ?” አለኝ።

“አሞኛል ቤቢዬ። በግድ ነው የማወራህ… ”

“እኔን! መች ቀድመህ ነገርከኝ ታዲያ?”

“አዪ ሳልሞት አልቀርም…” (የልጅ ማባበሉን ሳልወደው አልቀረሁም 🙂 )

“እኔን አልኩህ እኮ። በቃ አሁን ትድናለህ! ቀድመህ ብትነግረኝ፥ እስካሁን ትድን ነበር።”

“እንዴት ቤቢዬ መድሃኒቱን ታውቀው ነበር እንዴ?”

“ቀድሜ እኔን ስለምልህ ይሻልህ ነበር። አሁንም እኔን ስላልኩህ ቶሎ ይሻልሃል!”

🙂

“እኔን” ማለት፥ ዋጋ የማይከፈልበት ኢትዮጵያዊ ሀኪም፤ ሌላ የትም የማይገኝ ማፅናኛና የህመም ማስታገሻ ቃል፤ “አይዞህ” የሚለው ቃልም በአፅናኝነቱና ህመም አቅላይነቱ የሚደርስበት አይኖርም። የገረመኝና የቃሉን አቅም ይበልጥ ያስተዋልኩት በእህቴ ልጅ የ“እኔን” ፈዋሽነት እምነትና፣ “እኔን” ሲለኝ፥ ህመሜን ሊያቀልልኝ እንደሚችል ባለው ልበ ሙሉነት ነው። እሱ ታሞ “እኔን” በተባለ ቅጽበት የተሰማው እፎይታም ከእምነቱ ላይ ይስተዋላል። የእርሱ የ“እኔን” አስተዋፅኦ ታማሚውን መፈወስ ላይም ራሱን የቻለ አስተዋፅኦ እንዳለውም (as it matters) ተገንዝቧል። የ“እኔን” ኃይል ላይ የልጅ የዋህነት ሲጨመርበት ደግሞ ልዩ ነው!

ማን እንደ አማርኛ!?

11988652_1206632436029703_5111940244842036533_nልጅነት

በተንኮል አልባ ልብ፥ ዝም ብሎ ‘ሚፈስ፣
ሁሉም ሲጨልፈው፥ በ’ድሜ ሚደፈርስ፥
ልጅነት — ውኀነት፤
ልጅነት — ንጹሕነት፤
በጊዜ ‘ሚቆሽሽ፥ ያም ያም ሲጠልቅለት።

እርጅና ተጭኖት፣ በጥም የተጎዳ፣
አልፎ ሲናፍቀው፣ ሊያገኘው ሲዳዳ፣
በትዝታ ባልዲ፣ ‘ሚታገል ሊቀዳው. . .
ጥሙን ሚቆርጥበት፣ የቀዳ ሚጠጣው፤

ልጅነት — ውኀነት።
ልጅነት — ንጹሕነት።

/ዮሐንስ ሞላ (2005) “የብርሃን ልክፍት” ገጽ 57/

☀☀☀

አዲሱን ዓመት በተለያየ ችግር፣ የኑሮ አለመመቸትና አሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ ሆናችሁ ለምትቀበሉት ወዳጆቼ ሁሉ — እኔን!

P.S. ፎቶው የጓደኛዬ ልጅ ነው።

ልጅነቴ ናፈቀኝ…

547326_3699537895706_2029155825_nዝናቡ ጣሪያውን ሲቆረቁረው ሰማሁና እንደ ልጅነቴ፣ መለመላዬን ወጥቼ “ሩፋኤል አሳድገኝ” እያልኩ መቦረቅ አማረኝ። ሩፋኤል ላይ ዝናብ ሳይዘንብ የማይቀረው ነገር ደግሞ ሁሌም የሚገርመኝ ነገር ነው። ያው የሰፈሬን ሰማይ ነው የማየው።

ምድር ገላዋን ስትታጠብና ቆሻሻዋን ስታፀዳ ይመስለኛል። ሰዉም ንጽህናን መናፈቁ ግልፅ ሳይሆን አይቀርም። ግን ወዲያው እንቆሽሻለን። ከመቆሸሽ ጋር እንዋዋላለን። በሩፋኤል ፀበል የናፈቅነውን መንፃት፣ “ግባ” ያልነውን የጎመን ምንቸት፣ በእንጉጣጣሽ ቢላዋ ስንዝር፥ ሳይርቅ ጎትተን እናመጣዋለን። የገንፎ ምንቸትማ ወጣ ገባ ሲል በመሀል ቤት ሳይሰበርም አይቀር።

