በረኀቡ ለሚሰቃዩና የመራብ ስጋት ላለባቸው ወገኖች ለመድረስ በዋናነት የሚያስፈልገው ገንዘብ ሳይሆን ቅንነት ነው። የመንግስት ቅንነት ነው። ቅንነቱ ካለ ትክክለኛውን የተረጂዎች ቁጥር ተገንዝቦ ለነዋሪው ማስገንዘብ፣ ካዝናን መበርበር፣ ሲያንስ እና ቸግሮኛል ሲል ደግሞ ሕዝቡን ማስተባበር ይችላል። ቅንነቱ ከሌለ ግን በጎ ሰዎች ያሰባሰቡትን ገንዘብ ማድረሻ መንገዱም ክፍት ሳይሆን ቀርቶ መንገድ ላይ ሊቀርም ይችላል።
አሁን በየቅያሱ የሚተዋወቁ የተለያዩ የባንክ ቁጥሮችን ሳይም ግራ መጋባቴ አልቀረም። እዚህም እዚያም እንዲህ ያለ የገንዘብ ማሰባሰብ ከሚደረግ ይልቅ ማዕከላዊ (centralized) የእርዳታ ማሰባሰቢያ መንገድ ቢመቻች ሁላችንም እንረባረብ ዘንድ ቀላል እና ቀልጣፋ ይሆን ነበር። ምናልባት ህጋዊ ፈቃድ ስላላቸውም፥ መንግስት ይህንን የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር የማያዘጋጅ ከሆነ ወይም እስኪያዘጋጅ ድረስ፣ ከዚህ ቀደም ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የበጎ አድራጎት ማኅበራት ቢሳተፉ ጥሩ ይሆናል።
አሳማኝ እቅድና የስራ መስመር ከተዘረጋ፥ ገንዘብ መሰብሰብ ሁሌም ቀላል ነገር ስለሚሆን የመጨረሻ ድርጊት ነው መሆን ያለበት ብዬ አስባለሁ። ስለዚህ፥ ቢቻል እንደ ቀዳሚ ተግባር እቅዱን እና የስራ መስመሩን መዘርጋቱ ላይ ቢተኮር የምናደርገው እያንዳንዱ ድጋፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ይሆናል። (ለምሳሌ፥ እንደ ቀላል ማሳያ ብንመለከተው፣ በምግብ እጥረት ለተጎዱ ህጻናት የሚሰጥ በኒዩትሪሽን የበለጸገ ፈጣን ምግብ፥ ፕለምፒነትና ሌሎች የእርዳታ ምግቦች፥ በመጭበርበር ወጥተው ካልሆነ በስቀር ላልተፈቀደላቸው ድርጅቶች አይሸጡም። ወይስ ያው ስንዴ ነው የሚደርስላቸው? ምን ያህል? እሱስ የት ተፈጭቶ፣ በምን ተቦክቶና በምን ተበስሎ ነው መፍትሄ የሚሆነው?)
ምናልባት አሁን የሚተዋወቁት የባንክ ቁጥሮች እንዲህ ያለ ቅድመ ገንዘብ ስብሰባ እቅድ ነድፈው ይሁን፣ ገንዘቡ ይገኝ እንጂ እንደሚሆን እናደርገዋለን ብለው ባላውቅም፥ ላሳዩት ቅንነት፣ ለጥረታቸውና ኃላፊነቱን በመውሰዳቸው ሊመሰገኑ ይገባል።
① ዋልድባ ሩቁ፥ ወጣቶች ተሰብስበው እሳት ሊያጠፉ ሲሄዱ ተባረሩ የተባሉት ይቅር፥ እዚህ ቅርቡ ፒያሳ ጣይቱ ሆቴል እሳት የተነሳ ጊዜ ለማጥፋት የሚሞክረውን ሰው የማባረር ነገር ነበር።
② የዛሬ ሁለት ዓመት የሳውዲአረቢያን ግፍ በመቃወም የወጣውን ወጣት የእኛ አገር ፌደራሎች ምን ዓይነት ምላሽ ሰጥተውት እንደነበርም አይረሳንም።
③ የዛሬ 4 ዓመት፥ ፌስቡክ ላይ “ገበታ ለወገን” የሚል የበጎ አሳቢ ወጣቶች ቡድን ተከስቶ የነበረውን የምግብ እጥረት ችግር ለማገዝ፥ ያሰባሰበውን ገንዘብ ለተረጂዎቹ ለማድረስም ሆነ፣ እዚህ ለሚመለከታቸው አካላት ለማስረከብ ችግር ሆኖበት እንደነበርም እናስታውሳለን።
ሌላም ብዙ ነገሮችን ማስታወስ እንችላለን። እና አሁን የሚደረጉ ጥረቶችም ቢሆኑ ካለመንግስት ቅንነትና በጎ ማስተባበር ከቁጭት በቀር ምንም መፈየድ የሚችሉ አይሆኑምና በዚህ ረገድ የሚመለከታቸው አካላት ቢያስቡበት ጥሩ ይሆናል። አሁንም እላለሁ፥ ችግሩን ለመቅረፍና መፍትሄ ለማምጣት ገንዘብ ከመሰብሰብ በፊት መንግስት በቅንነት፣ ቀልቡን መሰብሰብና የታሰቡ በጎ ዓላማዎች እንዲሳኩ ለማገዝ መፍቀድ አለበት።
