በሰላሙ ጊዜ የሆድ የሆዳችንን እንጫወት ነበር። ያኔ እኔና አንቺ አፍ አፋፍ፥ ሚስጥር የባቄላ ወፍጮ ነበረ። ሁለታችንም ጋር የሚያድር የለም፤ ጨጓራችን እስኪወቀር፣ ምላሳችን ከረጢቱ እስኪራገፍ ድረስ ተናዘን፥ በወሬ ዱቄት የታጨቀ ከረጢት ከረጢታችንን ሸክፈን እንሄድ ነበር።
ነገር ያጋጨን እለት ያቆርሽውን ሁሉ አውጥተሽ ትነቁሪኝ ጀመረ። (ማቆር መቻልሽ የልብ ልብ ሳይሰጥሽም አልቀረ።)
መጣላታችን ልብሽ ውስጥ ሲነደፍ አገር በምስጢሬ የወሬ ስንጥቁን፥ ኩታ ሸምኖ አለበሰ።
ወዳጅ ያፈራኹበትን ነጻነትና፣ ያኔ ያወራሁት ነጻ ወሬ ሰንኮፍ ሆነው ሰውነቴ ላይ ተሰኩ። ተራማጅነትንም እረፍትንም ነሱኝ። ወዳጁን እንደቀበረ ሰው ቁም ለቁም ጢሜን ነጭቼ አገጬን ተገጠብኩ።
ቆጨኝ።
ክፉኛ ቆጨኝ።
ማውራቴ ቆጨኝ።
መስማትሽ ቆጨኝ።
ማወቄ ቆጨኝ።
ምን ነበር ባላውቅሽ ኖሮ? አንቺን ከማውቅሽ ምን ነበር ሌሎች ሌሎች ሰዎችን ባውቅ?
ማመኔ ቆጨኝ።
መጣላት የለም ያስባለኝ አፍቃሪ ሞኝነቴ ቆጨኝ።
ጆሮ ስላለሽ ቆጨኝ።
አልዋሽሽም፥ አፍ ስላለኝም ቆጨኝ።
“የሽንገላ አንደበቶች ዲዳ ይሁኑ” ይላል መጽሐፍ። እኔ ደግሞ ቅልብልብ አንደበቶችም ዲዳ ይሁኑ አልኩኝ።
“ቆይ ለስንጣላ” ብለሽ የሰማሽኝ ይመስል ስንጣላ የሰማሽኝን ሁሉ ቃል በቃል ለማሳጣት ተጠቀምሽበት።
ሚስጥሬን አሸሞርሽበት። ገመናዬን ወዳጅ አፈራሽበት።
የቅርብ ነበርሽና አንቺ ብለሽ ማን ሊጠራጠር?
ባለጊዜ ገድ የሰመረለት አትራፊ ነው። ቢጨምርም ቢቀንስም ገዢ አያጣም።
የፈለግሽውን ጨመርሽ። የፈለግሽውን ቀነስሽ።
“አወራሽ። ለፈለፍሽ። ሞላ አገሩ ሰማ።
ግደይኝ አንቺ ልክ ከጠላሽኝማ” አልልሽም።
እሱ ዘፈን ነው። “እዬዬም ሲደላ ነው” ይባላል፥ እሱ ፍቅር ነው። እሱ የ”እፍታው” ውጤት ነው። የእፍታው ጊዜ እንኳንና ገድለሽ ሄደሽ “ግደይኝ”፣ ሌላ ሌላም ይባላል። “ተባብረን ካልገደልን”ም ይባላል።
“ቆዳዬ ተገፎ፣ ይሁንልሽ ጫማ፣
ስጋየም ይደገም፣ ላንቺ ከተስማማ”
ይሄን ያለው ዘፋኝ መቼም “ይቅር ይበለኝ” ብሎ ጣቱን ስንቴ ነክሷል? ፍቅር እፍታው ላይ ደስ ይላል። የጅንጀናው ሰሞን ዓለም ነው። እንደህጻን ባለ ንጽህና ቅድስናን ያስናግራል። “ይድፋሽ” እስኪመጣ ድረስ “ልደፋ፣ ልሙት” ያለ ነው። “ወይ አምላኬ” ብሎ ማማረር እስኪተካ ድረስ “I am lucky” ማለት ደንብ ነው።
የእፍታው ጊዜ፥ አመሉም፣ ቋንቋውም ጉራማይሌ ነው።
“ጉንፌን አውልቄ ለበስኩኝ ቦላሌ”
በፍቅር ስንነፋረቅ አንቺን እመስል ብዬ ልቤ ላይ ያደረግኩትን ጉንፍ አውልቄ፥ የልቤን ቦላሌ ጥለሽው ከሄድሽበት አንስቼ ለብሼዋለሁ። ውሰጅልኝ የልብሽን ጉንፍ!
