ቅዱስ ላሊበላ፥ ከአንድ ወጥ ድንጋይ፣ መሰረቱ ከጣራው የተጣለ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን በሚያስደንቅና የሰው ልጅ ሊያስበው በማይችለው ጥበብ አንጾ አበረከተልን። ዓለም ዛሬም ድረስ በኪነ ህንጻው ይደመማል። ያየው ሰው ሁሉ ይደነቃል። “ላሊበላና ሞት ሁልጊዜ አዲስ ነው” እስኪባል ድረስ በታየ ቁጥር አዲስ ነው።
ምን ያህል የተጻፈ ቢነበብ፣ የተቀረጸ ቪዲዮ ቢታይ፣ ነገር አዋቂ ሰው ሲተርክ ቢሰማ፥ ደርሰው ሲያዩት ስሜቱ ከቃላት በላይ ነው። ልክ ልጅ መውለድን በሉት። (በዚሁ አጋጣሚ ያላያችሁት እዩት።) የራስን ልጅ ወልደው እስኪያቅፉ ድረስ፥ ምን ለልጅ ቢንሰፈሰፉ፣ የስሜቱን ከፍታ ያውቁት ዘንድ ከባድ ይመስለኛል። እንዲህ ያለውን ድንቅ ነገር ላሊበላ አበረከተልን።
እኛ ደግሞ፥ ለላሊበላ አድናቆት ይሁን ተብሎ፣ እጅግ በረቀቀ ቋንቋና ምስክርነት ከተጻፈ ወስዋሽና ቀስቃሽ ውዳሴ ጽሁፍ ውስጥ “አዳራሽ” የሚል ቃል መዘን፥ የነገርንና የክርክርን ድንጋይ ስንፈለፍልና፣ ጥላቻንና ፍረጃን ስናንጽ እንውላለን። ውዳሴ አጻጻፉ ላይ ስህተት ቢኖር እንኳን፥ ስለብዙው ጥሩ ነገር አድንቀን መጀመር እንችል ነበር። (በጣም የደነቀኝ ደግሞ፥ ላሊበላን አይቶት የማያውቅ ሰው ሁሉ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ሲሰጥ ነበር።)
ላሊበላ አካባቢ የነበሩት ድንጋያት ወደ ድንቅ አብያተ ክርስቲያናት ሲፈለፈሉ፥ በሌላ ቦታ ድንጋይ አልነበረም ማለት አይደለም። ቅዱስ ላሊበላ ድንጋያቱን ለህንጻ ቤተክርስቲያን አልሞ፣ ጥበብን ከፈጣሪ ጠይቆ ሲያገኝና ሀሳቡን ሲያሳካ፣ ሌሎች ድንጋያት ግን ለሌሎች ተግባራት ውለው ነው። ልክ እንደዚሁ፥ ነገርን ሁሉ በበጎም በጠማማም መልኩ መመልከት ሊፈጠር ይችላል።
ፋሲካን ለመብላት ቦታ እንዲያሰናዱ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ሲልካቸው “ወዴት እናዘጋጅ ዘንድ ትወዳለህ?” ሲሉት፥ “እነሆ፥ ወደ ከተማ ስትገቡ ማድጋ ውኃ የተሸከመ ሰው ይገናኛችኋል፤ ወደ ሚገባበት ቤት ተከተሉት፤ ለባለቤቱም። መምህሩ። ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ቤት ክፍል ወዴት ነው? ይልሃል በሉት፤ ያም በደርብ ላይ ያለውን የተነጠፈ ታላቅ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያም አሰናዱልን። ሄደውም እንዳላቸው አገኙና ፋሲካን አሰናዱ።” እንዳላቸው በመጽሐፍ ተነግሮናል። (የሉቃስ ወንጌል 22: 1-12; የማርቆስ ወንጌል 14:1-15) በመዝሙረ ዳዊት 47: 12 -13ም “ጽዮንን ክበቡአት፥ በዙሪያዋም ተመላለሱ፥ ግንቦችዋንም ቍጠሩ፣ በብርታትዋ ልባችሁን አኑሩ አዳራሽዋን አስቡ ለሚመጣው ትውልድ ትነግሩ ዘንድ።” ተብሎ ተጽፏል።
