መፅሐፍ በተናጥልም ሆነ በጅምላ ሲቃጠል አዲስ አይደለም። የዓለሙን ነገር ትተነው ስለአገር ቤቱ ብናወራ ከአዳዲስ ርዕዮተ ዓለማት ጋር እንዲቃጠሉ፣ እንዲሸሸጉ፣ አልያም በተለያየ መልኩ እንዲባክኑ የተፈረደባቸው በርካታ መፅሐፍት እንደነበሩ/እንዳሉ ይታወቃል። የሌላውን ንዶ የራስን የመገንባት ሽሚያ ነው። ‘ያን ካነበቡብኝ ይነቁና ጉዴ ይፈላል’ ‘እቺ ባቄላ ካደረች…’ የሚል ተራ ስጋትና ብልጣብልጥነትም አያጣውም። አንዳንዴ እንዳይነፃፀሩና እንዳይበላለጡም ይፈሯል። የ‘እኔ አውቅልህ፣ እኔ እጠብቅህ’ ዓይነት ለሕዝብ ያለ ንቀት ውጤትም ሊሆን ይችላል። ብቻ ግን መፅሐፍት በተለያዩ ጊዜያት በጅምላ የእሳት ሲሳይ ሆነዋል።
በተናጥል (የአንድን ፀሐፊ መፅሐፍ፣ ለራስ የገዙትን ኮፒ ለይቶ) ማቃጠል፣ በየስርቻው ሲደረግ የኖረ ሊሆን ቢችልም፣ ከፌስቡክ መምጣት ጋር ተያይዞ በይፋ ለማየት የቻልነው ነገር ነው። እኛ ዙሪያ ላይ ሲቃጠሉ ካየናቸው መፅሐፍት መካከል፥ የመጀመሪያዋም የእኔዋ “የብርሃን ልክፍት” ትመስለኛለች። ቃጠሎውም የተከናወነው የምረቃ ፕሮግራሙ ሳይደመደም በፊት ስለነበር፣ ያላነበበውን መፅሐፍ ለማቃጠል የወሰደው እርምጃው፥ ችግሩ ከይዘቱ ጋር ሳይሆን ፀሐፊው (እኔ) ላይ በነበረው ባዶ ጥላቻ ‘ልክፍት’ መሆኑን ብዙዎች መልስ ሲሰጡት ነበር።
እኔ ያኔ መፅሐፌ ላይ ይሰጡኝ የነበሩ ገንቢ አድናቆቶችና ትችቶች በመሰብሰብ ተጠምጄ ስለነበር እንደጥሩ ማስታወቂያነት ከመቁጠር በዘለለ፣ ልብ አላልኩትም ነበር። በተሰራጩ (broadcast-ed) መፅሐፍ ቃጠሎዎች ሰንጠረዥም ብዙ ጊዜ በመቃጠል ሪከርዱን የያዘችው የእኔ “የብርሃን ልክፍት” ሳትሆን አትቀርም። 🙂 ከዚያ በኋላም በሁለት ወዳጆች ተቃጥሎ ነበር። ዘንድሮ ደግሞ 2 መፅሐፍት በይፋ መቃጠላቸውን በፎቶ ተመልክተናል። የሌሊሳ ግርማ “አፍሮጋዳ” በራሱ በሌሊሳ እና የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም “አዳፍኔ” በግርማ።
ምናልባት “የራሱ ስለሆነ” ተብሎ ሊሆን ይችላል፥ የሌሊሳ ግርማ መፅሐፍ ማቃጠል ምንም ዓይነት ትኩረት አልሳበም ነበር። የግርማ መፅሐፍ ማቃጠል ጉዳይ ግን ህዝበ ፌስቡኩን ብዙ እያነታረከ እስካሁንም ቀጥሏል። “መፅሐፍ ለምን ይቃጠላል?” ብለው ሲሟገቱ የነበሩ ሰዎች ግን የሌሊሳ ላይ ያሳዩት ቸልተኝነት የሚደገፍ አይደለም። የራሱ ቢሆንም፥ መብጠልጠል ካለበትም ድርጊቱ ነው። ሰው የገዛ ልጁን “ልጄ ስለሆነች” ብሎ እንደፈለገው ማጎሳቆልና ጥቃት መፈፀም አይችልም። እንኳን የገዛ ልጁን የገዛ ራሱም ላይ እንዲህ ቢያደርግ ድርጊቱ ወንጀል ከሆነ ወንጀል ነው።
