“ትናንት” እና “ዛሬ”

ብዙ ጊዜ፥ የትናንቱን የማድነቅና የዛሬን ሰው የማኮሰስ ነገር አለ። በተለይ ከወዲያኛው ትውልድ ያሉ ሰዎች ያዘወትሩታል። ከወዲህም፥ “ዛሬ ቅቤ ንጠን ትናንትን እንቀባ” የሚሉ ንባብ ቀመስ ወጣቶች አሉ። እኔ የሰማኋቸው አባቶች ግን “ከትናንት ዛሬ ይሻላል” የሚሉ ይመስላል። ሁለት ገጠመኞቼን ላውጋችሁ። (ጨዋታዎቹ በጉራጊኛ ነበሩ። “ቃና ውስጤ ነው” ብለን ወደ አማርኛ መልሰናቸዋል። 🙂 )
 
ከዚህ ቀደም፥ አንድ ለቅሶ ቤት ውስጥ “የዛሬ ወንዶች ለሚስቶቻቸውና ለልጆቻቸው” እንዲሁም “የድሮ ወንዶች ለሚስቶቻቸውና ለልጆቻቸው” የሚል ርዕስ ጉዳይ ላይ በእድሜ ገፋ ገፋ ያሉ አባቶች ይጫወታሉ። ሁሉም በሚባል ደረጃ፥ የዛሬውን አደነቁ። የእኛ ጊዜ ወንድ “ወተትሽ ገነፈለልሽ። ልጅሽ አለቀሰልሽ።” ነበር የምንለው። ጠግቦ ሰክሮ በረሀብ የዋለች ሚስቱን ልደብድብ የሚልም አለ።”
 
“ፍራንክ ይዘን ስለገባን እርሷን እንንቃለን። እንዳባካኝ ነው የምንቆጥራት። ሲታሰብ ግን፥ ውሎ የሚገባውን የወንዱን ስራ እርሷም ልትሸፍነው ትችላለች። ወንዱ ግን የእርሷን የቤት ስራ ሊሸፍን አይችልም። ዛሬ ባብዛኛው ያቅም ያቅሙን ሰርቶ ይገባል። ስንት አለሽ? እኔ ጋር ይሄ አለ ተባብለው ነው። ሚስቱ ብታረግዝ አብሯት የሚጨነቀው ብዙ ነው። ሀኪም ቤት አብሯት ይሄዳል። ለልጁ ሮጦ ይገባል። …አንዳንዱ ነገር ይበዛና ያሳቅቃል እንጂ የተሻሻለው ይበዛል።” ምናምን ሲሉ ነበር።
 
ዛሬ ጠዋት ደግሞ ዘመድ ሞቶ ለቅሶ ልደርስ ሄጄ፥ ተመሳሳይ ዓይነት የዛሬን እና የትናንትን የማወዳደር ውይይት ስቦኝ ጆሮዬን ጣልኩ። ይህኛው፥ “የዛሬ ወጣቶች ያላቸው የመተባበር እና ሰው የመርዳት ሁኔታ” እና “የድሮ ወጣቶች የነበራቸው የመተባበር እና ሰው የመርዳት ሁኔታ” የሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያጠነጠነ ነበር።
 
መጀመሪያ “ትናንት ይሻላል” “ዛሬ ይሻላል” የሚሉ ድምጾች ተደበላልቀው ነበር። ቆይቶ ምክንያት ሲደረደር “ዛሬ ይሻላል” ወደሚለው አዘነበሉ። “በእኛ ጊዜ ክፋት ኖሮም ሳይሆን ሰው እርዳታ የሚያስፈልገው አይመስልም። በዚያም ሰው ልርዳ ብለህ ብታስብ መረጃም አይኖርም። ቤትህ ከሞላ ሁሉም ቤት የሞላ ይመስልሃል። ቤትህ ከጎደለ ሁሉም ቤት የጎደለ ይመስልሃል። አሁን ሰው ዘግቶ ይኖራል ተብሎ ይታማል እንጂ፥ ያሁን ሰው የተሻለ ይግባባል። በኮምፑተርም በስልክም ይገናኛል። ችግርህን ካወቀ ድንጋይ ፈንቅሎ ይረዳሃል። ደግሞ ገመናህም ሳይዘራ በትንሽ ሰው ያልቃል። መንገድ ያጣል እንጂ ሩጫ አላነሰውም። ድሮ ልስራ ላለ አልጋ ባልጋ ነበር።”
 
እንዲህ ዓይነት አባቶች እና እናቶች ይብዙልን! ትናንትን እያጣቀሱ ከመውቀስ ባለፈ፥ ዛሬም ላይ ያለውን የተሻለ ነገር እየነቀሱ እውቅናን ቢሰጡ ለተሻሉ መልካምነቶች ያነቃቃል።
 
ከዛሬም ነገ ይሻላል!
 
እድሜና ጤና ይስጥልን!

12936736_1353244648025346_6022529115159645969_nድራማው የቀን ቅኝት ነው፤ “ማለቂያው ሩቅ ነው” ስልሽ፥ ወዳጄ!

ከ15 ሚሊየን ሕዝብ በላይ በተራበበት አገር ውስጥ፥ ከአንድ ሺ ሚሊየነር ገበሬዎች ሸልመናል ይባልልኛል። ታዲያ ይኼ በአንድ ክልል ውስጥ ነው። የሌላውን የክልሉ ኮካዎች ሀላፊ ሰብስቦ ሲሸልመው ወሬውን እንሰማለን።

እንበል (let’s assume):

ያን ያህል ሚሊየነር ገበሬዎች አሉ። ሁሉም ያላቸው የሀብት መጠን አንድ ሚሊዮን በነፍስ ወከፍ ብቻ ነው እንበል። አንድ ሺህው በጋራ 1 ቢሊዮን ብር ሀብት ይኖራቸዋል ማለት ነው።

ታዲያ ይሄ ሁሉ ሚሊየነር ገበሬ ሞልቶ ረሀቡ እንዴት ተከሰተ?

“ድርቁ” አላልኩም። ድርቁ የተፈጥሮ ጉዳይ ነው። ዝናብ ሲመጣ፣ ዝናብ ሲሄድ የሚሆን ነገር ነው። ረሀቡ ግን ክፉ ቀንን አስቦ ምግብ ያለማስቀመጥ ውጤት ነው።

በአንድ አካባቢ ይህን ያህል ሚሊየነር ገበሬዎች አሉ ማለት፥ እንደከተማ ለሙስና እና ለዝርፊያ የተመቻቸ ሁኔታ ስለማይኖር፣ ኑሮው ይቀራረባልና የተቀሩት በብዛት በሺዎች የሚቆጠር ሀብት ይኖራቸዋል።

የኑሮ መሻሻል እና የሀብት መብዛት ደግሞ የአስተሳሰብ አድማስንም ይወስናልና (and the other way round) እንዴት ይሄ ሁሉ ሰው “ለነገ” ብሎ የማስቀመጥ ስነልቡና ሳይኖረው ቀረ?

እሺ እሱም ይቅር፥ በቀዬው፣ በክልሉ ይህን ያህል ሰው ሲራብ፥ ገበሬው ራሱ ቢያዋጣ ችግሩን/ገመናውን እዚያው ለዚያው ይሸፍነው አልነበር?

እሺ ይኼም ይቅር፥ “ወጧ እንዳማረላት ሴት” የሀላፊዎቹ “እዩኝ፣ ስሙኝ” ምንድን ነው?

ለሽልማቱስ ስንት ወጣ?