ስለአገራዊ ለውጥ ስናስብ: “የዘገየችበት ምንድን ነው ምክንያቱ?”

የእኛ ነገር…

“ስለለውጥ፥ ሌላ ሰው እና ሌላ ጊዜ የምንጠብቅ ከሆነ፥ ፈፅሞ አይመጣም። ለዘመናት ስንጠብቅ የኖርነው እኛው ራሳችንን ነው። የምንፈልገው ለውጥም ያው እኛው ነን።” (“Change will not come if we wait for some other person or some other time. We are the ones weve been waiting forWe are the change that we seek.”) ሴናተር ባራክ ኦባማ በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንቅስቃሴያቸው ወቅት፥ በታላቁ ማክሰኞ (Super Tuesday) አድርገውት ከነበረው መሳጭ ንግግራቸው መካከል ተቀንጭቦ፥ በጠንካራነቱና አነቃቂነቱ ሲታወስና በየቦታው ሲጠቀስ የኖረ ሕዝባዊ እውነት ነው።

በተለይ “ስንጠብቅ የኖርነው እኛው ነን” የሚለው ሀረግ፥ በየሰዉ አእምሮ እና አንደበት ተደጋግሞ ሲሰማ፥ ቁጭትንም፣ ተስፋንም፣ ጉልበትንም እኩል ይሰብካል። ከዚያም በፊት፥ በተለያዩ የማኅበረሰብ መብት እንቅስቃሴዎች ወቅት፣ ኪነጥበባዊ ስራዎችና ንግግሮች ውስጥ ሲጠቀስ የነበረ በመሆኑ፥ የሰዎችን ልብ በማሞቅ ረገድ የራሱን ሚና ተጫውቷል። ሆኖም፥ ባነቃቃባቸው ቦታዎች ሁሉ ጉልህ እርምጃዎችን አስወስዷል አያስብልም። በተለይ ወደ እኛ አገር ሲመጣ፥ ለነገር ማሳመሪያ፣ አልያም የድብርታም ቀንን ብርድልብስ መግፈፊያ ተብሎ፥ ተጠቅሶ የሚተወው ነገር ብዙ ነው።

“ነገር ከስሩ ውሃ ከጥሩ” (“Rome wasn’t built in a day”)

ያኔ ኦባማ ምርጫውን የማሸነፋቸው ወሬ ለዓለም ሲበሰር፥ የመገናኛ አውታሮች በሳም ኩክ “A Change Is Gonna Come” ሙዚቃ ሲናጡ ነበር። ታዲያ እንዲህ ነው፥ “Rome wasn’t built in a day” በሚል ሙዚቃ ታጅቦ፥ እያንዳንዱን ቀን ለትልቅ ለውጥ ክምችትነት ተጠቅሞና የለውጥ ግብአቶችን አጠራቅሞ፤ ላይ ታቹን አሳልፎ፣ ሜዳው ላይ ሲደርሱ የድል ሙዚቃዎችን መኮምኮም። አለዚያ ግን ዜማው ሁሉ “እንቦጭ… እንቦጭ” እና ወቅታዊ ሆኖ ይቀራል።

ለውጥ ዝግመታዊ እንደመሆኑ መጠን፥ ምሰሶዎቹም (the pillars) ብዙ ናቸው። ወደ ስራ ከመግባት በፊት፥ የምንፈልገው ለውጥ ምንድን ነው? አቅማችን ምን ያህል ነው? የትኛውን ምሶሶ ብንነቀንቀው ሌላውን ያናጋልንና ስራችንን ያቀልልናል? የትኛውን ምሶሶ ብናጠናክረው ሌላውን ይደግፍልናል? የትኛውን ክር ብንስበው፥ የምንፈልጋቸውን ነገሮች ሰብስቦ ያፈርጥልንና ከህልማችን ጋር ያቀራርበናል? (“ሀረጉን ብስበው ደኑን ሰበሰበው” እንዲሉ) እኔ የቱን ማድረግ እችላለሁ? ዙሪያዬ ያሉ ሰዎችስ ለውጡን በማቀላጠፍ ረገድ የትኛውን ተግባር ቢይዙ ያዋጣል? ትዕግስታችንስ ምን መምሰል ይኖርበታል? መግባባቶቻችን እና ኅብረተሰባዊነታችንስ? የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳት ያስፈልጋል።