ያም ሆነ ይህ፥ እዚህ ላይ የምንጫወተው ግን ስለተቃጠሉትና ስላቃጠሉትም አይደለም። ይልቅስ፣ ስለክስተቱ፣ ስለማቃጣሉና ስለስነልቡናዊ ምክንያቶቹ በ’በይሆናል’ መላምት ነው። ከታች በምሳሌነት የማነሳቸው፥ ነገሩን ይበልጥ ለማስረዳት ያህል ብቻ ነው። እንጂ የዚህ ፅሁፍ ዓላማ ከእለታት በአንዳንድ አርቦች እንደምናደርገው ጨዋታ ነው። (በነገራችን ላይ፥ መፅሐፍ ማቃጠል የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይም ነው። ህገ ወንጌል (the code) ከጥፋት ዱሎት ባይቀጣንም፣ ህገ ልቡናም (moral law) አለና ያንን ሳንዘነጋ ነው።)
በጅምላ ማቃጠል…
እንደሚታወቀው፣ ከዚህ ቀደም የተለያዩ ቦታዎች ላይ የእሳት እራት እንዲሆኑ የተዘመተባቸው መፅሐፍት ነበሩ። በጅምላ ስለተቃጠሉ መፅሐፍት ታታሪው ወዳጄ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ በጥናታዊ ዳሰሳው ሲያስታውሰን…
“…ቅጠሉን ገልጠን ስናይ፣ የታሪክ፣ የልቦለድና የትምህርት መጻሕፍትተከምረዋል። ‘የትንቢት ቀጠሮ’፣ ‘ሆኅተ ጥበብ’፣ ‘ፍቅር እስከ መቃብር’፣ ‘አርአያ’፣ ‘ከአፄ ልብነ ድንግል እስከ አፄ ቴዎድሮስ’። ብዙ የምናውቃቸው፣ አንብበን አስነብበን የተመሰጥንባቸው መጻሕፍት እዚህ ትንሽ የተራራ ቁልል ሠርተዋል። “ይኼ ነገር ምንድን ነው?” ብለን ተጠግተን የት/ቤቱን አስተዳደር ስንጠይቅ፣ “በእሳት ሊቃጠሉ የተዘጋጁ ናቸው” አሉን።
ደነገጥን፣ ተሳቀቅን። “ለምንድን ነው የሚቃጠሉት?” ስንል ደግሞ፥ “መጻሕፍቱ ደርግ ከሚከተለው ርዕዮተ ዓለም ጋር አብረው አይሄዱም። የሀገር አቆርቋዥና የፊውዳል ርዝራዥ አመለካከት የሰፈረባቸው ናቸው።” አለን። ….“እነ ፍቅር እስከ መቃብር፣ እነ አርአያ ሁሉ ሊቃጠሉ?” ……“የነዳጅ ጉዳይ ቸግሮን ነው እንጂ ይኼን ጊዜ በቦታው የአመድ ክምር ነበር የምታዩት። ነዳጁም ጠፍቶ ሳይሆን በየትኛው በጀት ይውጣ ብለን እየመከርንበት ነው።” አለን። (እንዳለ ጌታ ከበደ (2007) “ማዕቀብ” ገጽ፥ 204 የጋሽ ይልማ በረካ ትውስታ)
እዚሁ መፅሐፍ ላይ ደራሲው በ“ሰበር ትረካ” ምንጮቹን አጣቅሶ ሲቀጥል: “…የጥንቱ የቴሌቭዥን መምሪያ ኃላፊ አቶ ወሌ ጉርሙ በአደባባይ ላይ በሺህ የሚቆጠሩ መጻሕፍትን ያቃጠሉ የፕሬስ ነጻነት ቀበኛ ናቸው። የተቃጠሉትም የአስራተ ካሣ ስራዎች ስብስብ ናቸው። አስራተ ካሳ ሕዝቡን የመዘበሩ ቢሆኑም ከእውቅ ደራስያን ውጤቶች መካከል የእሳቸው መጻሕፍትም እንደሚገኙባቸው መዘንጋት የለበትም።… ትዝ ይለኛ በአወቅቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር የነበሩት ዶ/ር አለሜ እሸቴ ‘በሀገሪቱ ሕዝብና በሀገሪቱ ላይ የአእምሮ ረሀብ መልቀቅ ነው። መጻሕፍቱ የአድኃሪ አመለካከትን የሚያራምዱ ቢሆኑም አድኃሪ መሆናቸው ሊታወቅ የሚችለው ሊነበቡ ሲችሉ ብቻ ነው’ ሲሉ ነበር ቅሬታቸውን የገለጹት።” (አለስም፣ ጦቢያ ማነች? አዲስ ዘመን፣ ሚያዚያ 29/84)
