“ትናንት” እና “ዛሬ”

ብዙ ጊዜ፥ የትናንቱን የማድነቅና የዛሬን ሰው የማኮሰስ ነገር አለ። በተለይ ከወዲያኛው ትውልድ ያሉ ሰዎች ያዘወትሩታል። ከወዲህም፥ “ዛሬ ቅቤ ንጠን ትናንትን እንቀባ” የሚሉ ንባብ ቀመስ ወጣቶች አሉ። እኔ የሰማኋቸው አባቶች ግን “ከትናንት ዛሬ ይሻላል” የሚሉ ይመስላል። ሁለት ገጠመኞቼን ላውጋችሁ። (ጨዋታዎቹ በጉራጊኛ ነበሩ። “ቃና ውስጤ ነው” ብለን ወደ አማርኛ መልሰናቸዋል። 🙂 )
 
ከዚህ ቀደም፥ አንድ ለቅሶ ቤት ውስጥ “የዛሬ ወንዶች ለሚስቶቻቸውና ለልጆቻቸው” እንዲሁም “የድሮ ወንዶች ለሚስቶቻቸውና ለልጆቻቸው” የሚል ርዕስ ጉዳይ ላይ በእድሜ ገፋ ገፋ ያሉ አባቶች ይጫወታሉ። ሁሉም በሚባል ደረጃ፥ የዛሬውን አደነቁ። የእኛ ጊዜ ወንድ “ወተትሽ ገነፈለልሽ። ልጅሽ አለቀሰልሽ።” ነበር የምንለው። ጠግቦ ሰክሮ በረሀብ የዋለች ሚስቱን ልደብድብ የሚልም አለ።”
 
“ፍራንክ ይዘን ስለገባን እርሷን እንንቃለን። እንዳባካኝ ነው የምንቆጥራት። ሲታሰብ ግን፥ ውሎ የሚገባውን የወንዱን ስራ እርሷም ልትሸፍነው ትችላለች። ወንዱ ግን የእርሷን የቤት ስራ ሊሸፍን አይችልም። ዛሬ ባብዛኛው ያቅም ያቅሙን ሰርቶ ይገባል። ስንት አለሽ? እኔ ጋር ይሄ አለ ተባብለው ነው። ሚስቱ ብታረግዝ አብሯት የሚጨነቀው ብዙ ነው። ሀኪም ቤት አብሯት ይሄዳል። ለልጁ ሮጦ ይገባል። …አንዳንዱ ነገር ይበዛና ያሳቅቃል እንጂ የተሻሻለው ይበዛል።” ምናምን ሲሉ ነበር።
 
ዛሬ ጠዋት ደግሞ ዘመድ ሞቶ ለቅሶ ልደርስ ሄጄ፥ ተመሳሳይ ዓይነት የዛሬን እና የትናንትን የማወዳደር ውይይት ስቦኝ ጆሮዬን ጣልኩ። ይህኛው፥ “የዛሬ ወጣቶች ያላቸው የመተባበር እና ሰው የመርዳት ሁኔታ” እና “የድሮ ወጣቶች የነበራቸው የመተባበር እና ሰው የመርዳት ሁኔታ” የሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያጠነጠነ ነበር።
 
መጀመሪያ “ትናንት ይሻላል” “ዛሬ ይሻላል” የሚሉ ድምጾች ተደበላልቀው ነበር። ቆይቶ ምክንያት ሲደረደር “ዛሬ ይሻላል” ወደሚለው አዘነበሉ። “በእኛ ጊዜ ክፋት ኖሮም ሳይሆን ሰው እርዳታ የሚያስፈልገው አይመስልም። በዚያም ሰው ልርዳ ብለህ ብታስብ መረጃም አይኖርም። ቤትህ ከሞላ ሁሉም ቤት የሞላ ይመስልሃል። ቤትህ ከጎደለ ሁሉም ቤት የጎደለ ይመስልሃል። አሁን ሰው ዘግቶ ይኖራል ተብሎ ይታማል እንጂ፥ ያሁን ሰው የተሻለ ይግባባል። በኮምፑተርም በስልክም ይገናኛል። ችግርህን ካወቀ ድንጋይ ፈንቅሎ ይረዳሃል። ደግሞ ገመናህም ሳይዘራ በትንሽ ሰው ያልቃል። መንገድ ያጣል እንጂ ሩጫ አላነሰውም። ድሮ ልስራ ላለ አልጋ ባልጋ ነበር።”
 
እንዲህ ዓይነት አባቶች እና እናቶች ይብዙልን! ትናንትን እያጣቀሱ ከመውቀስ ባለፈ፥ ዛሬም ላይ ያለውን የተሻለ ነገር እየነቀሱ እውቅናን ቢሰጡ ለተሻሉ መልካምነቶች ያነቃቃል።
 
ከዛሬም ነገ ይሻላል!
 
እድሜና ጤና ይስጥልን!

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s