ይህን እያሰብኩ ልቤ ሩቅ ሩቅ ወደ ገጠሮቹ ሄደብኝ። ከተማውን ሳይ የማላውቀው፣ ወይም ድንገት በጉብኝት የማውቀውን ገጠር ነው የማስበው። ለበዓላት ድምቀት ቱባውን ባህል ኀሰሳ ገጠሩ ነው ባይኔ የሚዞረው። አሁንም እንደዚህ ሆነ። በምናብ ኀሰሳዬ መካከል በረሀብ የተጠቁ አካባቢዎች ያሉ ህፃናት ዐይኔ ላይ ተኮለኮሉ። የህፃን መልክ ሳይታይ ይታወቃል። መልካቸውን ማምጣት ቀላል ነው። የሆነ ፊት ላይ የልጅ ፈገግታና ንፅህና ማሰብ ነው። የማንንም ልብ መግዛትና ለርኅራኄ የሚያስገድድ ገጽ መገመት ነው።

እነሱ ዛሬ ዝናብ አያውቁም። እነሱ እንኳን “ሩፋኤል አሳድገኝ” ብለው ሊቦርቁ፣ ዛሬ ላይ ቢኮረኮሩም መሳቃቸውን እንጃ። ወላጆቻቸው ቀናቱንም ላይለዩ ይችላሉ። ሆድ ጠላቱ፥ ይበላል። ክፉኛ ያሳክካል። ይታከክበት፣ ገል ይሆን ቁራሽ አጥቶ ዝም ብሎ ያሳክካል። እንዲህ ላለ ሰው በዓል ቅንጦት ነው። ዝናብ ከሞት ወደ ሕይወት የሚመልስ ፈውስ ነው። ግን ይሄም ያልፍና ይረሳል። ተጎሳቁለን እንደማናውቅ እንንቀባረራለን። ተንቀባርረን እንደማናውቅ እንጎሳቆላለን። – ሌላ ጅምላ መከራ እስኪሰማ!

ያም ሆነ ይህ ግን አሁን ካልጋዬ ተነስቶ መለመላዬን ዝናብ ላይ መጣድ ነው ያማረኝ። ሁለት ቴፕ የተከፈተ ይመስል ሁለት ሙዚቃዎች ጆሮዬን እኩል ይደበድባሉ። የሁለቱ ንብርብር፣ ዝብርቅርቅ ያለ ድምፅ ፈጥሮ ያስጨንቃል።

“ዋይ ዋይ ሲሉ፣
የረሀብን ጉንፋን ሲስሉ”

እና

“ልጅነቴ ናፈቀኝ
ተመልሶ ላይመጣ”

ለሩፋኤል ፀበሉም ባይሆን የነገሮችን ህመም ልክ ላለማወቅ ልጅነት በጣም ይናፍቃል። የሰውን ዋይ ዋይታ ላለማስተዋል ልጅነት ወሳኝ ነው። ደግሞ መከራና ስቃዩ ሲቆጠር፣ ራስን ከመካራ ለማስጣል የመፍጨርጨርና መላ የመምታት ውሱንነቱ ሲታሰብ፣ “እዚህ ጋር አመመኝ” ብለው የማይናገሩት ነገር ሲታይ፥ ልጅነት ይሸክካል።

ዝናቡን የበረከት ያድርግልን!

አዲሱ ዓመትም ህፃናት የሚቦርቁበት፣ አረጋውያን የሚመርቁበት ይሁንልን! በዓሉንም የተቸገሩትን እያሰብን እንድናሳልፈው ይሁን!

እንኳን ተለየሽኝ!

“ምነው ተለየሽኝ መስከረም ሳይጠባ?79896127 (1)
እንቁጣጣሽ እያልን፥ ሳናጌጥ በአበባ”

ያሉትን ቀልቤ፥
እውነት መስሎኝ ያልኩሽ፥…
ዝም ብዬ ሳስበው፥
ለካስ ውሸቴን ነው፥ አይደለም ከልቤ!

መሄድሽ ለማይቀር፥ መስከረም ከራርሞ፣
¬ ጥቅምቱ ሲገባ፥ ብርዱ ሲበረታ፥
ከማቃስት ብቻ፣ ልቤ ባ’ንቺ ታምሞ፥
¬ ሙሾ ከማውረዱ፥ ነፍሴ በኀዘን ቃትታ፥
¬ ባዶ ቤት በበጋ፥ ፈዝዛ ተኮራምታ፥
ተሸሽጋ ከርማ፥ ከክረምት ተጋፍታ፣
ደስታ ከመጥለቋ ባ’ዲስ ፀሐይ ታይታ፥…

ሙዚቃ አድሼያለሁ…

“እንኳን ተለየሽኝ መስከረም ሳይጠባ?
እንቁጣጣሽ እያልን፥ ሳናጌጥ በአበባ”

ልብ አንዴ ተነስቶ መቆየት መክረሙ፥
ከተራ ሀሜት ጋርዶ፥ ይበዛል ህመሙ፤
እንጂ ምን ይረባል?
ደግሞስ ዓለሜዋ፥… ከአዲሱ ሰማይ ላይ፥
አዱኛ እንደሌለ፣ እንዳልሞላ ሲሳይ፥
ማን አየ? …ማን ያውቃል?