ደግሞ ራቁቴን ስታስቀሪኝ የቦላሌና የጉንፍ ወግ ቀርቶ አገለድምበት የነገር ሽርጥ ፍለጋ ተፍጨረጨርኩኝ።
ቀን አስማምቶን ተዋውቀን ስንኖር የመሰለኝ፥ ውሸት መሆኑን ቀን አጋጭቶን ስንተዋወቅ ገባኝ።
በነገርሽ ላይ፥ ይህን ይህን ሁሉ ያወቅኹት ዛሬ አይደለም። ነገር ባጋጨን ቅጽበት ነው።
እናቱን ነገር!
ስጉ አደረገኝ። ቤቴ እንደተዘረፈ እንዲሰማኝ አደረገኝ። ራቁቴን አስቀረኝ። ሳይሞላ የሞላ ያስመሰለውን ጎኔን ሁሉ ገላልጦት አንዘፈዘፈኝ። ያለኝን ሁሉ ይዘሽብኝ ስትሄጂ ተሰምቶኝ “ሂጂ” ስልሽ አነባሁ። ሂጂ-አትሂጂብኝ መሳቂያ አደረገኝ።
ግን ውሸት ምን ይሰራል? “አትሂጅብኙ” እርቃኔን ለመጠበቅ ነበር። ሰው የሚስጥር ተካፋዩን ደፍሮ “ሂጂ” አይልም። ቢል ወየው ለራሱ! ሚስጥር መካፈሉ ቢቀርም ልማድ አለ። ልማድ አጉል ነው። “ለገና የገዛኸው በግ፥ ስጋ ስላለ ለጥምቀት ይሁን ብለህ ብትተወው፣ ለጥምቀት ለማረድ ያሳሳህና በግ አርቢ ሆነህ ትቀራለህ” ይላል ወንድሜ። የግጭት ማግስቱ ነጻነት የመስጠቱን ያህል፥ ከነገ ወዲያው ወፍራም ማቅ ያለብሳል።
ያኔ “ሰዶ ማሳደድ ካማረህ ዶሮህን በቆቅ ለውጥ” ነው ጨዋታው።
ይሄን ተረት የቀመረው ሰው፥ የእኔ ቢጤ ይመስለኛል። ሳይቸግረው ሰዶ ሚስጥሩን ጥበቃ ሲያሳድድ የኖረ የኔ ቢጤ።
ምን ታረጊዋለሽ?
እጣ ፈንታ ነው!
አንቺ ሳትኖሪ በፊት… ድሮ ድሮ ግን ሕይወት እንዴት ነበር? ውሎ ገባው የት የት ነበር? ላንቺ ሳልነግርሽ በፊት ሚስጥሬን የትኛው ቋቴ ውስጥ ነበር የምሸሽገው? ወይስ ካንቺ በፊት ሰማይና ምድሬ ላይ ሚስጥር አልነበረም?
ሚስጥር ማጋራትን ካንቺ መምጣት ጋር ተማርኩኝ።
ሚስጥር መጠበቅን ካንቺ መሄድ ጋር ቀሰምኩኝ።
ይብላኝ የሸራረፍኩትን ለምታገኘኝ ለባለተራዋ ውዴ! ይብላኝ በተንሸዋረረ ዐይን እያየሁ፥ በተሸራረፈ ልቤ ውሃ ለምጣጣ እኔ!
እርሳት እርሳት አሉኝ እንዴት እረሳለሁ፥
ሞኝነቴን ብንቅ፥ ወዴት እበልጣለሁ?!