ከዘመን እግር ስር እንዳንወድቅ፥ የዘመኑን ለዘመኑ እንተውለት!

በአንድ ከተማ ውስጥ፥ ‘ትንቢት መናገር እችላለሁ።’ ብሎ በሀሰት የጉራ ወሬ የሚነዛ አንድ ወጣት ነበረ። የነብይነቱ ነገር ተዛምቶ ንጉሱ ጆሮ ይደርስና፥ “ጥሩት እስኪ ይህን መናጢ። እውን ነብይ እንደሆን፥ ይተንብይልና!” ይላሉ። ወጣቱ ተጠርቶ ንጉሱ ፊት ይቀርባል። ጥሪው ወጣቱን ኩራትና ጭንቀት መሀል ከትቶት፥ እጅ ከመንሳቱ “እንግዲያው ዘመኑን ተንብይልን” ይሉታል። የቤት ስራውን ተቀብሎ ወጣ። ለጉራ ያወራው ነገር ሕይወቱን ንጉስ ዳጃፍ ጥሎበታልና ትንቢቱን ካላደረገ ሰላም እንደማይሆን አውቋል። እምጥ ይግባ  እስምጥ፥ ተጨነቀ።

መንገድ ላይ ቀበሮ ታገኘውና፥ “ምን ሁነህ ነው?” ትለዋለች። “ሲያቀብጠኝ ትንቢት አውቃለሁ ብዬ ጉድ ሆንኩ።” ይላታል። “ችግር የለም። እኔ እረዳሃለኋ።” አለችው። “ኧረ ‘ባክሽ?” ባለማመን ጠየቀ። “የተጠየቅከው ትንቢት ምንድን ነው?” አለች ቀበሮ። “ዘመኑን ተንብይልን ነው ያሉት ጌቶች” አላት። “ይሄማ ቀላል ነው። ግን አንድ ቃል ግባልኝ?” አለች። “ምንድን ነው እሱ? ከዚህ ጉድ አውጭኝ እንጂ ደግሞ ምን ችግር?” አላት። “የምነግርህ ትንቢት ሰምሮ ስትመለስ ምግብ ይዘህልኝ ትመጣለህ።” አለችው። “ይሄማ ችግር የለውም። መላ በይኝ እንጂ።” አላት። “በል ዘመኑ የጦርነት ነው። ብለህ ንገራቸው።” አለችው።

የጭንቁን ምላሽ በማግኘቱ በወጉም ሳይሰናበታት ሲገሰግስ ሄዶ “ዘመኑ የጦርነት ነው።” ብሎ ተናገረና፣ ትንቢቱ ሰምሮ ነፍሱን አቆየ። ከዚያ ለቀበሮ እጅ መንሻ፥ ከወደ ኋላው ጦር ሸሽጎ ሲገሰግስ ሄደ። ቀበሮም ከሩቅ ሆና በጥርጣሬ ስትጠብቀው ጦሩን ወርውሮ ሳታት። ስላልገደላት ተማርሮ ተመለሰ።

ትንቢቱ በመስመሩ ዝናው ይበልጥ ጨምሮ፥ ድጋሚ ለቀጣይ ዘመን ትንቢት ታዘዘና፣ ከነጭንቀቱ ወደ ቀበሮ መንደር ሄዶ አገኛት። ዐይኑን በጨው አጥቦ፥ “ቀበሪት ሆይ ማሪኝ። በድዬሻለሁ። በባለፈው ስራዬ ተጸጽቻለሁ። እውነት ሀሳቤ እንደዛ አልነበረም። ግን ሰይጣን አሳሳተኝ። እባክሽን ከዚህ ጉድ አውጭኝ። እክሳለሁ።” እትት ብትት አለባት።