‘አትሂጅ’ ብሎ ዋትቶ፥
¬ ከሂያጅ ጋር ተጓትቶ?
የት ይቀር መስሎሻል፥ ዐይን ተንከራትቶ?
ይሻል ቀን ይመጣል!…
ወይ ከውጭ ያስገባል፥
…..የሄደበት አይቶ!
ወይ ውስጥ ውስጡን ያያል፤
…..የሚያርፍበት አጥቶ!

እናም እልሻለሁ፥…
እንኳን ሄድሽ ከፊቴ፤

አበባ ሸክፎ…
በወፍ ምሪ መጥቶ የሚቆም ከቤቴ፥
ከአደይ ተከታትሎ፥ የተስፋ ፏፏቴ፥
እንዳምነሸነሸኝ፥…

ባ ወ ቅ ሽ!…
ዞረሽ በተመለስሽ!
¬ ደጄን በቃኘሽው፥
ማማሩን ባደነቅሽ፥
¬ ጀርባዬን ባየሽው።

/ዮሐንስ ሞላ/

P.S. “ምነው ተለየሽኝ?” የዕውቁ ግርማ ነጋሽ ዘፈን መሆኑ ይታወቃል። ሙዚቃውን ለማዳመጥ ይህንን ይጫኑ: “ምነው ተለየሽኝ

መፅሐፍ ስለማቃጠል…

መፅሐፍ በተናጥልም ሆነ በጅምላ ሲቃጠል አዲስ አይደለም። የዓለሙን ነገር ትተነው downloadስለአገር ቤቱ ብናወራ ከአዳዲስ ርዕዮተ ዓለማት ጋር እንዲቃጠሉ፣ እንዲሸሸጉ፣ አልያም በተለያየ መልኩ እንዲባክኑ የተፈረደባቸው በርካታ መፅሐፍት እንደነበሩ/እንዳሉ ይታወቃል። የሌላውን ንዶ የራስን የመገንባት ሽሚያ ነው። ‘ያን ካነበቡብኝ ይነቁና ጉዴ ይፈላል’ ‘እቺ ባቄላ ካደረች…’ የሚል ተራ ስጋትና ብልጣብልጥነትም አያጣውም። አንዳንዴ እንዳይነፃፀሩና እንዳይበላለጡም ይፈሯል። የ‘እኔ አውቅልህ፣ እኔ እጠብቅህ’ ዓይነት ለሕዝብ ያለ ንቀት ውጤትም ሊሆን ይችላል። ብቻ ግን መፅሐፍት በተለያዩ ጊዜያት በጅምላ የእሳት ሲሳይ ሆነዋል።

በተናጥል (የአንድን ፀሐፊ መፅሐፍ፣ ለራስ የገዙትን ኮፒ ለይቶ) ማቃጠል፣ በየስርቻው ሲደረግ የኖረ ሊሆን ቢችልም፣ ከፌስቡክ መምጣት ጋር ተያይዞ በይፋ ለማየት የቻልነው ነገር ነው። እኛ ዙሪያ ላይ ሲቃጠሉ ካየናቸው መፅሐፍት መካከል፥ የመጀመሪያዋም የእኔዋ “የብርሃን ልክፍት” ትመስለኛለች። ቃጠሎውም የተከናወነው የምረቃ ፕሮግራሙ ሳይደመደም በፊት ስለነበር፣ ያላነበበውን መፅሐፍ ለማቃጠል የወሰደው እርምጃው፥ ችግሩ ከይዘቱ ጋር ሳይሆን ፀሐፊው (እኔ) ላይ በነበረው ባዶ ጥላቻ ‘ልክፍት’ መሆኑን ብዙዎች መልስ ሲሰጡት ነበር።

