ተስፋዬ ገ/አብ በዕውቀቱ በስም ዙሪያ የፃፈውን ፅሁፍ በማጣቀስ በዕውቀቱን የማንነት ቀውስ ውስጥ እንዳለ የሚገልፅ ፅሁፍ ፅፏል፡፡ከበዕውቀቱ ፅሁፍ ውስጥ በዕውቀቱ የግል ማንነቱን የፈታበትን መንገድ መመልከት እንደምንችል ፅሁፉም ከማንነት ጋር የሚያስተሳስረው ጉዳይ እንዳለ እኔም አምንበታለሁ፤ በቀደመው ፅሁፌም ገልጫለሁ፡፡
በመሰረቱ ማንኛውም ሰው የማንነት ጥያቄ አለበት፡፡ የማንነት ጥያቄ የሰው ልጆች ሁሉ የሚገጥማቸው የህይወት አንዱ ገፅታ ነው፡፡ ጥያቄው ያለው የማንነት ጥያቄህን እንዴት ትፈታዋለህ የሚለው ላይ ነው፡፡ አንዳንዱ ጥያቄውን በማፈን ለመፍታት ይሞክራል፡፡ አንዳንዱ ከአካባቢው አስተሳሰብ ጋር ራሱን በማላመድ በሌሎች መንገድ ማንነቱን ለመፍታት ይጥራል፡፡ አንዳንዱ የብሄር ፖለቲካ ራዲካሊስት መሆን ለመፍታት ይፍጨረጨራል፡፡ ወዘተርፈ፡፡
እንደበዕውቀቱ ያሉ ጥቂቶች ግን የማንነት ጥያቄን በዘልማድና በኋላቀር መንገድ ሳይሆን በሰለጠነ መንገድ ግለሰብ በመሆን (ሰው በመሆን ይፈቱታል)፡፡ የበዕውቀቱን ለዬት የሚያደርገው ይህን ግላዊ ጥያቄውን አደባባይ ላይ አውጥቶ መልካም ስራ ለመስራት ተጠቅሞበታል፡፡ አስቂኙ ነገር የበዕውቀቱ ግለሰብ መሆን ብዙ ብሔርተኞችን የማንነት ቀውስ ውስጥ ሳይከታቸው አልቀረም፡፡ የቆሙበትን መሰረት ንዶ እንደግለሰብ እንዲቆሙ ሲጠይቃቸው የሚያነበንቡት ተረት ሁሉ ባዶ ሆነባቸው፡፡ ማንነታቸው በቡድን ተረት ላይ የቆመ ነበርና፡፡
እንግዲህ ተስፋዬ በዕውቀቱ የማንነት ቀውስ እንደገጠመው በማሰብ የበዕውቀቱ ቀደምት የጥበብ ስራዎች ውስጥ የቡና አተላ እንደሚያነብ ሰው ሲወራጭ የነበረው ለምንድነው? የበዕውቀቱ አያት ስም ኦሮምኛ መሆኑ ብርቅና ለማንነት ቀውስ የሚዳርግ እንግዳ ነገር ስለሆነ ነው? ተስፋዬ የኢትዮጵያን ህዝብ ሁኔታ አልተረዳውም እንዳልል ቢያንስ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ስለሚከታተል የፖለቲከኞችን ስም ሳያውቅ የሚቀር አይመስለኝም፡፡ በነገራችን ላይ የማንነት ቀውሱ ተስፋዬ ገ/አብን ራሱን የሚመለከት ይመስለኛል፡፡ በትውልድ ቦታና በዘር ቆጠራ መካከል የተወጠረች ባተሌ ነፍሱን ተንኮል በመስራት የሚያሰቃያት ማንነቱን መፍታት አቅቶት ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ ተስፋዬ በዕውቀቱ የሰነዘረበትን በማስረጃ የተደገፈ ጡጫ ለመቋቋም እንዲህ ዓይነት ጭቃ ውስጥ መግባቱ በበኩሌ አቅመ ቢስነቱን ስለሚያሳዬኝ ቢያስቀኝም ያሳዝነኛል፡፡ አቅመ ቢስነቱን ለማወቅ ወደትንተናው ይዣችሁ ልግባ፡፡
በመጀመሪያ ተስፋዬ የበዕውቀቱን “ዳዊትና ጎልያድ” የተሰኘ ግጥሙን በመጥቀስ ግጥሙ ኃይማኖትን የሚያጣጥል እንደሆነ ለማሳዬት ይፍጨረጨራል፡፡ በሱ ቤት ከአክራሪ ኃይማኖተኞች ጋር ሊያጋጨው ነው፡፡ እስኪ ለዳኝነት እንዲረዳን ግጥሙን ልጥቀሰው፡-
እግዜርና ዳዊት አብረው ተቧደኑ
ብቻውን ታጠቀ ጎልያድ ምስኪኑ
አንዳንዱ ተገዶ ለሽንፈት ሲፈጠር
በጥቅሻ ይወድቃል እንኳንስ በጠጠር
ግጥም አንብባችሁ የምታውቁ ሁሉ እባካችሁ የዚህን ግጥም መልዕክት ንገሩኝ፡፡ ጎልያድን የጣለው ዕጣ ፈንታው እንጅ የዳዊት ጠጠር ኃይል ኖሮት አይደለም የሚል መልዕክት አይደለምን በዕውቀቱ ያስተላለፈው?