ካለጥቃቅን ለውጦች ትልልቅ ለውጦችንና የጋራ መሻሻሎችን ማሰብ፥ ትርፉ ጉንጭ አልፋነት ይሆንና፤ ችግሮችና ጭቆናዎች እየበዙና እየረቀቁ ሄደው፣ እኛም ለቅሶ እና እሮሮ አርቃቂዎች ሆነን እንቀራለን። ለምሳሌ፥ የትልቅ ኩባንያ ባለቤትነት ህልም ያለው ሰው፥ ከትንሽ ቁጠባ አንስቶ ቁርጠኝነቱን ማረጋገጥ ይኖርበታል። ስለነገው ህልሙ፥ ከዛሬው ፍላጎቱ ላይ የሚከፍለው መስዋዕትነት ይኖራል። ሳንቲም በመቆጠብ ውስጥ የሚያዳብረው ልማድና በምናቡ የሳለው “የተሻለ ኑሮ” ተደምረው፥ የሕይወት መመሪያውን ያረቁለታል እንጂ ከሰማይ አይወርድለትም።

የዚህ ጽሁፍ ዓላማ፥ ለውጥን በማዘግየት ረገድ በራሳችን (በለውጥ ናፋቂዎች) የሚደረጉ አፍራሽ ተግባራት ዙሪያ መጨዋወት ነውና የተወሰኑትን (በተለይ ከማኅበረሰብ ድረገጽ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ስር የሰደዱትን) እንይ።

“ከራስ በላይ ነፋስ”

ብዙ ነገሮችን መለወጥ እንፈልጋለን። ነገር ግን ሁሌም ራሳችንን እንጎትተዋለን። ልንላቀቃቸው የምንፈልጋቸው ሱሶች፣ ልንዛመዳቸው የምንፈልጋቸው ሞያዎች ቢኖሩም፤ ከቀደመውም ሳንራራቅ፣ ከኋለኛውም ሳንቀራረብ ዓመታት ይቀያየራሉ። አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር የእቅድ ዝርዝሮቻችንን ስንፈትሽ አምና ያቀድነው ላይ ተለጥጦ እንጂ ቀንሶ የሚሆን ነገር የለም። የምንናፍቃቸውን ለውጦች እንዳናይ የሚያራርቁን ብዙ ምክንያቶች ይኖራሉ። ታዲያ ግን፥ ለውጦቹ እኛ ነን ካልን፣ ለዘገዩ ለውጦችም ዋና ተጠያቂዎች እኛው እንሆናለን ማለት ነው።

ተደጋግሞ የመነሳቱን ያህል ብዙ ያልተተገበረውም “የራስን የአስተሳሰብ አድማስ መለወጥ” ነው። የራሳችንን አስተሳሰብ ለመለወጥ በማንፈቅድበትና በማንጥርበት ጊዜ፥ “እኛ ስንጠብቅ የኖርነው ለውጥ ነን” ብንል ከንግግር ያለፈ የሚሆን ነገር አይደለም። በመርህ ደረጃ፥ ብዙ ነገር በእኛ ቁጥጥር ስር ባልሆነበት ሁኔታም፥ ለመቀየር ቀላሉ የራሳችንን ጉዳይ ነው። የጥፍሩን ንጽህና መጠበቅ የማይችል ሰው ስለአካባቢ ንጽህና ላውራ ቢል ሰሚ አያገኝም። ሰሚ ቢያገኝ እንኳን፥ ኅሊናም ይጮህበታል። ሰዎችን የማያዳምጥ ሰው፥ ስለማዳመጥ ጠቀሜታ ላውራ ቢል ተመዝኖ ይቀላል።