የምር የምሩን እናውራ ከተባለም፥ አገሪቱ ላይ የተከሰተው የምግብ እጥረት እንጂ የገንዘብ እጥረት አይመስልም። ገንዘቡ ባንድም በሌላም መልኩ መንግስት እጅ ላይ አለ። ያለውን ገንዘብ በቅንነት ማስተዳደርና በአግባቡ መመደብ ችግሩን ያሻሽለዋል።
ማግስቱ
መቼም ከመልካም አስተዳደር ችግር ባሻገር የረኀቡ ዋዜማ የዝናብ እጥረት እንደነበረ ሁሉ፥ የረሀቡ ማግስትም የስነ ምግብ ስርዓት መዛባት (malnutrition) ይሆናልና፥ የሞተው ሞቶ የተረፈው ተርፎ፣ የጭንቅ ረኀቡ ጋብ ብሎ ሰማይ ሲያስገመግም፣ ደመና ተገላልጦ ዝናብ ማካፋትና የሰው ፊት እኩል መፍካት ሲጀምር፤…
ለቁመት የሚመጥን ክብደት የሌላቸው (wasted)፣ ለእድሜ የሚመጥን ቁመት የሌላቸው የአካልም የአእምሮም እድገታቸው የተጉላላ ቀንጨራ (stunted) ህጻናት፣ እንዲሁም አቅመ ቢስና ለቁመታቸው የማይመጥን ክብደት የሚኖራቸው (underweight) ህጻናትና ጎልማሶች መብዛታቸው አይቀርም። ትኩሱ ለቅሶ የቀደመውን እንደሚሸፍን ሆኖ እንጂ፥ አሁንም አሉ። እንግዲህ እነሱው ናቸው የድርቅ ትራፊ በሬዎችን ጠምደው ለምርት ደፋ ቀና የሚሉት።
በተለይ የእናቶችና የህጻናቱ ጉዳት ለትውልድ የሚያሳድረው ችግርም አያጣም። ያ የተለመደው እና መደበኛው የምግብ ድጋፍ የሚጠናቀርበት ወቅት ይሆናል። (በእርግጥ፥ የማስተባበሩ ነገር በጥንቃቄ ቢከወን ዛሬ ላይ የሚደረጉ የምግብና የመድኃኒት ድጋፎችን በንጥረ ምግቦች የበለጸጉ ማድረግ የነገውን ጉዳት መጠን ሳይቀንሰው አይቀርም።)
በከፍተኛ የምግብ እጥረት ታመው ለሚማቅቁ ሰዎች ማከሚያ የሚሆኑ በንጥረ ነገሮች የበለጸጉ (nutritious) ምግቦች ለማንም እንዳይሸጡ የሚከለከለው፥ ያልባሰባቸው ሰዎች መግዛት ስለቻሉ ብቻ እንዳይጠቀሙት ለመከላከል ነው። እንዲህም ሆኖ፥ በተለያዩ ሱቆች ውስጥ የእርዳታ ምግቦችን ገዝተን ተጠቅመን እናውቃለን። በአንድ ሰሞን የሆይ ሆይታ ዘመቻ የተቀጡ ነጋዴዎችም ነበሩ። (ለምሳሌ usa የምግብ ዘይትን ቤቱ ውስጥ ተጠቅሞ የማያውቅ ማነው?)
ይህ በሁለት መልኩ ይከናወናል። አንደኛው የተጎጂዎቹ ግንዛቤ ማነስ ጉዳይ ነው። ከለመዱት እንጀራና አምባሻ ላለመውጣት፣ የሚሰጣቸውን የበለጸገ ምግብ ገበያ አውጥቶ ሸጦ የለመዱትን ምግብ ለመግዛት የመጣርና ገንዘብ ለመያዝ የመፈለግ ነገር ይታያል። ያለመማራቸው ውጤት ነውና አንፈርድባቸውም። ሌላውና አሸማቃቂው ደግሞ፥ ከተራድኦ ድርጅቶች ውስጥ በግፍ ተሰርቆ/ተጭበርብሮ ወይም፥ እርዳታ ቦታው ጋር ባሉ አስተናባሪዎች ተሸቅቦ ወጥቶ፣ ገንዘብ መሰብሰቢያ ይደረጋል። ይህም ለፍርድ አይመችም። ይልቅስ ልብ ሰብሮ አንገት ያስደፋል።
እንግዲህ የመንግስት ቅንነት ጉዳይ ሲታሰብ ነገሩ እንዲህ አርቆ ማሰብ፥ ደግሞ ዞር ብሎ ከስሩ መፈተሽ ያስፈልጋል። በሌሎች ቦታዎች ያሉ የማጭበርበር እና የሸፍጥ ተግባራት፥ አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ጋር መከሰት ያለባቸው አይመስለኝም። መቼም አንሙት እንጂ፥ ትርፍ ብር ስላለን ትርፍ መብላት አንችልምና የተራቡትን ስናስብ የራሳችንን የመስገብገብ ጉዳይም ቅድመ ግምት ውስጥ መክተት ያስፈልጋል።