ደስታዬን ሳንሱር አታርጉት!

አንዳንድ ህልም የሚመስሉ ቀኖች አሉ። ቅዠት የሚመስሉ ስሜቶች አሉ። የዛሬው ደስታ እንደዚያ ነው። ከስንት ውጣ ውረድ፣ ለቅሶ፣ ምልልስና ተስፋ መቁረጥ በኋላ፥ የዞን 9 ጦማርያን በሙሉ (ከዚህ ቀደም የ2 ጦማርያንና የ3 ጋዜጠኞች ክስ መቋረጡ ይታወቃል) የተከሰሱበት የሽብር ክስ ተነስቶላቸው፣ በነጻ እንዲሰናበቱ የተበየነ ሲሆን፤ በፍቃዱ ኃይሉ ብቻ፥ በወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀጽ 257 እንዲከላከል ተበይኗል።
የእሱም ቢሆን፥ የተከሰሰበት አንቀጽ ቀላል እስር የሚያስቀጣ በመሆኑ፣ እስካሁን የታሰረው ተቆጥሮ በነጻ እንደሚሰናበት እናምናለን። ጠበቃው ባቀረቡት የዋስ መብት ውሳኔ ለማግኘት ለፊታችን ረቡዕ ጥቅምት 10 ተቀጥሯል።
zone-9nersበዚህ ጉዳይ ላይ ግራ የሚገባኝ ነገር…

“ወዳጆቼ ስለተፈቱ ደስ ብሎኛል” ስል… “ተው እንጂ ጆ! ምን የሚያስፈነጥዝ ነገር አለው? ‘በነጻ ተሰናብተዋል’ ከመባሉ ደስታ ይልቅ ጥፋት ሳይገኝባቸው በግፍ የታሰሩበት ዓመት ከምናምን ይበልጥ ያንገበግባል።” የሚሉኝ ወዳጆች ነገር ነው።

ሲጀመር፥ “በነጻ ተሰናብተዋል” የሚለውን ዜና ሙሉ ስሜት ለማወቅ ነገሩን በቤተሰብነት ስሜት ለማየት መጣርን ይጠይቃል። መፍረድ ቀላል ነው። ማናችንም ከቤተሰባችን አንዱ ታስሮ ቢፈታ፥ ስለመፈታቱ እንደሰታለን እንጂ፣ መታሰር ሳይገባው ስለታሰረበት ጊዜ አንብሰከሰክም። ያ ቆም ብለን ሂሳብ ስንሰራ፣ እያደር የምንበግንበት ጉዳይ ነው።

ደግሞ ምንም ነገር ሊሆን እንደሚችል (ከሆይሆይታና status update ያለፈ ምንም ዓይነት ነገር እንደማናደርግ) በሚታወቅበት አገርና ሁኔታ “እዬዬም ሲደላ ነው” ይባላልና በመፈታታቸው ደስታን መቆጠብ፣ በመታሰራቸው ያለማዘን ውጤት ካልሆነ፥ አጉል መመጻደቅ ነው።

ደግሞ፥ ሰዎች በግፍ የታሰሩበት ዓመት የሚያንገበግበን፣ “መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ ተሰናብተዋል” የሚል ብይን ስንሰማ ነው እንጂ፣ “ይከላከሉ” ተብሎ ሲፈረድ ያን ያህል ምላሽ አናሳይም። “በይቅርታ ተፈቱ” ሲባል እንኳን ያ ስሜት አይሰማንም። ታዲያ በግፍ የታሰሩበት ዓመት ከምናምን እንዳያንገበግበን ሲባል በሀሰት ወንጀል ክስ እንዲከራከሩ መበየን ነበረበት? ከዚያ ጥፋተኝነታቸው ባልታየበት ክርክር ሊፈረድባቸው ይገባ ነበር?

ማነው ከእስክንድር ነጋ ላይ ጥፋት ሳይገኝበት በግፍ የታሰረበትን ዓመት የሚቆጥረው?