ሁኔታዎች ላይ ያለን አቅም ውሱን ሲሆን፥ ራሳችን ላይ ልንበረታ ይገባናል። ዘለን የሰው አጥር ገብተን እናጽዳ ባንልም፥ የራሳችንን በማፅዳት ሂደት ውስጥ የምናጋባው እና የምናስተምረው ነገር አይጠፋም። ስለለውጥ ስናስብና የሰዎችን ግንዛቤ አስፍተን የለውጥ ደቀመዛሙርትን ለማስከተል ስንነሳም፥ መጀመሪያ የራሳችንን የግንዛቤ መጠን መፈተሽና ማጠናከር ያስፈልገናል። ሆኖም ግን፥ ነገሮችን እንደሚገባቸውና ለውጤት እንዲሆኑ ለማድረግ እንቅፋት የሚሆኑብን ውጫዊም (በባለጊዜዎች ክፋት የሚደረጉ) ውስጣዊም (ከእኛ የሆኑ) ጫናዎች አሉ። ውጫዊ ጫናዎቹን ለመቋቋምና የታሰርንበትን የባርነት ገመድ ለመፍታት ግን፥ መጀመሪያ ውስጣዊ ጫናዎችን በማስወገድ ኅሊናችንን ከገዛ ስጋችን ባርነት ማስወገድ ይኖርብናል። የነፋሱን አቅጣጫ ማስቀየስ በማንችልበት ሁኔታ፥ ራሳችንን የማጠንከር እና እንደ ሰርዶ ወደፈለግነው አቅጣጫ በብልሃት ተለምጦ ነፋስ የማሳለፍ ጥበብን ልናዳብር ይገባናል።

ለራስ የሚሰጥ አጉል ግምት (ego)

ጠቀሜታ ቢኖረውም፥ የብዙ ችግሮቻችንም ስር ነው። ለራሳችን የምንሰጠው ቦታ፥ በችሮታ የምንቀበላቸውንም ለሰዎች የምንሰጣቸውንም ነገሮች በመወሰን በኩል የራሱን ሚና ይጫወታል። ‘ego’ ጨቋኞችንም ተጨቋኞችንም እኩል ጠምዶ፥ ሰዎች በችግር አረንቋ እንዲኖሩ የሚያደርግ የትውልድ ትብታብ ነው።  ምናልባትም ከዚህ በታች የሚጠቀሱት “ለውጥ አናቃፊዎች” ስር መሰረትም ‘ego’ ነው።

በለውጥ ሂደት ውስጥ ዕውቅናን ማሠስ

ይሄ አደገኛው ማኅበረሰባዊ ችግራችን ነው። ከሽንፈትና ከአቅመቢስነት የሚመጣም ይመስላል። ሰዎች ትልቁን እና በልባቸው ያለውን ምስል ደርሰው እንደማይነኩት ሲያስቡና፣ “ካሰብኩት ባልደርስስ” የሚል ስጋት ሲያድርባቸው፥ “እየሰሩ ናቸው” እንዲባል በሂደቱ ውስጥ እውቅናን ይፈልጋሉ። አልያም፥ ለውጡን ከልባቸው ፈልገውት ሳይሆን፥ ‘ሀዋርያነቱ’ እንዲያስደንቃቸው አልመው ሲነሱም፥ በሂደት ውስጥ ውዳሴን ያስሳሉ። “እየሰሩ ነው” መባሉን ይፈልጉታል። ይህኔ ሚስጥረኝነትና ወዳጅነት አፈር ይበላሉ። አካሄዶችና ትልልቅ ጉዳዮች ፀሐይ ይመታቸዋል። ወዳጅነት ይጎለድፋል። እምነት ይጫጫል። ወዳጆቻችን እንዲያሙን ሽንቁር እናበጃለን።

ግልብነትና ትኩስ ትኩሱን ቃርሚያ… (አፍሮጋዳዊነት)

