‘ከሰማያዊ ፓርቲ ተባረሩ’ ስለተባሉት…

ነገረ ኢትዮጵያ / Negere Ethiopia ላይ ያገኘነው መረጃ እንዲህ ይላል…..
 
የሰማያዊ ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ በአራት አባላቱ ላይ የብሄራዊ ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ ያስተላለፈውን ከፓርቲው የማሰናበት ውሳኔ እንደማይቀበለው አስታወቀ፡፡
 
የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ዛሬ ጥር 9/2008 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ባካሄደው ስብሰባ አቶ ዮናታን ተስፋየ፣ አቶ እያስጴድ ተስፋየ፣ አቶ ዮናስ ከድር እና አቶ ጋሻነህ ላቀ ላይ የተላለፈውን ውሳኔውንም ሆነ ሂደቱን እንዳልተቀበለውና ውሳኔውም በሰማያዊ ደንብ መሰረት ተግባራዊ እንደማይሆን፣ ተባረሩ የተባሉት አባላትም በሙሉ ኃላፊነታቸው እንደሚቀጥሉ በሙሉ ድምጽ መወሰኑን የሰማያዊ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
 
‹‹የተላለፈው ውሳኔ የሰማያዊን መሰረታዊ ሀሳቦችና እምነቶች፣ ማለትም ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትና የግለሰብን ነጻነት የተጋፋ ስለሆነ ተቀባይነት የለውም›› ብለዋል ሊቀመንበሩ፡፡
 
የክስ አቀረራረቡም ሆነ የውሳኔ አሰጣጡ በሰማያዊ ደንብ መሰረት ምላዕተ-ጉባኤ ሳይሟላና ቃለ ጉባኤ ሳይፈረም የተሰጠ ውሳኔ በመሆኑ ውሳኔው ተቀባይነት የለውም ሲል ስራ አስፈጻሚው በሙሉ ድምጽ መወሰኑን ኢ/ር ይልቃል አስረድተዋል፡፡
———-
1. ይህ በእንዲህ እንዳለ፥ መግለጫው አሁንም የተሟላ ለመባል የሚያስችል አይመስለኝም።
 
2. “የብሄራዊ ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ”ው በሰማያዊ ፓርቲ ደንብ መሰረት፣ ጉባኤው ሳይሟላ እና ቃለ ጉባኤ ሳይፈረም ውሳኔ ስለመስጠቱ ምንም ዓይነት ተግሳጽ አይደርስበትም ማለት ነው?
 
3. 2ኛው ላይ ያለውን ጥያቄ መሰንዘሬ፥ ቀድሞ የተላለፈው ውሳኔ፥ “ጥፋት” የተባሉ ነገሮችን ዘርዝሮ የአቃቤ ህግ ምስክርነት ሰነድ ያዘጋጀ ስለሚመስል ነው።
 
4. ይህ በእንዲህ እንዳለ፥ ቅዳሜ ለወጣ ጋዜጣ እስከዛሬ ከሰዓት መጠበቅ ነበረባቸው?
 
ስህተት የትም አይጠፋም። የስህተቶቹን ደረጃ ስለመቀነስ መምከር ግን ያስፈልጋል። አሁንም ያልጠሩ ነገሮች አሉ። “አለባብሰው ቢያርሱ ባረም ይመለሱ” ይባላልና፥ አባላቱ በቅንነት እና በማስተዋል ቢመካከሩ መልካም ይሆናል።
 

የ“መባ” ፊልም አፍራሽ ስጦታዎች


12435678_884297928357908_2144729906_nመባ ፊልሙ

“መባ” የ“ረቡኒ”ዋ ቅድስት ይልማ ፊልም መሆኑን በሰማሁ ቅጽበት ነበር የማይበትን ቀን ቆርጬ ሲኒማ የተገኘሁት። “ረቡኒ” ላይ ካሳየችው ጥሩ ነገር አንጻር፥ ‘መባ ላይ ምን አምጥታ ይሆን?’ ከሚል ከፍተኛ ጉጉትና ጥበቃ ጋር ነበር ጀምሬ የጨረስኩት። ሆኖም ግን፥ እንደተለመዱት ‘ፊልሞቻችን’ ሆኖ ነው ያገኘሁት። የተፈረፈሩ የቴክኒክ ብቃቶችን እዚህና እዚያ፥ በየፊልሙ ሊያጋጥመን እንደሚችል ሁሉ፥ መባም የራሱን ጥሩ ነገሮች አያጣም። የመጠበቅ (expectation) ጣጣም ተጨምሮበት፣ ፊልሙ ይዞኝ እንዳልቆየና እንዳሰለቸኝ ልግለጽና፥ ከዋናው ጉዳዬ ጋር ልቀራረብ።

መባ (ዋና ገጸ ባህርይው)

መባ የህክምና ዶ/ር ነው። ሲኖር ሲኖር… በደረሰበት የአእምሮ ህመም ምክንያት ወደ ቤተሳይዳ የአእምሮ ህክምና ሆስፒታል ሄዶ ታክሞ፣ አገግሞ ወጥቶ እንደነበረ፥ ያልተተረከው የጀርባ ታሪኩ ያወሳል። የሞያም ነገር ተጨምሮበት፥ ሌሎች ታማሚዎችን በመርዳት የተሰማራ፣ የሰው ህመም የሚያመው ትሁት ጎልማሳ ነው። መባ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የሚዘምርለት ደጋፊ ባለሞያ ነው። ለታካሚዎቹ “መባ ሊመለስ ነው።” የሚለው ወሬ በራሱ ሰርግና ምላሽ ሆኖላቸው በዝማሬና በሆታ የጠበቁት ‘መሪ’ ነው። ከነበሩበት ባርነት ነጻ እንዲያወጣቸው ተስፋ የጣሉበት ‘መሲህ’፤ ዶ/ር መባ!

ከተመለሰ በኋላ፥ “መጣ… መጣ…” ተብሎ የተደነከረለት፣ ሲያዩት ብቻ እግሮቹ ስር ወድቀው የሚታዘዙለት ዓይነት ነው። በስሙ የተቀመሩ ዝማሬዎችን በኅብረት ያቀነቅኑለታል። በመምጣቱ ተስፋቸው የለመለመ ታካሚዎች አሉ። በወዳጁ በ30 ብር አልተሸጠም እንጂ፣ ‘ስቀለው ስቀለው’ ተብሎ ቀራንዮ አደባባይ አልዋለም እንጂ፥ ዶ/ር መባን ለ“መባ” ፊልም እንደ ኢየሱስ ነው የተሳለው ብንል ማጋነን አይሆንም። አስተምህሮዎቹም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃና ያላቸው ናቸው። ሕይወቱ ካለፈ በኋላም ራዕይው በደንብ ተዘክሮ፥ ታካሚዎቹን ከህክምና ተቋሙ ባንድ ጊዜ የማስወጣት (deinstitutionalization) ተቋማዊ እርምጃን አስወስዷል። ፊልሙ ሲገባደድም፥ አብዛኛውን የስነልቡና ሀኪም ትወክላለች የማታስብለው ዶ/ር ቤዛ በተራዋ ታካሚ ሆና ተቋሙ ውስጥ ስትታከምና፣ የዶ/ር መባ መንፈስ ሲንከባከባት ይታያል።

ሰዎች ቱግ ብለው ሲናገሩት ዶ/ር መባ በትህትና ሰባብሮ ይመልሳቸዋል። አጠገቡ ያለ ታማሚ ጫማ ክሩ ተፈትቶ ካየ፥ ዝቅ ብሎ ያስርለታል። የሆስፒታሉ መደበኛ ሀኪሞች ታካሚዎችን ሲናገሩ ቁጣ የተቀላቀለበት ከሆነ፥ እርሱ ቆም ብሎ ያስረዳላቸዋል። ታማሚን “ትንሽ ቀን እኔ ጋር ትቆይና ልያት” (ምህረትን) እስከማለት የሚደርስ ጥንካሬም አለው። ሆኖም ግን መባ አገጋሚ ነው። በዚህ የተነሳ ወይም በልበ-ስሱነቱ ሊሆን ይችላል፥ ታካሚዎቹ የቀድሞ ታሪካቸውን ሲናገሩ ሆዱ ይንቦጫቦጫል። ጫንቃው ህመማቸውን መሸከም ከብዶት ይንገዳገዳል። ሊረዳቸው ቁጭ ብሎም እርዳታ ያሻዋል። ከዚህ ባለፈ ሌላ የሚረዳት ታካሚ (ምህረት)፥ ከእርሱ ጋር የፍቅር የሚመስል ግንኙነት ለመጀመር እንደተወሰወሰች በሚመስል መልኩ ስትቀርበው፥ እርሷን ለመጠበቅ ያህል እንኳን አይጠብቃትም። – “ተዏት ከኔ ጋር” ይላል እንጂ። ‘እርሱም ልቡ ነገር ቢኖር ነው’ እንዳይባል፥ አሳሳሉ አያስገምተውም።  እንደ መልከጸዴቅ ነው!