እኔ ያኔ መፅሐፌ ላይ ይሰጡኝ የነበሩ ገንቢ አድናቆቶችና ትችቶች በመሰብሰብ ተጠምጄ ስለነበር እንደጥሩ ማስታወቂያነት ከመቁጠር በዘለለ፣ ልብ አላልኩትም ነበር። በተሰራጩ (broadcast-ed) መፅሐፍ ቃጠሎዎች ሰንጠረዥም ብዙ ጊዜ በመቃጠል ሪከርዱን የያዘችው የእኔ “የብርሃን ልክፍት” ሳትሆን አትቀርም። 🙂 ከዚያ በኋላም በሁለት ወዳጆች ተቃጥሎ ነበር። ዘንድሮ ደግሞ 2 መፅሐፍት በይፋ መቃጠላቸውን በፎቶ ተመልክተናል። የሌሊሳ ግርማ “አፍሮጋዳ” በራሱ በሌሊሳ እና የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም “አዳፍኔ” በግርማ

ምናልባት “የራሱ ስለሆነ” ተብሎ ሊሆን ይችላል፥ የሌሊሳ ግርማ መፅሐፍ ማቃጠል ምንም ዓይነት ትኩረት አልሳበም ነበር። የግርማ መፅሐፍ ማቃጠል ጉዳይ ግን ህዝበ ፌስቡኩን ብዙ እያነታረከ እስካሁንም ቀጥሏል። “መፅሐፍ ለምን ይቃጠላል?” ብለው ሲሟገቱ የነበሩ ሰዎች ግን የሌሊሳ ላይ ያሳዩት ቸልተኝነት የሚደገፍ አይደለም። የራሱ ቢሆንም፥ መብጠልጠል ካለበትም ድርጊቱ ነው። ሰው የገዛ ልጁን “ልጄ ስለሆነች” ብሎ እንደፈለገው ማጎሳቆልና ጥቃት መፈፀም አይችልም። እንኳን የገዛ ልጁን የገዛ ራሱም ላይ እንዲህ ቢያደርግ ድርጊቱ ወንጀል ከሆነ ወንጀል ነው።

ያም ሆነ ይህ፥ እዚህ ላይ የምንጫወተው ግን ስለተቃጠሉትና ስላቃጠሉትም አይደለም። ይልቅስ፣ ስለክስተቱ፣ ስለማቃጣሉና ስለስነልቡናዊ ምክንያቶቹ በ’በይሆናል’ መላምት ነው። ከታች በምሳሌነት የማነሳቸው፥ ነገሩን ይበልጥ ለማስረዳት ያህል ብቻ ነው። እንጂ የዚህ ፅሁፍ ዓላማ ከእለታት በአንዳንድ አርቦች እንደምናደርገው ጨዋታ ነው። (በነገራችን ላይ፥ መፅሐፍ ማቃጠል የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይም ነው። ህገ ወንጌል (the code) ከጥፋት ዱሎት ባይቀጣንም፣ ህገ ልቡናም (moral law) አለና ያንን ሳንዘነጋ ነው።)

በጅምላ ማቃጠል…

እንደሚታወቀው፣ ከዚህ ቀደም የተለያዩ ቦታዎች ላይ የእሳት እራት እንዲሆኑ የተዘመተባቸው መፅሐፍት ነበሩ። በጅምላ ስለተቃጠሉ መፅሐፍት ታታሪው ወዳጄ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ በጥናታዊ ዳሰሳው ሲያስታውሰን…

“…ቅጠሉን ገልጠን ስናይ፣ የታሪክ፣ የልቦለድና የትምህርት መጻሕፍትተከምረዋል። ‘የትንቢት ቀጠሮ’፣ ‘ሆኅተ ጥበብ’፣ ‘ፍቅር እስከ መቃብር’፣ ‘አርአያ’፣ ‘ከአፄ ልብነ ድንግል እስከ አፄ ቴዎድሮስ’። ብዙ የምናውቃቸው፣ አንብበን አስነብበን የተመሰጥንባቸው መጻሕፍት እዚህ ትንሽ የተራራ ቁልል ሠርተዋል። “ይኼ ነገር ምንድን ነው?” ብለን ተጠግተን የት/ቤቱን አስተዳደር ስንጠይቅ፣ “በእሳት ሊቃጠሉ የተዘጋጁ ናቸው” አሉን።

ደነገጥን፣ ተሳቀቅን። “ለምንድን ነው የሚቃጠሉት?” ስንል ደግሞ፥ “መጻሕፍቱ ደርግ ከሚከተለው ርዕዮተ ዓለም ጋር አብረው አይሄዱም። የሀገር አቆርቋዥና የፊውዳል ርዝራዥ አመለካከት የሰፈረባቸው ናቸው።” አለን። ….“እነ ፍቅር እስከ መቃብር፣ እነ አርአያ ሁሉ ሊቃጠሉ?” ……“የነዳጅ ጉዳይ ቸግሮን ነው እንጂ ይኼን ጊዜ በቦታው የአመድ ክምር ነበር የምታዩት። ነዳጁም ጠፍቶ ሳይሆን በየትኛው በጀት ይውጣ ብለን እየመከርንበት ነው።” አለን። (እንዳለ ጌታ ከበደ (2007) “ማዕቀብ” ገጽ፥ 204 የጋሽ ይልማ በረካ ትውስታ)