“እውነተኛ የሂስ መንፈስ የሌለበት ቦታ የህዝቡ ሂስ የጥበብ ደረጃን ያወጣል። ያወጣው ይፀድቃል። ህዝብ የወደደው ሁሉ እውነተኛ ነው።” (ሌሊሴ ግርማ (2004), ‘አፍሮጋዳ’) ይሄ እየኖርን ያለንበት ግልብ ዘመን ሀቅ ነው። በተድበሰበሱ እውነቶች ተከብበን በብዥታ እንመላለሳለን። ብዥታንም እንፈጥራለን። ብዙ ነገር ስላየን ብዙ ነገር ያወቅን ይመስለናል። ብዙ ሰው ስላደነቀን ጠቃሚ ነገር ያደረግን ይመስለናል። ብዙ ነገራችን የለብለብ ነው። የተጠበሰና የበሰለ ነገር አናውቅም። ብናውቅም ዙሩን ያጠነክርብናልና አንፈልግም። ሌሊሴ ዘመኑን በአንድ ቃል ሲጠቀልለውም “አፍሮጋዳ” ይለዋል። “ለእኛ የዘመኑ ታዋቂነት መንፈስ “አፍሮ” እና “ጋዳ” ተጠቃሽ ናቸው። የአፍሮጋዳ አስተሳሰብ የሚመነጨው ጥልቅነትን ከማለዘብ ነው።” በማለት እያብራራ።

ሰድቦ ለሰዳቢ መስጠት

በንግግር ወቅት ያልተገቡ ቃላቶችን መጠቀም፥ የግልጽነት ንግግራችንን ልባዊነት ላይ የሚያጠላው ነገር ይኖረዋል። ሰዎች በወዳጅነት ስሜት ሲያወሩም፥ በርዕሱ ላይ እንጂ በግል (personally) እንደማይጋጩ ያሳይ ይሆናል። ሆኖም ግን፥ ያንን ለማሳየት ከቁልምጫና ‘ወዳጄ ወዳጄ’ ከመባባል ጎን ለጎን ቃላት መረጣም ወሳኝ ነው። (ያው ዘንድሮ “ወዳጄ” ተብለን ነው የሚቀረቀርልን) ከምንናገርበት መንገድና ዘዬ ባላነሰ፥ የምንናገርበት ቦታም ለንግግራችን ፍሬያማነት ግብአት ይሆናል።

ጉራጌዎች “በመደረንዳ” የሚል የተለመደ ጠንካራ ቃል አላቸው። ትርጉሙ “በቦታችን” ማለት ነው። ብዙ የጉራጌ ወላጅ፥ ልጅ ያልተገባ ነገር ማድረጉን ቢመለከት፥ …ምናልባት፥ ገላጋይ ገብቶ እንደሚገባው ሳይቀጣው እንዳይቀር፣ ወይ ደግሞ ሰው ፊት አሳፍሮት ልጁ በእልህ ተበላሽቶ እንዳይቀር፣ ወይም ‘ነገ ለሚለወጥ ነገር ልጄን ሰድቤ ለሰዳቢ እንዳልሰጠው ከሚል አባታዊ ስስትና ስጋት የተነሳ፥… “ኧክስ በመደረንዳ!” (ጠብቅ በቦታችን) ብሎ ጥርሱን ነክሶ ያልፈውና ብቻውን ይቀጣዋል እንጂ፥ ጥፋቱን እዚያው ዘክዝኮ ለመገሰፅ አይሞክርም።

እርስበርሳችን የምንዘላለፍበት፣ ቅሬታ የምንገልፅበትና የምንወቃቀስበት አግባብነትና መንገድ፥ ስለመረጋጋትና ሀላፊነት የመሸከም አቅማችን የሚነግረን ነገር የለውም?  ለውጥ ፈላጊዎችስ እርስ በርስ ገመና ሸፋኞች መሆን የለብንም?