እንቀጥል…
ተስፋዬ እንዲህ ይላል፡ “ከሚስጥራዊ ስንኞቹ መካከል ጥቂት አገኘሁ” ይልና የሚከተለውን የበዕውቄን ግጥም ይጠቅሳል፡-
በነፍሴ ሰማይ ላይ
ቢሰርቅ ጣምራ ፀሃይ
አንዱን ጋርጃለሁ
ሌላው ደምቆ እንዲታይ
“ምን ማለቱ ነው ብዬ ሳስብ የአቶ በዳዳን ኦሮሞነት ሸሽጎ አያቱ ባልሆነ ስም እየተጠራ መቀጠሉን እየተቃወመ ይመስላል አልኩ” ይለናል ተስፍሽ ባተሌው (እዚህ ጋ እንድስቅ ይፈቀድልኝ ሃሃሃሃ… የምር ይህን ፅኁፍ ስፅፍ ሳቄ እያቋረጠኝ እንደነበር መደበቅ አልሻም)፡፡ እባካችሁ ነፍስ የስጋ ዘርን የምትወክልበትን ይህን በተቃርኖ የተሞላ የስነፅሁፍ ትንታኔ በመፃፍ ላዝናናችሁ ተስፋዬ አጨብጭቡ፡፡ ልጁ “ነፍስ” ብሎ ገጠመ፤ ተስፍሽ “ስጋ” ብሎ ተረጎመለት፡፡ ወይ ጉድ!
ተስፍሽ በማስከተል የጠቀሰው የሚከተለውን የበዕውቄን ግጥም ነው፡-
ቀንድ አውጣ ሆይ!
ውብ ዛጎልህ አማለለኝ
ከጎጆህ ላስወጣህ ነው (ይቅር በለኝ)
‘በዝግ ዓለም ሰማይ ጣራ ነው’ ይባላል
ያለውበት ነው እንጅ ያለቤት መኖር ይቻላል
እንግዲህ ለመሳቅ ተዘጋጁ፤ ተስፍሽ ይህን ግጥም ሲተነትነው እንዲህ ይላል፡-
“እነዚህ ስንኞች ለኔ የሰጡኝ ትርጉም በዕውቀቱ አቶ በዳዳን ከተሸሸጉበት ዛጎል ጎትቶ ለማውጣት መወሰኑን ነበር፡፡ በርግጥም እንደፎከረው ፈፅሞታል፡፡ ያለውበት መኖር እንደሚቻል ለማሳየት ሞክሯል፡፡”
እና ይሄ ሰው አያሳዝንም? ሃሃሃ እስኪ ተመልከቱ… በዕውቀቱ “ያለቤት መኖር ይቻላል፤ የማይቻለው ያለውበት መኖር ነው እንጅ፡፡ ስለዚህ ቀንዳውጣ ሆይ ውብ ዛጎልህን ልዋብበት፤ ያለቤት መኖር ስለምትችል” በሚል ግልፅ ቋንቋ የሰው ልጅ ካለውበት መኖር እንደማይችል በመግለፅ በተለይም ውበትን የምታስሰውን ገጣሚ ነፍሱን ሊገልፃት ሲሞክር፣ ተስፋዬ ግን አማርኛውን ፍፁም ገልብጦ “ያለውበት መኖር ይቻላል” ብሎ ተረጎመው፡፡ ይህ ነገር ግጥም አንብቦ ለማያውቅ ማንኛውም አማርኛ ቋንቋን ለሚያውቅ ሰው ግልፅ ነው፡፡ ወይ ተስፍሽ!
