
ዛሬ ምሽት አንድ ሰዓት ገደማ፥ ተሽቀዳድሜ ታክሲ ውስጥ ስገባ፥ “የሸገር የአርብ ምሽት ልዩ ወሬዎች” ጭራ ያዝኩት። አቅራቢው ወንድሙ ኃይሉ ነው። ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ በዲግሪ ተመርቃ ድንች ቀቅላ ስለምትሸጥ ሴት ነበር የደረስኩበት የመጨረሻው ወሬው።
“ሃና በተመረቀችበት ሞያ ሰርታ፣ ራሷን እና ቤተሰቧን፣ ከፍ ሲልም ሃገሯን ለማገልገል ብትመኝም፥ ከድግሪዋ ጎን የመጣው ፈተናዋ አንድ ዐይኗን የነጠቃት፣ ጉንጯን ያሳበጣት ህመም ደረስኩበት ያለችውን ህልሟን አራቀባት። ባመለከተችባቸው መስሪያ ቤቶችም ተቀባይ አሳጣት።” አለ ዜና አቅራቢው።
(ልብ አርጉ! “ባመለከተችባቸው መስሪያ ቤቶችም ተቀባይ አሳጣት” እንግዲህ በዝምድና እና በፖለቲካ ተሳትፎ ተደልድለው ከሚተርፉ ቦታዎች መካከል ነው እሱም። ምናልባትም ቀጣሪ ማጣቷ፥ “መቼስ ከዚህ ጋር በተያያዘ ቢሆን ነው ማይቀጥሩኝ እንጂ” የሚል ስሜት ፈጥሮባትም ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ፥ አሁን ህዝባዊ ነውራችን “ግፈኛና ሙሰኛ ቀጣሪዎችን” ያሳርፋቸዋል።)
የእርሷ ድምጽ እንዲህ ተከተለ…
“ፊቴ አባብጦ ነበረ። ሲያይህ ‘ምጽም’… ምናምን፣ ከንፈሩን የሚመጥብህ ሰው አለ። ብቻ ያስጠላል በቃ። እና የተወሰነ ጊዜ ሻሽ አድርጌ ነበር የምንቀሳቀሰው። ሻሽ ሳደርግ ሲብስብኝ ገልጬው መሄድ ጀመርኩኝ። ሀኪሞች ያሉት የካንሰር ዘር ነው።”
ይህ ፈተናዋ ወደ ቆሎ ሻጭነት እንደመራትና “አሁን ግን ውቤ በረሀ በመፍረሱ ምክንያት የቆሎው ነገር በጣም ስለቀዘቀዘብኝ ወደ ድንች ዞሬያለሁ። ድንች እሸጣለሁ።” ማለቷ ተሰማ።
ጋዜጠኛው ቀጠለ። “ስለሃና ሰምተው ተደንቀው ያወሩልኝ” ብሎ የአንደኛውን ወጣት ድምጽ እንዲህ አስገባው።
“ይገርምሃል ብዙ አሉ። በዲግሪ ተመርቀው የስራ እድል ግን የሚከፍትላቸውና የሚቀጥራቸው አካል በማጣት ቤት ውስጥ የተቀመጡ አሉ፥ ተሳስረው። ነገር ግን ይህቺ ልጅ ዲግሪ አለኝ ብላ ይህንን ስራ ሳትንቅ ለመስራት በመቻሏ በጣም ትልቅ አድናቆት ነው ያለኝ ለልጅቷም። የሚገርምህ ነገር ሰው የሚማረው ኑሮውን ለማሻሻል ነው። ቤተሰቡን ለማሻሻል ነው። ራሱን ለመለወጥ። በቢኤ ዲግሪ ተመርቃ ይሄ ስራ ትንሽ ነው ሳትል እዚህ ቦታ ላይ መስራቷ በራሱ ትልቅ ነገር ነው።”
[እርግጥ ነው። መደነቅ ያንስባታል! …ስራ ጠፍቶ ኮብልስቶን በተማረ ስትጠረብ፣ በሬም በባለዲግሪ (ግብርና የተማረ ሆኖም አይደለም) ስትገፋ፥ ዘንድሮ “50ኛ ዓመቴን አከብራለሁ” ባለው ቴሌቪዥናችን ተመልክተን “ጉድ” ብለናል። (በ2002 ዓ/ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የምረቃ በዓል ላይ፥ …ተመራቂው ስራ እንዳይንቅ እንደማሳሰቢያ ተነግሮ፣ ኮብልስቶን መጥረብ በመንግስት ባለስልጣን መጠቆሙንም አስታውሳለሁ።) …መሬት በባለ ዲግሪ ስትጎለጎል አይተን፥ የሰሪዋን ሞራል እያደነቅን የፖሊሲውን ነገር ተችተናል። በእርግጥ ስራ መልካም ነው። ከጥቃቅን ስራዎች አንስቶ በተማሩ ሰዎች ቢሰሩ የሚደነቅ ነው። ሆኖም ግን ስልጠናው አሁን የሚሰሩትን ስራ ሲያግዛቸው አልተመለከትንም። “ማስተርስ ዲግሪ አለኝ” ብሎ እርፉና ጅራፉን አሳርፎ አስተያየት የሚሰጠው ሰው አስቆጭቶናል። ሲሆንስ፥ እርሻውን ሲያዘምነው ብናይ “አበጀህ” እንለው ነበር።]
ጋዜጠኛው በዚህም ሳያበቃ፥ “የሃናን ድንች በዳጣ እያጣጣሙ ያገኘኋቸው ሁለት ማስቲካና ሲጋራ ሻጭ ሴቶች ስለድንቹ እንዲህ ብለዋል” ብሎ፥ የልጆቹን ድምጽ አስገብቶልናል።
አንደኛዋ….