ሽ ቡድንተኝነት

በተለይ “ያወቁ፣ የነቁ” ናቸው ተብለው ቦታ የሚሰጣቸው ሰዎች፥ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ርካሽ ቡድንተኝነት ውስጥ ሲጠመዱ ይስተዋላል። የቡድንተኝነቱ ርኩሰት፥ ሌሎችን ለመጉዳትና ለማግለል፣ ፊትና ዕድል ቢሰጣቸው የለውጥ ምሶሶ አጠናካሪ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎችን ስለሚያጠቃ ነው። ባነበብናቸው አንድ ሁለት መጽሐፍት ውስጥ ተከልለን፥ ሌሎች ሰዎች ላይ ስነልቡናዊ ጥቃት እናደርሳለን። ጥራዝ ነጠቅ የእውቀት ጋሻችንን ይዘን፥ የጥፋት ጦራችንን እንመዛለን። ለመነሳት የሚጥሩ ነፍሶችን፣ ለማወቅ የሚታትሩ ልቦችን፣ ግንዛቤያቸውን ለማስፋት የሚታገሉ ብላቴናዎችን ብቅ ሲሉ ጠብቀን፥ አቁስለን ጥልቅ እናደርጋቸዋለን። “ወፌ ቆመች” ላይ ያሉ ሰዎችን በደረት እንዳይድሁ ሳንካ እንሆንባቸዋለን። ሀሳባቸውን ሊገልጹ ሲሞክሩ፥ “እስኪ ዝም በሉ” ይባላል። የሆነ ነገር ለመጻፍ ሲጭሩ እንኳን፥ “ዘንድሮ ማንም እየተነሳ ይፈነጭበታል” ብለን የማሸማቀቅ ስራ እንሰራለን። ያው ጉዳዩም ርካሽ፣ ቡድንተኝነቱም ተራ ነውና፥ ደቀመዛሙርቶቻችን ያቀነቅኑልናል። በዚያ ሂደት ውስጥ፥ የለውጥ ሀዋርያት ቁጥሮችን እንቀንሳለን።

እኔ ያልኩት ካልሆነ… (ፍረጃ)

ጥቃቅን መንግስተኝነትም ሌላው ችግራችን ነው። በየቅያሱ ከመንግስት የምንጠይቃቸውን መብቶች እኛው ከወዳጆቻችን እንገፋ’ለን። “እኔ ብቻ ላውራ። የእኔ ብቻ ነው ልክ።” የሚል ሰው፥ መንግስትን “የመናገር መብቴን አትንጠቀኝ። አስተያየት ልስጥበት።” ይለዋል። ደግሞ በመንግስት ቂመኝነት የሚማረር ሰው፥ ወዳጁ ላይ ስር ሰደድ ቂም ይቋጥራል። …ደግሞ ወዲያ “ለውጥ፣ የሀሳብ ነፃነትና የምርጫ መብት” ጃዝ ገለመሌ እንላለን። ወዲህ ሰዎች የወደዱትን ስለመረጡ፥ ቅሬታን ከመግለፅ ባለፈ… በራስ የመስተሀልይ ልክ፣ በቀደመ ታሪክና በግል ፍላጎት ብቻ መዝነነው ተመራጮቹንም መራጮቹንም ባንድ ላይ እንወቅጣለን። ወቀጣችንን የሚወቅሱ ቢኖሩም የነገር ሰንኮፋችን እጥፉን ይዘረጋል። የሀሳብ ነፃነትም ሆነ ለውጥን መናፈቅ በመከባበር መታጀብ እንዳለበት! አለዚያ ይሄድ ይሄድና አንገቱ ጋር ሲደርስ ሲጥ ብሎ፣ እምነት ማጣት ተከትሎት፣ ‘ብዬ ነበር’ መባባልና እርስበርስ መወቃቀስን እንጂ ምንም አያስተርፍም።

የትልልቅ ምስሎች ልክፍት

ትንንሽ ሁኔታዎችንና የለውጥ መንደርደሪያዎችን አናደንቃቸውም። ልባችን ትልልቅ ለውጦችን በማሰብ ተጠምዶ፣ በመንገዱ ላይ የሚያገኛቸውን ትንንሽ ለውጦች ስለማይደነቅባቸው ሀሞቱ ቶሎ እንዲፈስ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። የማመስገንን እና የመደሰትን ጉልበት ብዙዎች እንስተዋለን። ስለዚህ ቶሎ ይደክመናል። ልባችን ትልቁን ነገር ብቻ ነውና የሚያየው፥ እዚያ ለመድረስ ያደረግናቸው ጥረቶች ምን ያህል ፈቅ እንዳደረጉን ሳናስብ፥ እዚያ አለመድረሳችንን እንረግማለን። በንጽጽር ውስጥ ሆነን ራሳችንን እንወቅሳለን። ሌሎች ሰዎች የነበሯቸውን እድሎችና፥ የማርያም መንገዶች ሳናውቅ፣ ቀድመውን ስለሆኑት ነገር እንገረማለን። ራሳችንን እንረግማለን። በአንጻሩ ደግሞ፥ ትንንሽ ምስሎችን ብቻ ይዘን እየተንቀሳቀስን በትንሽ ውጤቶች ብቻ ልባችን አርፎ ቁጭ ካለም ሌላ ችግር ነውና ሚዛኑን መጠበቅ ያሻል።