እዚሁ መፅሐፍ ላይ ደራሲው በ“ሰበር ትረካ” ምንጮቹን አጣቅሶ ሲቀጥል: “…የጥንቱ የቴሌቭዥን መምሪያ ኃላፊ አቶ ወሌ ጉርሙ በአደባባይ ላይ በሺህ የሚቆጠሩ መጻሕፍትን ያቃጠሉ የፕሬስ ነጻነት ቀበኛ ናቸው። የተቃጠሉትም የአስራተ ካሣ ስራዎች ስብስብ ናቸው። አስራተ ካሳ ሕዝቡን የመዘበሩ ቢሆኑም ከእውቅ ደራስያን ውጤቶች መካከል የእሳቸው መጻሕፍትም እንደሚገኙባቸው መዘንጋት የለበትም።… ትዝ ይለኛ በአወቅቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር የነበሩት ዶ/ር አለሜ እሸቴ ‘በሀገሪቱ ሕዝብና በሀገሪቱ ላይ የአእምሮ ረሀብ መልቀቅ ነው። መጻሕፍቱ የአድኃሪ አመለካከትን የሚያራምዱ ቢሆኑም አድኃሪ መሆናቸው ሊታወቅ የሚችለው ሊነበቡ ሲችሉ ብቻ ነው’ ሲሉ ነበር ቅሬታቸውን የገለጹት።” (አለስም፣ ጦቢያ ማነች? አዲስ ዘመን፣ ሚያዚያ 29/84)

“…በወለጋ… የኢሠፓአኮ ዋና ተጠሪ ንጉሤ ፋንታ ቀሳውስቱንና ሌሎቹን የሀይማኖት መሪዎች አስከብብቦ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን እንዲያቃጥሉ አዘዘ። ትዕዛዙን አንቀበልም ሲሉ እራሱ በርካታ መፅሐፍ ቅዱሳትን ሰብስቦ በሕዝብ ፊት አቃጠለ። መሀይምነት ነው ንጉሤ ይህን ያደረገው። በጣም የሚገርመው ግን በአሜሪካን ዩኒቨርስቲ ትምህርቱን የተከታተለውና ቀድሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተቀጣሪ የነበረው ዶ/ር ባሳዝነው ባይሳ ለምን በተደጋጋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ማቃጠል ዘመዳ ተባባሪ እንደሆነ ነው።’ (ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ፣ “የደም ዕንባ” ትርጉም ደበበ እሸቱ)

ይለናል።

በግለሰብ ደረጃ ተመርጠው ስለተቃጠሉ መፅሐፍት ምክንያት ብናነሳና ብናስብ፥ ከሞላ ጎደል የስነልቡና እና የስነ ባህርይ ውጤት ሊሆን ይችላል። በአንድም በሌላም መንገድ ትኩረት ይፈልጋሉና፥ ዓላማቸውም ከሞላ ጎደል በስነ ልቡና ጨዋታ የሚቃጠልበትን ሰው ወይም ወዳጆች ላይ ስነ ልቡናዊ ጥቃት ለመሰንዘር ይሆናል።

የራስን መፅሐፍ ማቃጠል

ከሳምንታት በፊት፥ ውዱ ደራሲ ሌሊሳ ግርማ የራሱን መፅሐፍ አቃጥሎ profile picture አድርጎት ነበር። የሆነ ዓይነት ብስጭት የወለደው ይመስላል። የተለጠፈው እኩለ ሌሊት ሲቃረብ ስለነበር ‘በሞቅታ መንፈስ ሊሆን ይችላል’ ብለን ማሰብ እንችላለን። አልያም እዚያ ‘አካባቢ የነበረ ሰው ሲጋራ ለኩሶ የጣላት ክብሪት በስህተት መፅሐፉን አቃጥላው፣ ሌሊሳም እንደ ጨዋታ ፎቶ ሲያነሳው ፎቶው አምሮት ለጠፈው’ ብለን በማለሳለስ መረዳትም እንችላለን። ከእነዚህ አንዱ ምክንያት ከሆነ፥ መቼስ ምን ይደረጋል?

