አ ድ ዋ

ልዩ፣ ንዑድ፣ ፅሩይ ፅዋ፥
የደግነት ጥልቅ ጣዕሟ፥
የመስዋዕት ጣሪያ፣ ማማ፤
የክብረት ጫፉ፣ ከተማ፤
የኩራት፥ የድል ፏፏቴ
የመውደድ፥ ሰፊ ገበቴ፤

“ትናገር…
ትመስክር!”

“አድዋማ ጦርነት ነው!”
በባለጌ ደፋር ግብዣ፥
ሰው ስለሰው የቀመሰው፣
ሰው ስለሰው ያፀደቀው፤
ነጻነት፣ ክብረት ኀሰሳ፣
ሰው ስለሰው የከፈተው፣
ሰው ስለሰው የከተተው፤
ቀን አሻግሮ፥ ሩቅ አይቶ…
ተንኮል ሴራ፣ ግፍ ለይቶ፣
በባርነት ዳፋ ግምት…
ያልወደቀውን ሊደግፍ፥
ያልዘመመውን ሊያነሳ፣
ሰው ስለሰው የገጠመው፣
ሰው ስለሰው ያሸነፈው…
ሰው ስለሰው አይቶ ፍዳ፣
ሰው ስለሀገር ቆጥሮ አበሳ፤
አድዋማ ብድራት ነው፥
ሰው ስለሰው የከፈለው።

“ሰው ሞቷል ሰው ሊያድን፥
ሰውን ሲያከብር!”

አድዋ ሰደድ ቁጣ ነው፤
የሰው ንብረት ተመኝቶ፣ ግዛት ሊያሰፋ ሽቶ፥
በድፍረት ልጥ የታሰረ፥ ተስፋ ሸክፎ መጥቶ፣
ከታፈረች መሬት ጥሎ፥
በዘመናይ ፍጭርጭሪት፥ ደቃቅ ልቡ አጉል አብጦ፣
ሰውነት ላይ ሊረማመድ፥ ሲንቆራጠጥ ወጥ ረግጦ፣
በቀቢጸ ወኔ ሲርድ፥
ለታየ ቅብዝብዝ ደፋር፣ ለነበር ከንቱ ሶላቶ፥
የተመለሰ አጸፋ፥ የተከፈለ ዋጋ ነው፤
ይኸው፥ ከያኔ አንስቶ…
ሰው በሰው ቁጣ ተረትቶ፣
ሰው በሰው ሕይወት ተገዝቶ…

“በክብር ይሄዳል…
ሰው ሊኖር፥ ሰው ሞቶ”

ቡርቂ ጡርቂያሙን ሆዳም፥
ስልጣኔ ያልደገፈው፥ ያልበረታን ከንቱ ፈሳም
አሳድዶ የተቀዳጀው፥
ሰው ስለሰው ያስተረፈው፥
ሰው ስለሰው ያወረሰው፥
አድዋማ ነጻነት ነው፤

“የተሰጠኝ ሕይወት ዛሬ በነጻነት፣
ሰው ተከፍሎበታል፣ ከደምና ካጥንት”

አድዋ ልዩ “መንፈስ ነው”
ሰውን ከሰው ጋር አጠራርቶ፣
ሁሉን በፍቅር አንጠራርቶ፣
እርስበርሱ አደራርሶ፥ አንዱን ካንዱ አለካክቶ፤
ከየእምነቱ፣ ከየቋንቋው፣
ከየቤቱ፣ ከየቀዬው…. ከየአስተሳሰቡ ጎራ፣…
ሆ ብሎ ተነስቶ፣ ከትቶ፥
በፍቅር ትዕዛዝ ተጠርቶ፥
“ማርያምን” ተብሎ ዘምቶ፣
በድል ያመላለሰው…
አድዋስ ቋንቋ ሰዋሰው፣
አድዋስ የክብር ጫፍ ነው፣
የአንድነት፣ የኩራት፥ ሙላት፣
ቀና አስብሎ አረማማጅ፥
ከዳር ዳር ሁሉን አዛማጅ፤

“በደግነት በፍቅር፣ በክብር ተጠርቶ፥
በክብር ይሄዳል… ሰው ሊኖር፣ ሰው ሞቶ።”

አድዋ ኧረ ሌላ ናት…
‘ከሶላቶ ጋር ክርክር፣ የእንካ ሰላንቲያ ጨዋታ፥
በተገጠመበት ቅጽበት፥ በተጀመረበት አፍታ፥
የምትሰማ ውብ ነገር’
ልብን ውርር… ጆሮን ኩርር…
የምታደርግ፥ ውድ ስሜት፣
ጫፍ አልቦ፥ እሷ ራሷ ጫፍ፣
የመርቀቅ አናት ከፍታ፥
የመቅለል ዳር፣ የማነስ ቋፍ፤
የአጃኢባት ሜዳ፥ ጉብታ።