“ኧረ ችግር የለውም። አሁንም ትንቢቱ ሰምሮ ስትመለስ ምግብ እንደምታመጣልኝ ቃል ከገባህ የባለፈውን እረሳዋለሁ።” ትለዋለች። “ይኸው ቃሌ! ሙች ስልሽ!” አላት። “በጄ! ዘመኑ የእሳት ነው ብለህ ንገር።” ትለዋለች። ሲገሰግስ ሄዶ “ዘመኑ የእሳት ነው” ብሎ፥ ሰምሮለት ነፍሱን አቆየ። ወደ ቀበሮም፥ በጆንያ ጭድ ሸክፎ መንገድ ጀመረ። እሷም ተንኮሉ ገብቷት ከሩቅ አይታው ወደጉድጓዷ ገብታ ተደበቀች። ደርሶ ጭዱን ሰግስጎ እሳት ለቀቀበት። ቀበሪትም በሌላኛው የጉድጓዱ ጫፍ ወጥታ “ትዝብት ነው” ዓይነት አይታው ተመለሰች።

ከእንግዲህ የነብይነቱ ነገር ካንዴም ሁለቴ ተፈትኖ ያለፈ ነውና፥ ለሶስተኛ ዘመን እንዲተነብይ ታዘዘ። “ወይኔ ጉዴ! ካንዴም ሁለቴ ቃሌን አጥፌ፣ ጭራሽ ግፍ ላደርግባት ሞክሬ ሳበቃማ፥ እንዴት አያታለሁ? በምን ዐይኔ?” ብሎ ቢሳቀቅም አማራጭ አልነበረውምና እንደምንም ሄዶ፥ “መቼስ አያርመኝም! ቀበሪት ሆይ ዳግመኛ ፊትሽ መጥቻለሁ። በደሌ ይቅር የማይባል ቢሆንም አንቺ አስተዋይ ነሽና ማሪኝ። መቼስ ‘ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት’ አይጠፋምና፤ እባክሽን…” ብሎ የምንተፍረቱን ተማጸናት።  ቀበሪትም “ይሁን! ግን አሁንም ትንቢቱ ሲሰምር ምግብ እንደምታመጣልኝ ቃል ግባ።” ትለዋለች።

“ይኸው ቃሌ! ከእንግዲህ ንግግር አላበዛም።” አላት። “በል ዘመኑ የጥጋብ ነው ብለህ ንገር” አለችው። ትንቢቱን አደረሰና ሰመረለት። ሲመለስም ስጋ ይዞላት መጣ። ፊቷ ቀርቦ፥ በደስታና በቃል ጠባቂነት ስሜት እየፈነጠዘ “ይኸው ቀበሮዬ ቃሌን ጠብቄ ይዤልሽ መጥቻለሁ።” አላት።

“አዬ፥ ይህንማ አንተ አይደለህም። ዘመኑ ነው የሰጠኝ። የጦርነት ጊዜ ነው ስልህ፥ ጦር ይዘህልኝ መጣህ። የእሳት ዘመን ነው ስልህ ጭድ ሸከፍክልኝ። ይኸው ዘመኑ የጥጋብ ቢሆን፥ ስጋ ይዘህልኝ መጣህና ‘ይህን አድርጌልሽ’ ልትል ያምርሃል። የሰጠኝ ዘመኑ ነው።” ብላ ያመጣላትን ይዛ ሄደች።

[አንድ ወዳጄ  “ከአንድ አባት የሰማሁት” ብሎ አጫውቶኝ የነበረን ተረት ትዝ ባለኝ መጠን፣ በራሴ አተራረክ የተየብኩት ነው።]

* * *

“ሰውን ማመን ቀብሮ” አለች የተባለላት ቀበሮ፥ ብዙ ተረቶቻችን ውስጥ ሰውኛ ባህርይ ተላብሳ ኖራ ታኗኑረናለች። በየዘመኑ የሚባሉ ሽሙጦችም በ“አለች ቀበሮ” ተዳርሰዋል። አይሞቀን አይበረደንም እንጂ፥ ለሰው ልጆች እኩይ ባህርያት ነቋሪ በመሆንም በብዙ ተረቶች ላይ እናገኛታለን። እዚህኛው ላይ ያለው ነገርም ካለአስረጅ የሰው ልጆችን ባህርይ በየፈርጁ የሚተች ነውና እሱን አንተነትነውም። – ሁሉም የየአቅሙን መልእክት ይምዘዝለት!

