ከ6 ዓመታት በፊት…

ለመጀመሪያ ዓመት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የStatistics ኮርስ አስተምር ነበር። በትምህርቱ ይዘት መሰረት ‘Sampling’ የሚል ምዕራፍ አለው። በእለቱ የማስተምራቸው ስለ ‘Random sampling techniques’ ነበር። (Statistics ኮርስ ወስዳችሁ የምታውቁ ሳታውቁት አትቀሩም።)

ጠመኔዬን ቀስሬ፥ አፌን ከፍቼ ላንቃዬ እስኪተረተር ድረስ እጮሃለሁ። ዐይን ዐይናቸውን እያየሁ ቅሬታ ያለ ሲመስለኝ፥ በራሴ ጊዜ ለማስረዳትና ነገሩ ለማብራራት እሞክራለሁ። እነሱ እቴ “ገብቷችኋል?” – ዝም! “አልገባችሁም?” – ጭጭ! …ይሄ በጣም ከሚያበሽቁት ነገሮች አንዱ ነበር። [ያው የመማማሪያ ቋንቋው እንግሊዘኛ ቢሆንም፣ የመረዳዳት ችግርም ስለነበር፥ ጉራማይሌ ነበር። በአማርኛ ላውራችሁ።]

Random Sampling Techniquesን ማስረዳት ጀምሬ፥ Cluster Sampling እና Stratified Samplingን በጋራ ለማስረዳት ፈልጌ ነገሬን ጀመርኩ። (ትምህርቱን ለማታውቁት፥ Cluster Sampling የሚባለው፣ ዋናውን ስብስብ ወደተመሳሳይ መደቦች ከፋፍለን፥ ከተመሳሳዩ መደቦች የተወሰኑትን… እንዳስፈላጊነቱ፥ ከመረጥናቸው ንዑስ መደቦች የተወሰኑትን አባላት ለናሙና መምረጥ የምንችልበት የናሙና አወሳሰድ ቴክኒክ ነው። በአንጻሩ Stratified Sampling ሲሆን ደግሞ፥ ዋናውን ስብስብ የተለያዩ ባህርያት ወዳላቸው መደቦች ከፍለን፥ ሁሉም ስለሚለያዩ፣ ከሁሉም ለመወከል የተወሰኑ አባላትን ለናሙና የምንመርጥበት የናሙና አወሳሰድ ቴክኒክ ነው።)

የቁጥር ትምህርት አብዛኛውን ተማሪ ያደናብራልና፥ ምንም እንኳን ሀልዮቱን የማስረዳ ቢሆንም፥ የምሳሌ መዓት መደርደር ነበረብኝ። በምችለው መልኩ በምሳሌ ሳስረዳ ቆየሁ። (ከዚህ በታች የምጽፈው የነገሩ ጉዳይ የሆኑትን ሁለቱን ብቻ ነው።)

Cluster Sampling ሳስረዳ፥

“ለምሳሌ የእኔን የማስተማር ብቃት በተመለከተ የተወሰናችሁትን መጠየቅ ፈልጎ ከሴትም ከወንድም የተወሰኑ ሰዎችን መምረጥ የሚፈልግ ሰው። መጀመሪያ ክፍሉን ወንድ እና ሴት አድርጎ ይከፍላል። ባንድ ክፍል ውስጥ ስለማስተምራችሁ ሁላችሁም በመማር ማስተማሩ ረገድ፥ ከግል አመለካከት ልዩነት ውጭ፣ ተመሳሳይ ምዘና ሊኖራችሁ ይችላል። ስለዚህ ሁለቱ ቡድኖች clusters ይባላሉ እና cluster sampling እንጠቀማለን።” ምናምን ምናን…

Stratified Sampling ሳስረዳ፥

“ከዚህ ክፍል ውስጥ መውሰድ የተፈለገው ናሙና በስርዓተ ጾታ ጉዳይ ላይ ጥናት ለማድረግ ቢሆን ኖሮ፣ ክፍሉን ወንድና ሴት ብሎ ቢደለድለው፥ በፆታ ጉዳይ ላይ የወንዶቹ እና የሴቶቹ አመለካከት ተመሳሳይ ይሆናል ተብሎ ስለማይጠበቅ፥ ንዑስ ቡድኖቹ strata ይባላሉ።” ዲዲ ዲዲ ዲዲ…

መልሼ ለCluster Sampling ምሳሌ ስጨምር፥

“ለምሳሌ ግቢው ውስጥ ስላለ የተማሪነት ሕይወት ማጥናት የሚፈልግ ሰው፥ ቢፈልግና እንደየመጣችሁበት አካባቢ ቢደለድላችሁ፣ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ አመለካከት ሊኖራችሁ ይችላል ተብሎ ስለሚታሰብ cluster sampling ሊጠቀም ይችላል።”

ደግሞ ለStratified Sampling ምሳሌ ልጨምር ብዬ…

“ለምሳሌ የባህል እሴቶችን ማጥናት የፈለገ ሰው፥ እንደየመጣችሁበት አካባቢ ቢደለድል የሁሉንም ባህል የሚያካትት ንዑስ ቡድን መመስረት ይችላል። እነዚያ ቡድኖች strata ይባላሉ።”

“ገባችሁ?” ዝም!

መረዳታቸውን በድካሜ መዘንኩትና፥ ሰዓቱም ስለደረሰ ወጣሁ። ድክም ብሎኝ ቢሮዬ ገብቼ ብዙም ሳይቆይ የቢሮ ስልክ አቃጨለ።

“ሃሎ”

“ሃሎ ጆኒ፥ ደህና ነህ?”

አለቃዬ ነበረች። አጠር ያለ ሰላምታ ተለዋውጠን ስናበቃ፥ እንደመሳቅ አለች። ካሳሳቋ ቀጥሎ የምትለው ነገር ለራሷም እንዳልተዋጠላት ገምቻለሁ። ‘assignment ባላዘዘችኝ ብቻ’ ብዬ ሳስብ፥ “ና ልልህ ነበር። ግን ስንገናኝ እናወራለን።” አለች።

“ምንድን ነው እሱ? ፈለግሽኝ?”

“ምን እባክህ፥ የዘንድሮ ተማሪ እኮ የማያመጣው ነገር የለም። አንተን በደንብ ስለማውቅህ እና ክሳቸው ላይ ምን ዓይነት ፅኑ አቋም እንዳለህ ስለማውቅ…”

ደነገጥኩ።

“ምን አሉ?”

“አሁን ሁለት ልጆች እኔ ጋር መጡና፥ ክፍሉን በዘር፣ በሀይማኖት እና በፆታ ከፋፍሎ ነው የሚያስተምረው’ ብለው ቅሬታ አሰምተው ነው። ባላምንበትም እንደው ሳታስበው ከሆነም ብዬ ነው።” አለችኝ።

መሳቅ ወይም መበሳጨት እንዳለብኝ አላውቅም ነበር። እንደፈለጉት ነበር የሰሙኝ። ስንገናኝ ተነተንኩላትና ተሳሳቅን። አብረን አዘንን።

“ግን ወዴት እየሄድን ነው ጆኒ? ከዓመት ዓመት የተማሪው ሁኔታ እየባሰበት መጣ። ትምህርቱን እርግፍ አድርገው ፖለቲካውን ነው የሚያስቡት እኮ።” አለች።

መልስ አልነበረኝም። ብቻ ግን ሀሞቴ ፍስስ አለ! ጥረቴን ቀሙኝ!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s