ውሻ በቀደደው…

ሌላው ማኅበረሰባዊ ችግራችን፥ በተቀደዱልን ቦዮች ሁሉ የመፍሰስ አባዜዎች ነው። ያም ይመጣል አጀንዳ ያቀብለናል፣ ተቀብለን እናቀነቅናለን። ደግሞ አጀንዳ ሲቀየርልን ቀይረን እንቀባበለዋለን። ተደጋግሞ የሚጠቀሰው “አስማተኞች እና ፖለቲከኞች የሰዎችን ትኩረት ከሚያከናውኑት ነገር ላይ ትኩረቶችን ማስቀየስ መፈለጋቸው ያመሳስላቸዋል” የሚለውን የናይጄሪያዊውን ደራሲ ቤን ኦክሪን አባባል ደጋግመን ብንጠቅሰውም፣ ጭራሽ አናስተውለውም። ስለዚህ በአስማተኞች እና በፖለቲከኞች አጀንዳ ማስጠምዘዝ መርሀ ግብር ሰለባ እንሆናለን። ሌሎችን የመከተል አባዜም አለ። “እነ ኧከሌ ካሉማ” ብለን ልክነትን በሰዎች እንመዝንና እንደናበራለን።

ዘርፈ ብዙ ማኅበረሰባዊ “ሳቦታጆቻችን”

የጎረቤት ዛፍ ጥሩ እያደገ፣ ቅርንጫፉ እየሰፋና እያበበ ሲሄድ… ከመደሰትና ያለውን የጋራ ጥቅም ከማሰብ ይልቅ፣ በጋራ ለሚቆጋን ፀሐይ ጥሩ መላ መሆኑን ከመገንዘብ ይልቅ፥ “ቅርንጫፍሽን ሰብስቢልኝ። የልጆቹን ዐይን እየጠነቆለብኝ ነው።” ….“ማነሽ… አበባሽ ደጄን አቆሸሸው። ዛፉን ቁረጪልኝ።” ….“ግንዱ ግድግዳዬን ሊሰብረው ነው። ተኛብን እኮ! ኧረ ይሄ ነገር ባጭር ይቆረጥ።” ….“ስሩ ወደቤቴ ገብቷል። ቤቴን ያፈርስብኛል ንቀይልኝ ይሄን ዛፍ።” እሪሪሪ… ይባላል። የፈረደበት ቀበሌ አለ፥ ነጠላ ጎትተው ለነገር ቅያስ ያካልላሉ።  “ምናምን አርጋበት እንጂ፥ ሰው ሲጫጫ ዛፏ ብቻውን የሚወዛ” የሚሉ ሀሜቶች ሊሰሙ ይችላሉ። – አገሩ የእኛ ነው! የተተከለው የምች መድኃኒት ቢሆን እንኳን፥ “ነገ ታምሜ እፈልገውም ይሆናል።” ብሎ መራራትም የለም።