ገጸባህርይ አሳሳልና መቼት

የአእምሮ ታማሚዎቹን የበዛ ጅልና መሳቂያ አድርጎ በተለመደው መልኩ የመሳል ነገር አለ። ውሎአቸው ፍጹም እርጋታ የራቀው፣ በነውጥ የተሞላ፣ እና ስለህመማቸውና ሀኪሞቻቸው በማውራት ብቻ የተሞላ አድርጎ ይስላል። ይሄ በቅርብ ከሚታየው ነባራዊ ሁኔታ የራቀ ከመሆኑ ባሻገር፥ ኅብረተሰቡ ለአእምሮ ህክምና ጣቢያዎችና ታማሚዎቹ ያለውን አመለካከት የሚያጠለሽና፣ መገለልን ሊሰብክ የሚችል ዓይነት ነው። ስፖርት ሲሰሩ፥ እንደ ህጻን ከቀ እስከ ቆ፥ ምልክቶቹን በሰውነታቸው ይሰራሉ። ምናልባት “መሳቂያ ይሁን” ተብሎ የገባ ነገር ይሆናል እንጂ፥ ይሄ ለህጻናት ወይም ለተለዩ የአእምሮ ታማሚዎች እንጂ፣ ለግቢ ሙሉ ታማሚ የማይመስል ነገር ነው። ግቢው እግርጌ አካባቢ፥ ሊያስዋኝ የሚችል የተኛ ኩሬ አለ። ምናልባት ምህረት ከመባ ጋር እንዳትገናኝ በተከለከለች ጊዜ፥ እንድትገባበትና ሌሎቹ ታካሚዎች ተሯሩጠው ገብተው እንዲያወጧት ብቻ የተመረጠ ቦታ ይመስላል። ደግሞም ውኀው ለፊልሙ ትዕይንት (scene) ተጨማሪ ግብአት ሊሆን ይችላል፥ የአእምሮ ህክምና ተቋም ውኀ ያለበት ቦታ ላይ ለመገንባት ግን ወይ ግድየለሽ አስተዳደር፣ አልያም የፊልም ባለሞያ መሆንን ብቻ የሚጠይቅ ይሆናል።

ፊልሙ የሚያቀነቅነው የህክምናን ዘዴ መቀየርና፣ ከ50 ዓመታት በፊት የነበረን የጽኑ አእምሮ ህሙማን ማቆያ ተቋማት የማፍረስ ፖሊሲ ዙሪያ ቢሆንም፥ ፊልሙ ላይ ምንም የጊዜ መቁጠሪያ ዓ/ም ስላልተጠቀሰ (እንደ “ከ40 ዓመት በፊት” ዓይነት) ፊልሙን በአሁን ጊዜነት ሲመዘን ጎዶሎ ያደርገዋል። ያኔ የነበረውን እንቅስቃሴ ማሳየት ነው የፈለገው እንዳይባልም፥ ሁኔታውን በሚመስል መልኩ አልቀረጸውም። ለምሳሌ፥ የጽኑ አእምሮ ታማሚዎቹ ድምጾች የታፈኑ ጩኸቶች ስለሚሆኑ እርስ በርስ በቡድን መዋልን ላንጠብቅ እንችላለን። የሚኖሩበት ሁኔታም ያኔ ችግር ተብሎ እንደተነሳው የተፋፈገ አይደለም። ምናልባት፥ እንደ በጥፊ መማታት እና ጆሮ አስይዞ መቅጣት ዓይነት የአካላዊ ጥቃቶች ሲፈጸሙ ማሳየቱ ከያኔው ወቅት ጋር ያቀራርበው ይሆናል። ሆኖም ግን፥ በዚህ አገርና ዘመን የአእምሮ ህክምና ተቋማት የሚደረግ አይደለምና ላሉን ጥቂት ተቋማትና ባለሞያዎች ክብረ-ነክ ሊሆን ይችላል። ችግሩ ኢ-ልብወለዳዊ ሆኖ እንደሚፈጸም የተደረሰበት ነው ከተባለም፥ የሰብአዊ መብት ጥሰት ነውና በወንጀል ዶሴ እንጂ በፊልም ጽሁፍ አይደለም መታየት ያለበት።

በነገራችን ላይ… “መባቅጂ (copy) ወይስ ኦርጂናል?

‘መባ’ ብዙ ነገሩ ከቶም ሻድያክ “ፓች አዳምስ” ጋር ይመሳሰላል። ይሄ ሆነ ተብሎም፣ አጋጣሚም ሊሆን ይችላል። ሆኖም ግን ተወዳጁ “ረቡኒ”ም ከ’ስዊት ኖቬምበር’ ጋር መመሳሰሉንና በዚህ የተነሳ ብዙ ተብሎ እንደነበርም ይታወሳል። ከፊልም ላይ ቅመሞችን (elements) ወስዶ፥ የራስ ታሪክ ላይ መዝራትም ሆነ፤ ከታሪኩ ጨልፎ፥ የራስ ቅመሞችን (elements) መቀየር ሁለቱም ጥበብ ቢሆኑም፥ ቅጂ ቅጂ ነው። ከሰው ፍርድ ቢሸሽም፣ ከኅሊና አያመልጥም። ቅድስት ግን፥ ታህሳስ 18/2008 ላይ ከታዲያስ አዲስ ጋር ባደረገችው ቆይታ ስለኦርጂናልነቱ ተጠይቃ፥ “ጥሩ ፊልም በተሰራ ቁጥር ኮፒ ነው ባይባል ደስ ይለኛል። ኮፒ ከሆነ ይታወቃል። …ኮፒ ነው መባል የጥሩ ስራ መገለጫ እየሆነ መጥቷል።” ስላለች እንተወው።

የጽኑ አእምሮ ማቆያ ተቋማት የማፍረስ ፖሊሲ (Deinstitutionalization)

እ.ኤ.አ. በ1950 ገደማ የተጀመረ፥ የጽኑ የአእምሮ ህሙማን እና ተፈጥሯዊ የአእምሮ እክል (mental retardation) ተጠቂዎችን፥ ከትልልቅ ማቆያ ተቋማት በማስወጣት፥ ተቋማቱን ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል የመዝጋት ፖሊሲ ነው። ይህም፥ በወቅቱ በህመም ሲሰቃዩ ለነበሩ ሰዎች እና ከዚያ በኋላ የታማሚዎቹን ዓለም ለተቀላቀሉ፥ የነበረው ጥቅምና ጉዳት በብዙ ባለሞያዎች ተተንትኖ ተመዝግቧል። በወቅቱ የነበረው የታማሚዎች አያያዝ ችግር፣ የወጪ ቅነሳ፣ እና ክሎርፕሮማዚን (ቶራዚን) የተባለው የመጀመሪያው የአእምሮ ህመም መድኃኒት (antipsychotic) መፈጠር ጋር ተያይዞ፥ ሰዎች ማኅበረሰቡ ውስጥ ሆነው መድኃኒቱን ቢጠቀሙ፥ በሽታቸውን ለማከም ይችላሉ ተብሎ መታመኑ፥ ፖሊሲውን በማርቀቅ እና በመተግበር ረገድ አንኳር ሚናዎችን ተጫውተዋል።