ነገር ግን፥ ሆነ ብሎ አቃጥሎት ከሆነ የስነልቡና ችግር ውጤት ተደርጎ ነው የሚታሰበው። ሌሊሳ መፅሐፉን ሲያቃጥል፥ ምናልባት ዛሬ ባለበት አስተሳሰቡና ችሎታው ሲመዝነው አፍሮጋዳ ቀልሎ ተሰምቶት ይሆናል? (በነገራችን ላይ በጣም የምወደው መፅሐፍ ነው። በደንብ አለመሸጡም እንዳበሸቀኝ አለ።) “እኔ እኮ ከአፍሮጋዳ በላይ ነኝ። ምን ሆኜ ፃፍኩት?” ብሎ ተብሰክስኮ አብዮታዊ እርምጃ ወስዶባት ይሆናል? ምናልባት፥ ከራሱ ስራ ጋር ተመዝኖ የላዕላይ ምስቅልቅል (superiority complex) ውስጥ ገብቶ? አልያም፥ እንዲያ ደክሞ አዘጋጅቷት ሽያጯ ጥሩ ስላልነበር፥ መፅሐፉንም ከዘመኑ ጋር ”አፍሮጋዳ“ ብሎ ንቋት ይሆናል? ወይም ሌላ ምክንያት።

የሌሎችን ሰዎች ለምን እናቃጥላለን?

1) ተቃውሞን ለመግለፅ?

ሰዎች በተፃፉ ነገሮች ላይ የተሰማቸውን ተቃውሞዎች ለመግለፅ መፅሐፍ ሲያቃጥሉ ማየት አዲስ አይደለም። ግርማም አዳፍኔን ያቃጠለው በዚሁ ተቃውሞን የመግለፅ ምክንያት መሆኑን ሲናገር ነበር።

ሆኖም ግን፥ ግርማን በዚህ ልኬት ማሰብ ለእኔ ከብዶኝ ነበር። ለተቃውሞ መፅሐፍ ማቃጠል ሰዎች ድምፃቸው አልሰማ ሲላቸው፣ “ብንታይ” በሚል ጉጉት የሚያደርጉት ነገር ነው። እንደ ግርማ ያለ፣ ከቋንቋ ቋንቋ አማርጦ መፃፍ፣ መናገርና ሀሳቡን ማስረዳት ይችላል የሚባል ሰው፣ ወይም ሀሳቡን በነፃነት ለመግለፅ በተሻለ ደረጃና ሁኔታ ላይ ያለ ሰው መፅሐፍ አቃጥሎ “ተቃውሞዬን መግለፄ ነው” ቢል ውኀ የሚያነሳ ማስረጃ ተደርጎ ላይቆጠርለት ይችላል።

በዚህ ጉዳይ ላይ አቶ በፍቃዱ ሞረዳ ሲተነትን “አንድ ሰዉ፣ አንድ ባልተስማማዉ፣ ባስከፋዉ፣ ባስነወረዉ… ጉዳይ ላይ ያለዉን ተቃዉሞ ለመግለፅ የሚወስደዉን አማራጭ ነዉ ግርማ የወሰደዉ፡፡ ይኼ ደግሞ የራሱ የግርማን ብቻ ዉሳኔ የሚጠይቅ እንጂ ለሕዝበ-ዉሳኔ አፍርሳታ የሚያስቀምጥ አይሆንም፡፡ አይደለም መፅሐፍ ፣ሰዉ ራሱን በማቃጠል ተቃዉሞዉን ይገልፃል፡፡ይህም በኢትዮጵያም ዉስጥ መከሰቱ የቅርብ ጊዜ እዉነታ ነዉ፡፡ የአርባ ምንጩን መምህር ያስታዉሷል፡፡ ….መፅሐፍን ከማቃጠል እስከ ራስንም ማቃጠል ድረስ የሚሄድ መብትን የተላበሰ ነፃ ማኅበረሰብ እስከመፍጠር የሚሄድ ነዉ፡፡” ብሎ ነበር።

እሱ ነገሩን ለማስረዳትና፣ የመፅሐፍ ቃጠሎን ለማስተባበል የወሰደው ምሳሌ በህግ አግባብ የሚሆን አይደለም። የአርባምንጩን መምህር የኔሰው ገብሬን ብንወስድ፥ በቃጠሎው ሕይወቱ ባያልፍ ኖሮ ራሱ ላይ ወንጀል በመፈፀም ቅጣት ይጠብቀው ነበር። (ይሄንን ድምዳሜዬ፥ ወዳጆች በአስተያየት ከ1949ኙ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሲሻር አብሮ ሳይቀር እንዳልቀረ ገልፀው አርመውኛል። እኔ ስፅፈው፥ ከዓመታት በፊት በሬድዮ ‘ራሱን ሊያጠፋ ሲል የተያዘው ግለሰብ ተቀጣ’ የሚል የምሳ ሰዓት ዜና መስማቴን በማስታወስ ነበር።)

2) የመቅዳት አባዜ?