ከዚህ የምንረዳው፥ “አዳራሽ” የሚለው ቃል፣ ሆን ተብሎ የተጣመመ አገባብ እንደሌለው ነው። መዝገበ ቃላት ብናገላብጥም፥ “አዳራሽ ማለት ታላቅ ቤት፣ ብዙ ሰው የሚያገባ፣ ይኸውም ክብ፣ ሰቀልኛ ነው።” ወይም “ወደ ታሰበበት ነገርና፣ ጉዳይ የሚያደርስና የሚያገናኝ አድራሽ፣ አቃራቢ።” ተብሎ ይተረጎማል። ለእኛ ግን፥ ለላሊበላ አድናቆት “ኢአማኒ ነኝ” ባለ ሰው በተጻፈ ጽሁፍ የተነሳ ቃል መዘን ለክርክር እናውለዋለን።
ቁጣ፣ ክርክር፣ ተሳዳቢነት፣ ዛቻና ፌዘኝነት በመጽሐፍ ቅዱስ አንዱም ጋር በአዎንታዊ መልኩ አልተጻፈም። እንዲህም አልተማርንም። ሆኖም ግን፥ የምናምነው አምላክ የማይወደውን ነገር ተጠቅመን፥ በሀይልና በማንኳሰስ፣ በትምክህትና በመመጻደቅ የእርሱን ቤት እንዳስከበርን እናስባለን። ነገር ግን “ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም አላቸው።” (የሉቃስ ወንጌል 5፥32) ተብሎ ተነግሮናልና እግዚአብሔር ማንን መቼ፣ እንዴት እንደሚጠራ ስለማናውቅ፥ “ኢአማኒ ነኝ” ላለ ሰው የማርያም መንገድ በሚከለክል መልኩ ሆ ብለን እንነሳለን። ከዚህም ባሻገር “እላችኋለሁ፥ እንዲሁ ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል።” (የሉቃስ ወንጌል 15፥7) ተብሎም ተነግሮናልና ኢአማኒ ሰው ንስሐ ሊገቡ ከሚችሉ ሰዎች መደብ ነውና፥ ከጻድቃን ይልቅ በእርሱ መጠራት በሰማይ ደስታ ይሆናል።
የሆነው ሆኖ፥ ይሄ ሁሉ ሲሆንስ ምን ላይ ቆመን ነው ሌላውን ሰው የምንዘልፈው? እኛ “አማኝ” መስለንና በስሙ ክርስቲያን ተብለን በጓዳም ባደባባይም ስንት ዓይነት ጽድቅ ሰርተን ጣታችንን ለመጠቆምና ድንጋይ ለማንሳት እንረባረባለን?
“ነኝ እንዳልል፥
የት ቆሜ መሆኔን አየሁ” እንዳለው ነው ጋሽ ሰለሞን ደሬሳ።
“አሁንም ያ ቆሜአለሁ ብሎ በራሱ የሚታመን ሰው እርሱ እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ።” (1ኛ ቆሮንቶስ 10:12) ተብሎም ተነግረናልና ሁሉም ነገር እንደ እኛ ሳይሆን እንደቸርነቱ ይፈጸምልን ዘንድ እንማጸናለን።
————
ትናንት በዕውቀቱ ስዩም ላንዲት ሴትዮ አስተያየት ለጥፎ የነበረው ምላሽ ላይ “Don’t waste your time with explanations: people only hear what they want to hear.” የሚለውን የPaulo Coelho ንግግር አስተያየት መስጫው ላይ አስፍሬ ነበር። (አስተያየታቸውንም አንብቤው፥ ቁጣውና ተግሳጹ እንዲሁም ነገር ፈልፋይነቱንና የማጋጨት ፍላጎታቸውን ብቻ ነበር ለማየት የታደልኩት።) በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ እርስ በርስ ማብራሪያ መሰጣጠትና መማማር እንዳለብኝ ስለተሰማኝ ነው ይህን ሁሉ መዘብዘቤ።
የሆነው ሆኖ ሰው መርጦ ማንበብና መርጦ መረዳት ይችላል። መፍረድና መወገን ግን በፍላጎት እና በስሜት ብቻ የሚወሰን አይመስለኝም።
ሰላም!