እንደማሳያ: እ.አ.አ. በ1955 በአሜሪካ አገር ውስጥ ከነበረው 164 ሚሊዮን አጠቃላይ የህዝብ ብዛት፥ 558,230 ያህል ጽኑ የአእምሮ ታካሚዎች በሕዝብ ሆስፒታሎች ውስጥ ነበሩ። በአንጻሩ ደግሞ በ1994 ከነበረው 260 ሚሊየን የአሜሪካ ህዝብ መካከል፥ 486,620 ያህሉ ሆስፒታሎች ውስጥ ይታከሙ ነበር። የቁጥሩ ለውጥ በግልጽ እንደሚያሳየው፥ በፊት ሆስፒታል ውስጥ ሆነው እንክብካቤ ሊያገኙ ይችሉ የነበሩ የጽኑ የአእምሮ ህሙማን አሁን ማኅበረሰቡ ውስጥ አሉ። – እንደማንኛውም ለውጥም፥ ይሄም የራሱ ፈተናዎችና ዕድሎች እንደሚኖሩት ይጠበቃል።

የዘርፉ እና የማኅበረሰብ ሳይንስ ባለሞያዎች፥ ፖሊሲው ያመጣውን ጥቅምና ጉዳት በሁለት ጎራ ቆመው ይከራከራሉ። አንዳንዶች፥ ‘በትልልቅ ተቋማት ውስጥ የአእምሮ ታማሚዎች ይያዙ የነበሩበት ሁኔታ፥ የሰው ልጆችን ክብር የሚነካ፣ ለተለያዩ  አካላዊና ወሲባዊ ጥቃቶች የሚያጋልጥ፣ አካላዊ ቅጣቶች ተበይነው የሚተገበሩበት፣ ነጻነትን የሚገፍ፣ የአእምሮና የመንፈስ ደህንነት ሰላምን የማያስከብር፣ እና ሆን ብሎ፥ ሰዎችን መሳቂያ መሳለቂያ የሚያደርግ ስለነበረ ፖሊሲው መፍትሄ አምጥቷል’ ይላሉ። ተቋማቱ፥ ጥገኝነትን፣ ልግምተኝነትን እና ስንፍናን እንዳበረታቱ አክለው ያስረዳሉ።

ሌሎቹ ደግሞ፥ ‘’ፖሊሲው ታካሚዎቹን ከተቋማቱ ስለማስወጣት እንጂ፣ ቀጥሎ መድኃኒት ስለማግኘት አለማግኘታቸው ግድ እንዳልሰጠው፣ በኅብረተሰቡ ውስጥ በስኬት እንዲኖሩ ለማገዝ አቅጣጫዎችን አለመቀየሱና፣ ስለመልሶ ማቋቋም አገልግሎቶች አለማሰቡ፥ የከፋ ተስፋ መቁረጥና መገለል ውስጥ ከቷቸው ነገሩን አባብሶታል’ ይላሉ። ፖሊሲው መተግበር ከጀመረ በኋላም፥ ታካሚዎቹ ከማኅበረሰቡ ጋር ሲቀላቀሉ፥ ያለባቸው ህመም በአልኮልና በተለያዩ እጾች ተባብሶ በሚያደርሷቸው ጥፋቶች ተከስሰው ወህኒ ይወርዳሉ በማለት፥ ከጥቃቅን የጓዳ ጥቃቶች አንስቶ እስከ ትልልቅ አገራዊ ወንጀሎች ጀርባ የአእምሮ ጤና ከግምት መግባት ያለበት ጉዳይ መሆኑን ይናገራሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ፥ 1/3ኛ ጎዳና አዳሪዎች የአእምሮ ታካሚዎች እንደሆኑ ይነገራል። ካለስራ መቅረት፣ ራስን የማጥፋት ሙከራዎች፣ ከሰዎች ጋር አለመገናኘትና መገለልም ከፈተናዎቹ መካከል ይጠቀሳሉ። ከዚህ በተጨማሪም፣ ፖሊሲው ብዙዎችን ጎዳና ላይ ጥሏቸዋል፣ ካለጤና ሽፋን አስቀርቷቸዋል፣ በተለየ ዓለም ውስጥ መገለልን አስተርፎላቸዋል ይላሉ ተከራካሪዎቹ።

የታሪክ መዛግብት እንደሚያስረዱትም፥ ያኔ በዓለማቀፍ ደረጃ የነበረው የተቋማቱ ሁኔታ ከዓለም በቃኞች ጋር የሚመሳሰል ነበር። በ1970 (እ.አ.አ) በበጀት እጥረትና በመድኃኒቶች ተስፋ ሰጪነት ምክንያት አብዛኞቹ ተቋማት ሲፈርሱ፤ ብዙ ታማሚዎች በቤት አጥነት ወይም በእጃዙር ተቋማት ውስጥ ቆይተዋል። የሁለቱ ጎራዎች ክርክር ባለበት፥ ከ1973 ጀምሮ፥ ከማፍረስ ይልቅ፣ ትልልቆቹን ተቋማት ወደ ማኅበረሰብ መንከባከቢያዎች በመቀየር እንዲተገበር እንቅስቃሴዎች ተጀምረው ለውጦች ታይተዋል።  የስነልቡና ታካሚዎች ህብረተሰብ (psychiatric community) ከማቋቋም ይልቅ፥ ህብረተሰቡን የስነ ልቡና ድጋፍ ሰጪ (community psychiatrists) እንዲሆን ማድረግ የሚለውም እንደመፍትሄ የተጠቆመ ነው።

ያለበት ሁኔታ
(ዓለማቀፍ)

እንደ የዓለም ጤና ድርጅት 2001 (እ.አ.አ) ሪፖርት በዓለም ላይ፥ ከ4 ሰው አንዱ በህይወት ዘመኑ የሆነ ጊዜ ላይ፥ በአእምሮ ወይም በነርቭ ቀውስ ጥቃት ይደርስበታል። 450 ሚሊዮን ሰዎች በአእምሮ ህመምና የባህርይ ነውጥ የተነሳ እየተሰቃዩ ይገኛሉ። ይህም የአእምሮ ጤና ችግሮችን፥ ከዋና ዋና የጤና ችግሮችና የአካል ጉዳት መዘዞች ተርታ ይመድባቸዋል። ህክምናዎች ቢኖሩም፣ 2/3ኛ ያህሉ የበሽታቸው ዓይነት ተለይቶ ቢታወቅም፥ ታማሚዎቹ የህክምና እርዳታ አይፈልጉም። ይህንን ችግር ከሚያባብሱ ነገሮች መካከልም፥ ማግለል፣ መድልዎ፣ እና ችላ መባል ይገኙበታል። “መገለል ባለበት የሰዉ ግንዛቤም አናሳ ይሆናል። ግንዛቤው ባልሰፋበትም መገለል ይበዛል።” ይላሉ አሰላሳዮች።

“አንዳንድ የአእምሮ ጤና ችግሮችን መከላከል እንችላለን። አብዛኛው የአእምሮና የባህርይ ቀውስ ደግሞ በተመጣጣኝ ወጪ መታከምና መዳን ይችላል። የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች ውጤታማ ሆነው በመኖር የማኅበረሰብ ዋና አካላት መሆን ይችላሉ።” ይላሉ። የጥናት ውጤቶች እንደሚያስረዱትም፥ ከ80 በመቶ በላይ የስኪዞፍረኒያ ታካሚዎች መድኃኒታቸውንና ህክምናቸውን ከጨረሱ በኋላ አያገረሽባቸውም። 60 በመቶ የሚሆኑ በድብርት የሚሰቃዩ ሰዎች በመድሃኒት እና በሀኪም ክትትል ሊያገግሙ ይችላሉ። 70 ከመቶ የሚጠጉ የመጣል በሽታ (epilepsy) ያለባቸው ሰዎች አስፈላጊው ህክምና ቢደረግላቸው መዳን ይችላሉ።

(አገራዊ)

የእኛ ሰው፥ ጤናማውንም አእምሮ የማሳመም አቅም አለው። በጋራ እንደመኖራችን፥ እርስበርስ መተያየታችንም ይበዛልና አሽሙሩም ተረቱም አቀጣጣይ ነው። የኑሮ ሁኔታውና የማኅበረ-ባህላዊው አኗኗርም አለ። ባህሉ የአእምሮ ህመምን ከእርኩሳን መናፍስት ጋር ስለሚያያይዘው አስፈላጊውን ህክምና ለማግኘት መንገዶች ቶሎ አይከፈቱም። መንገዶቹ በሚገኙበት አጋጣሚም ማኅበረሰቡ አግላይ ነው። ከጊዜ ወዲህ ጥቂት ለውጥ ቢታይም፥ ብዙ ከአእምሮ እክል ጋር የተወለዱ ህጻናት ቤት ውስጥ ይደበቃሉ እንጂ፤ ት/ቤት ለመላክ አቅሙም አማራጩም ብዙ አይደለም።