ሌሎች ሰዎች ሲያደርጉት ያየነውን ነገር ሳንመረምር የመቅዳት አባዜ ውጤት ሊሆን ይችላል። ይህንንም ስናነሳ፥ መፅሐፍት በተቃጠሉ ጊዜያት በዓለም ላይ አዲስ ክስተት እንዳልሆነ የሚያስረዱን ሰዎች ብዛትም የሚለው ነገር አለው። ሰው ሲታሰር፣ ሲገደልና ሲሰደድም በዓለም ላይ አዲስ አይደለም። ታዲያ ያ ድርጊቱን ትክክል ያደርገዋል?

3) የከፋ ጥላቻ?

4) አብሮ የመታየት ጉጉት?

አንዳንድ ሰዎች፥ ሌሎችን በመደገፍ የመግነንና አብሮ ከሰውዬው ጋር የመነሳት ፍላጎት ሲያድርባቸው የእነዛን ሰዎች ስም በማጠልሸት ስም የራሳቸውን ስም አብሮ የሚያስነሳ ድርጊት ሊያደርጉ ይችላሉ።

5) የጨቋኝነትን ሚና መጫወት?

ሰዎች ሌሎችን፣ በተለይ ከስራችን ናቸው ይሰሙናል፣ አርአያቸው ነን፣ ይከተሉናል ብለው ያሰቧቸው ሰዎች ላይ አቅማቸውን ማሳየት ሲፈልጉ እንደ መፅሐፍ ማቃጠል ያሉ ድርጊቶችን ሊያደርጉ ይችላሉ።

6) የበዛ የስሜት ተጋላጭነት?

ሰዎች የበዛ ስሜታዊነት ሲያጠቃቸው እንደ መፅሐፍ ማቃጠል ያሉ ድርጊቶችን በማከናወን እርካታን ሊያገኙ ይችላሉ። ይህም፥ ብዙ ጊዜ፣ ነገሮችን እነሱ ላይ እንደተደረገባቸው (so personally) ሲቆጥሩና ሲሰማቸው የሚያደርጉት ነገር ነው።

7) በቀላሉ መበሳጨትና፣ የተዋረዱ ሆኖ መቁጠር?

በተለይ ፀሐፊው የሚፅፍበት ጉዳይ ከእኛ ጋር በቀጥታ የሚያያዝ ከሆነ፥ እኛ የምንፈልገው ካልተፃፈ በቀላሉ ቅሬታ ሊሰማን ይችላል። ይሄ በተለይ ከታሪካዊና ፖለቲካዊ ፅሁፎች ጋር ተያይዞ ሊከሰት ይችላል። በመፃፋቸው ብቻ ከመንግስት ጋር ተጋጭተው የታሰሩ ሰዎችን ማሰብ በቂ ነው።

የስነ ባህርይ ቀውስ (personality disorder) ውጤት?

8) ለራስ የሚሰጥ ግምት ብዛት እና ሰባራ በራስ መተማመን (narcissistic personality disorder)

ይሄ ሰዎች ለራሳቸው የሚሰጡት ግምት ከፍ ሲል፣ መደነቅን አጥብቀው ሲሹ፣ ለሌሎች ሰዎች ስሜት ሳይሰማቸው፣ ከንቱ በራስ መተማመንና የራስ ግምት፣ በትችቶች በቀላሉ የተጠቂነት ስሜት ሲሰማቸው የሚወስዱት እርምጃ ሊሆን ይችላል።

9) የበዛ የተጠራጣሪነት ስሜት (paranoid personality disorder)

ተጠራጣሪነት እና ሌሎች ሰዎችን በጅምላ ያለማመን ባህርይም መፅሐፍ ሊያስቃጥል ይችላል። ይሄ ከማቃጠል አልፎም፣ መቃጠሉን የሚያወግዙትን በጅምላ እስከመሰደብ፣ ሲመችም አካላዊ ጥቃት እስከማድረስ ድረስ ሊሄድ ይችላል።

10) የጥገኝነት ስሜት (dependent (asthenic) personality disorder)

ለሚያደርጉት ነገር ሁሉ የሌሎችን ሰዎች ደጋፊ ስነልቡና በመፈለግ የማነፍነፍ ውጤት እንዲህ ያሉ ወጣ ያሉ ድርጊቶችን ሊያስደርግ ይችላል። ይህም ከታእታይ ምስቅልቅል (inferiority complex) ጋር ተያይዞ ሊብራራ ይችላል።

