የጊዜ መሮጥ ሁኔታ ከሰው ሰው፣ ከቦታ ቦታ የሚለያይ ቢሆንም፥ ስሜቱ ግን በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠር ነው። የጊዜ መሮጥ ስሜት፣ በተለይ ከዕድሜ መጨመር ጋር ተያይዞ ይሰማል። ዕድሜያችን ሲገፋ በአጭር ጊዜ ርቀት ውስጥ ብዙ ጉዳዮች ስለሚከናወኑ፣ ያቀድናቸውን ሁሉም ማሳካት ስለማንችል፣ ‘ጊዜው ሮጠ’ ያሰኘናል። ፍጥነቱም ከዓመት ዓመት የሚበረታና የሚጨምር ይመስላል። የምንከፍላቸው ክፍያዎችና ወጪዎቻችንም የጊዜውን መሮጥ ሊያባብሱት ይችላሉ።
በልጅነትና በጉርምስና፥ እንቅስቃሴዎችን ሁሉ ከዚያ በፊት ያልተከሰቱ፣ አዳዲስ ነበሩ። መገናኘት/መዋደድ እንጂ መለያየት ብዙም አይከሰትም። ቀናነትና ንፁህ የልጅነት የጨዋታ ስሜቶች እንጂ፥ የበረታ ክፋትና ተንኮል አይታሰብም ነበር። ለብዙ ነገር ጉጉትና መሻት ይታይብናል። በቆይታችን ውስጥ የሚከሰቱ ጉዳዮችም ብዙ አይሆኑም። ማኅበራዊ ተሳትፎዎቻችንና ኃላፊነቶቻችንም ያን ያህል አይሆኑም። በልጅነትና በጉርምስና፥ በቤተሰብ ስር ስለምንሆን፣ ለብዙ ውድቀቶቻችን እኛን የሚጨንቀን አይመስልም። ማስተባበያውና መሸሸጊያው ብዙ ነው። እዚህ ላይ ነጻነትን የመፈለግና ቁጥጥርን የመጥላት ነገር ሲደመርበት ጊዜው የተጎተተ ሊመስለን ይችል ይሆናል።
ዓመታት በተቀያየሩና ዕድሜያችን በገፋ ቁጥር ግን መሰላቸትና መጣደፍ ይመጣል። ጉዳዮችና ክስተቶችም ይደራረባሉ። ሲዋደድ የኖረ፥ ስለመጠላላት ይማራል። የሕይወት ኩነቶችን (vital events) – ማግባት፣ መውለድ፣ መሞት፣ ማግባት፣ መሰደድ… – የሚያስተናግዱ ወዳጆች ቁጥር ይጨምራል። የኩነቶቹ አካል እንድንሆንም ይጠበቅብናልና ሁሉም ጋር ለመድረስ እንኳትናለን። በሕይወታችን ውስጥ የሚያልፉ ጉዳዮች ዓይነትና ቀለማትም በዓመታት መጨመር ሂደት ውስጥ አብሮ ይጨምራል። በጉልምስና፥ ኀዘንና ደስታ፣ ድብርትና ፈንጠዝያ ይፈራረቃሉ።
ከዕድሜ መጨመር ጋር፣ የምንሄድባቸው ቦታዎችና የምናገኛቸው ሰዎችም ብዙ ናቸውና፥ ማኅበራዊ ሕይወታችንም ይለጠጣል። (በስራ ሕይወት ውስጥ ብንመለከተው፥ አንድ መስሪያ ቤት ውስጥ ብቻ ያሳለፈና፣ መስሪያ ቤት የሚቀያይር ሰው እኩል የማኅበራዊ ኃላፊነት የለባቸውም። እኩል ጊዜው አይሮጥባቸውም።) ለብዙ ነገር እንጓጓለን። ደግሞ ይሰለቸናል። ከዚያ፥ ከዓመታት በፊት የተፈፀመ ጉዳይ የትናንት ያህል ይሰማናል። ነገር ሲደራረብብን መርሳት እንጀምራለን። ለዚህም፥ የምንፈልጋቸውን ነገሮች ቅደም ተከተል የማስያዝ ፍላጎት ያድርብናል። ስለዕቅድና ስለማስታወሻ ደብተር ማሰብ እንጀምራለን። ስንዘገጃጅ ጊዜው ይነጉዳል።
