ሞልቶለት ለተገኘ… ከአመሻሽ ማራኪ ክስተቶች መካከል፥ የፀሐይን ወደ ምህራብ ማቆልቆል ተከትሎ፣ ወደ ቤተ አምልኮ (ቤተ ክርስቲያን፣ መስጊድ…) ሄዶ፣ ግቢ ውስጥ ሆኖ የእፎይታን አየር መሳብ፣ ጭንቀትን መዘርገፍ፣ መረጋጋትን መሰብሰብ፣ በዕምነት ሆኖ ተስፋን መሸከፍ፣ ከአምላክም ከራስም ጋር እኩል እያወሩ እርኩስ መንፈስን ማብሸቅ፣ ፈጣሪን መውቀስ፣ ራስን መፈተሽ፣ መፀፀትና ማመሰገን… ይጠቀሳሉ። (በተለይ የዕለቱ የአምልኮ መርሀ-ግብር ተጠናቅቆና የቀጣዩ ቀን መርሀ-ግብር ሳይጀመር፣ ግቢው ፀጥ ረጭ ሲል)
አመሻሽ ወደ ቤተ አምልኮ የሄደ ሰው ብዙ ዓይነት ትዕይንቶችን ሊመለከት ይችላል። እዚህም እዚያም ብቻቸውን የሚያወሩ አፎች ሞልተዋል። በየልቦቻቸው የሚራገሙና የሚዝቱ፣ በፀፀት የሚብሰከሰኩ፣ በምስጋና የሚፍነከነኩ፣ ስለነገ እየፀለዩ ነገን ከሩቅ እያዩ የሚደሰቱ፣ “የማታ እንጀራ” የሚለምኑ፣ የሚያማርሩ፣ የሆነ ዐይነት ከባድ ሸክም ከላያቸው ላይ እያስራገፉ ያሉ የሚመስሉ፣ ስለአገር ሰላም የሚማልዱ… ብዙ ዓይነት ሰዎች ይታያሉ። በየትኛውም ዓይነት ስሜት ውስጥ ሆነው ቢሞክሩት፥ እርጋታውና እርካታው አይጠረጠርም።
አማኝ ባይሆኑ እንኳን እግር ጥሎ አመሻሽ ዘው ቢሉ፥ ኢአማኒነት ተራግፎ ባይመለሱም በጥሩ መንፈስ ውስጥ ሆኖ መመለስ የሚቸግር ነገር አይደለም። በዓለም ላይ ስንኖርም፥ በዓለማዊነት አስተምህሮ ሳይቀር፣ ስለተስፋ ይሰበካል። ስለመረጋጋትና ጭንቀትን ስለማስወገድ መፍትሄ ጥቆማ ዓለም ይጨናነቃል። መበልጸግን ተከትሎ ስለሚጠፋ ሰላምና መረጋጋት ይሰበካል። ስለስበት ሀይል ይወራል። ከዛሬ ነገ ስለመሻሉ በተሰፋ ይነገራል። ሁሉም በየፊናው ደህንነቱን ለማረጋገጥ ስለጥበቃው ጥንካሬ ይዳክራል። ጥሪት መቋጠሪያ አጫጭር መንገዶችን ኀሰሣና ማስተዋወቅ ላይ ይደክማል። ብዙ ብዙ… መካሪውና ምክሩ ብዙ ነው። ምስጢሩና መንገዱ የትየለሌ ነው።
በየቤተ እምነቱም እነዚህ ጉዳዮች ይሰበካሉ። አማኞች ከአምላካቸው ጋር ሲነጋገሩ፥ በልባቸው “እደመጣለሁ” የሚል እርግጠኝነትና፣ “ይረዳኛል” የሚል ፅኑ ተስፋ አለ። “አድርጎልኛልና” ብለው ለምስጋና የሚመጡም አሉ። ሰማይ ተደፍቶ ትከሻቸው ላይ የወደቀ ሲመስላቸው ፈጣሪ ያቀናናል ብለው ያምናሉና ይሆንላቸዋል። ቢጎድል እና ቢሞላም የፈጣሪያቸውን መኖር ካሰቡ ቀጥሎ ስለሚኖራቸው እንቅስቃሴ መስመር መያዝ ጥሩ አጋዥ ይሆንላቸዋል። ከዚህም በላይ፥ ከሰው አእምሮ በላይ የሆኑ ችግሮቻቸውን ለፈጣሪ በመንገር ከእርሱ እርዳታ ማግኘት እንደሚችሉ ያምናሉ። ይህ የመረጡትና የተሰበኩት የሕይወት መመሪያቸው ውጤት ነውና ያተርፉበታል። (እዚህ ላይ መጥቀስ የፈለግኩት፥ ሄዶ በመቀመጥ ብቻ የሚገኙትን ጥቅሞች ነው።)
ታዲያ ይሄንን የሰው ልጆች እምነት፣ ሰላም፣ መረጋጋትና ተስፋ ለመንጠቅ ላይ ታች የሚሉ ሰዎች እንዴት የተረበሹና በክፋት ውስጥ ያሉ ናቸው? የሰዎችን የሕይወት መመሪያ ማፋለስን የራሳቸው የሕይወት መመሪያ አድርገው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች በእንዴት ዓይነት ጭንቀት ውስጥ የሚገኙ ናቸው?
አለማመን ምርጫ ነው። የሰዎችን እምነት ለመንጠቅ መባከን ግን ከራስ ወዳድነትም አልፎ ሌላ ጠሊታነትን የሚጠይቅ መርገምት ነው። ስለሚያምን “ሞኝ” በተባለው ሰው አኗኗር ላይ ክፉኛ መቅናትንም ይጠይቃል። አያድርስ ነው!
የፈጣሪ ሰላምና ፍቅር ይብዛልን!