“ድንቹ ቆንጆ ነው። በጣም ነው የሚጣፍጠው። ድንቹን ወደን ነው የምንበላው፤ ስለሚጣፍጥ። ዳጣውም በጣም ነው የሚጣፍጠው።” (ምስኪን! ሲጋራና ማስቲካ አዙራ፥ ባይጣፍጣትስ ከድንች ውጭ አማራጭ ያላት ይመስል። ግፋ ቢል ጮርናቄ ወይ ሻይ በዳቦ ቢተካላት ነው።)
ሌላኛዋ ቀጠለች….
“ቆንጆ ነው ድንቹ… ይጣፍጣል። ዳታውም ራሱ ይጣፍጣል። ቆንጆ ነው። የእሷ ደንበኛ ነኝ። ነጋዴ ነኝ። ሌላ ቦታ እየሰራሁ መጥቼ እዚህ ጋ በልቼ ነው ወደ ቤቴ የምሄደው።” (ደግሞ ሌላው አንጀት የሚበላ ቃል ከዚህች ምስኪን አፍ ውስጥ ሾልኳል። ከተራ አስከባሪ ጋር እየተሯሯጠች ጀብሎ ሸክፋ ማስቲካና ሲጋራ እየሸጠች፣ እኩል “ነጋዴ ነኝ” ስትል አንጀት አይበላም? ….በነገራችን ላይ፥ ሃና አራቱን ቅቅል ድንቾች ከዳጣ ጋር በ4 ብር ነው የምትሸጣቸው።)
ወንድሙ፥ የቀን ስራ እየሰሩ ኑሮን ለማሸነፍ የሚጥሩት የሃና እናት ወይዘሮ ዘነበችንም አናግሮ “ከባለድግሪዋ ልጃቸው ስለጠበቁት እና ስለሆነው አሁንም ስለሚመኙት ደግሞ የነገሩኝን ስሙ።” አለና ድምጻቸው እንዲህ ቀጠለ…
“ልጄ እንጀራ ታመጣለች ብዬ… ልፋቴን ሁሉ ታሳልፋለች ብዬ… የተቸገርኩትን ችግር ታወጣለች ብዬ ነበር ያሰብኳት። አሁን እሷ… ጓደኞቿ ሁሉ ስራ ላይ፣ እንጀራ ላይ ቁጭ ብለው፥ እሷ እንጀራው ሲጠፋ እግዚአብሔር ይመስገን ቅባቷን ትቀባለች፣ …ለወንድሞቿ ዳቦ ታተርፋለች፣ ለራሷም ሳሙና ትገዛለች፣ ትለብሳለች። የተሻለ ደሞ እግዚአብሔር (ካለ) ከዚህ ትበልጣለች። ከእነርሱም በልጣ ትሄዳለች ብዬ አስባለሁ።” አለመስማትን የሚያስመኝ ሲቃ ቀላቅለው ነው የሚያወሩት። (እንግዲህ የእኒህን ዓይነት ምስኪን እናቶችን እምነት፣ ተስፋ እና መጽናኛ ለመቀማት ነው የአገሬ ‘ኤቲየስቶች ነን ተብዬዎች’ ላይ ታች የሚሉት። – በልባቸው የማያምኑትን ሳይሆን፣ አማኒያንን የሚዘረጥጡትን ነው።)
“ሃና፥ አንድ ዓይኔን የቀማኝ፣ ዲግሪዬን አቅም ያሳጣብኝ ህመም ቢፈትነኝም፣ የሰው ከንፈር ቢያስመጥጥብኝም፣ እጅ አልሰጥም። ሁሉንም በድፍረት እጋፈጠዋለሁ። ….ነገሮችን መድፈር ደስ ይለኛል። ነገሮችን በመድፈሬ ነው እንጂ እንደሌላው አካል ጉዳተኛ ሲንቁኝ፣ ሲያንቋሽሹኝ፣ እያዩኝ ሲያማትቡ ምናምን ቤቴ የምቀመጥ ቢሆን ኖሮ እኔ እስከዛሬ በቃ ምንም አላውቅም ነበር።” ትላለች።