ታሞ ሰፈር ውስጥ ከሚታይ ሰው ይልቅ፥ ሆስፒታል የሚመላለሰው ላይ የበለጠ አይንና አፍ ይበዛበታል። በዚህ የተነሳ የተጋላጭነት መጠኑን ለማጥናት ቀላል አይሆንም። ሰውም ለአምሮና ለባህርይ ቀውሱ ሀኪም የሚያማክረው ከስንት አንድ ጊዜ ነው። አንድ ለእናቱ የሆነውን አማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ብዙዎች አግልለው ነው የሚመለከቱት። ከነስሙም “እብድ ሆስፒታል” ይባላል። ሆኖም ታካሚዎች ግቢው ውስጥ የሚተክሏቸውንና የሚንከባከቧቸውን አበቦች፣ የሚቀቧቸውን ግድግዳዎች እና የሚያዘጋጇቸውን የስነጽሁፍና የስነ ጥበብ ዝግጅቶች ስንመለከት አመለካከታችን ይለወጣል። የአእምሮ ህክምና ሆስፒታል ውስጥ ይነበባል፣ አትክልት ይተከካላል፣ የእደ ጥበብ ሞያ ይደረጃል፣ ኪነ ጥበብ በወጉ ይከየናል። እዚያ ጆሮ መያዝም ሆነ ሌላ ዓይነት ቅጣት የለም!

ተጠቂው የኅብረተሰብ ክፍል

ከአእምሮ ህመም ጋር በተያያዘ ተጋላጩና፣ እንክብካቤውን ባለማግኘት የሚጠቃው ደሀው ነዋሪ ነው። በዚህ የተነሳም የአእምሮ ጤና ህጎች፥ የማኅበረሰብ ህጎች ይሆናሉ። በአእምሮ ጤና ዙሪያ የሚሰሩ የኪነጥበብ ስራዎችም በአዎንታም ሆነ በአሉታ፥ በፖሊሲ ዙሪያ የሚታከኩ ስለሚሆኑ ሊታሰብባቸው ይገባል። ታካሚዎች ላይ ስለሚደርሱ ጥቃቶች ሲወራ፥ ህክምናውን እንዲያቋርጥ ማስገደድም ራሱን የቻለ ጥቃት ነው።

“መባ”ላይ፥ ወደ መጨረሻው… የስኪዞፍረኒያ ታካሚዋ ምህረት፥ መጀመሪያ “እኔ እብድ አይደለሁም” ማለቷን ባቆመች ጊዜ፥ “እዚህ ላንቺ የሚሆን መድኃኒት የለንም።” ሲሏት (ስኪዞፍረኒያ ታመው የዳኑ ዙሪያችን ያሉ ሰዎች መኖራቸውን ልብ ይሏል።)፥ “እኔ እኮ እብድ ነኝ” ብላ ህክምና እንደሚያሻት ስትገልጽ ትታያለች። ብዙም ሳይቆይ፥ ታካሚዎቹን ሁሉ ነድቷቸው፣ ከግቢ አስወጥቶ “ሁላችሁም ተሽሏችኋል። ሂዱ! መባ የሰጣችሁን ለዓለም ስጡ።” ብሎ በሩን ከውጭ ሲዘጋባቸው፥ ፍላጎታቸውን አውቆ እና ቤተሰብ አማክሮ አይደለም። ስለወደፊት እጣፈንታቸውና ስለሚገቡበት ቦታም አልተጨነቀም።

ራስ ሳይጠና ጉተና

ፊልም ለኪነጥበባዊ ውበቱ ብቻ ተብሎ ሊሰራ ይችላል። ደግሞ አገራዊና ማኅበራዊ ጉዳይ ሲያነሳ በአግባቡና ነባራዊ ሁኔታን ከግምት እንዲከት ይጠበቃል። ሳያውቁ የሚነሱ ከሆነ፥ ምክሩ “ከመጠምጠም መማር ይቅደም” ነው የሚሆነው። የፊልም ስራ ባለሞያ እንደሚያሻው ሁሉ፥ ህክምናውም ባለሞያ ያሻዋል። ይህንን ማንሳቴ፥ ዳይሬክተሯ ቅድስት ይልማ አማኑኤል ሆስፒታል ሄዳ ከባለሞያ ጋር ስላደረገችው ቆይታ ስለሰማሁ ነው። ሲጀመር፥ እዚያ የሄደችው ለማማከር ሳይሆን፣ የሆስፒታሉን Electroconvulsive therapy (ECT) ለመጠቀም ትብብር ጥየቃ ነበር። ያናገራት ባለሞያ ስለስክሪፕቷ አንዳንድ ነገሮችን አውርቷት፥ ‘መስተካከል ያሉባቸው ነገሮች አሉ። በሞያው ያለውን አስተያየት እንድንሰጥሽ፥ የፊልሙን ጽሁፍ ብትሰጪንም እንተባበርሻለን።’ ሲላት፥ “ከ70% በካይ ቀረጻው ሄዷልና የምቀይረው ነገር የለም” ብላ ነበር የመለሰችለት። (ሰኞ ታህሳስ 18/2008 ከሸገር 102.1 ታዲያስ አዲስ ጋር በነበራት ቆይታ ግን “መባን ለመስራት ወደ 6 ወር አካባቢ አማኑኤል ሆስፒታል ነበርኩ። እኔ ብቻ ሳይሆን ተዋንያኑም እዛ ነበሩ።” ብላ ተናግራለች። እስካሁን፥ ይሄ ሆስፒታሉ ከሚያውቀው ጋር እንደሚጣረስ ነው ያረጋገጥኩት።)

‘ከዚህ ባሻገር፥ ኪነ ጥበብ ህብረተሰብን ከአገልግሎቶች ጋር የሚያገናኝ ድልድይ ነው። በአእምሮ ጤና ዙሪያ እኛ አገር ብዙ ስራዎች አልተሰሩም። ታማሚዎቹን ከሰውነት ተራ የወጡ አድርጎ መቁጠርና እየተከተሉ መጎነታተል፣ ደግሞ መሸሽና መሮጥ የሚስተዋሉ የየእለት ክስተቶች ናቸው። ታዲያ ይህኔ ነው፥ “መች የጸደቀውን ዛፍ ነው፥ ልንቆርጠው መጋዝ የምናሰራለት?” ብሎ መጠየቅ የሚገባው። ተቋማቱን ማጠናከር፣ ለተጠቃሚዎች ግንዛቤ ማስፋትና ከኅብረተሰቡ ጋር ማቀራረብ፥ ከአንድ ‘ተራማጅ ሀሳብ’ ካነሳ፣ ተራማጅ የሆነ የኪነጥበብ ባለሞያ ቡድን የሚጠበቅ ነው። ለማንኳሰሱና ለማራራቁ ግን፥ ማኅበረሰቡ በቂና የጠነከረ የማግለል ልማድ አለው።

በጓን ለማድነቅ ፍየሏን ማረድ ለምን?

