ከ6 ዓመቱ የእህቴ ልጅ ጋር በስልክ እያወራን ነበር።
“ድምጽህ አይሰማም ነው የምልህ። ጮክ ማለት ትችላለህ?” አለኝ።
“አሞኛል ቤቢዬ። በግድ ነው የማወራህ… ”
“እኔን! መች ቀድመህ ነገርከኝ ታዲያ?”
“አዪ ሳልሞት አልቀርም…” (የልጅ ማባበሉን ሳልወደው አልቀረሁም 🙂 )
“እኔን አልኩህ እኮ። በቃ አሁን ትድናለህ! ቀድመህ ብትነግረኝ፥ እስካሁን ትድን ነበር።”
“እንዴት ቤቢዬ መድሃኒቱን ታውቀው ነበር እንዴ?”
“ቀድሜ እኔን ስለምልህ ይሻልህ ነበር። አሁንም እኔን ስላልኩህ ቶሎ ይሻልሃል!”
🙂
“እኔን” ማለት፥ ዋጋ የማይከፈልበት ኢትዮጵያዊ ሀኪም፤ ሌላ የትም የማይገኝ ማፅናኛና የህመም ማስታገሻ ቃል፤ “አይዞህ” የሚለው ቃልም በአፅናኝነቱና ህመም አቅላይነቱ የሚደርስበት አይኖርም። የገረመኝና የቃሉን አቅም ይበልጥ ያስተዋልኩት በእህቴ ልጅ የ“እኔን” ፈዋሽነት እምነትና፣ “እኔን” ሲለኝ፥ ህመሜን ሊያቀልልኝ እንደሚችል ባለው ልበ ሙሉነት ነው። እሱ ታሞ “እኔን” በተባለ ቅጽበት የተሰማው እፎይታም ከእምነቱ ላይ ይስተዋላል። የእርሱ የ“እኔን” አስተዋፅኦ ታማሚውን መፈወስ ላይም ራሱን የቻለ አስተዋፅኦ እንዳለውም (as it matters) ተገንዝቧል። የ“እኔን” ኃይል ላይ የልጅ የዋህነት ሲጨመርበት ደግሞ ልዩ ነው!
ማን እንደ አማርኛ!?
በተንኮል አልባ ልብ፥ ዝም ብሎ ‘ሚፈስ፣
ሁሉም ሲጨልፈው፥ በ’ድሜ ሚደፈርስ፥
ልጅነት — ውኀነት፤
ልጅነት — ንጹሕነት፤
በጊዜ ‘ሚቆሽሽ፥ ያም ያም ሲጠልቅለት።
እርጅና ተጭኖት፣ በጥም የተጎዳ፣
አልፎ ሲናፍቀው፣ ሊያገኘው ሲዳዳ፣
በትዝታ ባልዲ፣ ‘ሚታገል ሊቀዳው. . .
ጥሙን ሚቆርጥበት፣ የቀዳ ሚጠጣው፤
ልጅነት — ውኀነት።
ልጅነት — ንጹሕነት።
/ዮሐንስ ሞላ (2005) “የብርሃን ልክፍት” ገጽ 57/
☀☀☀
አዲሱን ዓመት በተለያየ ችግር፣ የኑሮ አለመመቸትና አሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ ሆናችሁ ለምትቀበሉት ወዳጆቼ ሁሉ — እኔን!
P.S. ፎቶው የጓደኛዬ ልጅ ነው።