ቫላንታይንስ ቀን…

ፍቅርን መካፈል፣ ፍቅርን መጋራት፣ ፍቅርን መዘከር፣ ፍቅር መስጠር፣ ፍቅርን ማውራት ሸጋ ነው። ዓመቱን ሙሉ በኑሮ ዱብ ዱብ እና በየእለት ንትርክ ተጋርደው የተዘነጉ የፍቅር አጋሮች፣ ወዳጆች እና ቤተሰቦች፥ በዚህ ቀንም ቢሆን ከወደቁበት፥ ሳይረገጡ በፊት ኧፈፍ ተደርገው፣ ትቢያቸው ረገፍ ረገፍ ተደርጎ ወግ ማዕረግ ቢያዩ ደስ ይላል። የእናቶች ቀንን የቀዳን፣ የሴቶች ቀንን የቀዳን፣ የሌላ የሌላውንም ቀን የቀዳን… የወደደ የፍቅር ቀንን (valentine’s day) ቢቀዳ ክፋት የለውም። ባይሆን፥ ወግ ወጉን ብቻ ተይዞ፣ ስነስርዓታዊ (ceremonial) በሆነ ዘይቤ ስንተራመስ መጠቋቆሚያ እንዳንሆን፥ ከቀይ ልብስ ባለፈ ልቦቻችንን እና አኗኗራችንን ስለማቅላት እንምከር።
ቫላንታይንስ ቀን ማለት ማስመሰል የሚሰበክበት ቀን አይደለም።
ቫላንታይንስ ቀን ማለት ግድ ከየቤት ውጭ የሚታደርበት ቀን ማለት አይደለም።
ቫላንታይንስ ቀን ማለት፥ ወንድ ሴቷን እንደሚያዝናና እና እንደሚጋብዝ ተደርጎ የሚታሰብበት ቀን አይደለም። (ሰምታችኋል “ከወደድከኝ ግሎባል ሆቴል ውሰደኝ” የሚል አሳፋሪ ዘመኑን ያልዋጀ ማስታወቂያ?)
ቫላንታይንስ ቀን ማለት፥ ሴቶች የወንድ ጥገኛ ናቸው ብለን የምናቀነቅንበት ቀን አይደለም።
ቫላንታይንስ ቀን ማለት፥ ተለክተው ተበድረው ቀይ ቀሚስ የሚያስቀድዱበት ቀን ማለት አይደለም።
ቫላንታይንስ ቀን ማለት፥ ስጦታ ስላልተሰጠን የምንኮራረፍበት ቀን አይደለም።
ቫላንታይንስ ቀን ማለት፥ እስከዛሬ ያለው በደል እና ግፍ በዝምታ ታልፎ ለዚህ ቀን ታርቀን ከነገ ጀምሮ ወይ መልሰን የምንዘጋጋበት፣ አልያም ሁሉን ረስተን አዳፍነን የምንዘልቅበት ቀን ማለት አይደለም።
ሲሆንስ፥ ይህን ቀን ታክከን ስለሆነልን ነገር ብናመሰግን፣ እድለኛነታችንን ብናደንቅና፣ ፍቅራችን እንዴት ወደተሻለ ደረጃ እና ሁኔታ ማሳደግ/ማሻገር እንደምንችል ብንመክር ዓላማውን አይስትም።

flowers-roses-red-rose-1680x1050-wallpaper_www.wallpaperhi.com_66

Happy Valentine’s Day!
ፍቅር ይብዛልን!