ፊልሙ የተሰራበት ዓላማ፥ “ተቋማትን ማፍረስን ስለማቀንቀን አይደለም” ካልን፥ “ፍቅርን ስለመስበክ” ይሆናል። ይህንንም ያጠናክርልን ዘንድ፥ የዶ/ር መባ ፍጹማዊነትና ፍቅርን ሰባኪነት፣ ስለፍቅር ፍቱን መድኃኒትነት የሚናገር የዶ/ር ካትሪን ሀምሊን ጥቅስ በፍሬም ተሰቅሎ መታየቱና፣ ዶ/ር ቤዛ በተራዋ ታማሚ ሆና “ምንም ዓይነት የጎን ጉዳት (side effect) የሌለው መድኃኒት ፍቅር ብቻ ነው።” ብላ ስትናገር፥ ፊልሙ ማስረጽ የፈለገው ዋና ጉዳይ ፍቅር እንደሆነ እንገነዘባለን።

በርግጥ ፍቅር ጥሩ ነው። ሆኖም፥ ፍቅር በሕክምና እና በሰዎች የመታከም መብት ዋጋ አይሰበክም። ዶ/ር ካትሪን ሀምሊን ስለፍቅር ፍቱን መድኃኒት ሲሰብኩ፥ በፊስቱላ የተጠቁ ታካሚዎቻቸውን ፍቅር ሰጥተው ብቻ ከነቁስልና ሰባራ ልባቸው እየላኳቸው አይደለም። ከየተጣሉበት ለቅመው ሲያመጧቸው እንጂ በር ከፍተው “ሂዱ ከዚ! ለእናንተ መድኃኒት የለም። በፍቅር ኑሩ።” ብለው ተቋማቸውንም አልዘጉም። ይልቅስ ‘አስፈላጊውን ቀዶ ጥገና፣ እንክብካቤና ድጋፍ ለማድረግ፥ እርሾው ፍቅር ነው’ ሲሉን፥ በፍቅር ተስበው መጥተው፣ ተጠቂዎችን በፍቅር ጠርተው የእኛን ትልቅ የቤት ስራ እየሰሩልን ነው እንጂ።

ከሞላ ጎደል ስናየው፥ “መባ” የሚሰጠን ስጦታ ጊዜውንና የአገራችንን ሁኔታ የዋጀ አይደለም።

ሰላም!

በተለይ ስለዮናታን…

10583842_558489044309215_4067362789194959249_n“ሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊውን ጨምሮ አራት አባሎቹን ማሰናበቱን አስታወቀ” መባሉን ተከትሎ፥ በተለይ ስለዮናታን…

ራሱን (ከጥር 2 በፊት)፥ ከፓርቲው ማግለሉን እስከገለጸበት ጊዜ ድረስ፥ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ስር፥ በአባልነት እና በሕዝብ ግንኙነት ኃላፊነት ጊዜው፣ ፓርቲውን ታምኖ ሲያገለግል የነበረው ዮናታን፥ እስር ቤት ውስጥ ባለበት፣ ራሱን መከላከል እና ጉዳዩን ተንትኖ ማስረዳት በማይችልበት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ (እንደማይጎበኝ ይታወቃል) የፓርቲውን ውሳኔ ሲሰማ ምን ይሰማው ይሆን?

ሲጀመር ውሳኔው አግባብ ነው? “ውሳኔ” ለመባል ይበቃል? ቀድሞ ዮናታን “ከፓርቲው ራሴን አግልያለሁ” ካለ በኋላ፥ “በዚህ በዚህ ምክንያት ከፓርቲው ተባረሃል” ማለትስ ፓርቲውን ከማስገመትና ለከሳሾቹ ግብአት ከመሆን ውጭ ጥቅም ይኖረዋል? አሳልፎ መስጠትስ ከዚህ አይሻልም?

ዮናታን ስለውሳኔው ለፓርቲው በደብዳቤ ማሳወቅ አለማሳወቁን ባላውቅም፥ በፌስቡክ በኩል ራሱን ከፓርቲው ማግለሉን ከገለጸ በኋላ፣ በፓርቲው ስራ ላይ እንደማይሳተፍ እሙን ነው። (ውሳኔውን በሰሙበት ወቅት፥ እንደ ቀልጣፋ አባልነቱ፣ ጉዳዩ ላይ ተወያይቶ መተማመን ላይ ለመድረስ አለመጣራቸውም፥ ‘ለአባላት ግድ የለሽ በመሆን’ ረገድ ያስገምታል።) ይህም ማለት፥ ሰማያዊ ፓርቲ፥ ከውሳኔ እና አካሄድ ለውጥ ባሻገር በፓርቲው ስራ ላይ ተሳትፎ ባለማድረግ ምክንያት አባላቶቹን ሊያሰናብት የሚችልበት የመተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ ሳይኖረው አይቀርም። (ከሌለው ይህም ፓርቲውን የሚያስገምት ሌላ ጉዳይ ነው።)

ታዲያ በስራ ገበታ ላይ ባለመገኘት ምክንያት መሰናበት ያለበትን ሰው፥ በገዛ ጊዜው ቀድሞ ፓርቲውን መሰናበቱን የገለጸን ወጣት “ዮናታን በማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ የታሪክና የጎሳ ጥላቻ ያላቸው ቅስቀሳዎችን በማድረግ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብና የተለያዩ የአገሪቱን ቀደምት መንግሥታት ታሪኮች ያጎደፈ፣ ለጥላቻ የሚያነሳሳ፣ በሕዝብ መካከል የባህል መከባበር እንዳይኖር የጥላቻ ቅስቀሳ አድርጓል።” ብሎ ምክንያት ማቅረብ በምን ዓይነት ሚዛን ነው ልክ የሚሆነው?

1. ሰማያዊ ፓርቲ የአቃቤ ህግን የክስ መዝገብ የማጠናከርና በምስክርነት የመቅረብ ሚና ኖሮት ይሆን? ወይስ በመንግስት ፊት ሞገስን ፍለጋ? ወይስ ‘ሰማያዊነትን’ ሰበካ እና ገጽ ግንባታ?

2. ፓርቲውን መልቀቁን ስለተናገረ ሰው፥ ባለፈው “አባላቶቼ በግፍ ታሰሩ” ብለው እንደ አቋም መግለጫ ዓይነት ደብዳቤ ጽፈው ስም ሲዘረዝሩ የእሱንም ስም መጥቀስ (እዚህ ሲዞር የነበረ ደብዳቤ ነበር)፣ አሁን ደግሞ “ከፓርቲው አባርሬዋለሁ” ማለት ምን ማለት ነው?

3. ዮናታን ‘የፓርቲው ደንብ ከእንግዲህ የእኔ ደንብ አይደለምና፣ የፓርቲ አይደለሁም’ ብሎ በራሱ መንገድ መኖሩና የተሰማውን ሲገልጽ መቆየቱ፥ …የታሪክና የጎሳ ጥላቻ ያላቸውን ቅስቀሳዎች ማድረግ፣ ታሪክ ማጉደፍ፣ ለጥላቻ ማነሳሳት እና በሕዝብ መካከል የባህል መከባበር እንዳይኖር የጥላቻ ቅስቀሳ ማድረግ… የሚሆነው በማን ተመዝኖ ነው?

4. ሚዛኑም፣ አስተያየቱም፣ ውሳኔውም ልክ ናቸው ብለን እናስብና… ዮናታንን ፓርቲውን ለመልቀቅ እስከማስወሰን ያደረሰውን ምክንያት መመርመር እና እንደፓርቲ ከእርሱ ውሳኔ እና ከነባራዊ ሁኔታዎች ለመማር መጣር አይቀድምም ነበር? የተሻለስ አይጠቅምም ነበር?

5. ያሉት አባላቱስ ይህን ውሳኔ ሲሰሙ በእጃዙር ጭቆና ውስጥ አይውሉም? እንደ ‘ሀሳቤን ብቀይር እንዲህ ይሆንብኛል’ ዓይነት ያለ፥ ‘ስጋት ወለድ ፍርሀት’ ውስጥ መኖር?

6. አዳዲስ አባላትስ ወደ ፓርቲው ይሳባሉ? ሰላማዊ ትግልን በተመለከተስ የሚያጠላው መጥፎ ነገር አይኖርም? (ካለፉ ታሪኮች ስንመለከትም እንደዚህ ዓይነት *ማሳጣቶች* እና ለከሳሾች መጠቀሚያ መሆን፥ የተለመዱ ስለሆነም ጭምር)

ይህኔ ነው፥ “ነጻነትን የማያውቁ ነጻ አውጪዎች” ማለት!

ዜናውን ለማንበብ ይህን ይጫኑ።

If you can, fit in. Otherwise, be considerate!

“Don’t be sheep in the era of goats'” says the #TaxiQuote 🙂 In fact, fitting in time or any norm is ideal; and it is what civilization is all about. But I say, be sheep, be goat, be whatever makes you happy… and whatever you think that you’ll fit in your desires.

Be the awkward you can be! But BE CONSIDERATE!

Enjoy your day!