ማነው ርዕዮት ዓለሙና በቀለ ገርባ በግፍ የታሰሩበትን ዓመት የቆጠረው? (መፈታት ከነበረበት ጊዜ ባሻገር የቆዩትን ትተነው)

ማነው ተመስገን ደሳለኝ በግፍ የታሰረበትን ዓመት የሚያሰላው?

ማነው እስር ላይ ያሉና ታስረው የተፈቱ ሌሎች የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በግፍ የታሰሩበትን ዓመት የሚቆጥረው?

ማነው ከቤተሰብና ወዳጅ እስር ቤት መመላለስ የባከነውን ወጪና ጊዜ የሚያሰላው?

ማነው እስር ቤት ውስጥ የመቆየትንና እስር ቤት የመመላለስን ስነልቡናዊ ጫና የሚያሰላው?

ስሜት ሳንሱር አይደረግምና ደስታዬንም ኀዘኔንም ሳንሱር አላስደርግም። ሳዝን አዝናለሁ። ስደሰትም እደሰታለሁ። ውሸት ምን ይሰራል? – ሲታሰሩ ካዘንኩት በላቀ ሲፈቱ ደስ ብሎኛል።

ከናካቴው ጠፍንጎ “እምጷ ቀሊጥ” ቢልም ምንም እንደማላመጣ አውቀዋለሁና መፈታታቸው ያስደስተኛል። እስር ቤት ውስጥ ካለ ሰው ይልቅ ከእኛ ጋር ያለ ሰው ለምኑም ለምንም ጠቀሜታው ላቅ ያለ ነውና፥ መፈታታቸው ያስደስተኛል። የቤተሰቦቻቸውንና ጓደኞቻቸውን ስቃይና ሰቀቀን አውቃለሁና፥ መፈታታቸው ያስደስተኛል። ወጣትነታቸው በከንቱ ሲማገድ ማየት ያመኛልና፥ መፈታታቸው ያስደስተኛል። ለምናፍቀው እንደሚገባን የመኖርና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት መከበር ማስያዣ ይሆን ዘንድ፥ የማንም ሰው ስጋና ኅሊና እስር ላይ እንዲቆይ አልመኝም።

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን፥ በከንቱ የባከኑ ጊዜያት ሳይሰሙኝና ሳያንገበግቡኝ ቀርተው አይደለም። የመንግስትንም ፀባይ አጥቼው አይደለም። ነገም ሌላው ታስሮ ተጨምሮ ‘free’ እያልን ብዙ ጊዜ እንደምናባክን ይሰማኛል። (እንደውም ቅድም ለተስፋለም “ፍቅረኛ ሆኑብኝ እኮ” ብዬው ስንስቅ ነበር። እንደ ፍቅረኛ ባንድ ቃል ሰማይን ከነጉዝጓዙ ይደፋብኛል። ደግሞ ሲፈልጉ ባንድ ቃል ከሰማይ ከፍ አድርገው ያስፈነጥዘኛል። ሳቄንም እንባዬንም መቆጣጠር እንደተሳካላቸው መግለጽ እችላለሁ። የአቅመ ቢስነት ውጤትና ኗሪነቴ ያስገኘልኝ ‘ትሩፋት’ ነውና ቢያበግነኝም ምንም አላመጣምና ለምጄዋለሁ።

በተረፈው ግን፥ ደስታዬን መሸሸግ አልችልም። ከዚህ ሁሉ ውጣ ውረድና ሰቀቀን በኋላ ጓደኞቼ ስለተፈቱልኝ በጣም ደስ ብሎኛል። የበፍቄንም ጉዳይ ቸር ወሬ እንደምንሰማ አምናለሁና በጉጉት እጠብቃለሁ። ደስታችን ሙሉ የሚሆነው ግን፥ በግፍ የታሰሩ ሁሉ ሲፈቱ ነው። ስለነሱ ዘወትር እንማልዳለን!

ለቤተሰብ፣ ወዳጅ ዘመድና ጓደኛ ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s