ወፍ በረራዊ ትውስታ: ነጻነት ወፍትህ!

ነጻነት የልጅነት ጓደኛዬ ነበረች። ነጻነት ዓለማየሁ። ክፉና ደግ አልነበረንም እንጂ እንዋደድ ነበር። ማለቴ በተለየ መልኩ እንዋደድ ነበር። አለ አይደል፥ የልጅነት መዋደድ? …ለምሳሌ፥ ሰው ሳይሞት ለመጀመሪያ ጊዜ ያሳዘነችኝ ነጺ ነች። ያኔ፥ “አይዞኝ” በትምህርትና በልምድ የሚባል ሳይሆን፥ ሰው አንጀት ሲበላ ተፈጥሮ ራሷ፥ ለሀበሾች ብቻ ደብቃ የሰጠችው፥ የሁለት እዮሽ አንጀት አርስ፥ የማፅናኛ ቃል እንደሆነ ነበር ያመንኩት። (ራሴን “አይዞሽ” ስል ማግኘቴን እንጂ፥ ከዚያ በፊት ቃሉን መስማቴን አላስታውስም።) የሆነ ገጸ ባህርይ ነገር ነበረች። ታሪካም የሆነች ህፃን። እሰማ እሰማና፥ አያት አያትና “አይዞሽ” እላታለሁ።

እህህ… ለምሳሌ፥ ስኳር ግዢ ተብላ ተልካ እንደሆነ፥ ስኳሩን ለእኔ ሳታስቀምስ ቤቷ አትሄድም ነበር። ስኳርነቱን የሚረጋገጠው በምላሴ ማህተም ነበር። “ምን ነካሽ?” ቢሏት፥ “እሱ ሳይቀምሰውና ምላሱን ወጣ ገባ እያረገ፣ ከንፈሮቹን እያጋጨ በምራቁ ሲያወራርደው ካልተየ፥ ስኳር ምኑን ስኳር ሆነ?” ሳትል ትቀር ነበር ብላችሁ? ብቻ እንዴትም ያህል ቸኩላ ቢሆን፥ ደጄን ሳትሳለም፣ እኔም እንዴትም ባለ ውክቢያ ውስጥ ደጇን ሳንሳለም አንተላለፍም። አለክልካ ትመጣና፥ “ቸኩያለሁ” ብላኝ ትሄዳለች።

ያኔ፥ እግር እንደምንም ከቤት ይውጣ እንጂ፥ ሳንተያይ ቤት ቤታችን እንደማንገባ፥ ጨረቃና ፀሐይ ቋሚ ምስክሮች ናቸው። እንዳይረሱት አድርገን ተልጠንባቸዋል። …ሰበብ ፈልገን የተገናኘንባቸው ጊዜያትም አይቆጠሩም። በቃ ተገናኝቶ ዝም፣ ፍጥጥ ነው። ድንገት የምታወራልኝ ነገር ካለ፥ ሰምቶ ሰምቶ “አይዞኝ” ማለት ነው። …በልጅነት ሰው ባይጠላላም፥ የእኛ መዋደድ ብርቱ እንደነበር ከርሞ ነው ያወቅኹት። ነፍስ ስዘራ ነው የገባኝ። ሰው ሳይ እርሷን ሳስታውስ ነው ክው የምለው። …እንደ ልጅ እንኳን “እወድሻለሁ” እንዳልላት፥ ልጅነታችንም ፀሐይ እየበላው፣ እየገፈፈ፣ ቀለሙን በመያዝ እና በመልቀቅ መካከል፥ ሁለቱም እያፈጠጡ፥ የምንምታታበት ወቅት ነበር።

ክፍለ ሀገር ሄደች….

(ሆኖም ግን፥ ያኔ የነበረኝን ጣፋጭ የልጅነት ስሜት፣ በሌላ ተርጉሜ አላራክሰውም። ፍሩድን ስላልሆንኩ እንደዛ ያለ ትንታኔ ለመስጠት አስቤም አላውቅ።) ታዲያ ምን አልኩ? ሳድግና ግጥም መጻፍ ስችል ሁለት ረጃጅም ግጥሞች አልፃፍኩላትም? 🙂

የጂጂን፥

ሸጋው ያንተ ፍቅር፥ የህልም እንጀራ ነው
ሆዴ ጠግቦ አልበላም፥ ዘንድሮም ረኀብ ነው።

ስሰማ ነጻነት እንጂ ሌላ ማን ትዝ አለኝ?
.
.

ባልተያያዘ ጨዋታ….

ፍትህ የምትባል ልጅ ነበረች። ት/ቤት ነው የማውቃት። አይኑካ ነበረች። ያይኑካ ነገር… ስሟን እንኳን ልወቅ ብዬ ሳጣራ ይገርማል። ማለቴ፥ ሰው ፍትህ ሲባል ስሰማ እሷ ላይ ነበር የመጀመሪያው። የሆነች ቀንበጥዬ ልጅ ነበረች። ደግሞ ጠይም ናት። (ፍቅር መልኩ ምንድን ነው ብባል፥ “ጠይም” እል ይመስለኝ ድረስ፥ i’m crazy about it 🙂 …no offence ቀያይ ወዳጆች፥ ደማችሁ ጠይም ነውና 😉 ) መቼስ መግባባት አይቀር ተግባባን። እንዲሁ ዝም ብሎ መግባባት። ወዲህ ወዲያ የሌለው መግባባት። ሁለት ሶስት ሳምንት ሲቆይ፥ ክራሹም እልም አለ። (እናቱ ነች!)

“ክራሽ ነበረኝ እኮ” ሳልላት መራራቃችን ግን ሳስበው ይነደኛል።

እና የአስቱካ…

የሰው ሰው ወድጄ፥ ያውም የተውሶ
የልቤን ሳልነግረው ሄደ ተመልሶ።

ስሰማ፥ ካለሷ ዐይኑካ ያልነበረ ይመስል፥ ፍትህ ስንቴ ትዝ አለችኝ?
.
.
.
እስኪ ባካችሁ፥ ነፃነትንና ፍትህን ካገኛችኋቸው፥ “አንቺ የልጅነት ንፁህ ወዳጁ… አንቺ ዐይኑካው… ዮሐንስ ሞላ ሰላም ብሏችኋል።” በሉልኝ በየተራው።

ሰላም!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s