“ትናገር አድዋ፥ ትናገር ሀገሬ፣
እንዴት እንደቆምኩኝ ከፊታችሁ ዛሬ።”

ፍቅርን የፈተሉበት፣ ኩራትን ያለቀቁበት፣
ድርና ማጉ ተስማምቶ፥
የሀበሻነት ልዩ ጋቢን፥ “መንፈሱን የሸመኑበት”
ለነፍስ ግዥ፥ ነፍስ ሸጠው…
ስጋን ለስጋ ገብረው፥ ወገንን የታደጉበት፣
ሀገርን የከለሉበት፣ አህጉር ያስታፈሩበት፣
ግዞትን የሸቀጡበት፣ ነጻነት የሸመቱበት፤
የማዕዘን ክቡር ድንጋይ፥ ወሰን ነው አድዋ ማለት፤

“አፍሪካ፣ እምዬ፣ ኢትዮጵያ፥
አዪዪ… ተናገሪ፣
የድል ታሪክሽን አውሪ።”

አድዋማ…
ጥቁርን ያስፈለቀቀ፣ ከነጭ ጥርስ ያስለቀቀ፣
ትምህተኛን ያሳፈረ፣ ሰውን በሰው ያስቆጠረ፣
የማይበጠስ ክር ነው፥ ነፍስን በዋጋ ያሰረ፥
የሰዋዊነትን ጉዳይ፥ በደም ዋጋ ያስከበረ፤
“አድዋ ይጮሃል እንጂ፥ ከቶ ማን ሊሰማው ችሎ?”
ከዘመን ዘመን ይጓዛል፥ ካ’ጥናፍ አጥናፍ ያስተጋባል፥
ብርቱ ድምፁ ልቆ፣ አይሎ።

“በደስታ፣ በክብር፣ በኩራት፣ በፍቅር፣
በድል እኖራለሁ ይኸው በቀን በቀን፥
ደግሞ መከራውን ያን ሁሉ ሰቀቀን፤”

ከሷ ወዲያ…
ጥቁር እንቁ ዋጋው ንሮ፥
ባለም ገበያ የከበረ፣
ለመድኃኒት የቸገረ፤
የአጥንት የስጋ ደመራ፣
ጥቁር ገላ ያበራበት፥
ለሰው ብርሃን፣ ለሰው ሙቀት፣
ለሰው ንቃት፣ ለሰው ድምቀት፤
የማንነት ልዩ ጎራ፣
የልዩነት ውብ ተራራ፥
ላለም ዓለም እንዲያበራ፥
ሰው በሞቱ ያማረበት፤
አድዋማ ብድራት ነው፥
ሰው ስለሰው የከፈለው።

“ምስጋና ለእነሱ፥ ለአድዋ ጀግኖች፣
ለዛሬ ነጻነት… ላበቁኝ ወገኖች።”

/ዮሐንስ ሞላ/

P.S. ግጥሙን ያዘመትኩት በኃይል በምወደው የእጅጋየሁ ሺባባው “አድዋ” ግጥም ስንኞች ነው። በድፍረት ያደረግኹት ሙከራ ነው። እናም ክብር ቢኖር፥ ለእርሷ ይሁንልኝ። ከዚያ በተጨማሪ፣ ግጥሙ የተቆሰቆሰው (inspired by)፥ የዛሬ ዓመት ከወዳጆቻችን ጋር የአድዋ ድል በዓልን በምንሊክ አደባባይ አክብረን፣ ጣይቱ ሆቴል ቁጭ ብለን ስንጫወት፥ ከጨዋታ ርዕሳችን አንዱ አድዋ ለእኛ ምን ማለት እንደሆነ መናገር ነበር። ሁሉም ሀሳቡን ሰጠ፣ ጨዋታው ሲቋጭ፥ “ዛሬ ማታ የሁላችንንም ሀሳብ የሚዳስስ ግጥም ፅፌ እለጥፋለሁ” ብያቸው ነበርና በማስታወሻ የጫርኩትን በት/ተ ጥቅስ አኑሬያለሁ። አብረን ስላሳለፍናቸውና ወደፊት ስለምናሳልፋቸው መልካም ቀናት፥ ወዳጆቼን እጅ ነስቻለሁ።

ከዓመት ዓመት ያድርሰን! የጀግኖች እናቶቻችን እና የአባቶቻችን በረከት ይደርብን!

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s