“…በወለጋ… የኢሠፓአኮ ዋና ተጠሪ ንጉሤ ፋንታ ቀሳውስቱንና ሌሎቹን የሀይማኖት መሪዎች አስከብብቦ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን እንዲያቃጥሉ አዘዘ። ትዕዛዙን አንቀበልም ሲሉ እራሱ በርካታ መፅሐፍ ቅዱሳትን ሰብስቦ በሕዝብ ፊት አቃጠለ። መሀይምነት ነው ንጉሤ ይህን ያደረገው። በጣም የሚገርመው ግን በአሜሪካን ዩኒቨርስቲ ትምህርቱን የተከታተለውና ቀድሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተቀጣሪ የነበረው ዶ/ር ባሳዝነው ባይሳ ለምን በተደጋጋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ማቃጠል ዘመዳ ተባባሪ እንደሆነ ነው።’ (ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ፣ “የደም ዕንባ” ትርጉም ደበበ እሸቱ)
ይለናል።
በግለሰብ ደረጃ ተመርጠው ስለተቃጠሉ መፅሐፍት ምክንያት ብናነሳና ብናስብ፥ ከሞላ ጎደል የስነልቡና እና የስነ ባህርይ ውጤት ሊሆን ይችላል። በአንድም በሌላም መንገድ ትኩረት ይፈልጋሉና፥ ዓላማቸውም ከሞላ ጎደል በስነ ልቡና ጨዋታ የሚቃጠልበትን ሰው ወይም ወዳጆች ላይ ስነ ልቡናዊ ጥቃት ለመሰንዘር ይሆናል።
የራስን መፅሐፍ ማቃጠል
ከሳምንታት በፊት፥ ውዱ ደራሲ ሌሊሳ ግርማ የራሱን መፅሐፍ አቃጥሎ profile picture አድርጎት ነበር። የሆነ ዓይነት ብስጭት የወለደው ይመስላል። የተለጠፈው እኩለ ሌሊት ሲቃረብ ስለነበር ‘በሞቅታ መንፈስ ሊሆን ይችላል’ ብለን ማሰብ እንችላለን። አልያም እዚያ ‘አካባቢ የነበረ ሰው ሲጋራ ለኩሶ የጣላት ክብሪት በስህተት መፅሐፉን አቃጥላው፣ ሌሊሳም እንደ ጨዋታ ፎቶ ሲያነሳው ፎቶው አምሮት ለጠፈው’ ብለን በማለሳለስ መረዳትም እንችላለን። ከእነዚህ አንዱ ምክንያት ከሆነ፥ መቼስ ምን ይደረጋል?
ነገር ግን፥ ሆነ ብሎ አቃጥሎት ከሆነ የስነልቡና ችግር ውጤት ተደርጎ ነው የሚታሰበው። ሌሊሳ መፅሐፉን ሲያቃጥል፥ ምናልባት ዛሬ ባለበት አስተሳሰቡና ችሎታው ሲመዝነው አፍሮጋዳ ቀልሎ ተሰምቶት ይሆናል? (በነገራችን ላይ በጣም የምወደው መፅሐፍ ነው። በደንብ አለመሸጡም እንዳበሸቀኝ አለ።) “እኔ እኮ ከአፍሮጋዳ በላይ ነኝ። ምን ሆኜ ፃፍኩት?” ብሎ ተብሰክስኮ አብዮታዊ እርምጃ ወስዶባት ይሆናል? ምናልባት፥ ከራሱ ስራ ጋር ተመዝኖ የላዕላይ ምስቅልቅል (superiority complex) ውስጥ ገብቶ? አልያም፥ እንዲያ ደክሞ አዘጋጅቷት ሽያጯ ጥሩ ስላልነበር፥ መፅሐፉንም ከዘመኑ ጋር ”አፍሮጋዳ“ ብሎ ንቋት ይሆናል? ወይም ሌላ ምክንያት።
የሌሎችን ሰዎች ለምን እናቃጥላለን?