ሆኖም መንግስትን እና የመንግስት አዛኝ ቅቤ አንጓቾችን (sympathizers) ባሰብኩኝ ጊዜ ተረቱ ትዝ ይለኛል። “ይህን አድርጌ… ይህን አምጥቼ” የሚሉ ባዶ ሽንገላዎችን፣ ጡዝጦዛዎችን (propogandas) እና የ‘ምርጫ’ (?) መቀስቀሻ ወሬዎችን በተለያዩ አጋጣሚዎች እንሰማለን። ከመንግስት መገናኛ ብዙአን ባሻገር፥ በደጋፊዎችና በዝም ብሎ ኗሪዎች አፍም “ለውጥ” መኖሩ የሚወራበት አጋጣሚ ብዙ ነው። በደፈናው “ከትናንት ዛሬ ይሻላል” ይባላል።

ኗሪዎቹም ብንሆን፥ ‘ይህን አድርጌ፣ ይህን ሰርቼ’ የሚለው ወሬ ሲበዛብን፣ ከበዓሉ ግርማ ዝነኛ ግጥም “ካለሰው ቢወዱት፣ ምን ያደርጋል አገር?” የሚለውን ስንኝ እያጉተመተምንም ቢሆን ዙሪያ ገባውን ማየታችን አይቀርም። አንድ አገር በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢሆን፥ የዛሬ 25 ዓመት እንደነበረው እንዲገኝ አይጠበቅም። (እንደምሳሌ፥ ዓለም በኤሌክትሮኒክስ ቴክኖሎጂ ሲያብድ፥ እኛ በጥቁርና ነጭ ቴሌቪዥን ልንገኝ አንችልም።) ባይንከባከቡትም፣ የተለየ ነገር ባያደርጉለትም፣ የዘመኑን ያህል፥ በንፋስ ተገፍቶም ይሁን በፍላጎት ተጎትቶ፥ ትንሽ ራሱን በዝግመተ ለውጥ ይገፋል።

‘አሉ’ የሚሏቸውን ለውጦች ሲዘረዘሩም የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን በመጥቀስ “ይህን ሰርቶ። ይህን አምጥቶ።” ይላሉ። ያቺ አፍ ላይ ተበይዳ የቀረችው 11 መቶኛ ኢኮኖሚ እድገትም ትነሳለች። ስለሚኖሩባቸውና  ስለኗሪዎቹ ሁኔታ ግድ ሳይሰጣቸው፥ እዚህ እና እዚያ የተዘራዘሩ፥ ከኮብልስቶን እስከ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ ከውኀ መስመር እስከ መብራት መስመር ዝርጋታ ማስፋፊያ ስራዎች፣ ከመንገድ እስከ ህንጻ በደፈናው በጅምላ ይዘረዘራሉ። ‘ኢኮኖሚው’ ብለው በጅምላ በመናገር ስለአማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢ ይደሰኩራሉ።

የውኀ እና የመብራት መጥፋት፣ የስልክ ኔትዎርክ መቆራረጥና የ‘system የለም’ ስራ መጓተቶች፣ የመንገዶች መፈርፈርና መቆፈር፣ የሙስናና የአገልግሎት ጥራት ነገር ሲነሳ የመንግስት ቢሮዎቹን በተናጥል እንድንጠይቅ መገፋፋትም ፋሽን ሆኗል። እንዲያውም የመንግስት ወዳጆች፥ ከሰፊው ሕዝብ ጋር፣ ሽፋን ለመስጠት፥ የመንግስት ቢሮዎቹን በችርቻሮ – ስለመብራት፥ መብራት ኃይልን፣ ስለስልክ ቴሌን እና ወዘተ – ሲያማርሩ ይሰማል። ሰፊው ሕዝብም እንደዚያው እንዲያደርግ  መገፋፋትም አለ።

“መንግስት ምን አደረገ? ኤልፓ ነው እንጂ” “መንግስትን ተዉት፥ ቴሌ ነው እንጂ” በሚሉ ወሬዎች ባለስልጣን መስሪያ ቤቶቹን ከመንግስት ለይተን እንድንመለከት ይገፋፉናል። (እጅ ሲሰርቅ ባለ እጁ ይወቀሳል፣ ይቀጣል እንጂ፤ እጁ ላይ ለብቻው ምን ይደርሳል? ምላስ ቢሳደብስ ለብቻው ይቆረጣል? ወይስ ነገሩ ጉንጭ አልፋ ሆኖ እንዲቀር ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ነው?)