11) የበዛ ትኩረት ፈላጊነት (histrionic personality disorder)

ሰዎች ትኩረት ሲፈልጉና የወሬ ርዕስ መሆን ሲመኙ፣ ከፀሐፊዎቹ ምላሽ ማግኘት ሲፈልጉ እንዲህ ያሉ ድርጊቶችን ሊፈፅሙ ይችላሉ።

12) የጠማሞች አድናቆት

ቪክቶር ሁጎ እንዳለው ጠማሞች ማድነቅ ሲፈልጉ ቅናትና ጥላቻ ማሳየት አንዱ መንገዳቸው ቢሆንስ? “The wicked envy and hate; it is their way of admiring. — Victor Hugo”

ሌሎች ምክንያቶችም እንደስሜታችን መጠን ሊገለፁ ይችላሉ።

የተሻሉ አዋጭ መንገዶች የሉም?

1) የማካካሻ መፅሐፍ እንዲፃፍ መጠየቅ?

“በሀይማኖት ተቋማት ዘንድ ይህ ይደረጋል። በቅርቡ አንድ የቤተክህነት ሰው “የጳጳሱ ቅሌት” ብሎ መፅሐፍ አሳተመ። ቅሌታም የተባሉት ጳጳስ ልቦለዳዊ አይደሉም። በሕይወት ያሉ ናቸው። መፅሐፉ የወጣ ሰሞን ደግሞ ጳጳሱ ከአንዳንድ የቤተክህነት ሰዎች ጋር ግጭት ውስጥ ገብተው ነበር። እናም ይህ መፅሐፍ ጳጳሱን መውገሪያ ድንጋይ ሆነ። ተሰራጭቶ ሕዝቡ እጅ ሳይገባም የመፅሐፉ አዘጋጅ ተያዘ። ከሽያጭ የተረፉትን እንዲያስረክብ ታዘዘ። ህግ ፊት ቀረበ። ከብዙ ቀናትም በኋላ “የጳጳሱ ቅሌት” አዘጋጅ “የጳጳሱ ስኬት” በሚል ርዕስ ሌላ መፅሐፍ አሳተመ። የእርቅ ደብዳቤ መሆኑ ነው።” (እንዳለጌታ ከበደ (2007) “ማዕቀብ” 2ኛ እትም፥ ተሻሽሎ የታተመ)

የማካካሻ መፅሐፍ ማስፃፍ፣ እንዲህ ባለ አምባገነንነት ሳይሆን፣ በሀሳብ ሙግት መሳካት ቢችል ምንኛ ትልቅ ስኬት ነው?

2) የራስን አንፃር ማኖር?

“ባሮጌ ቤት የሚኖረውን ሰው ተጥግቶ ቤትህ የማይረባ ነው ማለት አይገባም። ከበረቱ አጠገብ አዲስ ቤት መስራት ነው። ይህ አዲሱ ቤት ስለራሱም አዲስነት ሰለሌላውም አሮጌነት ይናገራል።….እውነት የራስዎም የውሸትም ማስረጃ ናት” (እጓለ ገብረ ዮሐንስ (1956) “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ”)

በዚህ ረገድ የተሾመ ገብረ ማርያም ቦካን (1994) “በአቶ አማኑኤል አብርሃም ዘብሔረ ቦጄ ከርከሮ ለተጻፈው “የሕይወቴ ትዝታ” የተሰጠ ማስተባበያ” መፅሐፍ መጥቀስ ይችላል። አቶ ተሾመ ማስተባበያ መፅሐፍ እስከማሳተም ድረስ ያደረሳቸው ትልቅ እውነትና የሚያስረዱት ነገር ቢኖራቸው እንደሆነ ግልፅ ነው። መፅሐፍ ባይፅፉና የአቶ አማኑኤልን ግለ ታሪክ አቃጥለው ብስጭታቸውን ገልፀው ቢሆን ኖሮስ?

እና ወዳጆች፥ ነገሮች ሲያነታርኩን ግልፅ ለማድረግና እኛም እኩል እንድንታይ ሌላውን ማጥፋትና ማቃጠል ሳይሆን፣ የእኛን ከጎን በማኖር ሰው እንዲያነፃፅር እውነቱን መርምሮ እንዲረዳ ብናደርግ የተሻለ አናተርፍም አይሆንም? ማኅበረሰብስ በተሻለ መልኩ አይቀረፅም?

እስኪ እንጨዋወት!