ድሮ ነበር…
አንድ በጊዜና በጥረቱ ብዛት ከድህነቱ ተላቅቆ ባለፀጋ የሆነ ሰው ነበረ። ቤቱ ውስጥ በአሽከርነት እንድታገለግለው ከገጠር ያመጡለትን ሴት ገና ሲያያት ይደነግጣል። በወቅቱ ሴቲቱ የለበሰችው አዳፋ ልብስ ነበር። እሱም በዝቶ ገላዋ ላይ ተበጫጭቋል። ለእግሯም ባዶ እግር ከመሆን የማይሻል የተበጣጠሰ ላስቲክ ጫማ (ኮንጎ) ነበራት። ስትራመድ እየጎተተችው፣ ጣቶቿም ወጣ ገባ ይሉ ነበር። እየሮጠች ያስጎነጎነችው የሚመስለው ፀጉሯም ተክበስብሶና አዋራ ተሰግስጎበት ለዓይን አይማርክም። ከጉዞ ብዛት ፊቷን ያወረዛው ላብም ውበቷ ላይ አጥልቶባት ይጨንቃል።
እድሏ ሆኖ ግን በዚህ ሁሉ መሀል የአዲሱ ጌታዋን ልብ ማቅለጥ አልተሳናትም ነበር። ነፍሱ እስክትበር ተከይፎባት ነበር። ባለፀጋው ከሀብቱ ብዛትና ከኑሮው ጥራት የተነሳ ቤቱ የሚቀጠሩ አገልጋዮችን ልብስ በአዲስ እንዲቀየር ትዕዛዝ ያስተላልፍ ነበርና፥ እንደልማዱ ያን ቀንም በአስቸኳይ እንዲፈፅሙ ለነባር አገልጋዮቹ ትዕዛዝ አስተላለፈ። ሴቲቱ ልብሷ በአዲስ ተተካላት። ታጥባም ፀጉሯን በአዲስ ተጎነጎነች። ውበቷም በአዲስ እንደተሰራ ሁሉ ሽልቅቅ ብሎ ወጣ። …ደስም አለው። አፈቀራት። (ማለት ክየፋው ባሰበት)።
አዲስ ለባብሳ ገና እንደተመለከታት “ኦ የማስባት ሴት…. እስከዛሬ ድረስ የጠበቅኋት የጎን አጥንቴ…” ሲል ለራሱ አጉተምትሞ፥ እርሷ ሳትሰማ ሌሎች አሽከሮቹን (ነባሮቹን) ቅያሪ ልብሶቿን እንዲያመጡለት ጠየቀ። እነሱም “እንዴ ጌታችን እንዴት ይሆናል? ልብሶቹ ከመንተባቸው ማደፋቸው? ያዩዋቸው ዘንድ አመጥኑዎትም! ስለምን ፈለጉዋቸው?” ብለው ቢያቅማሙ ገስፆ ላካቸው። (ባርነታቸውን እንደማስታወስ…. ያው ነው አለቃና ምንዝር።)
ከዚያም ብር ብለው ወጥተው ብር ብለው አመጡለት። ድርቶዋን። እርሱም ተቀብሎ አሰናበታቸው። ምንጉድ እንደሆነ ለማጣራት ቢጓጉም የጌታ ትዕዛዝ ነውና ካለልባቸው በሽቅድምድም ወጡ። ካለወትሮው (ለሌላ እንደማያደርገው) ቤቱን ሲያስጎበኛትና የስራ ድርሻዋን ሲያስረዳት ቆይቶ፣ መኝታ ክፍሉ ደረሱና እዚያ ያለ ያማረ ሳጥን እየጠቆማት የስራ ጉዳዮችን የተመለከቱ ነገሮች ስላሉት ከቦታው እንዳታንቀሳቅሰው።… እርሷም ታማኝ፤ ከዚያ ወዲያ ጭራሽ ሳጥኑን ለዓይኗም ረስታዋለች። (መቼስ የዛሬ ብትሆን እንዳትነካው ‘ንኪው’ ማለት ነበር።)
እናም ሲኖሩ ሲኖሩ… (ሲኖሩ ሲኖሩ ለመባል የማይበቃ ጊዜ ቆይተው) ስሜቱን መቋቋም አቃተው። በትህትናም ዘከዘከላት። ደስም አላት። (የዛሬን ቢሆን በፍቅራዲስ ነቅአጥበብ ‘ልዑል አስወደደኝ’ ዜማ ታጅባ ትቀውጠው ነበር።) ብቻ የሚቀልድባትም መስሏት ነው መሰል ተሽኮረመመች። ‘ኧረ እንዴት ይሆናል?’ ስትል እያልጎመጎመች! በልቧ…. ‘ባንዳፍ! የኔ ንጉስ! የኔ ጌታ! ኧረ እንዴት ተባርኬያለሁ አያ?!’ ስትል… ደግሞ አፍ አውጥታ ‘ኧረ አትቀልድ አንተው!’ ብላ ጌታዋን ልትሳፈጥ እየዳዳት….