ከዚህ በተጨማሪም፥ ለነገሮች የምንሰጠው ዋጋና፣ ነገሩን ከቀረበው በላይ አቅርቦ የመመልከት ሁኔታ (telescopy)፣ የጊዜን መሮጥ ስሜት ሊፈጥርብን ይችላል። ለቀድሞ ክስተቶች የምንሰጠው ዋጋ እና እነሱን የምንተርክበት መንገድ የሚፈጥረው ስሜትም (reminiscence effect) የጊዜን ሩጫ በማባባስ ረገድ የራሱ ሚና አለው። ሌላው የጊዜ መሮጥ የሚብራራበት መንገድ ደግሞ የአልበርት አንስታይን የአንፃራዊነት ሀልዮት (relativity theory) ነው። የእንቅስቃሴዎቻችን ዘርፈ ብዙነትና የበጎ አድራጎት ስራዎች ተሳትፎዎቻችንም የጊዜ መሮጥ መገለጫዎች ይሆናሉ። በተለይ ደግሞ፥ በዘመነ ቴክኖሎጂ፣ የስልክና የማኅበረሰብ ትስስር ድህረ ገፆች (social networks) አጠቃቀሞቻችን በራሳቸው የጊዜን መሮጥ ያባብሳሉ።
የምንወደውን ሰው፣ ወይም የምንጓጓለትን ጊዜ ስንጠብቅ የተጎተተ የመሰለን ጊዜ (ኮሜዲያን ተስፋዬ ካሳ ፍቅረኛውን ቀጥሮ፥ “ዛሬ 8 ሰዓት የለም እንዴ?” ያለበትን ቀልድ ያስታውሷል) ከምንወደው ሰው ጋር ስንገናኝ፣ አልያም የጓጓንለት ጉዳይ ደርሶ ሲመጣ፣ የጊዜው መሮጥ ይሰማናል። ደመወዝና ሌሎች የገቢ ክፍያዎች በዘገዩበት አጋጣሚ፣ እኛ የምንከፍላቸው ክፍያዎች (ለምሳሌ የት/ቤት ወጪ) ቶሎ ቶሎ የሚደርሱ ይመስለናል። ደመወዝ እስኪወጣ “ዘገየ” ያልነውን ጊዜ፣ ወጪው ሲደራረብብን “ሮጠ” እንለዋለን። በስራ ተጠምደን የምናሳልፈው ቀን፣ በመባከን ከምናሳልፈው ቀን ጋር ሲነፃፀርም የቸኮለ ነው። የስራ አካባቢው የሚጨንቀው ሰው፥ በስራ አካባቢው ከሚደሰት ሰው ጋር ሲነፃፀር፣ ጊዜው ይጎተትበታል።
ያም ሆነ ይህ ግን የጊዜ መሮጥ፥ ብስለት፣ ኃላፊነት፣ የሚወዱትና የሚጠብቁት ነገር መኖር፣ እና የኑሮን ጣዕም መረዳት የሚፈጥሩት ስሜት ነውና፥ ጤናማ ስሜት ነው። ዋናው ነገር የሚሮጠውን ጊዜ ማሯሯጥና ያሰብነውን ማሳካት ነው። ከዚያ በኋላ፥ ሮጠ፣ ዘገየ… ኬረዳሽ! እግራችንን ሰቅለን፥ በደበበ ሰይፉ ግጥም እናንጎራጉራለን። (ደበበ ሰይፉ (1992) “ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ (የብርሃን ፍቅር ቅጽ ፪)”)
ጊዜ በረርክ በረርክ
ጊዜ በረርክ በረርክ
ጊዜ በረርክ በረርክ
ግና ምን አተረፍክ?
ግና ምን አጎደልክ?
ሞትን አላሸነፍክ
ሕይወትን አልገደልክ።
እናንተ ጋር ግን ስሜቱ እንዴት ነው ወዳጆች?