127

እሾህ ልነቅልበት፣ እባጭ ላፈርጥበት
ያገባሁት እሾህ፥
ህመሜን ሊነቅል፣ ሊያሳርፈኝ ቀርቶ፥
ምዝምዝ አደረገኝ፣ በሽታዬ ጸና፤
እርሱው ተሰክቶ፥
ሌላ እሾህ ፈለገ ‘ሚያወጣው ጎትቶ፣
ኀሠሣ ሰላሜን፥ ከበጣሁት ቆዳ፥
ሆኖብኝ ሌላ ዕዳ።

/ዮሐንስ ሞላ/

አለማመን ምርጫ ቢሆንም ቅሉ…

12107807_1230523080297504_52349465818428065_nሞልቶለት ለተገኘ… ከአመሻሽ ማራኪ ክስተቶች መካከል፥ የፀሐይን ወደ ምህራብ ማቆልቆል ተከትሎ፣ ወደ ቤተ አምልኮ (ቤተ ክርስቲያን፣ መስጊድ…) ሄዶ፣ ግቢ ውስጥ ሆኖ የእፎይታን አየር መሳብ፣ ጭንቀትን መዘርገፍ፣ መረጋጋትን መሰብሰብ፣ በዕምነት ሆኖ ተስፋን መሸከፍ፣ ከአምላክም ከራስም ጋር እኩል እያወሩ እርኩስ መንፈስን ማብሸቅ፣ ፈጣሪን መውቀስ፣ ራስን መፈተሽ፣ መፀፀትና ማመሰገን… ይጠቀሳሉ። (በተለይ የዕለቱ የአምልኮ መርሀ-ግብር ተጠናቅቆና የቀጣዩ ቀን መርሀ-ግብር ሳይጀመር፣ ግቢው ፀጥ ረጭ ሲል)

አመሻሽ ወደ ቤተ አምልኮ የሄደ ሰው ብዙ ዓይነት ትዕይንቶችን ሊመለከት ይችላል። እዚህም እዚያም ብቻቸውን የሚያወሩ አፎች ሞልተዋል። በየልቦቻቸው የሚራገሙና የሚዝቱ፣ በፀፀት የሚብሰከሰኩ፣ በምስጋና የሚፍነከነኩ፣ ስለነገ እየፀለዩ ነገን ከሩቅ እያዩ የሚደሰቱ፣ “የማታ እንጀራ” የሚለምኑ፣ የሚያማርሩ፣ የሆነ ዐይነት ከባድ ሸክም ከላያቸው ላይ እያስራገፉ ያሉ የሚመስሉ፣ ስለአገር ሰላም የሚማልዱ… ብዙ ዓይነት ሰዎች ይታያሉ። በየትኛውም ዓይነት ስሜት ውስጥ ሆነው ቢሞክሩት፥ እርጋታውና እርካታው አይጠረጠርም።

አማኝ ባይሆኑ እንኳን እግር ጥሎ አመሻሽ ዘው ቢሉ፥ ኢአማኒነት ተራግፎ ባይመለሱም በጥሩ መንፈስ ውስጥ ሆኖ መመለስ የሚቸግር ነገር አይደለም። በዓለም ላይ ስንኖርም፥ በዓለማዊነት አስተምህሮ ሳይቀር፣ ስለተስፋ ይሰበካል። ስለመረጋጋትና ጭንቀትን ስለማስወገድ መፍትሄ ጥቆማ ዓለም ይጨናነቃል። መበልጸግን ተከትሎ ስለሚጠፋ ሰላምና መረጋጋት ይሰበካል። ስለስበት ሀይል ይወራል። ከዛሬ ነገ ስለመሻሉ በተሰፋ ይነገራል። ሁሉም በየፊናው ደህንነቱን ለማረጋገጥ ስለጥበቃው ጥንካሬ ይዳክራል። ጥሪት መቋጠሪያ አጫጭር መንገዶችን ኀሰሣና ማስተዋወቅ ላይ ይደክማል። ብዙ ብዙ… መካሪውና ምክሩ ብዙ ነው። ምስጢሩና መንገዱ የትየለሌ ነው።

በየቤተ እምነቱም እነዚህ ጉዳዮች ይሰበካሉ። አማኞች ከአምላካቸው ጋር ሲነጋገሩ፥ በልባቸው “እደመጣለሁ” የሚል እርግጠኝነትና፣ “ይረዳኛል” የሚል ፅኑ ተስፋ አለ። “አድርጎልኛልና” ብለው ለምስጋና የሚመጡም አሉ። ሰማይ ተደፍቶ ትከሻቸው ላይ የወደቀ ሲመስላቸው ፈጣሪ ያቀናናል ብለው ያምናሉና ይሆንላቸዋል። ቢጎድል እና ቢሞላም የፈጣሪያቸውን መኖር ካሰቡ ቀጥሎ ስለሚኖራቸው እንቅስቃሴ መስመር መያዝ ጥሩ አጋዥ ይሆንላቸዋል። ከዚህም በላይ፥ ከሰው አእምሮ በላይ የሆኑ ችግሮቻቸውን ለፈጣሪ በመንገር ከእርሱ እርዳታ ማግኘት እንደሚችሉ ያምናሉ። ይህ የመረጡትና የተሰበኩት የሕይወት መመሪያቸው ውጤት ነውና ያተርፉበታል። (እዚህ ላይ መጥቀስ የፈለግኩት፥ ሄዶ በመቀመጥ ብቻ የሚገኙትን ጥቅሞች ነው።)

ታዲያ ይሄንን የሰው ልጆች እምነት፣ ሰላም፣ መረጋጋትና ተስፋ ለመንጠቅ ላይ ታች የሚሉ ሰዎች እንዴት የተረበሹና በክፋት ውስጥ ያሉ ናቸው? የሰዎችን የሕይወት መመሪያ ማፋለስን የራሳቸው የሕይወት መመሪያ አድርገው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች በእንዴት ዓይነት ጭንቀት ውስጥ የሚገኙ ናቸው?

አለማመን ምርጫ ነው። የሰዎችን እምነት ለመንጠቅ መባከን ግን ከራስ ወዳድነትም አልፎ ሌላ ጠሊታነትን የሚጠይቅ መርገምት ነው። ስለሚያምን “ሞኝ” በተባለው ሰው አኗኗር ላይ ክፉኛ መቅናትንም ይጠይቃል። አያድርስ ነው!

የፈጣሪ ሰላምና ፍቅር ይብዛልን!

ናፈቀኝ… (ጂጂ)

“ናፈቀኝ… ደገኛው ቄስ ሞገስ፥ በፈረስ፣ በበቅሎ ተጉዞ ሲመጣ፥ 28574-2
ለዓመት በዓል ጨዋታ፥ ሰው እልል እያለ ሲቀበል በእምቢልታ፤
አንተዬ… በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ፤ ያገሩ ገነኛ ሆ እያለ ሲመጣ፣
አባዬ ናፈቀኝ የከብቶቹ ጌታ፥ ሲባርክ ሲመርቅ የቤቱን ጨዋታ፤
እምዬ እናታለም….
ጉልበትሽ ችሎታሽ ይበልጣል ከሺህ ሰው፥
__ ይኸው ሰውን ሁሉ እጅሽ አጠገበው፤
ናፈቀኝ… ያያ ታዴ ሆዴ…
“የሽመል አጓራ አይችልም ገላዬ
የኔ ሆድ አሌዋ ና ቁም ከኋላዬ፤
አያና ድማሙ አያና ድማሙ
አያና ድማሙ አያና ድማሙ፤
ዓባይ ወዲያ ማዶ ትንሽ ግራር በቅላ
ልቤን ወሰደችው ከነሥሩ ነቅላ።”
እያለ ሲዘፍን ትዝታው ገደለኝ
ዛሬ በሰው ሀገር የሰው ከብት እያየሁ እያንገበገበኝ
ወኻ ጃሪ ወኻ ኮሎ ሲሉ
ያባቴን በሬዎች የእናቴን መሰሉኝ፤”
~ እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ❤
ውስጧ ሆኜ፥ ሀገሬን ከሩቅ ከማይባቸው ምርጥ ሙዚቃዎች አንዱ! …እንግዲህ ከሀገር የራቃችሁ ወዳጆች፥ ይህንን ሙዚቃ መዝዤ ናፍቆት ሳጋግልባችሁ፥ ጉዳችሁ 🙂
መልካም የገና በዓል!

ከዘመን እግር ስር እንዳንወድቅ፥ የዘመኑን ለዘመኑ እንተውለት!