ብቻ ምንስ ብትሆን ያው ሴት ነችና ወግ የባህሉን ተግደርድራ ሆኑ። ተግባቡ። ተዋደዱ። ተኙ። ተነሱ።…. እንደ ገና ተኙ። እንደ ገና ተነሱ። ከዚያም ከናካቴው አልጋ ለመወራረስ (ለዘለዓለሙ ለመጋራት)፣ በነገር ሁሉም ‘አንተ ትብስ አንቺ’ ተባብለው ሊኖሩ፤ እግዚአብሔር ልጆች ቢሰጣቸው ደግሞ ምድርን ሊሞሏት…. ተስማሙና ተፈጣጠሙ። አሳዳሪዋ ባለቤቷ ሊሆን ነውና ሽማግሌ ላኪም ተቀባይም ሆኖ ጉድ ተባለላቸው። – ለሰሪና ላሰሪው። ድል ባለ የባለፀጋ ድግስ ተዳሩ። ላልከዳሽ፣ ላትከጂኝ ተባብለው። በወግ በማእረግ ቃል ተገባቡ።
ሲኖሩ ሲኖሩ… ልጆች ተወልደው፣ ቤቱ ውስጥ ተድላ ፀጋው ከነበረው በላይ በዝቶ፣ እንግዶች የሚያርፉበት – የዓለም የሲሳይ – የሚባል ቤት ሆነ። እርሷ ግን የመጣችበትን ስትረሳው ብዙም አልቆየ። ወዲያው ከንጉስ ቤት አኗኗር ጋር ራሷን አጣጥማና አስማምታ መኖር ጀመረች። ቋንቋውን፣ ስርዓቱን፣ ባህሉን፣ ዘመዱን፣ ቀዳዳውን፣ ድፍኑን… ሁሉን በአጭር ጊዜ አበጥራ አወቀች። አውቃም ልቧ አበጠ። መዝለል፣ ውጭ ውጭ ማለት አማራት።
ባል ነገሩን ሁሉ እየተመለከተ ይታዘባል። በዘዴ ፀባይዋን ታርም ዘንድ ሸንቆጥ ያረጋታል። እሷ እቴ… መስሚያዋ ጥጥ ሆኖባት ነበር። ጭራሽ ከአንዴም ሁለቴ ከሌሎች ሰዎች ጋር መሄዷን ይሰማል። በሰማበት ቅፅበት እሳት ይለብስ፣ ይጎርስና ወዲያው ደግሞ መለስ ይላል። ከልቡ ሳይቀዘቅዝ እንደበረደለት፣ ምንም እንዳልተፈጠረበት ሰው – ዝም። ጭጭ። ድራማውን መስራት።…. የሆዱን በሆዱ አድርጎ ‘እንዴት ዋልሽልኝ እመቤቴ?’ ይላታል። መልሷም ስርዓት ያጣ ጀመር።
ምሬቱ ሲደራረብ ለቅርብ ጓደኞቹ፣ ከዚያም ለቅርብ ጓደኞቿ፣ ከዚያ ደግሞ ለተከበሩ ሽማግሌዎች ተናገረ። ይመክሩ ይዘክሩለት ዘንድ ጠየቀ፤ አሳሰበ። ነገሩ መላ ቅጡን ማጣቱን የተረዱት ሰዎች ሁለቱንም ቀን ቆርጠው ሰበሰቧቸው። ከዚያም ሁለቱም አሉ ያሉትን ችግር እንዲናገሩ እድል ሲሰጣቸው፣ እርሱ እንደሚወዳትና ፀባይዋን አስተካክላ … እግዚአብሄር እስከፈቀደላቸው ጊዜ ድረስ ከርሷ ጋር አርጅቶ በተድላና በደስታ መኖር እንደሚፈልግ ተናገረ።