ሰው ስራው ጥሩ ከተቀላጠፈ፣ ፍላጎቶቹን ማሟላት፣ ለውጡ ፊቱ ላይ መታየት ሲጀምርና “ስራ እንዴት ነው?” ሲባል፥ ረገጥ አድርጎ “ተመስገን” ማለቱ ሲሰማ፥ ዞር ተብሎ፥ “በጤናው ነው ብለሽ ነው? ጠንቋይ ቤትማ ሳይሄድ አይቀርም።” ይባላል። ደም ያቃቡ፣ ጉቦ ያቃበሉ ይመስል፥ “ጉቦኛ ነው ስልሽ።” …“በሰው ደም ነው ቤቱን የሰራው።” ይባላል። ሌላም ሌላም …ሀሜቱ ብዙ ነው። ማነፍነፉና መሰለሉም አይቀሬ ነው። ሀሜቱ መሰረት ያለው ሲሆን፥ ደህና። ማነፍነፉና መሰለሉም የወንጀልን ጫፍ ለመያዝ ሲታለም ሸጋ ነው። ነገር ግን፥ በእለት ተእለት ኑሮ ሀሜቱ የሚቆሰቆሰው የምንጠረጥራቸውን ተግባራት እኩይ መሆናቸውን በማሰብ የተነሳ ሳይሆን፥ ወዳጃችን ቀና ቀና ማለት ከመጀመሩ ጋር ተያይዞ መሆኑ ነው የሚያሳዝነውና ለውጥ የሚያዘገየው።

አብረን ትምህርት ቤት ያልሄድነው ሰው፥ ስለሚያውቀን ብቻ፥ በትምህርት ሲሳካልን ቅር ይለዋል። ራሱን እየወቀሰ በንጽጽር ይለፋል። አምላኩን ሲያማርር ውሎ፥ ፀሎቱም “የኧከሌ አምላክ” ይሆናል፥ – የተሳካለትን ጎረቤቱን/ወዳጁን ስም ጠቅሶ። (ይህም በቅንነት ሲሆን ክፋት የለውም።) የምንሰራው አጥተን፣ ሰማይ ምድሩ ዞሮብን ስንንከራተት፥ መላ ያላማታን ሰው፣ “ምን በልተው አደሩ?” ብሎ ያልተጨነቀና ለእርጥባን ያላግደረደረን ሰው፣ ነቃ ነቃ ማለት ስንጀምርና የበለጥነው ሲመስለው ይበግናል።

በተለይ ግቢ የሚጋሩት ከሆነ፥ የጎረቤት ቤት መታደስ ለጸብ በቂ ምክንያት ነው። ከ “አሸዋው ግቢውን አቆሸሸው” እስከ “ድንበር ነክታችኋል” ድረስ ጸብ ለመጫር በተጠንቀቅ የሚቆመው ብዙ ነው። አንድ ሚስማር ሲመታ፥ ቀበሌ ተንጋግቶ ይመጣል። መቼም ቀበሌው ጎረቤት ሆኖ አይደለም… ጎረቤት ተሯሩጦ ሄዶ ጠቁሞ እንጂ። ለክፉ ጎረቤት የእኛ ቤት አለማደስ እንጂ፣ በእኛ ቤት ማደስ ተነሳስቶ የእርሱን እንዴት ሊያደርገው እንደሚችል ማሰብ ሞቱ ነው።

እንበልና፥ ግቢ ከሚጋሩ ሰዎች መካከል፣ አንደኛው በገቢ የማይጨነቅ ቤተሰብ ለውጥ ፈልጎ “ሙሉ ግቢውን ሲሚንቶ ላድርገው። መቼስ ከልኩ አያልፍም።” ብሎ ገንዘቡን አፍስሶ ሲሚንቶ ሲያስደርግ፥ ከጎረቤቶቹ መካከል ያንዱ አባወራ ልጁን ጠርቶ፥ “ካለሸር ሲሚንቶ ላድርገው አላለም። ምን እንደሚካሄድ ነቅተህ ተከታተል። እስኪ ዛሬ እንኳን ቁም ነገር ስራ። ነፈዝ!” ብሎት ሊሄድ ይችላል። ንፍገትን እንረግማለን። ስጦታዎችን እንጠራጠራለን።

ደግሞ የሚሰራና ጥሩ ላይ ያለ ወዳጃችንን፥ በመቆርቆር ስሜት፣ ስራውን ያቃናል፣ ለመልካምነቱ ሳንካ ነው ብለን ያሰብነውን ነገር ስንነግረው፥ ቅናት ነው፣ ምቀኝነት ነው፣ ይለናል። ቀና አስተያየት መስጠትም፥ ከምቀኝነትና ከተንኮለኝነት የሚያስደምር ነገር ነው። – አይገርምም፥ የእኛ አገር እንዲህ ነውና!