1) ተቃውሞን ለመግለፅ?
ሰዎች በተፃፉ ነገሮች ላይ የተሰማቸውን ተቃውሞዎች ለመግለፅ መፅሐፍ ሲያቃጥሉ ማየት አዲስ አይደለም። ግርማም አዳፍኔን ያቃጠለው በዚሁ ተቃውሞን የመግለፅ ምክንያት መሆኑን ሲናገር ነበር።
ሆኖም ግን፥ ግርማን በዚህ ልኬት ማሰብ ለእኔ ከብዶኝ ነበር። ለተቃውሞ መፅሐፍ ማቃጠል ሰዎች ድምፃቸው አልሰማ ሲላቸው፣ “ብንታይ” በሚል ጉጉት የሚያደርጉት ነገር ነው። እንደ ግርማ ያለ፣ ከቋንቋ ቋንቋ አማርጦ መፃፍ፣ መናገርና ሀሳቡን ማስረዳት ይችላል የሚባል ሰው፣ ወይም ሀሳቡን በነፃነት ለመግለፅ በተሻለ ደረጃና ሁኔታ ላይ ያለ ሰው መፅሐፍ አቃጥሎ “ተቃውሞዬን መግለፄ ነው” ቢል ውኀ የሚያነሳ ማስረጃ ተደርጎ ላይቆጠርለት ይችላል።
በዚህ ጉዳይ ላይ አቶ በፍቃዱ ሞረዳ ሲተነትን “አንድ ሰዉ፣ አንድ ባልተስማማዉ፣ ባስከፋዉ፣ ባስነወረዉ… ጉዳይ ላይ ያለዉን ተቃዉሞ ለመግለፅ የሚወስደዉን አማራጭ ነዉ ግርማ የወሰደዉ፡፡ ይኼ ደግሞ የራሱ የግርማን ብቻ ዉሳኔ የሚጠይቅ እንጂ ለሕዝበ-ዉሳኔ አፍርሳታ የሚያስቀምጥ አይሆንም፡፡ አይደለም መፅሐፍ ፣ሰዉ ራሱን በማቃጠል ተቃዉሞዉን ይገልፃል፡፡ይህም በኢትዮጵያም ዉስጥ መከሰቱ የቅርብ ጊዜ እዉነታ ነዉ፡፡ የአርባ ምንጩን መምህር ያስታዉሷል፡፡ ….መፅሐፍን ከማቃጠል እስከ ራስንም ማቃጠል ድረስ የሚሄድ መብትን የተላበሰ ነፃ ማኅበረሰብ እስከመፍጠር የሚሄድ ነዉ፡፡” ብሎ ነበር።
እሱ ነገሩን ለማስረዳትና፣ የመፅሐፍ ቃጠሎን ለማስተባበል የወሰደው ምሳሌ በህግ አግባብ የሚሆን አይደለም። የአርባምንጩን መምህር የኔሰው ገብሬን ብንወስድ፥ በቃጠሎው ሕይወቱ ባያልፍ ኖሮ ራሱ ላይ ወንጀል በመፈፀም ቅጣት ይጠብቀው ነበር። (ይሄንን ድምዳሜዬ፥ ወዳጆች በአስተያየት ከ1949ኙ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሲሻር አብሮ ሳይቀር እንዳልቀረ ገልፀው አርመውኛል። እኔ ስፅፈው፥ ከዓመታት በፊት በሬድዮ ‘ራሱን ሊያጠፋ ሲል የተያዘው ግለሰብ ተቀጣ’ የሚል የምሳ ሰዓት ዜና መስማቴን በማስታወስ ነበር።)
2) የመቅዳት አባዜ?
