“የአገር ልጅ የማር እጅ”
ባልተለጠጠ የጉዞ እቅድ፥ ብድግ ብዬ ነበር የሄድኩት። እንደነገ ልነሳ፥ አመሻሹ ላይ፥ የቀድሞውን የአውሮፓ ጉዞዬን እና፤ ነገሮች እንዳላሰብኳቸው ሄደው አስደስተውኝ እንደነበር ሳስታውስና፣ ይኽኛው እንዴት ሊሆን እንደሚችል በምናቤ ስስል ነበር። መቼም ርቀው ሄደው የራስን ሰው ሳያገኙ መቅረት የሚያጎድለው የማይታወቅ ነገር ይኖራልና፥ ያኔ መዳረሻ ቦታዬ ስደርስ፥ ያለሁበትን ከተማ ጠቅሼ ‘Any friend here? Coffee?’ ብዬ ነበር የፌስቡክ ገጼ ላይ እለጥፍ የነበረው።
ያ ‘የቡና እንጠጣ’ ጥሪዬ በጎ ምላሽ አግኝቶ፥ እጅግ ከሚገራርሙ ሰዎች ጋር እንዳገናኘኝ፣ በእንክብካቤ እንዳረሰረሰኝና፣ ባይሆን ኖሮ በቀላሉ ላላስብ የምችላቸውን ብዙ ነገሮች አሳስቦኝ እንደነበር ሳስታውስ፥ ድንገት ላፕቶፔን ከፍቼ አቴንስ እንደነበሩ ለማውቃቸው ሁለት የፌስቡክ ወዳጆቼ ‘Hi! If you’re still in Athens, and if convenient, may we grab coffee.’ የሚል የውስጥ መልእክት ላኩላቸው። አንደኛዋ ወዳጄ (ራሄል) በሞቅታ እና በአሉታ (በስራ ምክንያት ከከተማው ትንሽ ራቅ ብላ ነበር)፤ ሌላኛዋ (ቤቲ) ደግሞ፥ በተመሳሳይ ሞቅታ እና በአዎንታ መለሱልኝ።
ቢያንስ ቤቲን እንደማገኝ ሳውቅ ደስ አለኝ። ከሁለቱም ጋር ስልክ ተለዋወጥን። ከተማው ውስጥ የሌለችው ወዳጄን ቀድሜ ስላወራኋት ስለማረፊያዬ እና የሚቀበለኝ ሰው እንዳለ አጥብቃ ጠየቀችኝ። ለማረፊያው ሆቴል ቡክ እንዳደረግኩ፣ የሚቀበለኝ ሰው እንደሌለና፣ መደናበሩም የጉዞው አካል ነው ብዬ ስለማምን፥ የተቀባዩ ሰው ጉዳይ እንደማያሳስብ ገለጽኩላት። ሆቴል ማደሬን አልተስማማችምና ብዙ ተጨቃጨቅን። – እኔ ስግደረደር፣ እሷ ደግሞ በደግነትና በፍቅር ስትጋብዝ። (ከተማም ውስጥ ስለሌለች ‘oh, I am sorry’ ብላ ብታልፍም፥ ለኅሊናዋም በቂ ምህረት (excuse) ነበራት።)
“አመሰግናለሁ! ግን ስለሌሽም እኮ ብዙ አያስጨንቅም። ዝቅተኛ ዋጋ ያለውን ሆቴል ስለሆነ የያዝኩት ያን ያህል የሚያሳስብ አይሆንም።” አልኳት።
“እኔ ባልኖርም ቁልፍ ጓደኛዬ ጋር ስላለ እሷ ከፍታ ትጠብቅሃለች። ችግር የለውም። …ምንም ቢሆን ቤት ነው የሚሻልህ።” አለችኝ።
“ኧረ ባክሽ ችግር የለውም። እኔ እኮ just ቡና እንጠጣለን፣ ሰው አገኛለሁ ብዬ አስቤ ነው መንገሬ እንጂ ላጨናንቅ አይደለም።”
“ካኔና! አልተጨነቅኩም። ባላገኝህ እንኳን ደስ ይበለኝ…” አለች።
ያው ፍቅርና ቅንነት ያሸንፋሉና እጅ ሰጥቼ ተስማማሁ።
“ኢንዳክሲ!” አለች ከነሞቅታው። – ባለመኖሯ የተሰማትን ቅሬታ እየገለጸች።
የቤቷን አድራሻ እና የመጓጓዣዬን ነገር አስረዳችኝና ተሰነባበትን።
ቀጥሎ ከሌላኛዋ ወዳጄ (ቤቲ) ጋር አወራን። እሷም ስለማደሪያዬ ጉዳይ እና የሚቀበለኝ ሰው እንዳለ ጠየቀችኝ። ከራሄል ጋር የነበረንን ቃለ ምልልስ ዘከዘኩላት። በሁለተኛው ቀን ስራ አስፈቅዳ ቀርታ፥ ከተማውን አብረን ዞረን እንደምናይ ነገረችኝ። ፈጣሪን አመስግኜ ተኛሁና በቀጣዩ ቀን ለጉዞ ተነሳሁ።
የ’ስላሴዎች’ አገር