በአንድ ከተማ ውስጥ፥ ‘ትንቢት መናገር እችላለሁ።’ ብሎ በሀሰት የጉራ ወሬ የሚነዛ አንድ ወጣት ነበረ። የነብይነቱ ነገር ተዛምቶ ንጉሱ ጆሮ ይደርስና፥ “ጥሩት እስኪ ይህን መናጢ። እውን ነብይ እንደሆን፥ ይተንብይልና!” ይላሉ። ወጣቱ ተጠርቶ ንጉሱ ፊት ይቀርባል። ጥሪው ወጣቱን ኩራትና ጭንቀት መሀል ከትቶት፥ እጅ ከመንሳቱ “እንግዲያው ዘመኑን ተንብይልን” ይሉታል። የቤት ስራውን ተቀብሎ ወጣ። ለጉራ ያወራው ነገር ሕይወቱን ንጉስ ዳጃፍ ጥሎበታልና ትንቢቱን ካላደረገ ሰላም እንደማይሆን አውቋል። እምጥ ይግባ  እስምጥ፥ ተጨነቀ።

መንገድ ላይ ቀበሮ ታገኘውና፥ “ምን ሁነህ ነው?” ትለዋለች። “ሲያቀብጠኝ ትንቢት አውቃለሁ ብዬ ጉድ ሆንኩ።” ይላታል። “ችግር የለም። እኔ እረዳሃለኋ።” አለችው። “ኧረ ‘ባክሽ?” ባለማመን ጠየቀ። “የተጠየቅከው ትንቢት ምንድን ነው?” አለች ቀበሮ። “ዘመኑን ተንብይልን ነው ያሉት ጌቶች” አላት። “ይሄማ ቀላል ነው። ግን አንድ ቃል ግባልኝ?” አለች። “ምንድን ነው እሱ? ከዚህ ጉድ አውጭኝ እንጂ ደግሞ ምን ችግር?” አላት። “የምነግርህ ትንቢት ሰምሮ ስትመለስ ምግብ ይዘህልኝ ትመጣለህ።” አለችው። “ይሄማ ችግር የለውም። መላ በይኝ እንጂ።” አላት። “በል ዘመኑ የጦርነት ነው። ብለህ ንገራቸው።” አለችው።

የጭንቁን ምላሽ በማግኘቱ በወጉም ሳይሰናበታት ሲገሰግስ ሄዶ “ዘመኑ የጦርነት ነው።” ብሎ ተናገረና፣ ትንቢቱ ሰምሮ ነፍሱን አቆየ። ከዚያ ለቀበሮ እጅ መንሻ፥ ከወደ ኋላው ጦር ሸሽጎ ሲገሰግስ ሄደ። ቀበሮም ከሩቅ ሆና በጥርጣሬ ስትጠብቀው ጦሩን ወርውሮ ሳታት። ስላልገደላት ተማርሮ ተመለሰ።

ትንቢቱ በመስመሩ ዝናው ይበልጥ ጨምሮ፥ ድጋሚ ለቀጣይ ዘመን ትንቢት ታዘዘና፣ ከነጭንቀቱ ወደ ቀበሮ መንደር ሄዶ አገኛት። ዐይኑን በጨው አጥቦ፥ “ቀበሪት ሆይ ማሪኝ። በድዬሻለሁ። በባለፈው ስራዬ ተጸጽቻለሁ። እውነት ሀሳቤ እንደዛ አልነበረም። ግን ሰይጣን አሳሳተኝ። እባክሽን ከዚህ ጉድ አውጭኝ። እክሳለሁ።” እትት ብትት አለባት።

“ኧረ ችግር የለውም። አሁንም ትንቢቱ ሰምሮ ስትመለስ ምግብ እንደምታመጣልኝ ቃል ከገባህ የባለፈውን እረሳዋለሁ።” ትለዋለች። “ይኸው ቃሌ! ሙች ስልሽ!” አላት። “በጄ! ዘመኑ የእሳት ነው ብለህ ንገር።” ትለዋለች። ሲገሰግስ ሄዶ “ዘመኑ የእሳት ነው” ብሎ፥ ሰምሮለት ነፍሱን አቆየ። ወደ ቀበሮም፥ በጆንያ ጭድ ሸክፎ መንገድ ጀመረ። እሷም ተንኮሉ ገብቷት ከሩቅ አይታው ወደጉድጓዷ ገብታ ተደበቀች። ደርሶ ጭዱን ሰግስጎ እሳት ለቀቀበት። ቀበሪትም በሌላኛው የጉድጓዱ ጫፍ ወጥታ “ትዝብት ነው” ዓይነት አይታው ተመለሰች።

ከእንግዲህ የነብይነቱ ነገር ካንዴም ሁለቴ ተፈትኖ ያለፈ ነውና፥ ለሶስተኛ ዘመን እንዲተነብይ ታዘዘ። “ወይኔ ጉዴ! ካንዴም ሁለቴ ቃሌን አጥፌ፣ ጭራሽ ግፍ ላደርግባት ሞክሬ ሳበቃማ፥ እንዴት አያታለሁ? በምን ዐይኔ?” ብሎ ቢሳቀቅም አማራጭ አልነበረውምና እንደምንም ሄዶ፥ “መቼስ አያርመኝም! ቀበሪት ሆይ ዳግመኛ ፊትሽ መጥቻለሁ። በደሌ ይቅር የማይባል ቢሆንም አንቺ አስተዋይ ነሽና ማሪኝ። መቼስ ‘ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት’ አይጠፋምና፤ እባክሽን…” ብሎ የምንተፍረቱን ተማጸናት።  ቀበሪትም “ይሁን! ግን አሁንም ትንቢቱ ሲሰምር ምግብ እንደምታመጣልኝ ቃል ግባ።” ትለዋለች።

“ይኸው ቃሌ! ከእንግዲህ ንግግር አላበዛም።” አላት። “በል ዘመኑ የጥጋብ ነው ብለህ ንገር” አለችው። ትንቢቱን አደረሰና ሰመረለት። ሲመለስም ስጋ ይዞላት መጣ። ፊቷ ቀርቦ፥ በደስታና በቃል ጠባቂነት ስሜት እየፈነጠዘ “ይኸው ቀበሮዬ ቃሌን ጠብቄ ይዤልሽ መጥቻለሁ።” አላት።

“አዬ፥ ይህንማ አንተ አይደለህም። ዘመኑ ነው የሰጠኝ። የጦርነት ጊዜ ነው ስልህ፥ ጦር ይዘህልኝ መጣህ። የእሳት ዘመን ነው ስልህ ጭድ ሸከፍክልኝ። ይኸው ዘመኑ የጥጋብ ቢሆን፥ ስጋ ይዘህልኝ መጣህና ‘ይህን አድርጌልሽ’ ልትል ያምርሃል። የሰጠኝ ዘመኑ ነው።” ብላ ያመጣላትን ይዛ ሄደች።

[አንድ ወዳጄ  “ከአንድ አባት የሰማሁት” ብሎ አጫውቶኝ የነበረን ተረት ትዝ ባለኝ መጠን፣ በራሴ አተራረክ የተየብኩት ነው።]

* * *

“ሰውን ማመን ቀብሮ” አለች የተባለላት ቀበሮ፥ ብዙ ተረቶቻችን ውስጥ ሰውኛ ባህርይ ተላብሳ ኖራ ታኗኑረናለች። በየዘመኑ የሚባሉ ሽሙጦችም በ“አለች ቀበሮ” ተዳርሰዋል። አይሞቀን አይበረደንም እንጂ፥ ለሰው ልጆች እኩይ ባህርያት ነቋሪ በመሆንም በብዙ ተረቶች ላይ እናገኛታለን። እዚህኛው ላይ ያለው ነገርም ካለአስረጅ የሰው ልጆችን ባህርይ በየፈርጁ የሚተች ነውና እሱን አንተነትነውም። – ሁሉም የየአቅሙን መልእክት ይምዘዝለት!