ሌሎች ሰዎች ሲያደርጉት ያየነውን ነገር ሳንመረምር የመቅዳት አባዜ ውጤት ሊሆን ይችላል። ይህንንም ስናነሳ፥ መፅሐፍት በተቃጠሉ ጊዜያት በዓለም ላይ አዲስ ክስተት እንዳልሆነ የሚያስረዱን ሰዎች ብዛትም የሚለው ነገር አለው። ሰው ሲታሰር፣ ሲገደልና ሲሰደድም በዓለም ላይ አዲስ አይደለም። ታዲያ ያ ድርጊቱን ትክክል ያደርገዋል?
3) የከፋ ጥላቻ?
4) አብሮ የመታየት ጉጉት?
አንዳንድ ሰዎች፥ ሌሎችን በመደገፍ የመግነንና አብሮ ከሰውዬው ጋር የመነሳት ፍላጎት ሲያድርባቸው የእነዛን ሰዎች ስም በማጠልሸት ስም የራሳቸውን ስም አብሮ የሚያስነሳ ድርጊት ሊያደርጉ ይችላሉ።
5) የጨቋኝነትን ሚና መጫወት?
ሰዎች ሌሎችን፣ በተለይ ከስራችን ናቸው ይሰሙናል፣ አርአያቸው ነን፣ ይከተሉናል ብለው ያሰቧቸው ሰዎች ላይ አቅማቸውን ማሳየት ሲፈልጉ እንደ መፅሐፍ ማቃጠል ያሉ ድርጊቶችን ሊያደርጉ ይችላሉ።
6) የበዛ የስሜት ተጋላጭነት?
ሰዎች የበዛ ስሜታዊነት ሲያጠቃቸው እንደ መፅሐፍ ማቃጠል ያሉ ድርጊቶችን በማከናወን እርካታን ሊያገኙ ይችላሉ። ይህም፥ ብዙ ጊዜ፣ ነገሮችን እነሱ ላይ እንደተደረገባቸው (so personally) ሲቆጥሩና ሲሰማቸው የሚያደርጉት ነገር ነው።
7) በቀላሉ መበሳጨትና፣ የተዋረዱ ሆኖ መቁጠር?
በተለይ ፀሐፊው የሚፅፍበት ጉዳይ ከእኛ ጋር በቀጥታ የሚያያዝ ከሆነ፥ እኛ የምንፈልገው ካልተፃፈ በቀላሉ ቅሬታ ሊሰማን ይችላል። ይሄ በተለይ ከታሪካዊና ፖለቲካዊ ፅሁፎች ጋር ተያይዞ ሊከሰት ይችላል። በመፃፋቸው ብቻ ከመንግስት ጋር ተጋጭተው የታሰሩ ሰዎችን ማሰብ በቂ ነው።
የስነ ባህርይ ቀውስ (personality disorder) ውጤት?
8) ለራስ የሚሰጥ ግምት ብዛት እና ሰባራ በራስ መተማመን (narcissistic personality disorder)
ይሄ ሰዎች ለራሳቸው የሚሰጡት ግምት ከፍ ሲል፣ መደነቅን አጥብቀው ሲሹ፣ ለሌሎች ሰዎች ስሜት ሳይሰማቸው፣ ከንቱ በራስ መተማመንና የራስ ግምት፣ በትችቶች በቀላሉ የተጠቂነት ስሜት ሲሰማቸው የሚወስዱት እርምጃ ሊሆን ይችላል።
9) የበዛ የተጠራጣሪነት ስሜት (paranoid personality disorder)
ተጠራጣሪነት እና ሌሎች ሰዎችን በጅምላ ያለማመን ባህርይም መፅሐፍ ሊያስቃጥል ይችላል። ይሄ ከማቃጠል አልፎም፣ መቃጠሉን የሚያወግዙትን በጅምላ እስከመሰደብ፣ ሲመችም አካላዊ ጥቃት እስከማድረስ ድረስ ሊሄድ ይችላል።
10) የጥገኝነት ስሜት (dependent (asthenic) personality disorder)
ለሚያደርጉት ነገር ሁሉ የሌሎችን ሰዎች ደጋፊ ስነልቡና በመፈለግ የማነፍነፍ ውጤት እንዲህ ያሉ ወጣ ያሉ ድርጊቶችን ሊያስደርግ ይችላል። ይህም ከታእታይ ምስቅልቅል (inferiority complex) ጋር ተያይዞ ሊብራራ ይችላል።
11) የበዛ ትኩረት ፈላጊነት (histrionic personality disorder)
ሰዎች ትኩረት ሲፈልጉና የወሬ ርዕስ መሆን ሲመኙ፣ ከፀሐፊዎቹ ምላሽ ማግኘት ሲፈልጉ እንዲህ ያሉ ድርጊቶችን ሊፈፅሙ ይችላሉ።
12) የጠማሞች አድናቆት
ቪክቶር ሁጎ እንዳለው ጠማሞች ማድነቅ ሲፈልጉ ቅናትና ጥላቻ ማሳየት አንዱ መንገዳቸው ቢሆንስ? “The wicked envy and hate; it is their way of admiring. — Victor Hugo”
ሌሎች ምክንያቶችም እንደስሜታችን መጠን ሊገለፁ ይችላሉ።
የተሻሉ አዋጭ መንገዶች የሉም?