ስለረኀብ ሲነሳ፥ የአየር ንብረት ለውጥ ሀላፊነቱን እንዲወስድ ይሰብካሉ። “’ድርቅ (drought) የዝናብ መቅረት እንጂ የምግብ መጥፋት (famine) አይደለም። ድርቅ በአየር ንብረት ለውጥ ሊከሰት ይችላል። ረኀብ ግን የሰው እጅ አለበት። ዛሬም ዝናብ ተደግፈን፣ ከማሳ ወደ አፍ ነው የሚኖረው።” ስንል፥ “የፀረ ልማቶች ወሬ ነው እንጂ ሌላም ዓለም ይራባል።” ይሉናል። ስለ ስደት ሲወራ ደላሎችን በጅምላ ያወግዛሉ።

ለ25 ዓመታት አንቀጥቅጦ ሲገዛ የኖረ መንግስት አመሻሽ የዘረጋው ባቡር መንገድ ሳይቀር “ባቡር አሳየን” ይባልለታል። (ምኒልክ ያሳዩት ባቡር ተረስቶ። በነገራችን ላይ፥ የባቡር መንገዱ ውስብስብነት እንጂ ቀላልነት አይገባኝም። ይህንንም የተረዳሁት የሌሎች አገራትን መንገድ አሰራርና ቅርጽ ተመልክቼ፣ ሊሆን ይችል የነበረውን ሳስብ ነው።) የትምህርት ጥራቱ ጉዳይ ከቁብ ሳይገባ፥ በቁጥር የበዙትን ዩኒቨርስቲዎችና ተመርቀው ቤት የሚውሉትን ተማሪዎች ቆጥሮ ጉራ ይነዛለታል። …የዘመንን ትሩፋቶች ለመንግስት እንሰጣቸዋለን።

ይልቅስ ሀሳብን በነጻነት እንዳይገልጹ ማፈን፣ ፖለቲከኛውን በ”ሽብርተኛ” ታርጋ ማሰር፣ በልማት ሰበብ፥ ሰዎችን ከምቾት ቀጠናቸው ማፈናቀልና ኅልውናቸውን አደጋ ላይ መጣል፣ ነጻ የክርክር እና የውይይት መድረኮች እንዳይፈጠሩ መድከም፣ ስርዓተ ትምህርትን ከጥራት ብዛት የሚያደርጉ አቅጣጫዎችን መትከል፣ ሙስናና ዝርፊያን መሸሸግ፣ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞው የሚያሰማ ሕዝብ ላይ ጥቃትን ምላሽ ማድረግና ሌሎች ግፎች …ከዘመን እግር ስር ይወረውሩናል፥ እናወግዛቸዋለን!

ዘመኑ የሰጠንን ለዘመኑ እንተውለት። በመልካም አስተዳደር ሁኔታ ላይ ይወሰናልና፥ ዘመኑ የሰጠንንም እንደዘመኑ መቀበል አለመቀበላችንን እንፈትሽ!

ሰላም!

P.S. ይህ ጽሁፍ በአዲስ ገጽ መጽሔት ቅጽ 01 ቁ. 03 ታትሞ የነበረ ነው። አዲስ ገጽ መጽሔት በየሁለት ሳምንቱ የሚታተም ሲሆን፥ የቁ.04 እትም ቅዳሜ ታህሳስ 23/2008 ዓ/ም ለንባብ ውሏል። ቢሆንም በማተሚያ ቤት ዙሪያ በተፈጠረ ችግር የተነሳ፥ የእትሙ ቁጥር አናሳ ስለነበር፣ በአንባቢያን ጥያቄ መሰረት፣ አዘጋጆቹ ድጋሚ አሳትመው፥ ዛሬ ገበያ ላይ እንዲውል አድርገዋልና ባለፈው ቅዳሜ ፈልገው ያጡ፥ በቅርብ ያሉ አንባቢያን ሊያገኙት ይችላሉ። ላለፉ እትሞቹ ድረ-ገጹን – www.addisgets.com – ይጎብኙ። የፌስቡክ ገጹን –አዲስ ገጽ መጽሄት /Addis Gets Magazine – ተከትላችሁ ‘like’ን ብትጫኑም አስተዳዳሪዎቹ መረጃዎቹን ያደርሷችኋል።