አቴንስ አየር ማረፊያ እንደደረስን፥ ስልኬን አብርቼ ከዋይ-ፋይ ጋር ተገናኘሁ። ወዲያው ራሄል ደውላ፥ የምይዘውን አውቶቢስ ቁጥር አስታውሳኝ መንገዴን ቀጠልኩ። በነገረችኝ መሰረት ለ1 ሰዓት ገደማ በአውቶቢስ ተጉዤ፥ ታክሲዎች ወደቆሙበት ልሻገር ስል፥ ሸምገል ያሉ ሰው “Hi! Welcome Ethiopian” ብለውኝ እጃቸውን ለሰላምታ ዘረጉልኝ።
ከአንድ አንድ ከየት መሆኔን ስላወቁ ግርምም ደስም እያለኝ፥ እንደኢትዮጵያዊነቴ ከአንገቴ ደፋ ቀና ብዬ አጸፋውን መለስኩላቸው። በወፍ በረር ስለኢትዮጵያውያን ሰላማዊነት አወሩኝ። አባይንና አክሱምን ጠቃቀሱልኝ። “Haileselassie was a good politician” አሉኝ። ሌላም ሌላም የሚያውቋቸውን (እና ሳስበው፥ እኔን ሊማርኩ የሚችሉባቸውን) ነገሮች ጨራረፉልኝና ተሰነባበትን።
ከተደረደሩት ቢጫ ታክሲዎች ፊት ላለው ሾፌር፥ የቤቱን አድራሻ ሳሳየው “ግባ” ብሎኝ መንገዳችንን ቀጠልን። እሱም እንግዳነቴን አውቋልና “Where are you from?” ብሎ ጠየቀኝ። “Ethiopia” መለስኩለት። “Oh, country of Selassies” አለኝ። ተገርሜ፥ ማብራሪያ ጠየቅኩ… “I know Haileselassie, and Haile Gebresellasie. Nai?” ብሎኝ ሳቀና… “country of Haile Selassies” ብሎ እንደማስተካከል አደረገ። ተሳስቀን እየተጫወትን አድርሶኝ የቆጠረውን ብር ከፍዬ ወረድኩ።
‘Feel Like a Star’
ተበላ። ተጠጣ። ተጠገበ። በቡና ታጅበን ተጨዋወትን።
“ካርድ የለውም ግን ይህኔ ትሞላበታለች። እንግዲህ የሚቸግርህ ነገር ካለ፣ ቦታም ቢጠፋህ ደውልልን። ልጆቼም ስለሚያስቸግሩኝ እንግዲህ አላማሸሁህም። አንድ ጓደኛችንን በኋላ ይመጣል፥ እሱ ይዞህ ይወጣል። ቡና ማፍላት ከፈለግክ፣ ሌላም የምትፈልጋቸው ነገሮች ካሉ….” ብላ ቦታ ቦታ ጠቋቁማኝ፥ ሲም ካርድ ያለበትን ስልክ ሰጥታኝ ተሰናብታኝ ሄደች። ወዲያው ራሄል ደውላ ሰው እንደሚመጣልኝ ነገረችኝ። ብዙም ሳይቆይ፥ ሳሚና ሪታ ከሚባሉ ወዳጆች ጋር ስንቀባረር፣ ቢራዎቹን ስቀማምስ፣ ከተማ ለከተማ ስዞር አመሸሁ። የእነሱም እንክብካቤ ወደር አልነበረውም።
የራሄል ነገር እንዲህ ተተርኮ የሚያልቅ አይደለም። ለምሳሌ፥ “ይሄን ባስ ያዝ… እዚህ ውረድ… በዚህ ግባ… በል እዚህ ዞር ዞር በልና ሲደብርህ ወይ ደግሞ ሌላ ቦታ መሄድ ከፈለግክ መልሰህ ደውልልኝ።” ብላ ከተማውን በስልክ ሸኝታ አስጎብኝታኛለች። ቤቲም ባለችው ዕለት ስራ ፈቃድ ጠይቃ ያለሁበት መጥታ ይዛኝ ሄዳ ከተማውን ስታስጎበኘኝና ስትንከባከበኝ ውላ አመሻሹን ተለያየን።
የእንክብካቤዋን ነገር ሳስብ ወደፌስቡክ ጎራ ብዬ “Some people make you feel that you’re more important than what you actually are (or than that you thought you could be). I’ve seen the hospitalit-iest in Athens. Richo, you have left me speechless! You’re amazing that you’ve remote controlled my joy” ለጥፌ ዞር ስል የዛሬ 6 ዓመት ገደማ ‘feel like a star’ በሚል ሙዚቃ ታጅቦ ይሄድ የነበረ የቱርክ አየር መንገድ ማስታወቂያ ትዝ አለኝ።
ማስታወቂያው. . .