ሁልጊዜ አንጻር እንፈልጋለን። እኛ ማድረግ የማንችላቸውን ነገሮች፣ ወይም ለማድረግ እየቻልን ችላ ያልናቸውን ነገሮች፥ ሌሎች ሰዎች ሲያደርጉ ስናይ ዐይናችን ደም ይለብሳል። ደስታችንን ስንገልጽ እንኳን ካንገት በላይ ነው። ከዚህ በፊት፥ አንድ ወዳጄ “ሊስትሮ፥ ‘እኔም ሰፊ እሱም ሰፊ’ ብሎ ሰርጅን ላይ የሚቀናበት አገር” ብሎ ነበር። የችግሩን ስር ሰደድነት፥ ይህ ንግግር ፍንትው ያደርገዋል።

ብዙ ጊዜ ሰው ወዳጁን የሚለካውና የሚያዳንቀው በሐዘኑ ጊዜ ከጎኑ በመኖር ባለመኖሩ ነው። በእርግጥ ስናጣ አብሮን ያለ የክፉ ቀን ወዳጅ የልብ ነው። ስናዝን የሚያጽናናም ከየትም አይገኝም። መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን “ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ ወደ ልቅሶ ቤት መሄድ ይሻላል እርሱ የሰው ሁሉ ፍጻሜ ነውና፥ ሕያውም የሆነ በልቡ ያኖረዋልና።” የሚል ት/ት አለ። (መጽሐፈ መክብብ 7፥2) ሆኖም እዚህም ላይ ቢሆን፥ ለቅሶ ደራሹ ስለሚማረውና በልቡ ስለሚያኖረው ነገር እንጂ፣ ለቀስተኛው ላይ ስለሚፈጥረው በጎ ነገር ብቻ ተጨንቆም አይመስልም። ያ ለቅሶ ደራሽ፥ በግብዣችን ወቅትም፥ ድግሱን ታድሞ ከመሄድ ባለፈ ‘የደስታችን ተካፋይነቱ’ ሊፈተሽ ይገባዋል።

ምሳሌውን ነው ‘ቤት፣ ጎረቤት፣ ጓደኛ’ ያልኩት እንጂ፥ ችግሩ በየዘርፉና በየሁኔታው ውስጥ የሚስተዋል ነው። ስለለውጥ ስናስብ ‘የደስታ ተካፋይነታችንን’ ልንፈትሸው ይገባል።

እንዴት ይሻላል?

“ላለፉት 33 ዓመታት፥ ሁልጊዜ ጠዋት ራሴን በመስታወት ውስጥ እየተመለከትኩ፥ እጠይቃለሁ ‘ዛሬ የሕይወቴ የመጨረሻው ቀን ቢሆን ኖሮ፥ ዛሬ ልሰራ ያሰብኩትን ነገር ነበር የምሰራው’ ብዬ ራሴን ደጋግሜ እየጠየቅኩኝ፥ ደጋግሜ ያገኘሁት መልስ ‘አይ! አልነበረም!’ ሲሆን፥ የሆነ ነገር መለወጥ እንዳለብኝ አውቅ ነበር።” ብሎ ነበር የአፕል ካምፓኒው ስቲቭ ጆብስ። የምር፥ ዛሬ የሕይወታችን የመጨረሻው ቀን ቢሆን ኖሮስ? ታላቁ ማርቲን ሉተር ኪንግም፥ “ሰዎች እንዲጋልቧችሁ፥ ጀርባችሁን ለምጣችሁ አትመቿቸው።” ብሎ ነበር። (በረከታቸው ይደርብንና!)

በማርቲን ሉተር ኪንግኛ እንሰነባበት! – “Change does not roll in on the wheels of inevitability, but comes through continuous struggle. And so we must straighten our backs and work for our freedom. A man can’t ride you unless your back is bent.

እስኪ ጀርባችንን ቀና እናደርግና ጋላቢ ጨቋኞቻችንን እናንሸራትታቸው ዘንድ፥ አቋቋማችንን እንፈትሽ፣ ለውጦቻችን ስለዘገዩበት ጉዳይ እንጨዋወት።

ሰላም!