1) የማካካሻ መፅሐፍ እንዲፃፍ መጠየቅ?
“በሀይማኖት ተቋማት ዘንድ ይህ ይደረጋል። በቅርቡ አንድ የቤተክህነት ሰው “የጳጳሱ ቅሌት” ብሎ መፅሐፍ አሳተመ። ቅሌታም የተባሉት ጳጳስ ልቦለዳዊ አይደሉም። በሕይወት ያሉ ናቸው። መፅሐፉ የወጣ ሰሞን ደግሞ ጳጳሱ ከአንዳንድ የቤተክህነት ሰዎች ጋር ግጭት ውስጥ ገብተው ነበር። እናም ይህ መፅሐፍ ጳጳሱን መውገሪያ ድንጋይ ሆነ። ተሰራጭቶ ሕዝቡ እጅ ሳይገባም የመፅሐፉ አዘጋጅ ተያዘ። ከሽያጭ የተረፉትን እንዲያስረክብ ታዘዘ። ህግ ፊት ቀረበ። ከብዙ ቀናትም በኋላ “የጳጳሱ ቅሌት” አዘጋጅ “የጳጳሱ ስኬት” በሚል ርዕስ ሌላ መፅሐፍ አሳተመ። የእርቅ ደብዳቤ መሆኑ ነው።” (እንዳለጌታ ከበደ (2007) “ማዕቀብ” 2ኛ እትም፥ ተሻሽሎ የታተመ)
የማካካሻ መፅሐፍ ማስፃፍ፣ እንዲህ ባለ አምባገነንነት ሳይሆን፣ በሀሳብ ሙግት መሳካት ቢችል ምንኛ ትልቅ ስኬት ነው?
2) የራስን አንፃር ማኖር?
“ባሮጌ ቤት የሚኖረውን ሰው ተጥግቶ ቤትህ የማይረባ ነው ማለት አይገባም። ከበረቱ አጠገብ አዲስ ቤት መስራት ነው። ይህ አዲሱ ቤት ስለራሱም አዲስነት ሰለሌላውም አሮጌነት ይናገራል።….እውነት የራስዎም የውሸትም ማስረጃ ናት” (እጓለ ገብረ ዮሐንስ (1956) “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ”)
በዚህ ረገድ የተሾመ ገብረ ማርያም ቦካን (1994) “በአቶ አማኑኤል አብርሃም ዘብሔረ ቦጄ ከርከሮ ለተጻፈው “የሕይወቴ ትዝታ” የተሰጠ ማስተባበያ” መፅሐፍ መጥቀስ ይችላል። አቶ ተሾመ ማስተባበያ መፅሐፍ እስከማሳተም ድረስ ያደረሳቸው ትልቅ እውነትና የሚያስረዱት ነገር ቢኖራቸው እንደሆነ ግልፅ ነው። መፅሐፍ ባይፅፉና የአቶ አማኑኤልን ግለ ታሪክ አቃጥለው ብስጭታቸውን ገልፀው ቢሆን ኖሮስ?
እና ወዳጆች፥ ነገሮች ሲያነታርኩን ግልፅ ለማድረግና እኛም እኩል እንድንታይ ሌላውን ማጥፋትና ማቃጠል ሳይሆን፣ የእኛን ከጎን በማኖር ሰው እንዲያነፃፅር እውነቱን መርምሮ እንዲረዳ ብናደርግ የተሻለ አናተርፍም አይሆንም? ማኅበረሰብስ በተሻለ መልኩ አይቀረፅም?
እስኪ እንጨዋወት!