ራሄል ግን አትገርምም!?
አቴንስ
የገበያ ማዕከሎቹን እየጎበኘን አልፈን፣ ሞናስትራኪ እና አቢሲኒያ አዳባባዮችን ተንጎራደድንባቸው። – ሞናስትራኪ ድድ ማስጫ ነገር ነው። አቢሲኒያ ስሙና ታሪኩ በቀድሞ ሰዎች ብቻ የሚታወቅ ሆኖ፥ ንግድ የሚቀላጠፍበት ቦታ ነው። (ለኃይለ ስላሴ ክብር የተሰየመ እንደሆነ ሰምቻለሁ)
ድመትና ፍሉት
ሰማኝ። እዚያ አካባቢ ስለማኒከን ፒስ ይወራል። እንኳን ቦታው ደርሰው፥ ቤልጂየምን የሚያውቅ ሰው ‘ማኒከን ፒስን ሳታይ እንዳትመጣ’ ሊል ይችላል። ወይ ደግሞ በየጉዞ ማስታወሻው ስለማኒከን ፒስ ተዳንቆ ተጽፎ አንበበናል። – ሽንታሙ ልጅ ዝናው እንዲህ ነው።
ቤልጂየማውያኑም ስለማኒከን ፒስ ሲያወሩ እንደትልቅ ቅርስ በኩራት ነው። ለዚህም ይመስላል፥ ዙሪያ ገባው ያሉ ቤቶች የማኒከን ፒስን ምስል ደጃፋቸው ላይ በተለያየ መልክ የሚያስቀምጡት። ከአሻንጉሊት ወይም ቁልፍ መያዣ አንስቶ፥ እስከ ግዙፍ ቼኮሌት ድረስ በማኒከን ፒስ ቅርጽ ተሰርቶ ሲታይ፥ ማኒከን ፒስ ያጓጓል። ደርሰው ሲያዩት ግን፥ ደቃቅነቱን ትታዘባላችሁ። ብዙ የተባለለት የሽንታሙ ህጻን ልጅ ሀውልት፥ 61 ሴንቲሜትር ርዝመት ብቻ ነው ያለው። ታዲያ ይዘመርለት ዘንድ፥ ትልቀትና እንሰት ምን ቦታ አላቸው? – የሚሸከመው ታሪክ እንጂ!
የመኪና ገበያ እና የእስልምና አስተምሮ ምርምር የሚደረግበት መስኪድ የሚገኙበት፣ ጁቤል መናፈሻ ግቢ ውስጥ የሚገኘው፥ የጦር ሰራዊቱ ሙዚየም ውስጥ ሲገባም ይህንኑ ነው የሚታዘቡት። ያልታወሰ የጦር መሪ፣ ያልተዘከረ ባለታሪክ፣ ቦታ ያላገኘ የጦር መሳሪያ ያለ አይመስልም። ሁሉም በወግ በወጉ፣ በስርዓት በስርዓቱ ተሰድሮ፥ እዩኝ እዩኝ ይላል። ታዲያ እንደኢትዮጵያ ካለች የ3000 ዓመት ባለታሪክ አገር ለሄደ ሰው ቁጭቱ ብዙ ነው። ‘ሁሉም የቀደመውን አጥፍቶ የራሱን ለማድመቅ በሚሽቀዳደምበትና የአገሪቱን የታሪክ ዕድሜ ለመቀነስ በሚራኮትበት ሁኔታ ስንቱ ታሪክ ተንኮታኩቷል? ስንቱ ባለታሪክ ተፈቅፍቋል?’ ያሰኛል። ዛሬም የታሪክ ሽሚያ ላይ መሆናችን ያንገበግባል።
‘አይ አምስተርዳም’

ስለአምስተርዳም በምስል ታግዞ የሰማ፥ ወይም አምስተርዳምን ያየ ‘I AmSterdam’ የሚለውን የተቀረጸ ጽሁፍ ያስባል። እኔ ገና ከአውሮፕላን ማረፊያው ወጥቼ ታክሲ ፍለጋ ስሄድ ነበር የተመለከትኩት። ኋላ ግን፥ ወደ ሴንትራል አምስተርዳም ዘልቄ፣ ውስጥ ውስጧን ጎራ ስል፣ ‘ቡና’ ቤቶቿን ስመለከት፣ በየጉራንጉሩ ስሽሎከሎክ፥ …በአማርኛ “አይ አምስተርዳም” አልኩ። – I AmSterdam!? 🙂የአመለካከት ለውጥ ውጤቶች
መመለስ
ረጅም እድሜ ለመመለስ!