(እግዚኦ የእኛ ነውር ብዛቱ! ይህኔ ልመና ወጥታ ቢሆን ኖሮ ለማበረታታት እና ለማስተባበር የሚችለን የለም ነበር። አንሶላ አነጥፋ “እርዱኝ” ብትል ኖሮ ኪሳችንን ለመፈተሽ አንደኛ እንሆን ነበር።
እንዴት ነው “ሎተሪስ የዛሬ” እያለች የምትጮህ ዐይነ ስውር ምስኪን፣ እና ቆፍጠን ያለ ለማኝ፥ ጎን ለጎን (እሷ ገበያ ቃርሚያ ቆማ፣ እሱ መጽዋች ጥበቃ ተጎልቶ) ስናይ ምላሽ የምንሰጠው? …. አናውቅም፥ ለለማኙ አንድ ብር አውጥተን ለመጣል ካጎነበስንበት ስንነሳ በእጇ የያዘችውን ሎተሪ ለመበተን ትንሽ እስኪቀረን ድረስ ከእጇ ላይ አናግተንባት? (ካንዴም ሁለቴ አይቼ የማውቀውን መጥቀሴ ነው።)
“ልስራ” ብላ ስራ ፍለጋ ስትወጣ ግን የሚጠቋቆምባት ብዛቱ። ያኔ በተመረቀችበት የት/ት መስክ ልትሰራ ስትወጣ አግላዩ እንዳልበዛ፥ ምነው ዛሬ ድንች ስትቀቅል ከበቧት? ካላማጭ? ወይስ ለከንፈር መጠጣ እና ለመደነቅ ቅርብ ስለሆንን?
እንዴት ነው ሴት ወያላ ወይ ሊስትሮ ስናይ የምንሆነው? እንዴት ነው ትንሽ ዘነጥ ያለ ወያላ ሲያስተናግደን የምንሽቆጠቆጠው? እንዴት ነው አፉ የሚተሳሰር ባላገር ወያላ ላይ የምንጨማለቀው?)
.
.
ጋዜጠኛው “ሃና ወደፊት ጸዳ ያለ ድንች መቀቀያና መሸጫ ቤት የመከራየት፣ ከፍ ሲልም የመስራት ሃሳብ እንዳላት፣ አንድ ዓይንሽን ብታጪም ግድ የለም። በተመረቅሽበት ሞያ በታሪክ፣ ታሪክሽን እቀይርልሻለሁ የሚላት የግልም ሆነ የመንግስት ተቋም ብታገኝ ደግሞ የበለጠ እንደምትደሰት ነግራኛለች።” በማለት ወሬውን ቋጭቷል።
* * *
ማታ አረቄ ይዤ የተነሳሁትን ፎቶ ፌስቡክ ላይ ” “ኧረ ሻይ ነው” ብዬ ልቀውጠው? lol. አሁን እንደው፥ እንዴት ያለ፣ ረቂቅ አገራዊ ጉዳይ የምቀምስ አልመስልም?!” ከሚል ካፕሽናዊ ጨዋታ ጋር፥ መለጠፌን ተከትሎ፥ የሁለት ወግ አጥባቂ ወዳጆች መልእክት በውስጥ ደረሰኝ። አንዱ ዘለግ ያለ ስብከት ቢሆንም፥ ፍሬ ሃሳቡን ስንፈለቅቀው “ጌታን ተቀበል” የሚል ነው። ሌላኛው ደግሞ ወቀሳ አይሉት ሃሜት (ራሴን ለራሴ! ሃሃሃ) ግራ የሚያጋባ ነገር ነው። ወድጄና ፈቅጄ፣ ራሴ ላይ ላደረግኩት ነገር ነው እንግዲህ ይሄ ሁሉ። ባይሆንስ፥ ኑሮዬን ያውቁልኝ ይመስል። ውሎዬን ይውሉልኝ ይመስል ነው።
አሁን እንደው በፈጣሪ፥ ይሄ ይሄ ሲሰማ፥ እንኳን መጠጥ መርዝስ አያሰኝም ትላላችሁ?
“ለሳንባዬ አስቤ እንጂ የሚያስጨሱ በጣም ብዙ ምክንያቶች አሉኝ።” አለ ወዳጄ።
😦 😦
P.S. ፎቶ ከDe Birhan ገጽ የተገኘ።