እርሷም በባልነት ምንም እንዳልበደላት ገልፃ በትዳር ታስሮ ቤት መዋሉ ስለመረራት ንብረት ተካፍላ ልጆቿን ማሳደግ እንደምትፈልግ ተናገረች። ሁሉም ተገረመ። ባሏም። ሽማግሌዎቹም። እርሷ ግን ምናልባት መገረማቸው እንዳስገረማት እንጃ…. ሽማግሌዎቹ ለዳኝነት ተቸግረው እየተቅበዘበዙ….. አንዴ ባልን አንዴ ሚስትን ቀና ብለው በ ‘እንዴት እናድርገው’ እየተመለከቱ ቆዩ።
እርሱም ነገራቸው ገብቶት ኖሮ ‘ፈቃዷ ይሁን’ ሲል መለሰላቸው። “ንብረት ከመከፋፈላችን በፊት ግን እስከዛሬ ስለነበራት መልካምነት አንድ ስጦታ አለኝ።” ሲል ተናገረ። እነሱም በትህትናውና በመረጋጋቱ ተገረሙ። እርሷም ግራ ገባት። ‘ምን ይሆን?’ ብለው በጉጉት ጠበቁ።
አላትም… “እመቤቴ ሂጂና ከመኝታ ክፍል ስትመጪ አትንኪው ያልኩሽን ሳጥን አምጪው አላት።” እርሷም የመጣችበትን ጊዜና ቦታ እንደዘነጋ
“ከየት ስመጣ?” አለችው።
እርሱም “ከገጠር።” …..የረሳችው ነገር ስለተቆሰቆሰባት ተናዳ እየተመናቀረች ከመኝታ ቤት ሳጥኑን ይዛው መጣች። ፓ! ያማረ ነበር። በወርቅ ቅብ የተለበጠ ሳጥን። ልቧ እንደ አታሞ ድም ድም ይል ያዘ። ምን የሷ ብቻ? የሽማግሌዎቹም። ከዚያም ቁልፉን ሰጥቷት ከፍታው ውስጥ ያለውን እንድትወስድ ነገራት።…..
“ምናልባት የጉዞሽን አቅጣጫ ትለዪና ትወሲኝ ዘንድ ይረዳሽ ይሆናልና ነገም በጥንቃቄ አስቀምጪው አላት።”
ከፈተችው። ስትመጣ የለበሰቻቸው ልብሶች ነበሩ። ቆራጣ ኮንጎዋም አለ። የተሸነጣጠቁ እግሮቿን በኮንጎው፤ ቆስቋላ ገላዋን በቡትቶዎቹ አየቻቸው። ሀዘኑ ፀፀቱ ደቆሳት። ከፋት። ግራ ገባት። ግራ ገባቸው። ግራ ተጋቡ። እግሩ ላይ ወድቃ አለቀሰች።ስቅስቅ ብላ… በእድሏ፣ በሰራላት። ባፈጣጠሯ። በመርሳቷ። በጥቃቧ። በበደሏ። በሁሉም ነገር ምርርርርር ብላ ምህረት ጠየቀች።
ከዚያም አብረው መኖር ቀጠሉ። ልብሶቹና ሳጥኑ ግን ቦታ ቦታቸው ተመለሱ።
የነገን ማን ያውቃል? 🙂
‘የመጣንበትን እንዲያስታውሰንና የምንሄድበትን እንዲጠቁመን፣ ላለፉት ታሪኮቻችን ሁሉ ንቅሳት ቢኖረን (ያሉንን እንዳይጠፉ ብንንከባከባቸው)’ ስል አሰብኩ። 🙂
******
ከላይ የፃፍኩት በልጅነቴ የሰማሁትን አንድ ተረት፥ የዛሬ 3 ዓመት፣ ሙሉው ቢጠፋኝ ጊዜ እንደመጣልኝ በራሴ ያሰፋሁት (እንጀራ አሰፋች እንዲሉ) ታሪክ ነው። ያኔ ታሪኩን እንዳስታውሰው ቆስቋሽ የነበሩኝ የሶሊያና ሽመልስ እና የዮሐንስ ኃይሉ ገጠመኞች (በንቅሳት ዙሪያ) ነበሩ።