ሆኖም መንግስትን እና የመንግስት አዛኝ ቅቤ አንጓቾችን (sympathizers) ባሰብኩኝ ጊዜ ተረቱ ትዝ ይለኛል። “ይህን አድርጌ… ይህን አምጥቼ” የሚሉ ባዶ ሽንገላዎችን፣ ጡዝጦዛዎችን (propogandas) እና የ‘ምርጫ’ (?) መቀስቀሻ ወሬዎችን በተለያዩ አጋጣሚዎች እንሰማለን። ከመንግስት መገናኛ ብዙአን ባሻገር፥ በደጋፊዎችና በዝም ብሎ ኗሪዎች አፍም “ለውጥ” መኖሩ የሚወራበት አጋጣሚ ብዙ ነው። በደፈናው “ከትናንት ዛሬ ይሻላል” ይባላል።

ኗሪዎቹም ብንሆን፥ ‘ይህን አድርጌ፣ ይህን ሰርቼ’ የሚለው ወሬ ሲበዛብን፣ ከበዓሉ ግርማ ዝነኛ ግጥም “ካለሰው ቢወዱት፣ ምን ያደርጋል አገር?” የሚለውን ስንኝ እያጉተመተምንም ቢሆን ዙሪያ ገባውን ማየታችን አይቀርም። አንድ አገር በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢሆን፥ የዛሬ 25 ዓመት እንደነበረው እንዲገኝ አይጠበቅም። (እንደምሳሌ፥ ዓለም በኤሌክትሮኒክስ ቴክኖሎጂ ሲያብድ፥ እኛ በጥቁርና ነጭ ቴሌቪዥን ልንገኝ አንችልም።) ባይንከባከቡትም፣ የተለየ ነገር ባያደርጉለትም፣ የዘመኑን ያህል፥ በንፋስ ተገፍቶም ይሁን በፍላጎት ተጎትቶ፥ ትንሽ ራሱን በዝግመተ ለውጥ ይገፋል።

‘አሉ’ የሚሏቸውን ለውጦች ሲዘረዘሩም የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን በመጥቀስ “ይህን ሰርቶ። ይህን አምጥቶ።” ይላሉ። ያቺ አፍ ላይ ተበይዳ የቀረችው 11 መቶኛ ኢኮኖሚ እድገትም ትነሳለች። ስለሚኖሩባቸውና  ስለኗሪዎቹ ሁኔታ ግድ ሳይሰጣቸው፥ እዚህ እና እዚያ የተዘራዘሩ፥ ከኮብልስቶን እስከ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ ከውኀ መስመር እስከ መብራት መስመር ዝርጋታ ማስፋፊያ ስራዎች፣ ከመንገድ እስከ ህንጻ በደፈናው በጅምላ ይዘረዘራሉ። ‘ኢኮኖሚው’ ብለው በጅምላ በመናገር ስለአማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢ ይደሰኩራሉ።

የውኀ እና የመብራት መጥፋት፣ የስልክ ኔትዎርክ መቆራረጥና የ‘system የለም’ ስራ መጓተቶች፣ የመንገዶች መፈርፈርና መቆፈር፣ የሙስናና የአገልግሎት ጥራት ነገር ሲነሳ የመንግስት ቢሮዎቹን በተናጥል እንድንጠይቅ መገፋፋትም ፋሽን ሆኗል። እንዲያውም የመንግስት ወዳጆች፥ ከሰፊው ሕዝብ ጋር፣ ሽፋን ለመስጠት፥ የመንግስት ቢሮዎቹን በችርቻሮ – ስለመብራት፥ መብራት ኃይልን፣ ስለስልክ ቴሌን እና ወዘተ – ሲያማርሩ ይሰማል። ሰፊው ሕዝብም እንደዚያው እንዲያደርግ  መገፋፋትም አለ።

“መንግስት ምን አደረገ? ኤልፓ ነው እንጂ” “መንግስትን ተዉት፥ ቴሌ ነው እንጂ” በሚሉ ወሬዎች ባለስልጣን መስሪያ ቤቶቹን ከመንግስት ለይተን እንድንመለከት ይገፋፉናል። (እጅ ሲሰርቅ ባለ እጁ ይወቀሳል፣ ይቀጣል እንጂ፤ እጁ ላይ ለብቻው ምን ይደርሳል? ምላስ ቢሳደብስ ለብቻው ይቆረጣል? ወይስ ነገሩ ጉንጭ አልፋ ሆኖ እንዲቀር ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ነው?)

ስለረኀብ ሲነሳ፥ የአየር ንብረት ለውጥ ሀላፊነቱን እንዲወስድ ይሰብካሉ። “’ድርቅ (drought) የዝናብ መቅረት እንጂ የምግብ መጥፋት (famine) አይደለም። ድርቅ በአየር ንብረት ለውጥ ሊከሰት ይችላል። ረኀብ ግን የሰው እጅ አለበት። ዛሬም ዝናብ ተደግፈን፣ ከማሳ ወደ አፍ ነው የሚኖረው።” ስንል፥ “የፀረ ልማቶች ወሬ ነው እንጂ ሌላም ዓለም ይራባል።” ይሉናል። ስለ ስደት ሲወራ ደላሎችን በጅምላ ያወግዛሉ።

ለ25 ዓመታት አንቀጥቅጦ ሲገዛ የኖረ መንግስት አመሻሽ የዘረጋው ባቡር መንገድ ሳይቀር “ባቡር አሳየን” ይባልለታል። (ምኒልክ ያሳዩት ባቡር ተረስቶ። በነገራችን ላይ፥ የባቡር መንገዱ ውስብስብነት እንጂ ቀላልነት አይገባኝም። ይህንንም የተረዳሁት የሌሎች አገራትን መንገድ አሰራርና ቅርጽ ተመልክቼ፣ ሊሆን ይችል የነበረውን ሳስብ ነው።) የትምህርት ጥራቱ ጉዳይ ከቁብ ሳይገባ፥ በቁጥር የበዙትን ዩኒቨርስቲዎችና ተመርቀው ቤት የሚውሉትን ተማሪዎች ቆጥሮ ጉራ ይነዛለታል። …የዘመንን ትሩፋቶች ለመንግስት እንሰጣቸዋለን።

ይልቅስ ሀሳብን በነጻነት እንዳይገልጹ ማፈን፣ ፖለቲከኛውን በ”ሽብርተኛ” ታርጋ ማሰር፣ በልማት ሰበብ፥ ሰዎችን ከምቾት ቀጠናቸው ማፈናቀልና ኅልውናቸውን አደጋ ላይ መጣል፣ ነጻ የክርክር እና የውይይት መድረኮች እንዳይፈጠሩ መድከም፣ ስርዓተ ትምህርትን ከጥራት ብዛት የሚያደርጉ አቅጣጫዎችን መትከል፣ ሙስናና ዝርፊያን መሸሸግ፣ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞው የሚያሰማ ሕዝብ ላይ ጥቃትን ምላሽ ማድረግና ሌሎች ግፎች …ከዘመን እግር ስር ይወረውሩናል፥ እናወግዛቸዋለን!

ዘመኑ የሰጠንን ለዘመኑ እንተውለት። በመልካም አስተዳደር ሁኔታ ላይ ይወሰናልና፥ ዘመኑ የሰጠንንም እንደዘመኑ መቀበል አለመቀበላችንን እንፈትሽ!

ሰላም!

P.S. ይህ ጽሁፍ በአዲስ ገጽ መጽሔት ቅጽ 01 ቁ. 03 ታትሞ የነበረ ነው። አዲስ ገጽ መጽሔት በየሁለት ሳምንቱ የሚታተም ሲሆን፥ የቁ.04 እትም ቅዳሜ ታህሳስ 23/2008 ዓ/ም ለንባብ ውሏል። ቢሆንም በማተሚያ ቤት ዙሪያ በተፈጠረ ችግር የተነሳ፥ የእትሙ ቁጥር አናሳ ስለነበር፣ በአንባቢያን ጥያቄ መሰረት፣ አዘጋጆቹ ድጋሚ አሳትመው፥ ዛሬ ገበያ ላይ እንዲውል አድርገዋልና ባለፈው ቅዳሜ ፈልገው ያጡ፥ በቅርብ ያሉ አንባቢያን ሊያገኙት ይችላሉ። ላለፉ እትሞቹ ድረ-ገጹን – www.addisgets.com – ይጎብኙ። የፌስቡክ ገጹን –አዲስ ገጽ መጽሄት /Addis Gets Magazine – ተከትላችሁ ‘like’ን ብትጫኑም አስተዳዳሪዎቹ መረጃዎቹን ያደርሷችኋል።