ተስፍሽ ስለአባ ገብረሃና የተፃፈውን ግጥም ጠቅሶ የመተንተን ሙከራ እንኳን ሳያደርግ የልጅ ተንኮል ሞክሮ አልፎታል፡፡ እንዴት ለማያያዝ እንደሞከረ ለራሱ እንኳን የገባው አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ እዚህ ላይ ጊዜ አላጠፋም፡፡
ወደሌላው እንለፍ…
“በተለይ ገዢዎች ላይ ቅሬታና ቂም እየያዘ እንደመጣ የሚጠቁሙ ከጥቂት በላይ
ስንኞቹን ታዝቤያለሁ፡፡ አንዷ እንዲህ ትላለች፡”አልወጣም ተራራ ደመናውን ላብስ
ቀስተ-ደመናውን ሽቅብ ልቀለብስ
አልዋስም እኔ ካቡነ ተክሌ ክንፍ ከያዕቆብ መሰላል
እኔ መውጣት ሳስብ ሰማዩ ዝቅ ይላል… ዝቅ ይላል ያለው ሰማይ ስልጣን ነው”፡፡
ሃሃሃ… ይሄ ሰውዬ ግጥም ሊያስጠላኝ እኮ ነው፡፡ ይሄን የግጥም ግንዛቤውን ይዞ ነው በየመፅሃፎቹ ግጥም የሚደነጉር? ይህ ግጥም የሰው ልጆችን የምኞት ኃይልና የማድረግ አቅም የሚያሳይ ግጥም ነው፡፡ የእኛ ፍላጎትና ኮሚትመንት ካለ ሁሉን ነገር ማድረግ እንችላለን የሚለውን የምኞት ኃይል የሚገልፅ ግጥም ነው፡፡ ሌላ ነው ትርጉሙ የሚል ሰው ካለ ያስረዳኝ፡፡ ተስፍሽ ካለው ስልጣን ቅብጥርሶ ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ ግን ከበዕውቀቱ በሚልቅ እርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡ አለበለዚያ ግጥም ማንበብም ሆነ መፃፍ ባቆም ነው የሚሻለኝ፡፡
“የበዕውቀቱ ቀደምት ግጥሞች ከአሜን ባሻገር ላይ ከተጠቀሱት አቶ በዳዳ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማዬት ሞክሬያለሁ” ይላል ተስፍሽ ተንትኖት ልቡ ውልቅ ብሏል፡፡ አንድ ጤነኛ ፊደል የቆጠረ ሰው እንዴት ይሄን ሁሉ የአንድ ገጣሚ ግጥም ከአያቱ ስም ጋር ለማያያዝ ይሞክራል? እንደዛ ማሰቡ ራሱ የጤንነት ምልክት ነው?
“በዕውቀቱ የመፅሃፉን ርዕስ ለምን ‘ከአሜን ባሻገር’ ሲል እንደሰዬመው ምስጢር አልነበረም፡፡ በቀጥታ ከአያቱ ከአቶ በዳዳ ጋር ይያያዛል”
ይሄ ሰው አቶ በዳዳን ምን አድርጉ ነው እሚላቸው? አሁን ከአሜን ባሻገርና አቶ በዳዳን ምን አገናኛቸው? ተስፋዬ ይቀጥላል፡- “እሱም (በዕውቀቱም) በዚያው ምዕራፍ ላይ የሚከተለውን ገልፆ ነበር” ይልና በዕውቀቱን እንደሚከተለው ይጠቅሳል፡- “የተለያዩ ባህሎችን በአንድ በገና ውስጥ እንደተወጠሩ አውታሮች ማስተናገድ በማይታወቅበት ጥንታዊ ማህበረሰብ ውስጥ ግለሰቦች የገናና ባህሎችን ምልክት አሜን ብለው ከመቀበል ያለፈ ምርጫ አልነበራቸውም” ይሄ ምን ማለት ነው? መልቲ-ካልቸራሊዝም ስለማይታወቅበት ዘመን በማስታወስ ያን ዘመን በአሁኑ ዘመን ዕይታ እንዳናዬው ከመናገር ውጭ ሌላ ምን ትርጉም አለው?
ተገርማችሁ ሙቱ ብሎን ተስፋዬ የበዕውቀቱን አንድ ግጥም እንደሚከተለው ይጠቅሳል፡፡ የግጥሙ ርዕስ ‘ሉላዊነት’ ሲሆን ተስፍሽ ግን ለአተላ ንባቡ እንዲጠቅመው ርዕሱን ‘ሉአላዊነት’ በሚል አቅርቧታል፡፡ ተስፋዬ ብሶት ያዘለ ነው ብሎ የገለፀው ግጥም ይሄው፡-
የጋራችን ዓለም የጋራችን ሰማይ
የብቻችን ህመም የብቻችን ስቃይ
ትንታኔው፡- “በአንድ አገር ስር ዜጎች አብረው እየኖሩ፣ አንደኛው ወገን ስቃይ እንደሆነበት ሲነግረን አልገባ ብሎን ይሆን?” ይላል የገ/አብ ልጅ፡፡ ግጥሙ የሚያወራው ስለሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) ሆኖ ሳለ ተስፋዬ ግን ርዕሱን ቀይሮ ጠለፈው፡፡ በዕውቄ ግሎባላይዜሽንን ሊሳለቅበት የሞከረውን ግጥም ሰውዬው በቡና አተላ ስልት አነበበው፡፡
ደከመኝ፡፡ እስኪ በቀጣይ ክፍል ልጨርሰው እሞክራለሁ፡፡ እስከዚያው ተስፋዬ እንዲህ ጭቃ ውስጥ የገባው ለተንኮል ብሎ ነው ወይስ ተስፋዬ ይህን እንኳን መረዳት የማይችል ተራ የወሬ አሰናዳኢ ነበር የሚለውን ጥያቄ አስቡበት፡፡ እኔ ደግሞ የዚህን በሽተኛ ሰውዬ ፅሁፍ ከቁምነገር ቆጥሬ ጊዜዬን የማጠፋው ለምንደነው የሚለውን ጨምሬ በቀጣይ ክፍል እመለሳለሁ፡፡
ሰናይ ጊዜ!